ከወላጆች መለያየት ቋሚ አለመሆኑን መማር የህፃናት ተፈጥሯዊ እድገት አካል ነው። ይህም የመለያየት ስጋት በብዛት የሚከሰተው ከ6 ወር እስከ 3 አመት ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ ነው። ትናንሽ ህፃናት ወላጆቻቸው ወይም ዋና ተንከባካቢያቸው ከዓይናቸው ሲሰወሩ ጭንቀት ሊሰማቸው ይችላል ፣ ይህም የሆነው መለያየቱ ጊዜታዊ ብቻ መሆኑን ገና በሚገባ ባለመረዳታቸው ነው።
በልጅዎ ላይ የመለያየት ስጋት መኖሩን የሚጠቁሙ ዋና ዋና ምልክቶች
- ከፍተኛ ልቅሶ እና መረበሽ ፦ ከወላጅ በሚለዩበት ወቅት በቀላሉ የማይቆም ለቅሶ ፣ መወራጨት ወይም ቁጣ ማሳየት
- ወላጅን አጥብቆ መያዝ (Clinging) ፦ ከወላጅ ጋር ቋሚ አካላዊ ንክኪ መፈለግ ወይም በሄዱበት ሁሉ መከተል
- የእንቅልፍ መዛባት ፡ ወላጅ አጠገብ ሳይኖር ለብቻ ለመተኛት መፍራት ወይም ስለመለያየት አስፈሪ ህልሞችን ማየት
- አካላዊ መረበሾችን መግለጽ ፦ የመለያየት ሰዓት ሲደርስ የሆድ ህመም ፣ የራስ ምታት ወይም የማቅለሽለሽ ስሜት ይሰማኛል ማለት
ት/ቤት ወይም ህፃናት ማቆያ የመሄድ እምቢተኝነት ፦ ከቤት ለመውጣት ወይም ወላጅን ጥሎ ት/ቤት ለመግባት መጨነቅና መቃወም
የልጆችን የመለያየት ጭንቀት በጤናማ ሁኔታ ለመቆጣጠር የሚረዱ 6 ውጤታማ መንገዶች
- ቀስ በቀስ ማለማመድ ፦ መጀመሪያ ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ በመለየት ፣ ልጅዎት ተመልሰው እንደሚመጡ ያለውን እምነት እንዲያሳድግ ያድርጉ።
- አጭር የመሰናበቻ ልምድ መፍጠር ፦ በየቀኑ የሚደገም አጭር እና ፍቅር የተሞላበት የደህና ሁን አባባል ማለማመድ ልጅዎት እንዲረጋጋ ይረዳዋል።
- ቃልን መጠበቅ ፦ ተመልሰው የሚመጡበትን ሰዓት ለልጅዎት በግልጽ በመናገር በገቡት ቃል መሰረት በሰዓቱ ይገኙ።
- ቋሚ የጊዜ ሰሌዳ መከተል ፦ ሁልጊዜ በተመሳሳይ ሰዓት መሄድና መምጣት ለልጅዎት የደህንነት ስሜት ይሰጠዋል።
- የተረጋጋ ገጽታ ማሳየት ፦ ልጅዎትን በሚለዩበት ወቅት ጭንቀት ካላሳዩ ፣ ልጅዎት ሁኔታው ከባድ እንዳልሆነ ቀስ በቀስ ይረዳል።
አዲስ አካባቢን ማስተዋወቅ ፦ ልጅዎትን አስቀድመው ከአዲቡ ቦታ ወይም ክሚቆዩበት ሰው ጋር በደንብ ማስተዋወቅ ጭንቀታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሰዋል።
የልጆች የመለያየት ስጋት በሚኖርበት ወቅት መደረግ የሌለባቸው ድርጊቶች
- ተደብቆ መውጣት ፦ ልጆች ሳያዩ በድንገት መሄድ በልጅዎት ላይ ከፍተኛ ፍርሃትና በእርስዎ ላይ ያለውን እምነት እንዲያጣ ያደርገዋል ።
- መሰናበቻውን ማርዘም ፦ ልጅዎት ሲያለቅስ እየተመለሱ በማቀፍና በመሳም መሰናበቻውን ማርዘም ፣ መለያየቱ ለልጅዎት ይበልጥ ከባድ ያደርገዋል። ሲያለቅሱ ተመልሶ ማግኘቱም “ ካለቀስኩ ይመጣሉ” የሚል ተስፋ እንዲሰርጽ ያደርጋሉ።
መቆጣት ወይም መጮህ ፦ ልጅዎት በመለየቱ ምክንያት ስለፈራ መቆጣት የበለጠ እንዲጨነቅ ከማድረጉም ባለፈ ስሜቱን እንዲደብቅ ያስገድደዋል።
በመጨረሻም የመለያየት ስጋት የልጆች እድገት ተፈጥሯዊ ሂደት መሆኑን ተረድቶ በትዕግስት እና በርህራሄ መያዝ እጅግ አስፈላጊ ነው። በፍቅር እና በቋሚ ልምምድ የሚሰጥ ድጋፍ፣ ልጅዎት በራስ መተማመኑ እንዲጨምርና በጊዜ ሂደት ራሱን ችሎ እንዲቆም ይረዳዋል።



