በጉርምስና ወቅት የሚታዩ መደበኛ ለውጦች

Biruh Tesfaye
Jul 7, 2026
undefined

ጉርምስና ማለት ሕፃናት በአካላዊ እና በስሜታዊ ለውጦች ውስጥ አልፈው ወደ ወጣትነት ዕድሜ የሚሸጋገሩበት (የሚያድጉበት) የሕይወት ምዕራፍ ነው። የጉርምስና ዕድሜ ልጆች ተከታታይ የሆኑ ጉልህ፣ ተፈጥሯዊ እና ጤናማ ለውጦችን የሚያሳልፉበት ጊዜ ነው። ይህ ሁሉ ነገር በአንድ ጊዜ ሳይሆን በሂደትና ቀስ በቀስ የሚከሰት ነው። 

በጉርምስና ወቅት የሚታዩ ለውጦች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦

  • የውስጣዊ እና ውጫዊ አካላት ዕድገትና መጎልመስ
  • በልጆች የብልት አካላት ላይ የሚታዩ ለውጦች
  • የአንጎል (የአእምሮ) ለውጦች
  • ማኅበራዊ እና ስሜታዊ ለውጦች

ጉርምስና የሚጀምረው መቼ ነው?

የጉርምስና ዕድሜ የሚጀምረው ሃይፖታላመስ (hypothalamus) ተብሎ የሚጠራው የአንጎል ክፍል ጎናዶትሮፒን-ሪሊዚንግ ሆርሞን (GnRH) የተባለ ሆርሞን ማመንጨት ሲጀምር ነው። ሃይፖታላመስ ይህንን ሆርሞን ፒቱዩታሪ እጢ (pituitary gland) ወደሚባለው ሌላ የአንጎል ክፍል ይልካል። ጎናዶትሮፒን-ሪሊዚንግ ሆርሞን የልጁን ፒቱዩታሪ እጢ በማነቃቃት ሁለት ተጨማሪ ሆርሞኖችን እንዲለቅ ያደርገዋል፤ እነሱም ሉቲናይዚንግ ሆርሞን (LH) እና ፎሊክል-ስቲሙሌቲንግ ሆርሞን (FSH) ናቸው። 

እነዚህ ሆርሞኖች በደም አማካኝነት ወደ ጾታ አካላት ማለትም ወደ እንቁልጢ (ovaries) ወይም የወንድ የዘር ፍሬ (testes) ይጓዛሉ። ይህ ደግሞ የጾታ አካላት እንደየጾታው ኢስትሮጅን (estrogen) ወይም ቴስቶስትሮን (testosterone) የተባሉ የጾታ ሆርሞኖችን መልቀቅ እንዲጀምሩ ያነሳሳቸዋል። እነዚህ መልእክተኛ ሆርሞኖች ደግሞ ግልጽ የሆኑትን የጉርምስና ምልክቶችን ያስከትላሉ።

ይህ ብዙውን ጊዜ ለሴት ልጆች ከ10-11 ዓመት ባለው ዕድሜ፣ ለወንድ ልጆች ደግሞ ከ11-12 ዓመት ባለው ዕድሜ አካባቢ ይከሰታል። ነገር ግን፣ የጉርምስና መጀመሪያ ዕድሜ ለሴት ልጆች ከ8-13 ዓመት፣ ለወንድ ልጆች ደግሞ ከ9-14 ዓመት ባለው ክልል ውስጥ ቢሆን መደበኛ ነው። በትክክል መቼ ጉርምስና እንደሚጀምር ለማወቅ የሚያስችል መንገድ የለም። በአንጎል እና በሆርሞን መጠን ላይ የሚታዩ የመጀመሪያ ለውጦች ከውጪ ስለማይታዩ፣ ጉርምስና ገና አልተጀመረም ብሎ ማሰብ የተለመደ ነው።

በጉርምስና ወቅት የሚታዩ አካላዊ ለውጦች

የጉርምስና ዕድሜ በአጥንት፣ በጡንቻ፣ በስነ-ተዋልዶ እና በሌሎች በርካታ የሰውነት ሥርዓቶች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ግልጽ የሆኑ ተከታታይ ሁኔታዎችን ያቀፈ ነው። በጉርምስና ወቅት የሚታዩ አካላዊ ለውጦች በደረጃ የሚከሰቱ እና ቀስ በቀስ የመከሰት አዝማሚያ አላቸው። 

ሴት ልጆች

ከ9–11 ዓመት

  • ጡት ማደግ ይጀምራል፦ ይህ አብዛኛውን ጊዜ ጉርምስና መጀመሩን የሚያሳይ የመጀመሪያው በግልጽ የሚታይ ምልክት ነው። ይህ የሚጀምረው በአንድ ወይም በሁለቱም የጡት ጫፎች ስር ትናንሽ፣ ጠንከር ያሉና ሲነኩ የሚጠዘጥዙ እብጠቶች ( buds) በመፈጠር ነው። በሚቀጥሉት አንድ ወይም ሁለት ዓመታት ውስጥ ደግሞ ጡቶቹ እያደጉ ይሄዳሉ። የቀኝ እና የግራ ጡት በተለያየ ፍጥነት ሊያድጉ ይችላሉ። እንዲሁም ጡት በሚያድግበት ወቅት መጠነኛ የመውጋት ወይም የመከርረር ስሜት ሊኖረው ይችላል። በጡት ጫፍ ዙሪያ ያለው ጠቆር ያለ ክፍል (አሪኦላ/Areola) እንዲሁ እየሰፋ ይሄዳል። 
  • ፈጣን የሰውነት ዕድገት (Growth spurt) ይከሰታል፦ አንዳንድ የሰውነት ክፍሎች፤ እንደ ራስ፣ ፊት እና እጅ ያሉ ከሌላ የሰውነት ክፍል በበለጠ ፍጥነት ሊያድጉ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ የልጅዎ የሰውነት ቅርጽ ተመጣጣኝ ያልሆነ እንዲመስል ሊያደርገው ይችላል። በአማካይ፣ ሴት ልጆች ከ5–20 ሳንቲም ሜትር ያድጋሉ። ብዙውን ጊዜ ዕድገታቸው ከ16–17 ዓመት ዕድሜ አካባቢ ይቆማል።
  • የሰውነት ቅርጽ ይለወጣል፦ ለምሳሌ ያህል፣ የሴት ልጆች ዳሌ እየሰፋ ይሄዳል።
  • ብልት አካባቢ ፀጉር ማደግ ይጀምራል፦ በሴት ብልት ዙሪያ ባሉት የቆዳ እጥፋቶች ላይ ጠቆር ያሉ፣ ሻካራ እና ጥቅልል ያሉ ፀጉሮች መታየት ይጀምራሉ።
  • የሰውነት ጠረን መኖር ሊጀምር ይችላል። ለዚህም ዲኦድራንት መጠቀም ይረዳል። 

ከ12–14 ዓመት 

  • ጡቶች ማደጋቸውን ይቀጥላሉ። 
  • የብብት ፀጉር ማደግ ይጀምራል፦ የፊት እና የሰውነት ፀጉርም እንዲሁ ይጨምራል።
  • ከማሕፀን ፈሳሽ መውጣት ይጀምራል፦ የወር አበባ ከመጀመሩ ጥቂት ወራት በፊት ነጭ ወይም ውሃ መሳይ ፈሳሽ ከማሕፀን መውጣት ይጀምራል። ይህ ፈሳሽ መደበኛ ክስተት ነው። ነገር ግን ፈሳሹ የሚያሳክክ፣ የሚያም ወይም መጥፎ ጠረን ያለው ከሆነ ሐኪም ማማከር ያስፈልጋል።
  • የብልት አካባቢ ጠጉር ይበልጥ እየተጠቀለለ እና እየወፈረ ይሄዳል። ቅርጹም የተገላቢጦሽ ሶስት ማዕዘን ቅርጽ የሚይዝ ይሆናል።
  • የወር አበባ መታየት ይጀምራል፦ ብዙውን ጊዜ የወር አበባ የሚጀምረው ጡት ማደግ ከጀመረ ከ2 ዓመት በኋላ ነው፤ ሆኖም ግን እስከ 4 ዓመት ሊዘገይ ይችላል። 

ወንድ ልጆች

ከ11–12 ዓመት

  • የውጪው የብልት አካል (ብልት፣ የዘር ፍሬ እና የዘር ፍሬ ከረጢት) ማደግ ይጀምራሉ፦ አንደኛው የዘር ፍሬ ከሌላኛው በበለጠ ፍጥነት ሊያድግ ይችላል። 
  • የብልት አካባቢ ፀጉር ማደግ ይጀምራል፦ በጊዜ ሂደት እየጠቆረ እና እየወፈረ ይሄዳል።
  • የቁመት መጨመር፦ የቁመት መጨመር (በተለምዶ በዓመት ከ2 እስከ 2 ተኩል ኢንች ያህል) የሚታይ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ ከዕድገት ጋር የተያያዘ የጡንቻ ወይም የአጥንት ቁርጥማት (Growing pains) ሊያስከትል ይችላል።
  • በሰውነት አወቃቀር ላይ የሚታይ ለውጥ፦ በሰውነት ውስጥ ያለው የስብ ክምችት እየቀነሰ ይሄዳል።
  • የሰውነት ጠረን መኖር መጀመር፦ የሰውነት ጠረን መኖር ሊጀምር ስለሚችል ዲኦድራንት መጠቀም ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

ከ12–14 ዓመት

  • ፈጣን የሰውነት ዕድገት ያጋጥማል፦ ልጅዎ ረጅም ይሆናል፣ እንዲሁም ደረቱ እና ትከሻው እየሰፉ ይሄዳሉ። አንዳንድ የሰውነት ክፍሎች፤ እንደ ራስ፣ ፊት እና እጅ ያሉ ከከሌሎች የሰውነት ክፍሎች በበለጠ ፍጥነት ሊያድጉ ስለሚችሉ፣ ለተወሰነ ጊዜ የሰውነት ቅርጹ ተመጣጣኝ ያልሆነ ሊመስል ይችላል። በአማካይ፣ ወንድ ልጆች ከ10–30 ሳንቲም ሜትር ያድጋሉ። ብዙውን ጊዜ ዕድገታቸው ከ18–20 ዓመት ዕድሜ አካባቢ ይቆማል።
  • መጠነኛ የጡት ማደግ ሊታይ ይችላል፦ ይህ በወንድ ልጆች ላይ የተለመደ ነው። ነገር ግን የማይጠፋ ከሆነ ወይም በጣም እያደገ ከመጣ ሐኪም ማማከር ጥሩ ነው።

ከ13–15 ዓመት

  • በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ ፀጉር ማደግ ይጀምራል፦ በብብት ስር፣ በፊት እንዲሁም በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ ያድጋል። የእግር እና የእጅ ፀጉርም እየበዛ ይሄዳል። አንዳንድ ወጣቶች እስከ 20ዎቹ መጀመሪያ ዕድሜያቸው ድረስ የሰውነት ፀጉራቸው ማደጉን ሊቀጥል ይችላል።
  • የቴስቶስትሮን (testosterone) ሆርሞን ይመረታል፦ ይህ ሆርሞን የዘር ፍሬዎች የወንድ የዘር ፈሳሽ (sperm) እንዲያመርቱ ያነሳሳል።
  • የብልት መቆም እና የዘር ፈሳሽ ማፍሰስ (Ejaculation) ሊጀምር ይችላል፦ በዚህ ወቅት፣ የብልት መቆም ያለምንም ምክንያት በራሱ ጊዜ ሊከሰት ይችላል። ይህ መደበኛ መሆኑንና ሌሎች ሰዎችም እንዲሁ በግልጽ እንደማያስተውሉት ለልጅዎ ያስረዱት። በእንቅልፍ ወቅት የሚከሰት የዘር ፈሳሽ መፍሰስ ብዙውን ጊዜ "የሌሊት ህልም" (wet dream) ተብሎ የሚጠራውም ሊያጋጥመው ይችላል።

ከ14–15 ዓመት

  • ማንቁርት (የአዳም አፕል) በግልጽ መታየት ይጀምራል እናም የልጅዎ የድምፅ ሳጥን እየተለቀ ይሄዳል፣ ድምፁም "ይሰባበራል"፤ በመጨረሻም የጎረነነ (ወፍራም) ይሆናል። የአንዳንድ ታዳጊ ወንዶች ድምፅ በአንድ ዓረፍተ ነገር ውስጥ እንኳ ሳይቀር እየቀጠነና እየወፈረ ሊዋዥቅ ይችላል። ይህ ሁኔታ በሂደት ይስተካከላል።
  • የዘር ፍሬዎች፣ ብልት እና የዘር ፍሬ ከረጢት ማደጋቸውን ይቀጥላሉ፤ እንዲሁም የዘር ፍሬ ከረጢቱ ቀለም እየጠቆረ ይሄዳል። 
  • የጡንቻ መጠን ይጨምራል። 
  • ብጉር (Acne) መውጣት ይጀምራል። 

በጉርምስና ወቅት ምን ዓይነት ስሜታዊ ለውጦች ይከሰታሉ? 

በጉርምስና ጊዜ ሆርሞኖች ሰውነት ላይ ለውጥ እንደሚያመጡት ሁሉ፣ በውስጣዊ ስሜት ላይም ለውጥ ያመጣሉ። ሰውነት እራሱን ከአዲሶቹ ሆርሞኖች ጋር እያስማማ ባለበት ሁኔታ ውስጥ፣ አእምሮም በተመሳሳይ መልኩ ራሱን የማስማማት ሂደት ላይ ይገኛል። በጉርምስና ወቅት፣ ግራ መጋባት ወይም ከዚህ በፊት አጋጥመው የማያውቁ ጠንካራ ስሜቶች ሊሰሙ ይችላሉ። ስለሚቀያየረው የሰውነትዎ ገጽታ መጨነቅ ሊጀምሩ ይችላሉ። እንዲሁም ከተለመደው በተለየ ሁኔታ የመበሳጨት ወይም የቁጣ ስሜት ሊያጋጥም ይችላል። 

ከማኅበራዊ ጫናዎች ጋር ተዳምሮ የጾታ ሆርሞኖች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር የስሜት መለዋወጥን፣ የድንገተኛ ስሜት መለዋወጦችን እና በቤተሰብ ውስጥ አለመግባባትን ሊያስከትል ይችላል። በተጨማሪም ለራስ ያለ የመተማመን ስሜት ላይ ችግር ሊፈጠር ይችላል፤ ወይም ከጾታዊነት ጋር የተያያዙ እንደ ፍላጎት፣ ግራ መጋባት እና ፍርሃት ያሉ በርካታ የተለያዩ ስሜቶች ሊሰሙም ይችላሉ።

ከፍተኛ የሆኑ ስሜታዊ ወይም የባህሪ ችግሮች ካጋጠሙ፤ ለምሳሌ የጭንቀት፣ የድብርት፣ ከፍተኛ የስሜት መዋዥቅ ወይም ራስን የመጉዳት ስመት ካሉ፤ የጤና ባለሙያ ማማከር በጣም አስፈላጊ ነው። 

በጉርምስና ወቅት የሚታዩ ሌሎች ውጫዊ እና ውስጣዊ አካላዊ ለውጦች

አንጎል

የታዳጊዎች አንጎል ዕድገት በባህሪ እና ማኅበራዊ ክህሎቶች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። አንጎል እያደገ በመጣ ቁጥር ራስን የመቆጣጠር፣ የማቀድ፣ ችግር የመፍታት እና ውሳኔ የመወሰን ክህሎቶችም የበለጠ ይዳብራሉ። ይህ ሂደት የ20ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ እስኪደርስ ድረስ ይቀጥላል።

አጥንት፣ የሰውነት ክፍሎች እና የሰውነት ሥርዓቶች

የሰውነት ክፍሎች ይበልጥ እያደጉና እየጠነከሩ ይሄዳሉ። የሳንባ ሥራ ይሻሻላል፣ እጅና እግሮች ያድጋሉ፣ እንዲሁም አጥንቶች በውፍረትና በስፋት ይጨምራሉ።

መደናቀፍ (Clumsiness)

በጉርምስና ወቅት ልጆች በጣም በፍጥነት ስለሚያድጉ፣ የሰውነታቸው የስበት ማዕከል (center of gravity) ይቀየራል፤ ይህንን ለመልመድ ደግሞ አእምሯቸው የተወሰነ ጊዜ ሊወስድበት ይችላል። ይህ ሁኔታ የሰውነት ሚዛን አጠባበቅ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ለተወሰነ ጊዜ ትንሽ መደናቀፍ ወይም ዕቃዎችን የመጣል ባህሪ ሊያዩ ይችላሉ፣ እንዲሁም የመጎዳት ዕድልም ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።

አካላዊ ጥንካሬ

በዚህ ወቅት የጡንቻዎች ጥንካሬ እና መጠን ይጨምራል። የእጅና የዓይን ቅንጅት (hand-eye coordination)፣ እንዲሁም እንደ ኳስ መያዝ እና መወርወር ያሉ የእንቅስቃሴ ክህሎቶች በጊዜ ሂደት እየተሻሻሉ ይሄዳሉ።

ቆዳ እና ፀጉር

በፊት፣ በትከሻ እና በጀርባ ቆዳ ላይ የሚገኙ እጢዎች በጉርምስና ወቅት የበለጠ ቅባት ያመነጫሉ። ይህ ደግሞ በቆዳ ላይ ቅባት እንዲከማች እና የቆዳ ቀዳዳዎች እንዲደፈኑ ያደርጋል፤ ይህም ለብጉር (Acne) መውጣት ምክንያት ይሆናል። በፊት፣ ጀርባ ወይም ደረት ላይ ብጉር ሊወጣ ይችላል። አንዳንድ ሰዎች ላይ የሚወጣው ብጉር ከሌሎች ይልቅ የከፋ ሊሆን ይችላል። ጸጉራቸውም ይበልጥ ቅባትማ ሊሆንና ደጋግመው መታጠብ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። 

የእንቅልፍ ልምዶች

የእንቅልፍ ልምዶች ይቀየራሉ፤ ብዙ ልጆች በሌሊት ዘግይተው መተኛት እና በቀን ደግሞ አርፍደው መነሳት ይጀምራሉ።

ላብ

በጉርምስና ወቅት በብብት ስር እና በብልት አካባቢ አዲስ ዓይነት የላብ እጢ ይበቅላል። የቆዳ ባክቴሪያዎች ይህ እጢ በሚያመነጨው ላብ ላይ ስለሚመገቡ የሰውነት ጠረን ሊያስከትል ይችላል። የግል ንፅህና አጠባበቅ በጣም አስፈላጊ ነው።

ጥርስ

ልጆች ሁለተኛውን የመንጋጋ ጥርሳቸውን በ13 ዓመት ዕድሜ አካባቢ ያወጣሉ። ሦስተኛው የመንጋጋ ጥርስ ከ14 እስከ 25 ዓመት ባለው ዕድሜ መካከል ሊበቅል ይችላል። ጤናማ ጥርስ እና ድድ ለታዳጊ ልጅዎ ጤና ወሳኝ በመሆናቸው፣ የታዳጊዎች የጥርስ እንክብካቤ አስፈላጊ ነው።

ክብደት

በዚህ ወቅት ክብደት መጨመር ያጋጥማል። የታዳጊዎች ጨጓራ እና አንጀት በመጠናቸው ስለሚጨምሩ ተጨማሪ ካሎሪ ፣ ፕሮቲኖች እና ማዕድናት ያስፈልጋቸዋል። ለአጥንት ዕድገት እና ለደም ዝውውር ከፍተኛ የካልሲየም እና የአይረን ይዘት ያላቸው ምግቦች ጠቃሚ ናቸው።

ጉርምስና መቼ ያበቃል?

ለሴቶች ልጆች፣ ጉርምስና በተለምዶ ከ15 እስከ 17 ዓመት ባለው ዕድሜ አካባቢ ያበቃል። ለወንዶች ልጆች ደግሞ፣ ከ16 እስከ 17 ዓመት ባለው ዕድሜ አካባቢ የማክተም አዝማሚያ አለው። እዚህ ላይም ቢሆን፣ እያንዳንዱ ልጅ የተለያየ በመሆኑ እነዚህ የእድሜ ክልሎች ሊለያዩ ይችላሉ።

 

Comments (0)