ስብ መቀነስ Vs ክብደት መቀነስ፡ ልዩነቱን መረዳት
ብዙ ሰዎች የጤና ጉዞአቸውን ሲጀምሩ በመጀመሪያ የሚጠቅሱት ግብ “ክብደት መቀነስ እፈልጋለሁ” የሚለውን ነው። ክብደት መቀነስ ጤናን ሊያሻሽል ቢችልም፣ በሚዛን ላይ ዝቅተኛ ቁጥር ማየት ብቻ በቂ አይደለም። በጣም አስፈላጊው ግብ የሰውነታችንን ስብ መቀነስ ነው። ስብ በመቀነስ እና ክብደት በመቀነስ መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት ሰዎች ጤናማ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ዘላቂ ውሳኔን እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።
ክብደት መቀነስ ምንድነው?
ክብደት መቀነስ አጠቃላይ የሰውነት ክብደት መቀነስን ሲያመለክት፣ ይህም የሚያጠቃልለው፡-
- የሰውነት ስብ
- የጡንቻዎችን
- የውሃ ክብደት እና
- ግልይኮጅን (የተከማቸ ሃይል ሰጪ ምግብ) ነው።
በሌላ አነጋገር፣ ሚዛን ላይ የሚያዩት ቁጥር ወረደ ማለት ጤናማ እየሆኑ ነው ወይም የሰውነት ስብ እየቀነሱ ነው ማለት አይደለም።
ፈጣን ክብደት መቀነስን የሚያመጡ የተለመዱ ምክንያቶች
በሚከተሉት ምክንያቶች ሰዎች ክብደት በፍጥነት ሊቀንሱ ይችላሉ።
- ከባድ የካሎሪ ገደብ ካደረጉ
- የሰውነት ፈሳሽ በማጣት የሚመጣ ድርቀት
- ህመም
- ከመጠን በላይ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ
ለምሳሌ፣ አንድ ሰው በጣም ዝቅተኛ-ካርቦሃይድሬት ባለው አመጋገብ በሳምንት ውስጥ ከ3-5 ኪሎ ግራም ሊቀንስ ይችላል፣ ነገር ግን አብዛኛው ቀድሞ የሚከሰትው ከስብ ይልቅ የውሃ ክብደት መቀነስ ነው።
ስብ መቀነስ ምንድን ነው?
ስብ መቀነስ ማለት በተለይ የጡንቻን መጠን በመጠበቅ የሰውነት ስብን በማጥፋት ላይ ያተኮረ ነው። ይህኛው ክብደት የመቀነስ መንገድ በአጠቃላይ ጤናማ እና የበለጠ ዘላቂነት ያለው ግብ ነው። ስብን መቀነስ:-
- የደም ስኳር ቁጥጥርን ያሻሽላል
- የደም ግፊትን ለመቆጣጠር ይረዳል
- የኮሌስትሮል መጠንን ለመቆጣጠር ይረዳል
- የአካል ብቃትን
- የሰውነትን ክብደት ለረጅም ጊዜ ለመመጠን ይረዳል
አጠቃላይ ክብደት ከመቀነስ በተለየ መልኩ ስብ መቀነስ አጠቃላይ የሰውነት ስብጥርን በማሻሻል ላይ ያተኩራል።
የሚዛን ቁጥር ለምን አሳሳች ሊሆን ይችላል?
ሰዎች ሚዛን ላይ የሚያዩት ቁጥር በፍጥነት በማይለወጥበት ጊዜ ተስፋ ይቆርጣሉ። ሆኖም ግን የሰውነት ክብደት በሚከተሉት ምክንያቶች በተፈጥሮ ይለዋወጣል
- የሰውነት ውሃ ማጠራቀም
- የሆርሞን ለውጦች
- ብዙ ጨው በመውሰድ
- ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማገገም
- በምግብ አፈጫጨት ለውጦች
ጥሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርግ እና በአግባቡ የሚመገብ ሰው ስቡን እያጠፋ ጡንቻውን ሊጨምር ይችላል። በዚህ ሁኔታ ጤንነታቸው እና ቁመናቸው እየተሻሻለ ቢሆንም ሚዛኑ ላይ የሚያዩት ቁጥር ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል።
ስለዚህ ባለሙያዎች በሰውነት ክብደት ላይ ብቻ ከመተማመን ይልቅ እነዚህን መከታተል ይመክራሉ።
- የወገብ ዙሪያ ልኬት
- የኢነርጂ ደረጃዎች
- ጥንካሬ እና የአካል ብቃት
- የልብስ መስፋት እና መጥበብ
- መለኪያው ካለ የሰውነት ስብ መቶኛ ልኬት
ጡንቻ ዋጋ አለው!
የጡንቻ ሕብረ ሕዋስ በሜታቦሊዝም በጣም ንቁ ነው። ይህም ማለት በእረፍት ጊዜ እንኳን ሰውነት ተጨማሪ ካሎሪዎችን እንዲያቃጥል ይረዳዋል። ሰዎች በፍጥነት ክብደታቸውን ሲቀንሱ ከስብ ጋር ጡንቻን ሊያጡ ሲችሉ። ይህም:-
- ሜታቦሊዝምን ያዘገያል
- ጥንካሬን ይቀንሳል
- ድካምን ይጨምራል
በክብደት መቀነስ ወቅት የተመጣጠነ ምግብ መመገብን እና ስፖርታዊ ስልጠናን አስፈላጊ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ የጡንቻን መጠን መጠበቅ ነው።
ጤናማ የስብ መቀነስ Vs ጤናማ ያልሆነ ክብደት መቀነስ
ጤናማ የሆነ የስብ መቀነስ
ጤናማ የስብ መቀነስ የሚከተሉትን ያጠቃልላል።
- መጠነኛ የካሎሪ ቅነሳ
- መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ
- የጥንካሬ ስልጠና
- በቂ ፕሮቲን መውሰድ
- ጥሩ እንቅልፍ መተኛት
- የረጅም ጊዜ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች
በሳምንት ከ 0.5 -1 ኪ.ግ (1-2 ፓውንድ) መቀነስ ተቀባይነት ያለው ክብደት የመቀነስ ፍጥነት ነው።
ጤናማ ያልሆነ ክብደት መቀነስ
ጤናማ ያልሆኑ ክብደት የመቀነስ ዘዴዎች የሚከተሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ:-
- እራስን ማስራብ
- የዲቶክስ ሻይ ወይም እንክብሎችን
- ከመጠን በላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረግ
- ከባድ የሰውነት እርጥበት ማስወገጃ ዘዴዎች
እነዚህ ዘዴዎች ጊዜያዊ ክብደት መቀነስ ሊያስከትሉ ቢችሉም፣ ነገር ግን ለረጅም ጊዜ ለማቆየት አስቸጋሪ ናቸው። እነዚህ ዘዴዎች በተጨማሪም ጤና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።
ለጤና የትኛው የተሻለ ነው?
ስብን መቀነስ በአብዛኛዎቹ ሁኔታዎች አጠቃላይ ክብደትን ከመቀነስ የተሻለ የበለጠ ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ፡-
- ጡንቻውን እየጠበቀ ስቡን የሚቀንስ ሰው ትንሽ ክብደት ቢቀንስም ጤናማ ሊሆን ሲችል
- ሌላ ብዙ ክብደትን በፍጥነት የቀነስ ሰው ብዙ ጡንቻ እና ውሃ ስለሚያጣ ሰውነቱን ያዳክማል።
ለዘላቂ የስብ መቀነስ ጠቃሚ ምክሮች
1. ለፕሮቲን ቅድሚያ ይስጡ
ፕሮቲን በስብ ቅነሳ ወቅት ካሎሪ ለመቀነስ እና ጡንቻን ለመጠበቅ ይረዳል። ጥሩ የፕሮቲን ምንጮች የሚከተሉትን ያካትታሉ።
- እንቁላል
- ዓሳ
- ዶሮ
- ምስር
- ባቄላ
2. የጥንካሬ ስልጠናን ያካትቱ
ክብደት እንደማንሳት ያሉ የጥንካሬ ልምምዶች ጡንቻን ለመጠበቅ እና ለመገንባት ይረዳሉ።
3. እራስዎን አያስርቡ
እራስን ከመጠን በላይ በማስራብ የሚመጣ ፈጣን ክብደት በዘላቂነት ለመቀጠል አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ የጤና እክል ሊያስከትልብዎ ይችላል።
4. በቂ እንቅልፍን ያግኙ
ደካማ እንቅልፍ የረሃብ ሆርሞኖችን እና የምግብ ፍላጎትን ይጨምራል።
5. በረጅም ጊዜ ልማዶች ላይ ያተኩ
ዘላቂ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች ከአጭር ጊዜ የምግብ ገደቦች የበለጠ ውጤታማ ናቸው።




