35 ዓመት ከሞላሽ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ማርገዝ
በአሁኑ ጊዜ የመጀመሪያ ልጅን ከ35 ዓመት በኋላ መወለድ በጣም የተለመደ እየሆነ መጥቷል። ለትምህርት እና ለስራሽ ቅድሚያ ሰተሽ፣ ትክክለኛውን የትዳር አጋር እየጠበቅሽ ወይም በሌላ ምክንያት ቆይተሽ ከሆነ ብቻሽን አይደለሽም። ከ35 ዓመት በኋላ የሚኖር እርግዝና የተወሰነ ተጨማሪ ትኩረትን የሚፈልግ ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ ሴቶች በተገቢው የቅድመ ወሊድ እንክብካቤ ጤናማ እርግዝና ሊኖራቸው እና ጤናማ ሕፃናትን መውለድ ይችላሉ።
ከ35 ዓመት በኋላ የሚፈጠር እርግዝናን ምን የተለየ ያደርገዋል?
ከ35 ዓመት በኋላ የሚፈጠር የመጀመሪያ እርግዝና ላይ ከእድሜ ጋር የሚመጡ አንዳንድ የእርግዝና አደጋዎች እየጨመሩ ሊሄዱ ስለሚችሉ ተገቢው ጥንቃቄ ያስፈልገዋል እንጂ እርግዝና ከፍተኛ አደጋ ወይም ችግር ይኖረዋል ማለት አይደለም።
ቆየት ብሎ ልጅ የመውለድ ጥቅሞች
ቆየት ብለው እናቶች የሚሆኑ ሴቶች የሚከተሉትን ጥቅሞች ሊያገኙ ይችላሉ።
- ከፍተኛ የስሜት ብስለት
- የተሻለ የኢኮኖሚያዊ አቅም
- የተሻለ እና የተረጋጋ የስራ ህይወት
- ለእናትነት የተሻለ ዝግጅት
- መደበኛ የቅድመ ወሊድ ቀጠሮዎች ላይ በተሻለ ትኩረት መገኘት እና
- የተሻለ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ልምዶችን የመከተል ዕድል የተወሰኑት ጥቅሞች ናቸው።
አደጋዎችን መረዳት
ስነ-ተዋልዶ
እድሜ እየጨመረ ሲሄድ የእንቁላል ቁጥር እና የጥራት ደረጃ እየቀነሰ ስለሚሄድ ለአንዳንዶች እርግዝናን የበለጠ አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል። በአንዳንድ ሁኔታዎች አጋዥ የስነ-ተዋልዶ ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላሉ።
የእርግዝና ችግሮች
ከ35 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች ለሚከተሉት ችግሮች ያላቸው ተጋላጭነት ሊጨምር ይችላል።
- የእርግዝና የስኳር በሽታ
- ከእርግዝና ጋር የተያያዘ ከፍተኛ የደም ግፊት
- ከእንግዴ ልጅ ጋር የተያያዙ ችግሮች
- ከመውለጃ ጊዜ የቀደመ ምጥ
መደበኛ የቅድመ ወሊድ እንክብካቤ እነዚህን ሁኔታዎች ቀደም ብሎ ለመለየት እና ለማስተዳደር ይረዳል።
የዘረ-መል ሁኔታዎች
ዳውን ሲንድሮምን ጨምሮ አንዳንድ ከዘረ-መል ጋር የተያያዙ ችግሮች የመከሰት እድል ከእድሜ ጋር እየጨመረ ሊሄድ ስለሚችል የጤና ባለሙያዎች የሚከተሉትን ሊመክሩ ይችላሉ።
- በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት የሚደረግ ቅድመ ምርመራ
- ወራሪ ያልሆነ የቅድመ ወሊድ ምርመራ
- የእንሽሪት ወሃ ምርመራ
በጣም ተገቢ የሆኑት ምርመራዎች ባንቺ የግል ሁኔታዎች ላይ የተመሰረቱ ናቸው።
ለጤናማ እርግዝና ጠቃሚ ምክሮች
- ቅድመ ወሊድ እንክብካቤን ቀደም ብለሽ ጀምሪ፦ እርግዝናሽን እንዳወቅሽ በቶሎ የመጀመሪያ የቅድመ ወሊድ ክትትልሽን አቅጂ።
- ጤናማ አመጋገብ ተመገቢ:- ፍራፍሬዎችን፣ አትክልቶችን፣ እህሎችን፣ ፕሮቲንን፣ ጤናማ ቅባቶችን እና በካልሲየም እና አይረን የበለፀጉ ምግቦችን ተመገቢ። ከ400-800 ማይክሮግራም ፎሊክ አሲድን የያዘ የቅድመ ወሊድ ቫይታሚን ውሰጂ።
- ንቁ ሁኚ:- መራመድ፣ መዋኘት እና የቅድመ ወሊድ ዮጋ የደም ዝውውርን ሊያሻሽሉ፣ የጀርባ ህመምን ሊቀንሱ እና ጤናማ ክብደትን ሊደግፉ ይችላሉ። አዲስ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከመጀመርሽ በፊት ሁልጊዜ የእርግዝና ክትትል ሃኪምሽን አማክሪ።
- ከእርግዝና በፊት የነበሩብሽን የጤና ችግች በአግባቡ አስተዳድሪ:- እንደ ስኳር በሽታ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት ወይም የእንቅርት በሽታ ያሉ ሁኔታዎችን በእርግዝናሽ ወቅት በደንብ ተቆጣጠሪ።
- ጎጂ ንጥረ ነገሮችን አስወግጂ:- ማጨስን፣ አልኮልን እና የመዝናኛ ንጥረ-ነገሮችን አስወግጂ።
- ተጨማሪ ክትትል:- እንደ ጤናሽ ሁኔታ የሚከተሉት ሊያስፈልጉሽ ይችላሉ።
- ተጨማሪ የቅድመ ወሊድ ክትትል ጉብኝቶች
- ተጨማሪ የአልትራሳውንድ ምርመራዎች
- የደም ግፊት እና የደም ስኳር ክትትል
- የፅንስ እድገት ግምገማዎች
እነዚህ ምርመራዎች የአንቺን እና የሕፃኑን ደህንነት ለማረጋገጥ ይረዳሉ።
- ምጥ እና ወሊድ:- ከ35 ዓመት በላይ የሆናቸው እናቶች በወሊድ ወቅት የምጥ መርፌ፣ የወሊድ እርዳታ ወይም በቀዶ ጥገና ማዋለድ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ሆኖም ግን አብዛኛዎቹ ያልተወሳሰበ የመሃጽን ወሊድ ይኖራቸዋል። የወሊድ እቅድሽ በጤናሽ፣ በጽንስሽ ሁኔታ እና በምጥሽ በሃሪ ላይ የተመሠረተ ይሆናል።
መቼ ወደ ጤና ተቋም መሄድ አለብሽ?
የሚከተሉት ሁኔታዎች ጋካጋጠሙሽ የሕክምና እርዳታን ማግኘት አለብሽ፦
- ከመሃጸን ደም መፍሰስ
- የእንሽሪት ወሃ መፍሰስ
- ከባድ የሆድ ህመም
- ቀጣይነት ያለው ከባድ ራስ ምታት
- ብዥ ያለ እይታ
- የፊት ወይም የእጅ እብጠት
- የፅንስ እንቅስቃሴ መቀነስ
- ትኩሳት
- ከ37 ሳምንታት በፊት መደበኛ እና የማያቋርጥ የመሃጸን ቁርጠት
ፈጣን የሕክምና እርዳታ ከባድ ችግሮችን በአግባቡ ሊከላከል ይችላል።
የስነ-ልቦና ደህንነት
በማንኛውም እድሜ እርግዝና ፈታኝ ሊሆን ይችላል። የቅድመ ወሊድ ትምህርቶችን መከታተል፣ በቤተሰብ እና በጓደኞች በቂ ድጋፍ በማግኘት እና ከሃኪምሽ ጋር ስለ ጭንቀት ወይም ድብርት በመወያየት የስነ-ልቦና ጫናን መቆጣጠር ትችያለሽ። ጤናማ አእምሮ ለተሳካ እርግዝና እጅግ አስፈላጊ ነው።
በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎች
ከ35 ዓመት በኋላ ጤናማ ልጅ መውለድ እችላለሁ?
በሚገባ! መደበኛ የቅድመ ወሊድ እንክብካቤ ያላቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆኑ እናቶች በጤናማ እርግዝና ጤናማ ሕፃናትን መውለድ ይችላሉ።
ግዴታ በቀዶ-ጥገና መውለድ ያስፈልገኛልን?
የግድ አይደለም! እድሜ ሲጨምር በቀዶ-ጥገና የመውለድ እድል ከሌሎች ትንሽ ከፍ ያለ ቢሆንም ከ35 ዓመት በላይ የሆኑ አብዛኛዎቹ ሴቶች በተሳካ ሁኔታ በምጥ መውለድ ይችላሉ።
የዘረ-መል ምርመራ ማድረግ አለብኝ?
እሚቻል ከሆነ የዘረ-መል ምርመራ ለሁሉም እርጉዝ ሴቶች ይመከራል(በተለይም ከ35 ዓመት በኋላ)። የትኞቹ ምርመራዎች አስፈላጊ ላንቺ አስፈላጊ እንደሆኑ ለማወቅ ሃኪምሽን በሚገባ አማክሪ።




