ስለ ርግብግቢት(Fontanelle) ማወቅ ያልብዎት ነገሮች

Betelhem Kenea
Jun 16, 2026
undefined

የጨቅላ ሕፃንዎን የራስ ቅል በእጅዎ ሲዳስሱ በዙሪያው ካለው ጠንካራ አጥንት በተለየ ለስላሳ ቦታ መኖሩን አስተውለው ይሆናል።በተጨማሪም ሕፃንዎ ላይ እንዲህ አይነት ለስላሳ ቦታ መኖሩ ተፈጥሮአዊ ነው ወይስ እክል ነው ብለው አስበው ሊሆን ይችላል።  ይህ በራስ ቅል ላይ ያለ ለስላሳ ቦታ ርግብግቢት (Fontanelle) ብለን የምንጠራው ሲሆን በጨቅላ ሕፃናት ላይ የሚኖር በዙሪያው ባሉ አጥንቶች መካከል የሚፈጠር ተፈጥሮአዊ ክፍተት ነው። 

በእውነቱ ከሆነ የሕፃንዎ ርግብግቢት የተለየ ክትትል እና ትኩረት ባይፈልግም የጨቅላ ሕፃናት ምን ያህል ስስ እና ጥንቃቄ የሚሹ መሆናቸውን የሚያስታውስ ትልቅ ምልክት ነው።

ርግብግቢት (Fontanelle) ምንድን ነው?

የአንድ ጨቅላ ሕፃን ጭንቅላቱ ትልቁ የሰውነት ክፍሉ ነው። ይህ የሰውነት ክፍል በበርካታ አጥንቶች መገናኘት የተፈጠረ ሲሆን ፤ እርስ በርሳቸውም በስፌት መሰል መጋጠሚያዎች (Sutures) ተያይዘዋል።  ይሁን እንጂ፤ ሶስት እና አራት አጥንቶች በሚገናኙበት ቦታ ላይ የተፈጠረ ክፍተት ርግብግቢት ወይም ፎንታኔል (Fontanelle) ተብሎ ይጠራል።

የፊተኛው ርግብግቢት (Anterior fontanelle) የሚገኘው በትክክል የሕፃንዎ ራስ አናት ላይ ነው። አብዛኛውን ጊዜ በእጅዎ የልጅዎን ጭንቅላት ሲነኩ ለስለስ ብሎ የሚሰማዎት ክፍል ይህ ነው። የፊተኛው ርግብግቢት ስፋቱ በአማካይ 2.1 ሴንቲ ሜትር ሲሆን መጠኑም የአንድ ስሙኒ ሳንቲም ያህል ነው። አብዛኛውን ጊዜ የልጅዎ የመጀመሪያ የልደት በዓል ካለፈ በኋላ የፊተኛው ርግብግቢት ብዙም ሳይቆይ ይዘጋል።

የኋለኛው ርግብግቢት (Posterior fontanelle) ደግሞ ከፊተኛው ርግብግቢት የሚያንስ ሲሆን መጠኑም ወደ 0.5 ሴንቲሜትር ያህል ነው። በአማካኝም የኋለኛው ርግብግቢት የሚዘጋው ሕፃንዎ የ2 ወይም የ3 ወር እድሜ ሲደርስ ነው።

ርግብግቢት መኖሩ ምን ይጠቅማል?

ከወራት እስከ አመት ባለው ጊዜ ውስጥ ይህ ርግብግቢት የሚዘጋ ከሆነ መጀመሪያውኑስ መኖሩ ምን ጥቅም ይኖረዋል ብለው አስበው ይሆናል። በጨቅላ ሕፃናት ላይ ርግብግቢት መኖሩ የሚከተሉት ጥቅሞች አለው።

  1. በወሊድ ወቅት የሕፃኑን ራስ ቅል ቅርጽ በመቀየር (molding) ከማህፀን በቀላሉ እንዲያልፍ ይረዳል
  2. ፈጣን የአዕምሮ እድገት እንዲኖር ይረዳል ፡ ከወሊድ በኋላ የሕፃን አእምሮ በጣም በፍጥነት ያድጋል። ይህም ስለሆነ የርግብግቢት መኖር በጨቅላነት እና በልጅነት እድሜ ጭንቅላት ሲያድግ አብሮ የራስ ቅል እንዲሰፋ ያስችላል።
  3. ከቀላል ግጭቶች ይጠብቃል፡ የጨቅላ ሕፃን የራስ ቅል የመለጠጥ ባህሪ ያለው መዋቅር መሆኑ ቀላል ተጽዕኖዎችን የመቀበል እና የማሰራጨት ችሎታ ስላለው እያደገ ላለው አእምሮ ጥበቃን ይሰጣል።
  4. የሕፃንዎን ጤንነት ለመከታተል ይረዳል፡ የሕፃንዎን የራስ ለስላሳ ቦታ በእጅዎ በመዳሰስ የሕፃንዎን ጤንነት በቀላሉ መከታተል እና በሽታን ሊያመለክቱ የሚችሉ ማናቸውንም ለውጦች ማወቅ ይችላሉ።
  5. የምርመራ ሂደቶችን ለማከናወን ይረዳል፡ የሕፃን ራስ ላይ የሚገኘው ይህ ክፍተት የጤና ባለሙያዎች እንደ አልትራሳውንድ ያሉ ምርመራዎችን በማድረግ የአዕምሮ ጤንነትን በቀጥታ እንዲገመግሙ ያስችላቸዋል።

ርግብግቢት ላይ የሚኖሩ ለውጦች ምን ያሳያሉ?

በጨቅላ ህፃንዎ ርግብግቢት ላይ የሚታዩ ለውጦች የሕፃንዎ አጠቃላይ ጤንነት አመላካች ሊሆኑ ይችላሉ።

         የርግብግቢት መወጠር (መጎበጥ) 

የጨቅላ ህፃንዎ ርግብግቢት ወጠር ብሎ ከታይዎት ወይም ያበጠ ከመሰልዎት ፤ ምክንያቶቹ የሚከተሉት ሊሆኑ ይችላሉ።

  • የህፃንዎ ርግብግቢት ማበጥ የጀመረው ከወደቀ በኋላ ከሆነ፤ ይህ የጭንቅላት ጉዳት ሊሆን ስለሚችል ወዲያውኑ የሕክምና እርዳታ ማግኘት አለብዎት። የጭንቅላት ጉዳት ሲኖር ተያይዞ የሚመጣ የመወርወር ፀባይ ያለው ማስመለስ/ማስታወክም ሊኖራቸው ይችላል።
  • የልጅዎ ርግብግበት ወጠር ብሎ ከታየዎት ነገር ግን ምንም አይነት የመውደቅ አደጋ ካላገጠመው፤ መንስኤው የቫይረስ ወይም የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ሊሆን ይችላል። ይህም ሲሆን ህፃናት በተጓዳኝ ትኩሳት ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ፣ ያለወትሮ መነጫነጭ ወይም ከመጠን በላይ መተኛት ሊታይባቸው ይችላል።
  • አልፎ አልፎ የርግብግቢት ማበጥ መንስኤ ሃይድሮሴፋለስ (Hydrocephalus) ሊሆን ይችላል። ይህም ማለት የአንጎል ውስጥ ፈሳሽ መከማቸቱ ሲሆን የራስ ቅሉ እንዲሰፋ እና ይህን ተከትሎ ርግብግቢት ወጠር ብሎ እንዲታይ ያደርገዋል።
  • በተጨማሪውም ፤ የርግብግቢት ማበጥ መንስኤዎቹ  አንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ ወይም በጭንቅላት ውስጥ ጫና የሚፈጥር እጢ መኖርም ሊሆን ይችላል።

          የርግብግቢት መሰርጎድ

ወደ ውስጥ የገባ/ የሰረጎደ ርግብግቢት በአብዛኛው የሚከሰተው በሰውነት ውስጥ ፈሳሽ እጥረት (Dehydration) ሲከሰት ነው። ይህም በተደጋጋሚ ተቅማጥ ፣ ማስመለስ ፣ በቂ ፈሳሽ አለመውሰድ ወይም በከፍተኛ ትኩሳት ምክንያት ሊከሰት ይችላል።

ከእነዚህ ጋር በተያያዘ የሚታዩ የድርቀት ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው።

  • የአፍ እና የምላስ መድረቅ
  • የሽንት መጠን መቀነስ
  • ድካም ወይም እንቅልፍ መብዛት
  • የዓይኖች መሰርጎድ
  • በሚያለቅሱበት ጊዜ እንባ አለመኖር ወይም መቀነስ

          ቀድሞ የሚዘጋ ርግብግቢት 

የሕፃንዎ ጭንቅላት በመደበኛ ሁኔታ እያደገ ከሆነ ፣ ርግብግቢታቸው ብዙም ጉልህ ሆኖ ባይሰማዎትም ብዙ የሚያሳስብ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ፤ የሕፃንዎ ርግብግቢት ከላይ ከተገለጸው ጊዜ በፊት ተዘግቷል ብለው ከጠረጥሩ የጤና ባለሙያዎች እንዲመረምሩት ማድረግ አስፈላጊ ነው።

አንዳንድ ጊዜ የርግብግቢት ከጊዜው በፊት መዘጋት ምክንያቱ ክራኒዮሲኖስቶሲስ (Craniosynostosis) ተብሎ የሚጠራ የጤና እክል ነው። ይህም የሕክምና ሁኔታ የሚከሰተው የጭንቅላት አጥንቶችን የሚያገናኙት ሱቸሮች (sutures) ከተገቢው ጊዜ በፊት ሲዘጉ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ይህ በሽታ የሕፃናትን የጭንቅላት ቅርጽ ሊቀይር ቢችልም በጊዜው በቀዶ ሕክምና ከታከመ ግን በጨቅላ ሕፃንዎ ላይ ለወደፊት ተጨማሪ የጤና ችግር አያስከትልም። በጊዜ ካልታከመ ግን የጭንቅላት ግፊት መጨመር ፣ ራስ ምታት ፣ የእይታ ችግር ፣ እንዲሁም በአንዳንድ ሕፃናት በእድሜአቸው ከሚጠበቀው እድገት መዘግየት ሊያስከትልባቸው ይችላል።

          የርግብግቢት መስፋት/ መተለቅ

የርግብግቢት ከተለመደው ጊዜ ቀድሞ መዘጋት የጤና እክል አመልካች እንደሆነው ሁሉ፣ ከተለመደው ጊዜ ዘግይቶ መዘጋቱ እና መስፋቱም የተወሰኑ የጤና ችግሮች ምልክት ሊሆን ይችላል።

  • አኮንድሮፕሌዢያ (Achondroplasia) : የአጥንት ማያያዣ ሕብረ ሕዋስ (Cartilage) እና የአጥንት እድገትን የሚጎዳ ህመም ሲሆን አኮንድሮፕሌዢያ ያለባቸው ሰዎች በዋነኛነት አጭር ቁመትም  ይኖራቸዋል።
  • ሃይፖታይሮዲዝም (Hypothyroidism) ፡ ይህም በታይሮይድ ሆርሞን ምርት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር የታይሮይድ እጢ ችግር ነው። 
  • ዳውን ሲንድረም (Down syndrome) ፡ በዳውን ሲንድረም የሚታየው የርግብግቢት ዘግይቶ መዘጋት በአጥንት እድገትና መጠንከር (ossification) መዘግየት ምክንያት ነው። እንዲሁም ከዳውን ሲንድረም ጋር ተያይዞ ሊኖር የሚችለው የታይሮይድ ሆርሞን እጥረት (hypothyroidism) ይህን መዘግየት የበለጠ ሊያባብሰው ይችላል። 
  • የቫይታሚን ዲ እጥረት (Rickets): ሪኬትስ በቫይታሚን ዲ እጥረት ምክንያት በአጥንት መገንባት (ossification) ላይ መዘግየትን የሚያስከትል በሽታ ሲሆን፣ እንደ የራስ ቅል አጥንት መለስለስ (Craniotabes) ፣ የእጅ አንጓ እና የቁርጭምጭሚት ማበጥ ፣ የአከርካሪ አጥንት ቅርጽ መዛባት(Scoliosis) ፣ እግር መጣመም (bow legs) ያሉ ሌሎች ምልክቶችንም ሊያሳይ ይችላል።
  • በአንጎል ውስት የሚፈጠር የግፊት መጨመርም የዘገየ የርግብግቢት መዘጋት እና መተለቅ ያመጣል።

ሆኖም ግን እነዚህ የጤና እክሎች ከርግብግቢት ዘግይቶ መዘጋት በተጨማሪ ሌሎች ምልክቶች እንደሚኖሯቸው በመገንዘብ ሕፃንዎ በመደበኛ ሁኔታ እያደገ ከሆነ ብዙም መጨነቅ አያስፈልግዎትም።

የሕፃንዎን ርግብግቢት እንዴት መንከባከብ ይችላሉ?

  • ርግብግቢት ጠንካራ በሆነ የመከለከያ ሽፋን (membrane) የተሸፈነ በመሆኑ ፤ የሕፃንዎን ርግብግቢት ሆነ ራስ በጥንቃቄ ከመዳሰስ ፣ ከማጠብ እና ከማበጠር አይከለክልዎትም። 
  • ሕፃንዎን ሲይዙ ሁልጊዜ ጭንቅላቱን እና አንገቱን ይደግፉ ፤ እንዲሁም በዚህ ለስላሳ የራስ ክፍል ላይ ከመጠን በላይ ጫና ከማሳረፍ ይቆጠቡ።
  • ሕፃንዎ ከእንቅልፍ ነቅቶ በሚቆይበት ጊዜ የጭንቅላቱን አቅጣጫ በመቀያይር እና አልፎ አልፎም በእርስዎ ክትትል በሆዱ እንዲተኛ በማድረግ የራስ ቅሉ ቅርጽ በጊዜ ሂደት ጠፍጣፋ (Plagiocephaly) እንዳይሆን ይከላከሉ።
  • በተጨማሪም ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች :-የርግብግቢት መጉበጥ ፣ መሰርጎድ ፣ ያለጊዜው ወይም ዘግይቶ መዘጋት ካስተዋሉ ወደ ጤና ባለሙያ ልጅዎትን በመውሰድ የሕፃንዎን ጤና መጠበቅ ይችላሉ።

Comments (0)