የሕፃናት ማራመጃ ጋሪዎች ልጅዎን እየጎዱ እንደሆነ ያውቃሉ?

Elsabet Azezew
Jul 14, 2026
undefined

                              የሕፃናት ማራመጃ ጋሪዎች ልጅዎን እየጎዱ እንደሆነ ያውቃሉ? 

እንደ ወላጅ ልጅዎ ጤናማ ሆኖ እንዲያድግ፣ አዳዲስ ክህሎቶችን እንዲያዳብርና ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የሚረዱ የሕፃናት ምርቶችን መምረጥ ይፈልጉ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ምርቶች ውጫዊ ጥቅማቸው ጎልቶ ቢታይም፣ ከጀርባቸው ግን ያልታሰቡ አደጋዎችን ይዘው ሊመጡ ይችላሉ። ከእነዚህ ከፍተኛ ክርክርና ትችት ከሚነሳባቸው የሕፃናት ዕቃዎች መካከል አንዱ የመራመጃ ማራመጃ ጋሪ (Baby Walker) ነው።

የሕፃናት ማራመጃ ጋሪዎች በወላጆች ዘንድ በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውሉ እና ተወዳጅነት ያላቸው ቢሆንም የሕፃናት ሐኪሞች ግን እንዲጠቀሙባቸው በጭራሽ አይመክሩም። ምክንያቱም እነዚህ ጋሪዎች ሕፃናትን ለከባድ አደጋዎች ከማጋለጣቸውም በላይ የተፈጥሮ የዕድገት ሂደታቸውን ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ። እንዲያውም እንደ አሜሪካ የሕፃናት ሕክምና አካዳሚ (AAP) ያሉ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ተቋማት ወላጆች እነዚህን ጋሪዎች ከመጠቀም እንዲቆጠቡ በጥብቅ ያሳስባሉ።

በዚህ ጽሑፍ የማራመጃ ጋሪዎች በሕፃናት ላይ የሚያስከትሏቸውን ጉዳቶች እና የልጅዎን ጤናማ ዕድገትና የመራመድ ክህሎት የሚደግፉ አስተማማኝ አማራጮችን በዝርዝር እንቃኛለን።

           የሕፃናት ማራመጃ ጋሪዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለምን አይመከሩም?

የሕፃናት ማራመጃ ጋሪዎች (Baby Walkers) በሕፃናት ሐኪሞች ዘንድ ፈጽሞ የማይመከሩባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦ 

  • ቀድሞ ለመራመድ አያግዙም 

ብዙ ወላጆች ጋሪ ሕፃናትን በፍጥነት እንዲራመዱ ይረዳል ብለው ቢያምኑም ጥናቶች ግን ተቃራኒውን ያሳያሉ። ጋሪ የሚጠቀሙ ሕፃናት ከማይጠቀሙት ይልቅ የመቀመጥ፣ በጉልበት የመዳህ፣ የመቆም እና የመራመድ እድገታቸው የዘገየ ነው።

  • የሰውነት እንቅስቃሴ (motor) እድገትን ያስተጓጉላሉ

ጋሪዎች ሕፃናትን ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ የሰውነት አቀማመጥ እንዲቆሙ ስለሚያስገድዷቸው፣ በራሳቸው ጊዜ ለመራመድ የሚያስፈልጋቸውን የሰውነት ሚዛን፣ ቅንጅት (Coordination) እና የጡንቻ ጥንካሬ በአግባቡ እንዳያዳብሩ ያግዷቸዋል። 

  • በጉልበት የመዳህ ጊዜን ይቀንሳሉ

በጉልበት መዳህ የሰውነት ጥንካሬን፣ ቅንጅትን እና የአንጎል እድገትን ለማዳበር የሚረዳ ትልቅ የእድገት ደረጃ ነው። በጋሪ ውስጥ ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ይህን አስፈላጊ የእድገት ደረጃ ሊገድብ ይችላል።

  • በሰውነት አቋም እና በአራማመድ ዘይቤ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ

ሕፃናት ጋሪው ላይ ለመንቀሳቀስ የእግር ጣቶቻቸውን ጫፍ ብቻ ስለሚጠቀሙ  ያልተለመደ የአረማመድ ልምድ እንዲኖራቸው ሊያደርግ እና በዳሌ፣ በጉልበት፣ በቁርጭምጭሚት እና በታችኛው እግር ላይ አላስፈላጊ ጫና ሊፈጥር ይችላል። 

  • ለከባድ አደጋ ያጋልጣሉ  

ጋሪዎች ሕፃናትን ካለአቅማቸው በጣም በፍጥነት እንዲንቀሳቀሱ ስለሚያስችሏቸው ከደረጃ ላይ እንዲወድቁ፣ እንዲገለበጡ ወይም ከቤት ዕቃዎችና ግድግዳዎች ጋር በኃይል እንዲጋጩ ያደርጋቸዋል። 

  • አደገኛ ዕቃዎች ላይ በቀላሉ እንዲደርሱባቸው ያደርጋሉ

ጋሪዎች ሕፃናትን ከፍ አድርገው ስለሚያስቀምጧቸው እንደ ትኩስ ፈሳሽ፣ ስለታማ ዕቃዎች፣ ምድጃዎች እና የኤሌክትሪክ ገመዶች ያሉ አደገኛ ነገሮች ላይ በቀላሉ እንዲደርሱባቸው ያደርጋሉ ። ይህ ደግሞ ለቃጠሎ እና ለሌሎች ከባድ አደጋዎች ይዳርጋቸዋል።

  • የሐሰት የደኅንነት ስሜት ይፈጥራሉ 

ልጅዎ በጋሪው ውስጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ ስለሚመስልዎት ዘና ሊሉ ይችላሉ። ነገር ግን መሣሪያው እጅግ ፈጣን በመሆኑ በቅርብ ሆነው እየተከታተሉት እንኳ እርስዎ ከመድረስዎ እና ምላሽ ከመስጠትዎ በፊት ሕፃኑ በፍጥነት አደጋ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። 

          የመራመድ ክህሎትን የሚደግፉ አስተማማኝ አማራጮች ምንድን ናቸው? 

የልጅዎን ጤናማ ዕድገት እየደገፉ በነፃነትና በደኅንነት እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ከሕፃናት ማራመጃ ጋሪዎች ይልቅ የሚከተሉትን የተሻሉ አማራጮች እንዲጠቀሙ ይመከራል፦ 

  • የማይንቀሳቀሱ የመጫወቻ ጋሪዎች (Stationary activity centers)

ሕፃናት በአንድ ቦታ ላይ ሆነው ደኅንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ እንዲዘልሉና እንዲጫወቱ የሚረዱ ከመሆናቸውም በላይ ትክክለኛ የእግር ዕድገትን ይደግፋሉ። አብዛኞቹ ለተለያዩ የዕድገት ደረጃዎች የሚሆኑ የሚነቃቀሉ መጫወቻዎችንና መመገቢያ ትሪዎችን ያካትታሉ። 

  • የሚገፉ መጫወቻዎች (Push Toys) 

እነዚህ መጫወቻዎች ሕፃናት መራመድ እንዲለማመዱ ትልቅ እገዛ ያደርጋሉ። ሆኖም እንዳይገለበጡና ጉዳት እንዳያደርሱባቸው ክብደት ያላቸውና ጠንካራ መሆን ይኖርባቸዋል። ሕፃናቱ እነዚህን መጫወቻዎች በሚጠቀሙበት ጊዜም የቅርብ ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል። 

  • የሕፃናት መጫወቻ አጥሮች (Playpens)

ሕፃናት በነፃነት እንዲንቀሳቀሱና እንዲጫወቱ የሚያስችል ሙሉ በሙሉ ደኅንነቱ የተጠበቀና የታጠረ ቦታ እንዲኖር ያደርጋሉ። 

የሕፃናት ማራመጃ ጋሪ ለመጠቀም ከወሰኑ ግን የሚከተሉትን ምክሮች ይከተሉ

  • ጋሪው ላይ የሚቆይበትን ጊዜ በቀን ከ10 ደቂቃ ያልበለጠ ያድርጉት 
  • ልጅዎ ጋሪውን በሚጠቀምበት ጊዜ የቅርብ ክትትል ያድርጉለት
  • ልጅዎ ሁለቱንም እግሮቹን ሙሉ በሙሉ ወለሉ ላይ ማሳረፍ በሚችልበት ልክ የጋሪው ከፍታ ዝቅ ያለ መሆኑን ያረጋግጡ 
  • ልጅዎ ወለሉን በጣቶቹ ጫፍ ብቻ የሚነካ ከሆነ (ተረከዙ በአየር ላይ ከቀረ) ጥቂት እስኪያድግ ድረስ ጋሪውን ከመጠቀም ይቆጠቡ  

Comments (0)