የእናት እና የህጻን ጤና መጠበቅ የአንድ ሀገር ዕድገት እና የጤናማ ትውልድ መሰረት ነው። አብዛኛውን ጊዜ ትኩረታችን በእርግዝና ወቅት እና ከወሊድ በኋላ ባለው ጊዜ ላይ ቢሆንም፣ ከእርግዝና በፊት (Preconception care) የሚደረግ እንክብካቤ ግን ከሁሉም የበለጠ ወሳኝ ነው። ልጆችን በዕቅድ መውለድ እና አስቀድሞ መዘጋጀት ለቤተሰብ ብልጽግና መሰረት ነው።
ቅድመ-እርግዝና እንክብካቤ ምንድን ነው?
ከእርግዝና በፊት የሚደረግ እንክብካቤ ማለት፣ አንዲት ሴት እርጉዝ ከመሆኗ በፊት፣ የእሷን እና የባለቤቷን ጤና ለመጠበቅ፣ ለማሻሻል እና ለማንኛውም ችግር ቅድመ መፍትሄ ለመስጠት የሚደረግ ጥረት ነው። ይህ የህክምና ምርመራዎችን፣ የአኗኗር ዘይቤ ማሻሻያዎችን እና የስነ-ልቦና ዝግጅትን ያጠቃልላል።
ለምን አስፈለገ?
- ጤናማ እርግዝናን ለማረጋገጥ፡ የእናትን ጤና ማወቅ፣ እንደ ደም ግፊት፣ ስኳር፣ ወይም ሌሎች የውስጥ ደዌ በሽታዎችን አስቀድሞ በመቆጣጠር፣ በእርግዝና ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን (ለምሳሌ፡ የደም ግፊት መጨመር፣ የፅንስ መጨንገፍ) ይቀንሳል።
- የህጻኑን ጤና ለመጠበቅ፡ ህጻኑ ከተወለደ በኋላ ሊያጋጥሙት የሚችሉ የጤና ችግሮችን፣ እንደ ዝቅተኛ የውልደት ክብደት፣ ወይም የመውለድ ጉድለቶችን (ለምሳሌ፡ የነርቭ ቱቦ ጉድለቶች) አስቀድሞ ለመከላከል ይረዳል።
- የእናት ጤና አጠባበቅ፡ እርግዝና በእናትየው አካል ላይ ትልቅ ጫና ይፈጥራል። አስቀድሞ መዘጋጀት፣ እናትየው ይህን ጫና የመቋቋም አቅም እንዳላት ያረጋግጣል።
ከእርግዝና በፊት ምን መደረግ አለበት?
1. የህክምና ምርመራ
- ለእናቶች፡ እንደ ደም ግፊት፣ ስኳር፣ የደም አይነት፣ የHepatitis B፣ የHIV/AIDS እና የሌሎች የአባላዘር በሽታዎች ምርመራዎችን ማድረግ። በተጨማሪም፣ኩፍኝ ክትባቶችን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።
- ለአባቶች፡ የአባቶች ጤና በህጻኑ ጤና ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። እንደ HIV/AIDS ወይም ሌሎች የአባላዘር በሽታዎችን መመርመር አስፈላጊ ነው። የደም አይነት ምርመራ (Rh factor) ለሁለቱም ወላጆች ወሳኝ ነው።
2. የአኗኗር ዘይቤ ማሻሻል
- ጤናማ አመጋገብ፡ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ እንደ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ እና ፕሮቲን (ስጋ፣ እንቁላል፣ ጥራጥሬ) ያሉትን ማካተት። አስቀድሞ ፎሊክ አሲድ (Folic Acid) መውሰድ የመውለድ ጉድለቶችን ለመከላከል በጣም ወሳኝ ነው።
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፡ መካከለኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የእናትን ጤና ያሻሽላል እና በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱ ችግሮችን ይቀንሳል።
- አልኮል እና ሲጋራ አለመጠቀም፡ እነዚህን መርዛማ ነገሮች አለመጠቀም፣ የህጻኑን ጤና ለመጠበቅ ወሳኝ ነው። ሲጋራ ማጨስ የፅንስ እድገትን ሊያደናቅፍ ይችላል።
3. የስነ-ልቦና ዝግጅት
- የጋራ ውሳኔ እና ሃላፊነት፡ እርግዝና የባልና ሚስት የጋራ ውሳኔ መሆኑን መረዳት። ስለ ቤተሰብ እቅድ እና የወደፊት ህይወት አብሮ መወያየት አስፈላጊ ነው።
- የስነ-ልቦና ድጋፍ፡ ለእናቶች እና አባቶች የስነ-ልቦና ድጋፍ መስጠት፣ ጭንቀትን ለመቀነስ እና ሰላማዊ ቤተሰብ ለመገንባት ይረዳል።




