የወተት ጥርስ አስተዳደግ

Eyasu Yebeltal
Feb 12, 2026
undefined

                  የወተት ጥርስ አስተዳደግ 

የመጀመሪያው ጥርስ የሚወጣበት እድሜ የአንዱ ህፃን ከሌላኛው ይለያያል፤ ነገርግን አብዛኛው ልጆች አንድ አመት እድሜ እስኪሞላቸው ድረስ የመጀመሪያ ጥርሳቸውን ያበቅላሉ። 

ልጄ የመጀመሪያ ጥርሱን መች ማብቀል ይጀምራል? 

አንዳንድ ሕፃናት የመጀመሪያ ጥርሳቸውን አብቅለው ይወለዳሉ፤ ሌሎች ገና 4 ወር ከመሆናቸው በፊት ጥርስ ማውጣት ይጀምራሉ የተቀሩት ደግሞ ከ12 ወር በኋላ ይጀምራሉ። ነገርግን አብዛኛዎቹ ሕፃናት ጥርስን ማውጣት የሚጀምሩት በ6 ወር ዕድሜ አካባቢ ነው፡፡

ልጄ ጥርስ እያበቀለ መሆኑን በምን ማወቅ እችላለው?

አንዳንድ ሕፃናት ጥርስ በሚያበቅሉበት ወቅት ምንም ምልክት ላያሳዩ ቢችሉም አብዛኞቹ ግን ከሚከተሉት ምልክቶች መካከል የተወሰኑት ይኖሯቸዋል።   

  • የድድ መቅላት እና ማበጥ 
  • መለስተኛ ትኩሳት 
  • የጉንጭ ቀይ መሆን
  • ፊታቸው ላይ ሽፍታ መኖር
  • ጆሯቸውን በተደጋጋሚ ማሻሸት
  • ከወትሮው የበለጠ በላሃጭ መዝረክረክ
  • ያገኙትን ዕቃ ማኘክ
  • እንቅልፍ ማጣት

ሆኖም በተደጋጋሚ የሚሰማው ህፃናት ጥርስ ማብቀል ሲጀምሩ ተቅማጥ ይኖራቸዋል የሚለውን የሚደግፍ በቂ መረጃ የለም። 

የሕፃናት ጥርስ አድገት በቅደም ተከተል 

ከታች የተጠቀሰው በአብዛኛው ህፃናት ላይ በወራት ቅደም ተከተል የሚታየው የጥርስ አስተዳደግ ሂደት ነው። ከዚህ ውጪ የጥርስ አስተዳደግ ሂደት ያላቸው ህፃናት ጤናማ አይደሉም ማለት አይደለም፤ነገርግን ልጅዎ እስከ 13 ወር ድረስ ምንም ጥርስ ካላበቀለ የጥርስ ሃኪም ያማክሩ። 

  • የታችኛው የፊት ጥርሶች - እነዚህ ብዙውን ጊዜ ከ5 እስከ 7 ወር አካባቢ የሚበቅሉ የመጀመሪያዎቹ ጥርሶች ናቸው
  • የላይኛው የፊት ጥርሶች - እነዚህ ከ6 እስከ 8 ወራቶች ውስጥ ይወጣሉ
  • የላይኛው የጎን ጥርሶች - እነዚህ በሁለቱም በኩል  ከ9 እስከ 11 ወራት አካባቢ ይወጣሉ
  • የታችኛው የጎን ጥርሶች - እነዚህ በሁለቱም በኩል ከ10 እስከ 12 ወራት አካባቢ ይወጣሉ
  • የመጀመሪያ መንጋጋ ጥርስ - እነዚህ ከ 12 እስከ 16 ወራት አካባቢ ይወጣሉ
  • የውሻ ክራንቻ - እነዚህ ከ16 እስከ 20 ወራት አካባቢ ይወጣሉ
  • ሁለተኛው የመንጋጋ ጥርስ - እነዚህ ከ20 እስከ 30 ወራት አካባቢ ይወጣሉ

አብዛኞቹ ህፃናት ዕድሜያቸው 2 ዓመት ከግማሽ ሲሞላቸው ሁሉም የወተት ጥርሶቻቸውን አብቅለው ይጨርሳሉ ፡፡

ለልጄ የወተት ጥርስ እድገት ህመምን ለመቀነስ ምን ማድረግ እችላለው? 

  • ልጅዎ ጥርስ እያበቀለ ለመሆኑ አንዱ ማሳያ ያገኙትን ነገር ማኘክ መጀመር ነው፤ ይህም በሚሆንበት ወቅት ልጅዎ ከ6 ወር በላይ ከሆነ ጤናማ የሆኑ እንደ ፍራፍሬዎች፣ ደረቅ ዳቦ የመሳሰሉ ምግቦች እንዲያኘክ ይስጡት። ይህን በሚያደርጉበት ጊዜ ትንታን ለመከላከል በቅርብ ይከታተሉ። 
  • የጥርስ መቦርቦርን ስለሚያስከትሉ ስኳር የበዛባቸውን ምግቦችን ከመስጠት ይቆጠቡ።
  • ፓራሲታሞል ወይም አይቡፕሮፊን የህመም ማስታገሻዎች ከ3 ወር በላይ ለሆኑ ህፃናት ሃኪምዎን አማክረው መስጠት ይችላሉ።
  • በንፁህ ጣት ድዳቸውን ማሸት እና የተለያዩ ጨዋታዎችን ማጫወት ህመሙን እንዲረሱት ይረዳል።
  • ከወትሮ የበለጠ የለሃጭ መዝረክረክ ቆዳቸው ላይ ሲቆይ ሽፍታ ሊፈጥር ስለሚችል በየጊዜው ማድረቅ ሽፍታን ለመከላከል ይረዳል

Comments (0)