ስለ ቤት ለቤት ህክምና ምን ያህል ያውቃሉ?

Biruh Tesfaye
Feb 18, 2026
undefined

የቤት ለቤት ህክምና ለታካሚ ድጋፍ ለመስጠት በማንኛውም የጤና ባለሙያ የሚሰጥ የአንድን ታካሚ የጤና ሁኔታ እስከሚቻለው ድረስ ለማከም የሚረዳ አገልግሎት ነው። የቤት ለቤት የሕክምና አገልግሎት ዓላማ የግለሰቦችን ጤና መጠበቅ፣ የሕይወት ጥራታቸውን ማሻሻል እና በራሳቸው የመንቀሳቀስ ወይም የመኖር ነፃነታቸውን መደገፍ ነው። በተጨማሪም አረጋውያን ያሉበትን የመንቀሳቀስና አቅም ለማሻሻልና ለመጠበቅ፣ እንዲሁም ወደ ተቋማት (እንደ አረጋውያን መርጃ ማዕከላት ወይም ሆስፒታል) መግባትን ለመከላከል ሲባል በቤታቸው ውስጥ የጤና እና የማህበራዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ ነው።

የቤት ለቤት የሕክምና አገልግሎቶች እንደ አስፈላጊነታቸው በፕሮግራም ሊደረጉ ይችላሉ። ከጥቂት ሰዓታት ጀምሮ እስከ ሙሉ 24 ሰዓት አብሮ በመኖር የሚሰጥ የቤት ውስጥ እንክብካቤን ያካትታል።

የቤት ለቤት እንክብካቤ ከተቋም (ሆስፒታል ወይም ማቆያ) ሕክምና ይልቅ በርካታ ጥቅሞች አሉት። ከነዚህም መካከል 

  • በሚታወቅ እና በሚመች አካባቢ ውስጥ የሚሰጥ እንክብካቤ ስለሆነ ታካሚው ምቾት ይሰማዋል 
  • አንድ ታካሚ ላይ ሙሉ ትኩረት ስለሚሰጥ እንክብካቤው ይጨምራል
  • የጤና ባለሙያዎች ታካሚዎችመድኃኒቶቻቸውን በአግባቡና በሰዓቱ መውሰዳቸውን እንዲሁም የጤና ሁኔታቸውን በቅርበት መቆጣጠር ይችላሉ
  • ተደጋጋሚ ወደ ሆስፒታል የመመላለስ (መተኛት) አጋጣሚን ይቀንሳል
  • ቤተሰቦች ላይ የሚኖረው ጫና ይቀንሳል
  • ከአረጋውያን መርጃ ተቋማት ጋር ሲነጻጸር ወጪ ቆጣቢ መሆኑ

የቤት ለቤት ህክምና የሚያስፈልጉዋችው ሰዎች ምን አይነት ናችው?

የቤት ለቤት እንክብካቤ አገልግሎት ለተለያዩ ሰዎች እጅግ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ከእነዚህም መካከል፦

  • በእድሜ የገፉ እና እገዛ የሚያስፈልጋቸው አዛውንቶች
  • የተለየ አይነት ክትትል የሚያስፈልጋቸው ሰዎች
  • የአካል ጉዳት ያለባቸው እና እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ሰውች
  • ለብዙ ጊዜ የቆየ የጤና እክል ያጋጠማቸው ሰዎች
  • ከአደጋ ወይም ከህመም በሁዋላ እንዲያገግሙ ለመርዳት

የቤት ለቤት ህክምና ላይ ምን አይነት ስራዎች ይሰራሉ?

አንድ ታካሚ በቤቱ ውስጥ ሊያገኛቸው የሚችላቸው የጤና አገልግሎቶች ዘርፍ በጣም ሰፊ ነው። ታካሚው አስፈላጊ የሆኑትን ቅድመ ሁኔታዎች እስካሟላ ድረስ፣ በማንኛውም የጤና ጉዳይ ላይ እንክብካቤ ማግኘት ይችላል። እንደ በሽተኛው ፍላጎት፣ የተለያዩ የጤና ባለሙያዎች ቤታቸው ድረስ በመሄድ ሊንከባከቧቸው ይችላሉ። ለምሳሌ፦ ነርሶች፣ ተንከባካቢዎች (caregivers) እና ቴራፒስቶች በታካሚው ቤት ውስጥ የአጭር ወይም የረጅም ጊዜ እንክብካቤ ሊሰጡ ይችላሉ። የታካሚው ሐኪም ወይም ከፍተኛ የጤና ባለሙያ የህክምና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የህክምና ግምገማ በማድረግ የቤት ለቤት እንክብካቤ ለታካሚው ተመራጭ መሆኑን ይወስናል። 

የቤት ለቤት የሕክምና አገልግሎቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦

  • የቀንተቀን ውሎዎቻቸውን እንዲያከናውኑ መርዳት( ማልበስ,ማብላት,ማጠብ)
  • ለአንድ ታካሚ እንደ ህመሙ አይነት ለአጭር ወይም ለረጅም ጊዜ የሚቆይ እንክብካቤ (tracheostomy care, catheterization, ventilation care)
  • ቁስልን ማጠብ  
  • መድሃኒቶችን መስጠት
  • ህመምን ማስታገስ
  • የአልጋ ላይ ቁስል እንዳይፈጠር ታካሚውን ማንቀሳቀስ ወይም አልጋው ላይ ቦታ ማቀያየር
  • ጥንካሬን እና የመንቀሳቀስ አቅምን መልሶ ለማግኘት የሚደረግ የፊዚዮቴራፒ (Physical therapy) ሕክምና
  • የመግባባት አቅምን ለማሻሻል የሚደረግ የንግግር ሕክምና (Speech therapy)

ቤት ለቤት ከሚሰሩ ስራዎች አንዱ በተለያየ የጤና እክል ምክንያት ስለሚደረግ የሽንት ቱቦ ካቴተራይዜሽን ስለሚባል ሂደት እንመለከታለን

የሽንት ቱቦ ካቴተራይዜሽን ምንድን ነው?

ካቴተራይዜሽን የምንለው ሰዎች ተፈጥሮዋዊ በሆነ መንገድ ለመሽናት ሲቸገሩ ቀጭን ቱቦ ወደ ሽንት ፊኛቸው በማስገባት እንዲሸኑ ለማገዝ የሚረዳ ሂደት ነው።

የሽንት ቱቦ ካቴተር መቼ ሊታዘዝ ሊታዘዝ የሚችልበት ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው፡

  • አጣዳፊ የሆነ የሽንት አለመሽናት ሲኖር (ሙሉ ለሙሉ መሽናት ሲያስቸግር)
  • አንድ ታካሚ የሚወስደውን ፈሳሽ እና የሚያወጣውን ልኬት ማወቅ ሲያስፈልግ 
  • ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል ከመግባት በፊት
  • የመራቢያ አካላት ላይ ቀዶ ጥገና የተደረገላቸው ሰዎች 
  • ሽንታቸውን መቆጣጠር ለማይችሉ ሰዎች
  • ለብዙ ጊዜ አልጋ ላይ ለሚቆይ ሰው
  • የተለያዩ የጤና እክሎች ያለባቸው ሰዎች (multiple sclerosis, cord injury, dementia)

የሽንት ቱቦ ካቴተር የገባለት ሰው ምን አይነት እንክብካቤዎች ያስፈልጉታል?

ካቴተርዎን ከመንካትዎ ወይም ከመንከባከብዎ በፊት እና በኋላ ሁልጊዜ እጅዎን በሳሙና እና በውሃ ወይም በአልኮል (sanitizer) መታጠብ ይኖርብዎታል።

  • ከካቴተሩ የሚወጣው ሽንት የሚቀመጥበትን ፕላስቲክ በቀን ሁለት ጊዜ መቀየር
  • የመራቢያ አካላትን በየቀኑ ትንሽ ሳሙና እና ውሃ በመጠቀም ማጽዳት(ወንድ ከሆነ በፊት ለፊት የሚገኘውን ቆዳ ወደ ሁዋላ አድርጎ ማጽዳት፤ ሴት ከሆነች ደግሞ በጎን እና በጎን ያሉትን ቆዳዎች በመክፈት ከፊት ወደሁዋላ ማጽዳት
  • ሽንቱ የሚቀመጥበትን ፕላስቲክ ሁልጊዜ መሬቱ ላይ ማድረግ ወይም ከሽንት ፊኛ በታች ማድረግ 
  • የካቴተር ቱቦው እንዳይታጠፍ ወይም እንዳይጠማዘዝ ጥንቃቄ ማድረግ
  • የሽንት የሚቀመጥበትን ፕላስቲክ (drainage bag) ሁልጊዜ መሬቱ ላይ ማድረግ ወይም ከሽንት ፊኛ በታች ማድረግ ምክንያቱም ከፍ ካለ ሽንቱ ወደ ታች እንዳይፈስ ያደርጋል
  • በካቴተሩ ላይ ወይም ካቴተሩ ወደ ሰውነትዎ በሚገባበት አካባቢ ምንም ዓይነት ፓውደር ወይም ሎሽን አይቀቡ

ካቴተር ገብቶልዎት ባለበት ወቅት፣ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንን ለመከላከል እንዲረዳዎት በቂ ፈሳሽ መጠጣት ይኖርብዎታል። የሽንትዎ ቀለም ከጠቆረ፣ ይህ በቂ ፈሳሽ እንዳልወሰዱ የሚጠቁም በመሆኑ የሚጠጡትን የፈሳሽ መጠን መጨመር ይኖርብዎታል።

የሽንት ቱቦ ካቴተር የሚያስከትለው ጉዳቶች

ካቴተርን የመጠቀም ዋነኛው አደጋ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን (UTI) ነው። ካቴተሩን ለረጅም ጊዜ በተጠቀሙ ቁጥር ለዚህ ኢንፌክሽን የመጋለጥ እድልዎ እየጨመረ ይሄዳል።

ሌሎች የካቴተር ችግሮች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦

  • አለርጂ መፍጠር
  • የሽንት ፊኛ ጠጠር 
  • የደም ኢንፌክሽን (septicemia)
  • ደም የቀላቀለ ሽንት  (hematuria)
  • የኩላሊት ጉዳት (ለብዙ ጊዜ የሚጠቀሙ ሰዎች ላይ)
  • የኩላሊት ኢንፌክሽን
  • የሽንት ቧንቧ መቁሰል ወይም መጎዳት

የሽንት ቱቦ ካቴተር በገባልዎት ጊዜ እንደ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣  መግል የቀላቀለ ሽንት፣ በመራቢያ አካላት አካባቢ የማቃጠል ስሜት፣ ደም የቀላቀለ ሽንት ወይም መጥፎ ጠረን ያለው ሽንት ካዪ የሽንት ቱቦ ካቴተር ተያያዥ  ጉዳት ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ እነዚህን እና የተያያዙ ምልክቶችን ሲያዩ አቅራቢያዎ ወዳለ የህክምና ቦታ መሄድ ይኖሩበታል።

 

Comments (0)