ተወንጫፊ ማስታወክ ምንድነው?
ተወንጫፊ ማስታወክ ማለት ትውከት በድንገት በከፍተኛ ኃይል በመውጣት ብዙ ርቀት ከአፍ ውስጥ በመተኮስ የሚጓዝበት ሁኔታ ሲሆን በትናንሽ ሕፃናት ላይ በተለይም ከተመገቡ በኋላ ሊያዩት ከሚችሉት የተለመደ ማቃር ወይም ማስተፋት የተለየ አስደንጋጭ እና ድንገተኛ የማስመለስ አይነት ነው።
መንሰኤዎች
አልፎ አልፎ ማስታወክ ብዙ ጉዳት በሌላቸው ቀላል ምክንያቶች ሊከሰት ቢችልም ተወንጫፊ ማስታወክ በተለይም አዲስ በተወለዱ ሕፃናት እና ልጆች ላይ ልዩ ሁኔታዎችን ሊያመለክት ይችላል። አንዳንድ የተለመዱ መንስኤዎች የምንላቸው:-
1. ፓይሎሪክ ስቴኖሲስ
ከ3 ወር በታች በሆኑ አዲስ የተወለዱ ሕፃናት በተለይም ከ2-8 ሳምንታት እድሜ ላይ በጣም የተለመደ ሲሆን በጨጓራ የታችኛው ጫፍ ላይ ያለው ጡንቻ (ፓይሎረስ) ጠባብ ስለሚሆን ምግብ ወደ ትንሹ አንጀት እንዳይገባ ይከላከላል። ምልክቶች፡-
- ሕፃናቱ ከተመገቡ በኋላ ኃይለኛ ተወንጫፊ ማስታወክ
- የማያቋርጥ ረሃብ
- ክብደት መቀነስ ወይም ደካማ የሆነ ክብደት መጨመር
- ድርቀት
ወዲያውኑ የሕፃናት ሐኪምዎን በማነጋገር ፓይሎሪክ ስቴኖሲስ በቀላል ቀዶ ጥገና የሚታከም ሲሆን ብዙውን ጊዜ ህፃናቱ ከቀዶ ጥገና በኋላ በፍጥነት ይድናሉ።
2. የጨጓራ በሽታ
የጨጓራ እና የአንጀት ቫይረስ ወይም ባክቴሪያ ኢንፌክሽን በሚኖርበት ጊዜ ይከሰታል።
ምልክቶቹም፡-
- ማስታወክ
- ተቅማጥ
- ትኩሳት
- ደካማ የምግብ ፍላጎት
ልጅዎ በሰውነት ድርቀት እንዳይጎዳ በቂ ፈሳሽ መስጠት እና የጨጓራ ህመምን መንስኤ ለማከም የህክምና እርዳታን
3. የአንጎል ውስጥ ግፊት መጨመር
ከተወንጫፊ ማስታወክ በተጨማሪ በጨቅላ ሕፃናት እርግብግቢት (የጭንቅላት ለስላሳ ቦታ) ላይ ያልተለመደ እብጠት ካለ፣ የሚጥል በሽታ አይነት ማንቀጥቀጥ ወይም ራስን የመሳት ስሜት ምልክቶች ካስተዋሉ የድንገተኛ ጊዜ እንክብካቤን ይፈልጉ።
4.የአንጀት መዘጋት
እንደ የአንጀት መታጠፍ ወይም የአንጀት መወተፍ ያሉ የአንጀት መዘጋት ምክንቶች መንስኤዎች ሊሆን ሰለሚችሉ ደም የቀላቀለ ሰገራ፣ የሆድ እብጠት ወይም ምንም አይነት ሰገራን ካልዩ በአፋጣኝ የድንገተኛ ጊዜ እንክብካቤን ይፈልጉ።
መቼ የድንገተኛ ጊዜ እንክብካቤን ይፈልጉ?
ልጅዎ ላይ የሚከተለው ካለ ወደ በፍጥነት ለሕፃናት ሐኪምዎ ይደውሉ ወይም አስቸኳይ እርዳታን ይፈልጉ።
- ከአንድ ጊዜ በላይ የሚከሰት ተወንጫፊ ማስታወክ
- አረንጓዴ ቀለም ያለው ማስታወክ
- የሰውነት ድርቀት ምልክቶች:- የአፍ መድረቅ፣ እንባ አለመኖር፣ የሰረጎዱ አይኖች እና ጥቂት ወይም ያልረጠበ ዳይፐር
- ደካማ ክብደት መጨመር ወይም ክብደት መቀነስ
- የሆድ እብጠት ወይም በመንካት ጊዜ ህመም
- ቡና የሚመስል ወይም ደም ያለበት ትውከት
- ከመጠን በላይ እንቅልፍ ወይም ብስጭት
ልጅዎት ላይ ተወንጫፊ ማስታወክን መመልከት አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም እያንዳንዱ ማስታወክ ድንገተኛ አይደለም። ነገር ግን እንደ ወላጅ ስሜትዎን በማመን የሆነ ነገር ትክክል የማይመስል ከሆነ ከልጅዎ ጤና እንክብካቤ አቅራቢ ጋር ለመገናኘት አያቅማሙ።ያስታውሱ፣ ብቻዎን ከመጨነቅ ሁል ጊዜ መጠየቅ እና መረጋጋት የተሻለ ነው።



