በዳይፐር ምክንያት ህፃናት ላይ የሚከሰት የቆዳ ሽፍታ ማለት በህፃናት ላይ ቀጥታ ከዳይፕር ጋር ንክኪ ያለው የአካል ክፍል ላይ የሚፈጠር የተለመደ የቆዳ መቆጣት ነው።
ይህ አይነቱ የቆዳ ሽፍታ በረጠበ እና በአግባቡ በማይቀየር ዳይፐር ወይም በቆዳ ቶሎ የመቆጣት ዝንባሌ ምክንያት የሚከሰት ሲሆን በአብዛኛው ህፃናት ላይ ቢታይም ማንኛውም ዳይፐር የሚጠቀም አዋቂም ላይ ሊከሰት ይችላል።
በዳይፐር ምክንያት የሚከሰት የቆዳ ሽፍታ ምልክቶች
- ከዳይፐር ጋር ቀጥታ ንክኪ ያለው ቆዳ ላይ ቀይ፣ ህመም ያለው ሽፍታ
- ልጅዎ ከተለመደው የበለጠ ምቾት የማጣት ምልክቶች ሊያስተውሉ ይችላሉ፤በተለይ ዳይፐር በሚቀይሩበት ጊዜ እና የተቆጣው የቆዳ አካባቢ በሚነካበት ወቅት
መች ወደ ጤና ተቋም መሄድ አለብኝ?
ከጥቂት ቀናት የቤት ውስጥ ህክምና በኋላ የህፃኑ ቆዳ የማይሻሻል ከሆነ ሃኪም ያነጋገሩ፡፡ የሚከተሉት ምልክቶች ካሉ በሃኪም የሚታዘዙ መድኃኒቶች ያስፈልግዎታል፡፡
- የተሰራጨ ወይም ያልተለመደ ሽፍታ
- ከቤት ውስጥ ሕክምና በኋላ እየተባባሰ የመጣ ሽፍታ
- መድማት፣ ማሳከክ ወይም መግል መያዝ
- ህፃናት በሚሸኑበት ወይም ሰገራ በሚሉበት ጊዜ ማልቀስ
- ትኩሳት
- ልጅዎ በጣም የታመመ ከመሰለ ወይም ደካም ድካም ካለው
በዳይፐር ምክንያት የሚከሰት የቆዳ ሽፍታ ለምን ይከሰታል?
- ሰገራ ወይም ሽንት ከቆዳ ጋር ለረጅም ሰዐት ንክኪ ሲኖራቸው ቆዳን ሊያመረቅዙ ይችላሉ።
- አጥብቆ የሚይዝ ዳይፐር ማድረግ ከቆዳ ጋር በመተሻሸት ሽፍታ ሊያስከትል ይችላል።
- ለልጅዎ የሚጠቀሙትን የንፅህና መጠበቂያ እቃዎች ሲቀይሩ ከቆዳው ጋር አለመስማማት ምክንያት ሊሆን ይችላል።
- ዳይፕር የሚደረግባት የአካል ክፍል እርጥበት እና ሙቀት የሚይዝ ስለሆነ ለባክቴሪያ እና ለፈንገስ ኢንፌክሽን የተጋለጠ ነው።
- ለልጅዎ አዲስ ምግብ በሚያስጀምሩበት ወይም ጡት ለሚጠቡ ህፃናት እናትየው አመጋገቧን በምትቀይርበት ወቅት የልጅዎ የሰገራ ይዘት እና ድግግሞሽ ስለሚቀየር ለቆዳ ሽፍታ ሊያጋልጥ ይችላል። በተጨማሪም ተቅማጥ ቀደም ሲል የነበረን የዳይፐር ሽፍታ ይበልጥ እንዲባባስ ሊያደርግ ይችላል።
- በዳይፐር ውስጥ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ሰገራ እና ሽንት በመዋሃድ አሞኒያ (ammonia) የተባለ ኬሚካል ይፈጥራሉ። ይህ ደግሞ ቀለል ያለ የኬሚካል ቃጠሎን ሊያስከትል ይችላል። ዳይፐር በሚቀይሩበት ወቅት የሚወጣው ሽታ የአሞኒያ ሽታ ይኖረዋል። ይህ ሁኔታ በብዛት የሚከሰተው በጨርቅ ዳይፐሮች ላይ ነው።
- በተፈጥሮ በቀላሉ የሚቆጣ ቆዳ ያላቸው በዚህ አይነቱ የቆዳ ሽፍታ የመያዝ እድላቸው ከፍ ያለ ነው።
- ፀረ ባክቴሪያ መድሃኒቶችን ህፃኑ ወይም እናትየው የምትውስድ ከሆነ በተለያየ ምክንያት የቆዳ ሽፍታ ሊያስከትል ይችላል።
በዳይፐር ምክንያት የሚከሰት የቆዳ ሽፍታን እንዴት መከላከል ይቻላል?
በዳይፐር ምክንያት የሚከሰት የቆዳ ሽፍታን ለመከላከል ዋንውኛው መንገድ ከዳይፐር ጋር ቀጥታ ንክኪ ያላቸውን የቆዳ ክፍሎች ንጹህ እና ደረቅ አደርጎ መጠበቅ ነው። ይህንንም ለማድረግ የሚከተሉትን አቅጣጫዎች ይከተሉ።
- የልጅዎን ዳይፐር ቶሎ ቶሎ ይቀይሩ
- ዳይፐር በሚቀይሩበት ጊዜ ልጅዎን ለብ ባለ ውሃ ያፅዱ፤ የሚጠቀሙት ማንኛውም ጨርቅ ወይም ሳሙና አልኮል እና ሽታ አለመኖሩን ያረጋግጡ
- የልጅዎን ቆዳ በሚያደርቁበት ጊዜ በጨርቅ ማሸት የቆዳ መቆጣትን ሊያባብስ ስለሚችል በራሱ እንዲደርቅ መተው ወይም በንጹህ ፎጣ ነካ ነካ ማድረግ በቂ ነው።
- የልጅዎን ዳይፐር በሚያደርጉበት ጊዜ አጥብቀው አይሰሩት
- ልጅዎ ለተወሰኑ ሰዐታት ያለ ዳይፐር ወይም ሽንት ጨርቅ እንዲቆይ ያደርጉ።
- ልጅዎ በተደጋጋሚ የቆዳ ሽፍታ የሚያጋጥመው ከሆነ ዳይፐር በቀየሩ ቁጥር ቆዳውን አፅድቶ ቫስሊን መቀባት ሽፍታ ለመቀነስ ይረዳል
- የልጅዎን ዳይፐር ከቀየሩ በኋላ እጅዎን በአግባቡ ይታጠቡ። ይህም የበሽታ አምጪ ተዋህሲያንን መዛመት ለመቀነስ ይጠቅማል
- የሕፃናትን ቆዳ ለመንከባከብ እና ከመጠን በላይ እርጥበትን ለመመጠን ዱቄት(powder) የንፅህና መጠበቂያዎችን መጠቀም የተለመደ ቢሆንም ይህ ህፃናት በሚተነፍሱበት ወቅት ወደ ሳምባ በመግባት የተለያዩ ችግሮችን ሊያስከትል ስለሚችል እነዚህን ከመጠቀም ይቆጠቡ።
ዳይፐር ወይስ የሽንት ጨርቅ መጠቀም ይሻላል?
ብዙ ወላጆች ምን ዓይነት ዳይፐር መጠቀም እንዳለባቸው ያሳስባቸዋል፡፡ የቆዳ ሽፍታን ከመከላከል አንፃር ዳይፐር ወይም የሽንት ጨርቅ መጠቀም አንዱ ከሌላው የተሻለ ነው የሚያስብል መረጃ የለም። ስለሆነም የእርስዎ ኢኮኖሚ የሚፈቅደውን እና ለልጅዎ የሚስማማውን የዳይፐር ወይም የሽንት ጨርቅ አይነት ይጠቀሙ።
ከላይ የተጠቀሱትን መከላከያ መንገዶች በአግባቡ ከተገበሩ ማንኛውም አይነት ዳይፐር ወይም የሽንት ጨርቅ ቢጠቀሙም የቆዳ ሽፍታን ማስወገድ ይችላሉ። በተጨማሪም የሽንት ጨርቅ የሚያጥቡበት ጊዜ አልኮል እና ሽታ በሌለው ሳሙና መሆኑን ያረጋግጡ።
በዳይፐር ምክንያት ለሚከሰት የቆዳ ሽፍታ ሕክምናው ምንድነው?
በቤት ውስጥ የሚደረግ ህክምና
- ዳይፐር ወይም ሽንት ጨርቅ በጊዜው መቀየር
- ያለ ዳይፐር ወይም ሽንት ጨርቅ እንዲቆዩ ማድረግ (ቢያንስ በየቀኑ 3 ጊዜ ለ10 ደቂቃ)
- ሽፍታው እስኪጠፋ ድረስ ሰፋ ያሉ ዳይፐሮችን መጠቀም
- ለህፃናት ተብሎ የተዘጋጁ ዚንክ ኦክሳይድ (zinc oxide) እና ቫዝሊን (petroleum jelly) ቅባቶችን መጠቀም
- ሽፍታው እስኪጠፋ ድረስ ልጅዎን ለብ ባለ ውሃ በየቀኑ ገላውን ማጠብ
የዳይፐር ሽፍታ አብዛኛውን ጊዜ በቤት ውስጥ በሚደረግ እንክብካቤ ከ2 እስከ 3 ቀናት ውስጥ ይጠፋል፤ ሆኖም ከዚያ በላይ ሊቆይ የሚችልባቸው ሁኔታዎች አሉ።
የጤና ተቋም ህክምና
ከላይ የተዘረዘሩትን የቤት ውስጥ ህክምና አድርገው የልጅዎ ሽፍታ የማይሻሻል ወይም የሚባባስ ከሆነ የሚከተሉት የህክምና አማራጮች ሊደረግልዎት ይችላል።
- ስቴሮይድ ክሬም (steroid cream)- ቀለል ያለ (ከ0.5% እስከ 1% የሆነ) የሀይድሮኮርቲሶን (hydrocortisone) ስቴሮይድ ክሬም በቀን ሁለት ጊዜ፣ ለ3 እስከ 5 ቀናት መቀባት።
- ፀረ ፈንገስ ቅባቶች
- ፀረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች
በእነዚህ መድኃኒቶች በመታገዝ የልጅዎ የዳይፐር ሽፍታ ሙሉ በሙሉ ለመጥፋት አንድ ሳምንት ወይም ከዚያ በላይ ሊፈጅበት ይችላል።



