ለልጆች የቀን እንቅልፍ (Napping) ፦ ለሁለንተናዊ ዕድገት የማይተካ የጤና ፍላጎት

Betelhem Kenea
Jun 18, 2026
undefined

ልጆች በቀን ውስጥ የሚያስፈልጋቸው የእንቅልፍ መጠን ቢለያይም የቀን እንቅልፍን በአግባቡ ማግኘት ለማስታወስ ችሎታ መጎልበት ፣ ለስሜት መረጋጋት እና ለሌሎችም የጤና ጥቅሞች ወሳኝ ሚና ይጫወታል። 

በመሆኑም ልጆች በቂ እረፍት ካላገኙ አካላዊ እና አእምሮአዊ ብቃታቸው ሊቀንስ ስለሚችል እንደ እድሜያቸው ተገቢውን የእንቅልፍ ሰዓት ማግኘት ይኖርባቸዋል።

           የቀን እንቅልፍ ለልጆች የሚሰጣቸው ጥቅሞች

በቀን ውስጥ ለጥቂት ሰአታት የሚወሰድ እንቅልፍ ከእረፍት ባለፈ ለአካላዊ እና አእምሮአዊ ጤና የሚሰጣቸው ጥቅሞች የሚከተሉት ናቸው። 

    1. የማስታወስ እና የመማር ብቃት 

እውነታን የማስታወስ ብቃት (Declarative Memory) : በቀን ውስጥ የተወሰነ እንቅልፍ የሚተኙ ህፃናት አዳዲስ ቃላትን ፣ ቁጥሮችን እና ትምህርታዊ መረጃዎችን የማስታወስ ብቃታቸው ከማይተኙ ህፃናት በከፍተኛ ሁኔታ ይበልጣል፤ ምክንያቱም እንቅልፍ መተኛት የተማሩትን እውቀት ከአጭር ጊዜ ወደ ረጅም ጊዜ ትውስታ ለማሸጋገር ስለሚረዳ ነው።

ክስተቶችን የማስታወስ ብቃት (Episodic Memory) : እንቅልፍ አእምሮ የዕለት ተዕለት ልምዶችን በቅደም ተከተል እንዲደራጁ ስለሚረዳ ልጆች በቀን ውሎአቸው ያጋጠሟቸውን ክስተቶች ይህም ለምሳሌ :- ‘ዛሬ ትምህርት ቤት ምን ተማርን? ፤ ዛሬ መናፈሻ ሄደን ምን ተጫወትን?’  እና የመሳሰሉትን በዝርዝር የማስታወስ ችሎታቸውን ይጨምራል። 

ክህሎትን የማስታወስ ብቃት (Procedural Memory) : የቀን እንቅልፍ አእምሮ በልምምድ ያገኘውን አካላዊ ክህሎት (ለምሳሌ ፦ ጫማ ማሰር ፣ ብስክሌት መንዳት) እንዲአሰርጽ ስለሚረዳ፣ ህፃናት አዳዲስ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን እና ቴክኒኮችን በፍጥነት እንዲለምዱ ያግዛል። 

   2. የስሜት ብስለት እና መረጋጋት

ሳይንቲስቶች እንቅልፍን 'የስሜት ማረጋጊያ’ ይሉታል። ልጆች በቂ የቀን እንቅልፍ ካገኙ ለሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች የተረጋጋ ምላሽ እንዲሰጡ እና በጨዋታም ጊዜ ከጓደኞቻቸው ጋር የተሻለ ማህበራዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው ያደርጋል።

አንድ ህፃን በቂ የቀን እንቅልፍ ካላገኘ ስሜቱን የመቆጣጠር አቅሙ ይዳከማል። ይህም ለከፍተኛ ለቅሶ ፣ ለንዴት እና ለብስጭት ይዳርገዋል።

   3. የተሻለ ትኩረት እና ንቃት 

የቀን እንቅልፍ የአእምሮን ድካም በማስወገድ ህፃኑ ከእንቅልፍ በኋላ አዳዲስ ነገሮችን ለመመርመርና ለመማር ዝግጁ እንዲሆን ያደርገዋል። 

በቂ እንቅልፍ የሚያገኙ ልጆች በትምህርት ቤት ወይም በቤት ውስጥ የሚሰጣቸውን መመሪያዎች የመቀበልና የመፈጸም አቅማቸው ከፍተኛ ነው። 

             “እንቅልፍ እንቅልፍን ይወልዳል”

ብዙ ወላጆች ልጃቸው በቀን ካልተኛ ማታ የተሻለ እንቅልፍ ይተኛል ብለው ያምናሉ። ይሁን እንጂ ህፃናት በተለይ ከአምስት አመት በታች የሆኑት የቀን እንቅልፍ ካላገኙ ከመጠን በላይ ንቁ እና ተነጫናጭ ይሆናሉ ፤ ይህም ማታ በመደበኛው ሰዓት ለመተኛት እንዲቸገሩ ያደረጋቸዋል።        

            የቀን እንቅልፍ እና የአእምሮ መብሰል 

ልጆች የቀን እንቅልፍ በቂ ማግኘታቸው አስፈላጊ ቢሆንም እንቅልፍ የመተኛት ፍላጎታቸው እድሜአቸው በጨመረ ቁጥር እየቀነሰ ይመጣል። 

ልጆች የቀን እንቅልፍ ፍላጎታቸው መቀነስ አእምሮአቸው መረጃን የማቀናጀት እና የመሸከም አቅሙ እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ተፈጥሮአዊ የብስለት ምልክት እንጂ የእንቅልፍ እጥረት ችግር አለመሆኑም መረዳት ይገባል።

ልጅዎ የቀን እንቅልፍ መተኛት ካቆመ እና በቀን ውስጥ ንቁ፣ ደስተኛ እንዲሁም ማታ ላይ በደንብ የሚተኛ ከሆነ፣ ይህ የአእምሮው መብሰል ምልክት ሊሆን ስለሚችል የግድ እንዲተኛ ማስገደድ ላይጠበቅብዎት ይችላል። 

የእድሜ ክልልየጠቅላላ እንቅልፍ መጠን (በ24 ሰዓት)የቀን እንቅልፍ ሁኔታ
0-4 ወራት14-17 ሰዓትበቀን 3-4 ጊዜ
4-12 ወራት12-15 ሰዓትበቀን 2 ጊዜ (ጠዋትና ከሰዓት)
1-2 ዓመታት11-14 ሰዓትበቀን 1 ጊዜ (1-2 ሰዓት የሚቆይ)
3-5 ዓመታት10-13 ሰዓትእንደ አስፈላጊነቱ / ወደ ጸጥታ ጊዜ ሊቀየር ይችላል
ከ5 ዓመት በላይ9-12 ሰዓትቀስ በቀስ ሙሉ በሙሉ ሊቆም ይችላል

ይህ ሽግግር አእምሮአቸው በጥቂት እንቅልፍ ራሱን እንዲያረጋጋ ፣ መረጃዎችን እንዲያደራጅ እና ለሌሊት እረፍት እንዲዘጋጅ የቀን እንቅልፍ ጊዜ ከስልክና ከማንኛውም ትኩረት ከሚበታተኑ ነገሮች በራቀ የጸጥታ ጊዜ መተካት ይኖርበታል ።

Comments (0)