በመሳሳም ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎች !
መሳሳም ፍቅርንና ቁርኝትን ለመግለጽ የሚረዳ ተፈጥሯዊ መንገድ ቢሆንም፣ በምራቅና በቀጥታ የአፍ ለአፍ ንክኪ አማካይነት የተወሰኑ ባክቴሪያዎችና ቫይረሶች ሊተላለፉ ይችላሉ። ምንም እንኳ አጠቃላይ የመተላለፍ ዕድሉ በአብዛኛው ዝቅተኛ ቢሆንም፤ አንደኛው ሰው ኢንፌክሽን፣ የከንፈር ቁስለት (Cold sores)፣ የድድ መድማት ወይም በአፉ ውስጥ ክፍት ቁስል ካለበት የበሽታዎቹ የመተላለፍ አጋጣሚ በእጅጉ ይጨምራል።
በመሳሳም ሊተላለፉ የሚችሉ ዋና ዋና የጤና እክሎች እንደሚከተለው ቀርበዋል፦
- ጉንፋን (Common Cold)
የጉንፋን ቫይረሶች በምራቅ እና በትንፋሽ ጠብታዎች አማካኝነት ይሰራጫሉ። በበሽታው የተያዘን ሰው መሳም በተለይም በሽታው በጀመረበት የመጀመሪያዎቹ ቀናት ውስጥ ቫይረሱን በቀላሉ ሊያስተላልፍ ይችላል።
ምልክቶቹ
-የአፍንጫ ፈሳሽ መበራከት ወይም መዘጋት
- የጉሮሮ ህመም
- ሳል
- ማጥሸት
- መጠነኛ ትኩሳት
- ግላንዱላር ትኩሳት / ሞኖኑክሊዮሲስ (Glandular Fever / Infectious Mononucleosis)
ብዙ ጊዜ "የመሳሳም በሽታ" ተብሎ የሚጠራው ይህ ህመም በኤፕስታይን-ባር ቫይረስ (EBV) የሚመጣ ሲሆን በዋናነትም በምራቅ ልውውጥ አማካኝነት ይተላለፋል።
ምልክቶቹ
- ትኩሳት
- ከባድ የጉሮሮ ህመም
- የልምፍ እጢዎች ማበጥ (Swollen lymph nodes)
- ከፍተኛ የድካም ስሜት
- የቶንሲል ማበጥ
አብዛኛውን ጊዜ በቂ ዕረፍት በማድረግ፣ በቂ ውሃ በመጠጣትና እንደ ፓራሲታሞል ወይም አይቡፕሮፌን ያሉ የሕመም ማስታገሻዎችን በመውሰድ በራሱ ይድናል።
- የከንፈር ቁስለት / የአፍ ሄርፒስ (Herpes Simplex Virus - Cold Sores)
በሄርፒስ ሲምፕሌክስ ቫይረስ የሚመጣና በተለምዶ "የአፍ ምች" የሚባለው ይህ እክል በዋናነት በመሳሳም ይተላለፋል። ቫይረሱ ይበልጥ ተላላፊ የሚሆነው ቁስሉ በሚታይበት ወቅት ቢሆንም ምንም ዓይነት ምልክት በማይታይበት ጊዜም አልፎ አልፎ ሊተላለፍ ይችላል።
ምልክቶቹ
- በከንፈር ወይም በአፍ ዙሪያ የሚወጡ ሕመም ያላቸው ውሃ የቋጠሩ ቁስሎች
- ስሎቹ ከመውጣታቸው በፊት የሚኖር የመውጋት ወይም የማቃጠል ስሜት
- ቁስሎቹ እየዳኑ ሲሄዱ የሚፈጠር ቅርፊት
ለቫይረሱ ዘላቂ ፈውስ የሌለው ቢሆንም ምልክቶቹን መቆጣጠር ይቻላል። ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የሚሸጡ በቆዳ ላይ የሚቀቡ የፀረ-ቫይረስ ክሬሞች (እንደ ዶኮሳኖል / Docosanol ያሉ) ወይም በሐኪም ትዕዛዝ የሚወሰዱ ክኒኖች (እንደ አሳይክሎቪር /Acyclovir ወይም ቫላሳይክሎቪር / Valacyclovir ያሉ) ሕመሙን ሊቀንሱ እና የበሽታውን ቆይታ ሊያሳጥሩ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪም ሕመሙን እና እብጠቱን ለመቀነስ ውሃ የቋጠሩ ቁስሎችዎ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ የተነከረ ፎጣ ይያዙበት።
- ሄፓታይቲስ ቢ የጉበት ቫይረስ (Hepatitis B)
ይህ የጉበት ቫይረስ በዋናነት በደምና በግብረ-ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፍ ቢሆንም በበሽታው ከተያዘ ሰው የሚወጣ ደም ወይም ምራቅ በመሳሳም ወቅት ከሌላኛው ሰው ክፍት ቁስል ወይም ከሚደማ ድድ ጋር ንክኪ ካደረገ ሊተላለፍ ይችላል።
ምልክቶቹ
- የድካም ስሜት
- ትኩሳት
- ማቅለሽለሽ
- የቆዳ ወይም የዓይን ቢጫ መሆን (ወፍ በሽታ/jaundice)
- የሽንት ቀለም መጥቆር
አጣዳፊ (Acute) ሄፓታይቲስ ቢ አብዛኛውን ጊዜ በእረፍትና በበቂ ፈሳሽ ይድናል። ሥር የሰደደ (Chronic) ከሆነ ግን ረዘም ያለ የፀረ-ቫይረስ መድኃኒት ሕክምና እና መደበኛ የሕክምና ክትትል ያስፈልገዋል።
- የአፍ ኪንታሮት (HPV Warts)
አንዳንድ የሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ (HPV) ዓይነቶች የአፍና የጉሮሮ ሕብረ ሕዋሳትን ሊያጠቁ ይችላሉ።በመደበኛ መሳሳም የመተላለፍ ዕድላቸው አነስተኛ ቢሆንም ረዘም ያለና ጥልቅ መሳሳም ሲኖር ግን የመተላለፍ ስጋቱ ይጨምራል።
አብዛኞቹ ሰዎች ምንም ምልክት አያሳዩም። ሆኖም አንዳንድ የቫይረሱ ዓይነቶች የአፍ ኪንታሮትን ሊያስከትሉ ወይም ለጉሮሮ ካንሰር የመጋለጥ ዕድልን ሊጨምሩ ይችላሉ።
አብዛኞቹ በራሳቸው ጊዜ የሚጠፉ ቢሆንም፤ ካልጠፉ ወይም ከተሰራጩ በቀዶ ሕክምና ማስወገድ፣ ክራዮቴራፒ (በፈሳሽ ናይትሮጅን ኪንታሮቱን በማቀዝቀዝ ማስወገድ)፣ ሌዘር ሕክምና ወይም የሚቀቡ ኬሚካሎችን (እንደ ትራይክሎሮአሴቲክ አሲድ / Trichloroacetic acid ያሉ) በመጠቀም ማከም ይቻላል።
- የማጅራት ገትር በሽታ
ለማጅራት ገትር በሽታ ምክንያት የሆኑ ባክቴሪያዎች በምራቅ እና በትንፋሽ ጠብታዎች አማካኝነት ሊሰራጩ ይችላሉ።ጥልቅ ወይም ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ መሳሳም በበሽታው የመያዝ ዕድልን ይጨምራል።
ምልክቶቹ
- ድንገተኛ ትኩሳት
- ከባድ የራስ ምታት
- የአንገት መገተር
- ሽፍታ
- ግራ መጋባት ወይም ከፍተኛ የእንቅልፍ ስሜት
ይህ አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልገው ከባድ በሽታ ነው።
- የጥርስ መበስበስን የሚያመጡ ባክቴሪያዎች (Tooth Decay-Causing Bacteria)
ለጥርስ መበስበስ ተጠያቂ የሆኑ ባክቴሪያዎች በምራቅ በኩል ሊተላለፉ ይችላሉ። በተለይም ወላጆች ሕፃናትን ከንፈራቸውን በመሳም ወይም የአፍ ንጽሕና መጠበቂያ ዕቃዎችን በማጋራት ሳያውቁት እነዚህን ባክቴሪያዎች ለልጆቻቸው ሊያስተላልፉ ይችላሉ።
- የጆሮ ደግፍ በሽታ (Mumps)
የጆሮ ደግፍ በሽታ በምራቅ እና በትንፋሽ ጠብታዎች አማካኝነት ይሰራጫል። በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር መሳሳም ወይም ሌላ የቅርብ ንክኪ ማድረግ ቫይረሱን ሊያስተላልፍ ይችላል።
ምልክቶቹ
- የምራቅ እጢዎች ማበጥ
- ትኩሳት
- የራስ ምታት
- የጡንቻ ህመም
- የድካም ስሜት
ለጆሮ ደግፍ በሽታ እስካሁን የተገኘ ልዩ መድኃኒት የለውም። በመሆኑም ሕክምናው በዋናነት የሚያተኩረው ቫይረሱ ከሰውነት እስኪወጣ ድረስ በቂ ዕረፍት በማድረግ፣ ፈሳሽ አብዝቶ በመጠጣት እንዲሁም ሕመምና ትኩሳትን በሚያስታግሱ መድኃኒት ላይ ነው።
- ቂጥኝ (Syphilis)
ምንም እንኳን ቂጥኝ በዋናነት በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፍ ቢሆንም በበሽታው የተያዘ ሰው አፉ ውስጥ ወይም ከንፈር ዙሪያ የቂጥኝ ቁስል ካለ በመሳሳም ሊተላለፍ ይችላል።
ምልክቶቹ
- ኢንፌክሽኑ በተከሰተበት ቦታ ላይ የሚወጣ ሕመም የሌለው ቁስል (Chancre)
- የቆዳ ሽፍታ (በተለይ በእጅ መዳፍና እግር ላይ)
- የፍርንትት (lymph nodes) እብጠት
- ትኩሳት እና የድካም ስሜት
- አንዳንድ ባታ ላይ የሚከሰት የፀጉር መርገፍ
- ሕክምና ካልተደረገለት በአንጎል፣ በልብ፣ በዓይንና በነርቭ ሥርዓት ላይ ከባድ ጉዳት ያደርሳል።
ቂጥኝ በአንቲባዮቲክስ (በተለይም በፔኒሲሊን) በቀላሉ የሚታከም ሲሆን ቀድሞ መታከሙም የከፋ ጉዳትን ለመከላከል ይረዳል።
በእነዚህ በሽታዎች የመያዝ አድሎን እንዴት መቀነስ ይችላሉ?
- የከንፈር ቁስለት፣ ጉንፋን ወይም የአፍ እክል ያለበትን ሰው ከመሳሳም ይቆጠቡ
- የሚስሙት ሰው ወይም እርስዎ ክፍት ቁስል ወይም የሚደማ ድድ ካልዎት አይሳሙ
- እጅን አዘውትሮ በመታጠብና የአፍ ንጽሕናን በአግባቡ በመጠበቅ ራስዎን ይጠብቁ
- የመጠጫና የመመገቢያ ዕቃዎችን፣ የጥርስ ብሩሽንና የከንፈር ማለስለሻዎችን (Chapstick) ከሌሎች ጋር አያጋሩ
- እንደ ሄፓታይቲስ ቢ ክትባት ያሉ ክትባቶችን በወቅቱ ይውሰዱ
- የማይሻሻል የአፍ ቁስል፣ የፍርንትት እብጠት ወይም ሌሎች አሳሳቢ ምልክቶችን ካስተዋሉ በፍጥነት ሐኪምዎን ያማክሩ።


