የወር አበባ ራስ ምታት (Menstrual Migraine) የወር አበባ ዑደትዎ በሚደርስበት ጊዜ አካባቢ የሚከሰት የተለመደ የማይግሬን አይነት ነው።ይህም በቀጥታ ከሆርሞን ደረጃዎች ለውጦች ጋር የተያያዘ ነው፣ በተለይም የኤስትሮጅን መዋዠቅ። እነዚህ የማይግሬን ጥቃቶች አብዛኛውን ጊዜ የወር አበባዎ ከመጀመሩ ከሁለት ቀናት በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ እስከ ወር አበባዎ ሦስተኛው ቀን ድረስ ይከሰታሉ። ሆኖም ይህ ለእያንዳንዱ ሰው ሊለያይ ይችላል።
በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት የራስ ምታት በጣም የተለመደ ክስተት ነው። የወር አበባ መምጣት ከሚጀምርበት ጊዜ አንስቶ እስከ ማረጥ (menopause) ድረስ ሊቀጥል ይችላል። በቅርብ ጊዜ በተደረገ ጥናት እንደታየው፣ ማይግሬን ካለባቸው ሴቶች መካከል እስከ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ከወር አበባ ጋር የተያያዘ የራስ ምታት ሊያጋጥማቸው ይችላል። የወር አበባ ከሚመጣባቸው ሰዎች መካከል ደግሞ እስከ 60 በመቶ የሚሆኑት በወር አበባ ዑደታቸው ወቅት የራስ ምታት ያጋጥማቸዋል።
ሁለት ዋና ዋና በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት የራስ ምታት ዓይነቶች አሉ፡
- ወር አበባ ጊዜ ብቻ የሚከሰት ራስ ምታት (Pure Menstrual Migraine)፦ ይህ የአይነት ራስ ምታት የሚከሰተው የወር አበባ በሚመጣበት ጊዜ ብቻ ነው፣ ማለትም የወር አበባ ከመጀመሩ ከሁለት ቀናት በፊት እስከ ተጀመረ በሦስተኛው ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ። በሌሎች የወሩ ጊዜያት ምንም ዓይነት ህመም አይኖርም። ይህ ከሦስት ተከታታይ የወር አበባ ዑደቶች ቢያንስ በሁለቱ ውስጥ ይከሰታል። ማይግሬን ካለባቸው 100 ሴቶች መካከል ከአንዷ ያነሱት ብቻ ይህ አይነት የራስ ምታት እንዳላቸው ይታመናል።
- ከወር አበባ ጋር የተያያዘ ራስ ምታት (Menstrual Related Migraine)፦ ይህ የደግሞ ከወር አበባ ውጪ በሌሎች የወሩ ጊዜያትም ይከሰታል። የሆርሞን ለውጡ አሁንም ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ቢሆንም፣ ሴቷ በወር አበባ ዑደቷ ወቅት ብቻ ሳይሆን በየተደጋጋሚ ጊዜያት የማይግሬን ህመም ያጋጥማታል።
ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
የራስ ምታቱ አብዛኛውን ጊዜ በጭንቅላትዎ በአንድ በኩል ብቻ ያጋጥማል። በግንባርዎ አካባቢ ህመም መሰማቱ የተለመደ ቢሆንም፣ በሌሎች የጭንቅላት ክፍሎች ላይ ሊከሰት ወይም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሊዛወር ይችላል። እነዚህ ምልክቶች እንደየሰዉ ሁኔታ በጥቂቱ ሊለያዩ ይችላሉ። ምልክቶቹ ለጥቂት ሰዓታት ያህል ሊቆዩ ይችላሉ፤ ሆኖም ግን ለበርካታ ቀናት ሊቀጥሉ የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው።
በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት የራስ ምታት ከማንኛውም የማይግሬን ህመም ጋር በርካታ ተመሳሳይ ምልክቶችን ይጋራል፤ እነዚህም የሚከተሉትን ሊጨምሩ ይችላሉ፦
- የሚወጋ ወይም የሚመታ ዓይነት የራስ ምታት (ብዙውን ጊዜ በጭንቅላት በአንድ በኩል ብቻ)
- በብርሃን፣ በድምፅ ወይም በሽታ የሚባባስ ራስ ምታት
- ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ ወይም የሆድ ቁርጠት
- በአንዳንድ ሰዎች ላይ የራስ ምታቱ ከመጀመሩ በፊት እንደ ብልጭልጭ ብርሃናት ወይም የእይታ መጋረድ ያሉ ቅድመ ምልክቶች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ
- የምግብ ፍላጎት መቀነስ
- የመደናገር ወይም የማዞር ስሜት
- የድካም ስሜት
በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት የራስ ምታት ከሌሎች የራስ ምታቶች በምን ይለያል?
- ረጅም ጊዜ የሚቆዩ እና ይበልጥ ብርቱ ናቸው፦ በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት የራስ ምታት ከሌሎች የራስ ምታቶች ጋር ሲነፃፀሩ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆዩ እና ይበልጥ የበረቱ ይሆናሉ። ከራስ ምታቱ በተጨማሪ፣ የማቅለሽለሽ ወይም የማስታወክ፣ እንዲሁም በብርሃን እና በድምፅ የመባባስ እድሉ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።
- ብዙውን ጊዜ ያለ ቅድመ-ምልክት (aura) የሚከሰቱ ናቸው፦ በሌሎች የወሩ ጊዜያት የሚከሰት ማይግሬን አብዛኛውን ጊዜ ቅድመ-ምልክት አለው፣ ከወር አበባ ጋር የተያያዙ የማይግሬን ጥቃቶች ግን ያለ አውራ የመከሰት እድላቸው ከፍተኛ ነው።
- ለህክምና ይበልጥ አስቸጋሪ ናቸው፦ ከወር አበባ ጋር የተያያዙ የማይግሬን ህመሞች በህክምና ለመዳን ወይም ለማስታገስ ይበልጥ ፈታኝ ሊሆኑ ይችላሉ።
በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት የራስ ምታት ለምን ይከሰታል?
ማይግሬን እና የሆርሞን ደረጃዎች ጥብቅ ቁርኝት አላቸው። የኤስትሮጅን (estrogen) ሆርሞን መጠን መቀነስ ለየማይግሬን ህመም የተለመደ ቀስቃሽ (trigger) ነው። የኤስትሮጅን መጠን ከእንቁላል መውጣት (ovulation) ጥቂት ቀደም ብሎ የሚጨምር ሲሆን፣ የወር አበባ ሲጀምር ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል፤ ይህም በወር አበባዎ ወቅት የማይግሬን ጥቃት የመከሰት እድሉን ይጨምራል።
ፕሮስታግላንዲን (prostaglandins) በመባል የሚታወቁት ሆርሞኖችም ከማይግሬን ህመም ጋር ይያያዛሉ። የወር አበባዎ በሚደርስበት አካባቢ ሰውነትዎ ከፍተኛ መጠን ያለው ፕሮስታግላንዲን ይለቃል። እነዚህ ንጥረ ነገሮች ለወር አበባ ሕመም (ቁርጠት) መንስኤ ከመሆናቸውም በላይ የማይግሬን ሕመም የመከሰት እድልን ይጨምራሉ።
ማረጥ (menopause) በሚቀርብበት ጊዜ የኤስትሮጅን መጠን ስለሚዋዥቅ የማይግሬን ጥቃቶች ሊባባሱ ይችላሉ። ከማረጥ በኋላ ግን የወር አበባዎ ሲቆምና የኤስትሮጅን መጠንዎ ሲረጋጋ ሁኔታው ሊሻሻል ይችላል። ሆኖም ይህ ለሁሉም ሰው አንድ አይነት አይደለም፤ ከማረጥ በኋላም ቢሆን ለዓመታት ሊቀጥል ይችላል።
ከሆርሞን ጋር ያልተያያዙ ቀስቃሽ ነገሮችም ከወር አበባ ጋር በተያያዙ የማይግሬን ጥቃቶች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።በወር አበባ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰት አይረን እጥረት፣ የአእምሮ ውጥረት፣ የውሃ እጥረት (dehydration)፣ የእንቅልፍ መዛባት፣ እና የተወሰኑ የምግብ ወይም የመጠጥ ዓይነቶች ፤በተለይም ከሆርሞን ለውጦች ጋር ተደራርበው በሚከሰቱበት ጊዜ ፤ የህመሙን የመከሰት እድል ሊጨምሩ ይችላሉ።
በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት የራስ ምታት እንዳለብዎ እንዴት ማወቅ ይቻላል?
በወር አበባ ጊዜ ለሚከሰት የራስ ምታት የሚደረግ ልዩ የላቦራቶሪ ወይም የሕክምና ምርመራ የለም። ይህ ሁኔታ እንዳለብዎ ለማወቅ ዋነኛው መንገድ ቢያንስ ለሦስት ወራት ያህል ማስታወሻ (diary) መያዝ ነው።
በዚህ ማስታወሻ ላይ የሚከተሉትን ይመዝግቡ፦
- የማይግሬን ህመም የሚያጋጥምዎት ቀናት
- የማይግሬን ህመሙ ብርታት (severity)፣ ተያያዥ ምልክቶችን፣ እንዲሁም ህመምዎን የሚያስታግሱ ወይም የሚያባብሱ ነገሮችን
- የወር አበባዎ የሚመጣባቸው ቀናት
ይህ የሕመምዎን እና የወር አበባ ዑደትዎን በቀላሉ በመከታተል በመካከላቸው ግንኙነት እንዳለ ለማረጋገጥ ይረዳዎታል።
- በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት የራስ ምታት መስፈርት፦ የወር አበባዎ ከመጀመሩ ከሁለት ቀናት በፊት አንስቶ እስከ ወር አበባዎ ሦስተኛው ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ የማይግሬን ህመም የሚያጋጥምዎት ከሆነ እና ይህም ከሦስቱ የወር አበባ ዑደቶች ቢያንስ በሁለቱ ውስጥ የሚከሰት ከሆነ የወር አበባ ምታት ይባላል።
ሐኪምዎ ባሳዩት ምልክቶች እና በማስታወሻዎ ላይ ባሰፈሩት መረጃ ላይ በመመስረት በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት የራስ ምታት እንዳለብዎ ማረጋገጥ ይችላሉ። እንዲሁም ለራስ ምታቱ ሌላ የተለየ ምክንያት አለመኖሩን ለማረጋገጥ የደም ምርመራዎችን እና የምስል ምርመራዎችን (እንደ CT scan ወይም MRI ያሉ) ሊያዙልዎት ይችላሉ።
በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት የራስ ምታት ህክምና ምንድን ነው?
በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት የራስ ምታት ሕክምና እንደ ሰዉ ሁኔታ ሊለያይ ይችላል፣ ማለትም ሕመሙ የሚያጋጥማት በወር አበባዋ አካባቢ ብቻ ነው ወይስ በሌሎች የወሩ ጊዜያትም ጭምር የሚለው ይወሰናል።
መደበኛ የማይግሬን መድኃኒቶች በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት የራስ ምታትን ለማከም ያገለግላሉ። እነዚህም የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
- የድንገተኛ ጊዜ መድኃኒቶች (acute medicines)፦ የማይግሬን ጥቃት በሚከሰትበት ጊዜ ህመሙን ለማስታገስ እና ለማቆም የሚወሰዱ።
- የመከላከያ መድኃኒቶች (preventive medicines)፦ የማይግሬን ህመሙ የሚደጋገምበትን ድግግሞሽ እና የሕመሙን ብርታት ለመቀነስ በቋሚነት የሚወሰዱ።
የህክምና አማራጮቹም የሚከተሉትን ያካትታሉ፡
የህመም ማስታገሻዎች
በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት የራስ ምታትን ለማስታገስ መደበኛ የህመም ማስታገሻዎችን መጠቀም ይችላሉ። እነዚህም ፓራሲታሞል (paracetamol) እና አይቡፕሮፌን (ibuprofen) ያካትታሉ። ከባድ የወር አበባ ህመም (ቁርጠት) የሚያጋጥምዎት ከሆነ፣ ይበልጥ ጠንከር ያሉ ስቴሮይድ ያልሆኑ የብግነት ማስታገሻ መድኃኒቶች (NSAIDs) ሊረዱዎት ይችላሉ። እነዚህም ናፕሮክሰን (naproxen) እና ሜፌናሚክ አሲድ (mefenamic acid) ናቸው። ነገር ግን መድሃኒቶቹን ከመውሰድዎ በፊት ሃኪም ማማከር እንዳይረሱ።
ትሪፕታንስ (Triptans)
አንዳንድ ጊዜ ሐኪምዎ በወር አበባዎ አካባቢ ባሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ትሪፕታንስ (triptans) በመባል የሚታወቁ መድኃኒቶችን እንድትወስዱ ሊመክር ይችላል። ፍሮቫትሪፕታን (frovatriptan) የተባለው የትሪፕታን ዓይነት ለዚህ ተግባር በብዛት ጥቅም ላይ ይውላል። መድኃኒቱን የሚወስዱት አብዛኛውን ጊዜ የማይግሬን ጥቃት ይከሰታል ብለው በሚጠብቁባቸው ቀናት ነው። የወር አበባዎ መደበኛ እና የሚገመት ከሆነ፣ ይህ ጊዜ የወር አበባዎ ከመጀመሩ ከሁለት ቀናት በፊት እስከ ከጀመረ ከሦስት ቀናት በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ ሊሆን ይችላል። የወር አበባዎ መደበኛ ካልሆነ ደግሞ የወር አበባዎ በሚጀምርበት ቀን አንስቶ ለሦስት ቀናት ትሪፕታንስ መውሰድ ሊረዳ ይችላል።
የህመም ማስታገሻዎችን ወይም ትሪፕታንስን በጣም በተደጋጋሚ እና ለረጅም ጊዜ መውሰድ ከመድኃኒት መብዛት የሚመጣ የራስ ምታት (medication overuse headache) ሊያስከትል ይችላል። ይህ የራስ ምታትዎን ሊያባብስ የሚችል ተጨማሪ ችግር ነው።
የእርግዝና መከላከያዎች
ጥምር የሆርሞን እርግዝና መከላከያዎች (Combined hormonal contraception) በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት ራስ ምታትን ለመቆጣጠር ይረዳሉ፣ ምክንያቱም እነዚህ መከላከያዎች ኤስትሮጅን እና ፕሮጄስቶገን የተባሉትን ሁለቱን ሆርሞኖች ይይዛሉ።
ቅድመ ምልክት(አውራ /aura) ያለው የማይግሬን ህመም ወይም ለስትሮክ (stroke) የሚያጋልጡ ሌሎች ምክንያቶች ካሉዎት ጥምር የእርግዝና መከላከያዎችን መውሰድ አይችሉም። ምክንያቱም እነዚ መድሃኒቶች ለስትሮክ የመጋለጥ እድላቸውን የሚጨምር ሊሆኑ ይችላሉ። የተቀናጀውን ክኒን በመውሰድ ላይ እያሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅድመ ምልክት(አውራ /aura) ያለው የማይግሬን ህመም ከተከሰተብዎት ለሐኪምዎ ያሳውቁ። ወደ ሌላ ዓይነት የእርግዝና መከላከያ እንድትቀይሩ ሊመክሩዎት ይችላሉ። ነገር ግን ይህ ቢኖርዎትም ሚኒ-ፒል (mini-pill/ ፕሮጄስቶገን ብቻ ያለው ክኒን) መውሰድ ይችላሉ።
የሆርሞን ማሟያዎች (Hormone supplements)
የኤስትሮጅን ማሟያዎች አንዳንድ ጊዜ የወር አበባ ከመጣበት በፊት እና በሚመጣበት ወቅት የኤስትሮጅን መጠንዎን ለማስተካከል ያገለግላሉ። እነዚህ በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት ራስ ምታት ላለባቸው አንዳንድ ሰዎች ሊረዱ ይችላሉ። ሆኖም ግን ምን ያህል በጥሩ ሁኔታ እንደሚሰራ ለማረጋገጥ በቂ ማስረጃ የለም።
የኤስትሮጅን ማሟያዎች በቆዳ ላይ በሚጣበቅ ፕላስተሮች (skin patches) ወይም ጄል (gel) መልክ ይመጣሉ። በአጠቃላይ የወር አበባዎ ከመጀመሩ ከሁለት ቀናት በፊት በመጀመር ለሰባት ቀናት ያህል ይጠቀሙባቸዋል። የሚሰሩትም የወር አበባዎ መደበኛ ከሆነ ብቻ ነው።
የማቅለሽለሽ ማስታገሻዎች (Antiemetics)
ከማይግሬን ሕመም ጋር ተያይዞ የማቅለሽለሽ ስሜት ለሚያጋጥማቸው ሰዎች፣ የማቅለሽለሽ እና የማስታወክ ስሜትን የሚቀንሱ መድኃኒቶችን ጨምሮ መስጠት ይቻላል።
ያለ መድኃኒት እንዴት መቀነስ ይቻላል?
ያለ መድኃኒት በተፈጥሯዊ መንገድ በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት ራስ ምታትን ለመቆጣጠር የሚረዱ የተለያዩ የሕይወት ዘይቤ ማስተካከያዎች አሉ። የሆርሞን መዋዠቅ የሚያስከትለውን የራስ ምታት የሚያባብሱ ወይም የሚያስታግሱ ነገሮችን ለይቶ ለማወቅ ጥቂት ሙከራዎች ማድረግ ሊያስፈልግዎት ይችላል። ለምሳሌ፦ ብርሃን ሕመም የሚያስከትልብዎት ከሆነ ፣ ጨለም ያለ ክፍል ውስጥ ማረፍ ይቻላል።
ተጨማሪ ጠቃሚ ምክሮች፦
- በቂ እንቅልፍ ያግኙ
- የተመጣጠነ እና ሰዓቱን የጠበቀ ምግብ ይመገቡ
- መደበኛ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ያድርጉ
- የአእምሮ ውጥረትን (Stress) ለመቀነስ ይሞክሩ
- በቂ ውሃ ይጠጡ
መቼ ነው ወደ ጤና ባለሙያ ዘንድ መሄድ ያለብዎት?
ከሚከተሉት ሁኔታዎች አንዱ ካጋጠመዎት ከጤና ባለሙያ ጋር ቀጠሮ ይያዙ፦
- ከወር አበባዎ ጋር ተያይዞ ብርቱ/ጽኑ የሆነ የራስ ምታት የሚያጋጥምዎት ከሆነ።
- የማይግሬን ሕመምዎ ድግግሞሽ ወይም ብርታት የሚጨምር ከሆነ፣ ወይም ደግሞ የራስ ምታትዎ ዓይነት ከተቀየረ።
- አዲስ ወይም የተለየ የመድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳት (side effects) እያጋጠመዎት ከሆነ።
- ሕመሙን ለማከም የሚወሰዱ መድኃኒቶች መስራት ካቆሙ ወይም የዕለት ተዕለት ሕይወትዎን የሚረብሹብዎት ከሆነ።




