ልጅዎ ማታ ማታ እግሬን አመመኝ! እያለ ከእንቅልፉ ይባንናል?

Elsabet Azezew
Jun 30, 2026
undefined

                          ልጅዎ ማታ ማታ እግሬን አመመኝ! እያለ ከእንቅልፉ ይባንናል? 

                              የዕድገት ሕመም ምንድን ነው ?

ይህ በህፃናት ላይ ለእግር ሕመም መንስኤ ከሆኑ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን በአብዛኛው ዕድሜያቸው ከ3 እስከ 12 ዓመት በሆኑ ሕፃናት ላይ ይስተዋላል። ስሙ "የዕድገት ሕመም" ይባል እንጂ  ከሰውነት ማደግ ሂደት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። 

ቀደም ሲል ሰዎች ይህ ሕመም የሚከሰተው አጥንቶች በፍጥነት በሚያድጉበት ጊዜ እንደሆነ ስለሚያምኑ ይህንን ስያሜ ሰጥተውታል። ይሁን እንጂ ከዕድገት ጋር ምንም ዓይነት ትስስር እንደሌለው በምርምር ቢረጋገጥም ስሙ ግን ሳይቀየር እስካሁን ሊዘልቅ ችሏል። የዚህ እክል ትክክለኛ መንስኤ በውል ባይታወቅም በሕፃኑ አካል ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳያስከትል በራሱ ጊዜ ይጠፋል። 

              የዕድገት ሕመም (Growing pains) በእርግጥ እውነተኛ ሕመም ነው? 

አዎ፣ የዕድገት ሕመም ልጅዎ በእርግጥም የሚሰማው እውነተኛ የእግር ቁርጥማት ነው። ስለዚህ ይህ ስሜት ሕፃኑ በምናቡ የፈጠረው ወይም ለማስመሰል የሚናገረው ሳይሆን በትክክል የሚያምመው እውነተኛ ክስተት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። 

                የዕድገት ሕመም ምልክቶች ምንድን ናቸው? 

የዕድገት ሕመም በአብዛኛው በሕፃናት እግር ላይ (በባት፣ በቅልጥም አጥንት፣ በጭን ወይም በጉልበት ጀርባ) የሚከሰት ቢሆንም  አልፎ አልፎ ግን በእጆቻቸው ላይም ሊሰማ ይችላል። ይህ ሕመም የሚከተሉት መለያ ባህርያት አሉት ፦ 

  • በአብዛኛው በሁለቱም እግሮች ላይ እኩል ይኖራል 
  • አመሻሽ ወይም ሌሊት ላይ ስለሚጀምር ልጅዎን ከእንቅልፍ ሊቀሰቅሰው ይችላል 
  • ከጥቂት ደቂቃዎች እስከ ብዙ ሰዓታት ሊቆይ እና በቀናት ወይም በሳምንታት ልዩነት እየተመላለሰ ሊመጣ ይችላል 
  • ጠዋት ላይ እንዲሁም ሕፃናቱ እረፍት በሚያደርጉበት ወቅት ሙሉ በሙሉ ይጠፋል  
  • ብዙ የአካል እንቅስቃሴ በሚደረግበት ቀን ሕመሙ የመቀስቀስ ዕድሉ ከፍተኛ ነው 
  • ይህ እክል በሰውነት ላይ ምንም ዓይነት እብጠት፣ መቅላት፣ መደበኛ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ መቸገር ወይም ማነከስን አያስከትልም 

              ሕፃናቱ የሚሰማቸው የሕመም ስሜት ምን ዓይነት ነው? 

ብዙ ሕፃናት የዕድገት ሕመም ሲሰማቸው ጥልቅ የሆነ የቁርጥማት ወይም የውጋት ስሜት እንዳለው ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ የሕመሙ ባህሪ ከአንድ ሕፃን ወደ ሌላው ሊለያይ የሚችል ሲሆን መጠኑም በጣም ቀለል  ወይም ከባድ ሊሆን ይችላል። 

              የዕድገት ሕመም መንስኤ ምንድን ነው ? 

የሕክምና ባለሙያዎች የዕድገት ሕመም ትክክለኛ መንስኤ ምን እንደሆነ በውል ባያውቁም  ለዚህ እክል መከሰት መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው የሚገምቷቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ግን አሉ ፦

  • ከፍተኛ የአካል እንቅስቃሴ 

ሕፃናት በቀን ውስጥ በብዛት የሚሮጡና የሚጫወቱ ከሆነ የጡንቻዎች ከአቅም በላይ መድከምና መዛል ለሕመሙ መከሰት ዋነኛ ምክንያት ሊሆን ይችላል። 

  • የአካል አቋም ችግሮች 

የመገጣጠሚያዎች ከመጠን በላይ መተጣጠፍ (Hypermobility)፣ ጠፍጣፋ እግር (Flat feet)፣ የአከርካሪ አጥንት መጣመም (Scoliosis) እና መሰል የአካል አቋም ችግሮች በሰውነትና በእግሮች ላይ ተጨማሪ ጫና ይፈጥራሉ።

  • የንጥረ ነገር እጥረት 

የቫይታሚን ዲ (Vitamin D) እጥረት ወይም የአጥንት እፍጋት ማነስ (Low bone density) በአጥንትና በጡንቻዎች ጥንካሬ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል 

  • ጭንቀት ወይም የስሜት መረበሽ 

እነዚህ የጡንቻ ሕመም፣ ራስ ምታት እና የሆድ ሕመም ሊያስከትሉ ይችላል።

  • ዘረመል (የቤተሰብ ታሪክ)  

ወላጆች ወይም የሕፃኑ እህትና ወንድሞች ተመሳሳይ ሕመም የነበረባቸው ከሆነ በሕፃኑ ላይ የመከሰት ዕድሉ ከፍተኛ ነው።  

                  የዕድገት ሕመም ምርመራ ምን ይመስላል?

የዕድገት ሕመምን ለይቶ ለማወቅ የሚረዳ የተለየ የላቦራቶሪ ወይም የምስል ምርመራ የለም። ይልቁንም የልጅዎ ሐኪም አካላዊ ምርመራ በማድረግና የእርስዎን ማብራሪያ መሠረት በማድረግ ሁኔታውን ይገመግማል። ለዚህም ሐኪሙ የሚከተሉትን ዝርዝር ጥያቄዎች ሊጠይቅዎት ይችላል፦

  • ሕመሙ በትክክል የሚሰማው የትኛው የሰውነት ክፍል ላይ እንደሆነ፤
  • የሕመሙ ስሜት ምን ዓይነት ባሕርይ (ቁርጥማት ወይስ ውጋት) እንዳለው፤
  • ሕመሙ መቼ መቼ እንደሚጀምርና ሲመጣስ ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ፤
  • ሕመሙ በተቀሰቀሰበት ዕለት ልጅዎ ምን ዓይነት የአካል እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደነበረ፤
  • የሕመሙ ስሜት በስንት ጊዜ ልዩነት እየተመላለሰ እንደሚመጣ፤
  • ሕመሙን የሚያሻሽሉ (እንደ ማሸት) ወይም ይበልጥ የሚያባብሱ ነገሮች መኖራቸውን።

የልጅዎ የሕመም ስሜት ከዕድገት ሕመም የተለመዱ ባሕርያት ጋር የማይመሳሰል ከሆነ፣ ሐኪሙ ሌሎች የጤና ችግሮችን ከግምት ውስጥ ለማስገባትና ለማረጋገጥ የደም ምርመራዎችን ወይም የምስል ምርመራዎችን (እንደ ኤክስሬይ(X-rays) ወይም ኤምአርአይ(MRI)) ሊያዝ ይችላል። እነዚህ ተጨማሪ ምርመራዎች የሚከተሉት ሁኔታዎች ካሉ ሊያስፈልጉ ይችላሉ

  • ሕመሙ በአንድ እግር ላይ ብቻ ተለይቶ የሚከሰት ከሆነ
  • ሕፃኑ ዕረፍት በሚያደርግበት ወቅትም ሕመሙ የማይተወው (የማይሻሻል) ከሆነ፤
  • ከሕመሙ ጋር ተያይዞ በእግሩ ላይ እብጠት፣ መቅላት ወይም ትኩሳት ከተስተዋለ
  • ልጅዎ የመገጣጠሚያ ሕመም ካለው

                  የዕድገት ሕመም ህክምና ምንድን ነው? 

የዕድገት ሕመም በሂደት በራሱ ጊዜ የሚጠፋ በመሆኑ ልዩ የሆነ የሕክምና ክትትል ወይም መድኃኒት አያስፈልገውም። ይሁን እንጂ የልጅዎን ምቾት ማጣት ለመቀነስና የሕመሙን ስሜት ለማስታገስ የሚከተሉትን ቀላል የቤት ውስጥ መፍትሔዎች መተግበር ይችላሉ ፦ 

  • ሕመም የሚሰማውን የእግር ክፍል ቀስ አድርጎ ማሸት 
  • የእግር ጡንቻዎችን ቀስ አድርጎ መለጠጥ (Stretching) ማለማመድ 
  • ለብ ባለ ውኃ የተነከረ ጨርቅ ሕመም በሚሰማው ቦታ ላይ ማድረግ ወይም ልጅዎን ለብ ባለ ውኃ ማጠብ 
  • ሕመሙ በጣም ከበረታ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የሚሸጡ እንደ ፓራሲታሞል ወይም አይቡፕሮፌን ያሉ የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን መስጠት 
  • መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ማበረታታት

                መቼ ሐኪሞችን ማማከር ያስፈልጋል ?

ምንም እንኳ የዕድገት ሕመም በአጠቃላይ አሳሳቢ ባይሆንም በልጅዎ ላይ የሚከተሉትን ምልክቶች ካስተዋሉ ግን የሌላ ከባድ የጤና ችግር ማሳያ ሊሆን ስለሚችል ሳይዘገዩ ወደ ሕክምና መውሰድ ተገቢ ነው ። 

  • ከፍተኛ፣ የማያቋርጥ እና እየጨመረ የሚሄድ ሕመም 
  • ሕመሙ በአንድ እግር ላይ ብቻ ተለይቶ የሚሰማ ከሆነ 
  • ሕመም በሚሰማበት አካባቢ እብጠት፣ መቅላት ወይም የሙቀት ስሜት መኖር 
  • ማነከስ ወይም ለመራመድ መቸገር 
  • በጡንቻ ላይ ጓጉል/እብጠት (Lump) መኖር 
  • የሽንት ቀለም ባልተለመደ ሁኔታ መጥቆር (ወደ ቡናማነት ማዘንበል) 
  • ሕመሙ ጠዋት ድረስ የሚቀጥል ወይም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን የሚያስተጓጉል ከሆነ
  • ከእግር ሕመሙ ጋር ተያይዞ ትኩሳት፣ክብደት መቀነስ ወይም ከከፍተኛ ድካም ካለ ሐኪምዎችን ማማከር ይኖርቦታል።

              የዕድገት ሕመም ምን ያህል ጊዜ ይቆያል?

ይህ እክል ለወራት ወይም ለዓመታት እየተመላለሰ ሊከሰት ይችላል ። ለአብዛኞቹ ሕፃናት ዕድሜያቸው 12 ዓመት አካባቢ ሲሆን ሕመሙ ሙሉ በሙሉ የሚቆምላቸው ቢሆንም በአንዳንዶች ላይ ግን ወደ ታዳጊነት ዕድሜ ከተሸጋገሩ በኋላም ሊቀጥል ይችላል። 

              ልጅዎ የዕድገት ሕመም ካለው ምን ይጠብቁ?

የዕድገት ሕመም ምንም ዓይነት አደጋ የሌለውና ዘላቂ የጤና ችግር የማያስከትል ክስተት ነው። ይሁን እንጂ የልጅዎን ምቾት በመንሳት ማታ ማታ ከእንቅልፉ ሊቀሰቅሰው ወይም በሕመሙ ወቅት እንቅስቃሴውን በጊዜያዊነት ሊያስተጓጉል ይችላል። በመሆኑም ይህ የዕድሜ ክልል እስኪያልፍና ሕመሙ በራሱ ጊዜ እስኪጠፋ ድረስ፣ የልጅዎን ስቃይ ለመቀነስ ውጤታማ የሆኑ የቤት ውስጥ መፍትሔዎችንና የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ተገቢ ነው። 

Comments (0)