ልጅዎ ተቅማጥ ሲይዘው ምን መመገብ አለበት?
ሊከለክሏቸው የሚገቡ ምግቦችና መጠጦችስ የትኞቹ ናቸው ?
ልጅዎ ተቅማጥ ሲይዘው መጨነቅዎ አይቀርም። ተቅማጥ ከሚያስከትለው ከፍተኛ ፈሳሽ ሰገራ በተጨማሪ በተለይም በትናንሽ ሕፃናት ላይ የሰውነት ፈሳሽ እና የኤሌክትሮላይት እጥረት ሊያስከትል ይችላል። ስለሆነም በዚህ ወቅት ልጅዎ ምን መብላትና መጠጣት እንዳለበት የትኞቹን ምግቦች ደግሞ ማስወገድ እንደሚገባ አውቆ ተገቢውን የቤት ውስጥ እንክብካቤ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው።
በዚህ ፅሁፍ የተቀመጠውን መረጃ በመያዝ የልጅዎን ማገገም መደገፍ እና የጎንዮሽ ጉዳቶችን መቀነስ ይችላሉ።
ልጅዎ ተቅማጥ በሚይዘው ጊዜ ሊሰጡት የሚገቡ ምግቦችና መጠጦች
ልጅዎ ተቅማጥ በሚይዘው ጊዜ በቂ የሰውነት ፈሳሽ እንዲኖረው ማድረግና ትክክለኛውን ምግብ መስጠት በፍጥነት እንዲያገግም ይረዳዋል። በዚህ ወቅት አልሚ እና ለመፈጨት ቀላል የሆኑ ምግቦችን በትንሽ በትንሹ በተደጋጋሚ መስጠት ይመከራል።
ጨቅላ ሕፃናት (ከ1 ወር እስከ 1 ዓመት)
ጡት የሚጠቡ ሕፃናት እንደተለመደው መጥባታቸውን በደንብ መቀጠል አለባቸው። የእናት ጡት ወተት በቂ ፈሳሽ፣ አልሚ ንጥረ ነገሮች እና ኢንፌክሽንን ለመዋጋት የሚረዱ ፀረ-እንግዳ አካላትን (Antibodies) ይሰጣል።
የፎርሙላ ወተት የሚመገቡ ሕፃናትም ወተቱን መጠጣት መቀጠል አለባቸው። ሆኖም በጤና ባለሙያ ከተመከረ በጊዜያዊነት ላክቶስ የሌለው (Lactose-free) የፎርሙላ ወተት መጠቀም ሊያስፈልግ ይችላል።
በተጨማሪም በተቅማጥ ምክንያት የጎደለውን የሰውነት ፈሳሽና ኤሌክትሮላይቶች ለመተካት የኦአርኤስ (ORS) ፈሳሽ በተደጋጋሚ መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው።
ታዳጊ ሕፃናት (ከ1 እስከ 5 ዓመት)
ቀኑን ሙሉ በተደጋጋሚ የኦአርኤስ (ORS) ፈሳሽ በማስጎንጨት አነስተኛ መጠን ያላቸውን ምግቦች በየጊዜው ይስጧቸው። ሊሰጧቸው ከሚችሏቸው ምግቦች መካከል ፦
- የሩዝ አጥሚት/ሾርባ (Rice porridge)፦ ምንም ቅመም ያልተጨመረበት የተቀቀለ ነጭ ሩዝ ወይም መረቅ
- የተፈጨ ሙዝ ፣ ደረቅ ቶስት (የተጠበሰ ዳቦ) ወይም የተቀቀለ ድንች
- በደንብ የበሰለ የዶሮ ሥጋ፣ ዓሣ ወይም እንቁላል
- ለስላሳ ሆነው የበሰሉ አትክልቶች (እንደ ካሮት እና ዱባ ያሉ)
አደግ ያሉ ሕፃናት (ከ6 እስከ 12 ዓመት)
በተደጋጋሚ ፈሳሽ በተለይም የኦአርኤስ (ORS) ፈሳሽ እንዲጠጡ ያበረታቷቸው። ከዚህ በተጨማሪ ለመፈጨት ቀላል የሆኑ የተመጣጠኑ ምግቦችን ይስጧቸው፦
- ምንም ያልተጨመረበት ነጭ ሩዝ፣ ፓስታ፣ ቶስት፣ ደረቅ ብስኩት (Crackers) ወይም የተቀቀለ ድንች
- እንደ የዶሮ ሥጋ፣ ዓሣ ወይም እንቁላል ያሉ ስብ የሌላቸው የፕሮቲን ምንጮች
- የተቀቀሉ አትክልቶች (እንደ ካሮት እና ዱባ ያሉ)
ልጅዎ ማገገም ሲጀምር ቀስ በቀስ ወደ መደበኛ አመጋገቡ ይመልሱት። አንዳንድ ሕፃናት መደበኛ አመጋገባቸውን እንደገና ሲጀምሩ አነስተኛና ጊዜያዊ ተቅማጥ ሊያጋጥማቸው ይችላል፤ ይህም ሁኔታ አንጀታቸው ሙሉ በሙሉ እያገገመ ሲሄድ በራሱ ይስተካከላል።
ልጅዎ ተቅማጥ ሲኖረው መስጠት የሌለብዎት ምግቦች
ልጅዎ ተቅማጥ በሚይዘው ጊዜ አንጀቱ ስለሚቆጣ ፈሳሾችንና ንጥረ ነገሮችን የመምጠጥ አቅሙ ይቀንሳል። የተወሰኑ ምግቦችና መጠጦች ደግሞ ወደ አንጀት ውስጥ ተጨማሪ ውሃ በመሳብ፣ አንጀትን በማስቆጣት ወይም ለመፈጨት አስቸጋሪ በመሆን ምልክቶቹን ሊያባብሱ ይችላሉ።
የልጅዎ አንጀት አግግሞ እስኪበቃ ድረስ የሚከተሉትን ምግቦችና መጠጦች ከመስጠት ይቆጠቡ፦
- የፍራፍሬ ጭማቂዎች እና የለስላሳ መጠጦች
በተለይም የፖም (አፕል)፣ የፒር እና የቼሪ ጭማቂዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ስኳር (ፍሩክቶስ እና ሶርቢቶል) የያዙ በመሆናቸው ወደ አንጀት ውስጥ ተጨማሪ ውሃ ይስባሉ። ይህም ተቅማጡን ሊያባብስ እና የሰውነት ፈሳሽ እጥረትን ሊጨምር ይችላል።
- ወተት እና የወተት ተዋጽኦዎች
እንደ ወተት፣ አይብ፣ እርጎ እና አይስክሬም ያሉ ተዋጽኦዎችን ከልጅዎ አመጋገብ ላይ ለጊዜው ያስወግዱ ። በተቅማጥ ወቅት የአንጀት ግድግዳ ላክቶስን (የወተት ስኳርን) ለመፈጨት የሚያስፈልገውን "ላክቴዝ" የተባለ ኢንዛይም የማምረት አቅሙ ይቀንሳል። ይህም ጊዜያዊ የላክቶስ አለመስማማት (Lactose Intolerance) በማስከተል ተቅማጥን፣ የሆድ መነፋትና ቁርጠትን ያባብሳል።
ሆኖም ግን ለሚጠቡ ሕፃናት የእናት ጡት ወተት መስጠትዎን በፍጹም ማቋረጥ የለብዎትም። የእናት ጡት ወተት ለሕፃኑ ምርጥ የንጥረ ነገር እና የፈሳሽ ምንጭ ነው።
- ቅባት የበዛባቸው፣ የተጠበሱ እና ከፍተኛ ስብ ያላቸው ምግቦች
እንደ ፒዛ፣ በርገር፣ ቺፕስ፣ ኬክ፣ ዶናት እና ሶሴጅ ያሉ ምግቦች ለመፈጨት ከባድ በመሆናቸው የተቆጣው የምግብ መፈጨት ሥርዓት ላይ ተጨማሪ ጫናን ይፈጥራሉ። ከዚህም በተጨማሪ የአንጀት እንቅስቃሴን በመጨመር ተቅማጡ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆይ እና ሕፃኑ ቶሎ እንዳያገግም ያደርጋሉ።
- ከፍተኛ ፋይበር ያላቸው እና ጋዝ የሚፈጥሩ ምግቦች
እንደ ብሮኮሊ፣ ጎመን፣ ባቄላ፣ አተር፣ በቆሎ፣ ሽምብራ፣ አረንጓዴ ቅጠላቅጠሎች እና ልጣጭ ያላቸው ፍራፍሬዎች ከፍተኛ ፋይበር በውስጣቸው ስላላቸው የአንጀት እንቅስቃሴን በመጨመር የሆድ መነፋትን ፣ ቁርጠትን እና ምቾት ማጣትን ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ስለሆነም ልጅዎ ተቅማጥ ሲኖረው ለሆድ ቀላል የሆኑ፣ ለስላሳ እና አነስተኛ ፋይበር ያላቸው ምግቦችን ይምረጡ።
- ፕሩን (ደረቅ ፕለም) እና ፕለም
ሰገራን የማለስለስ ተፈጥሯዊ ባህሪ (Laxative effect) ያላቸው እንደ ሶርቢቶል ያሉ ተፈጥሯዊ ስኳሮችን በውጣቸው በመያዛቸው ሰገራውን ይበልጥ ፈሳሽ በማድረግ ተቅማጡን ሊያባብሱት ይችላሉ።
- በርበሬ እና ቅመም የበዛባቸው ምግቦች
በጣም ኮምጣጣ፣ በርበሬ ወይም ቅመም የበዛባቸው ምግቦች የጨጓራና የአንጀት ግድግዳዎችን በማስቆጣት የሆድ ሕመም እና ቁርጠትን ይጨምራሉ።
- ካፌይን ያላቸው መጠጦች
እንደ ቡናና ሻይ ያሉ መጠጦች አንጀትን በማነቃቃት የአንጀት እንቅስቃሴን ስለሚጨምሩ ተቅማጥ እንዲባባስ ያደርጋሉ።
ሐኪሞች ጋር መቼ መሄድ ያስፈልጋል?
ልጅዎ ላይ ከሚከተሉት ምልክቶች መካከል አንዱን እንኳን ካስተዋሉ ወዲያውኑ የሕክምና እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋል ፦
- እንደ የአፍ መድረቅ፣ የዓይን መጎድጎድ (መሰርጎድ)፣ ሲያለቅሱ እንባ አለመኖር ወይም ከ6 ሰዓት በላይ ሽንት አለመሽናት ያሉ የሰውነት ፈሳሽ እጥረት (dehydration ) ምልክቶች
- በሰገራ ውስጥ ደም ወይም ንፍጥ የሚመስል ፈሳሽ (Mucus) መኖር
- የማይቀንስ ወይም ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት
- ከባድ ወይም እየባሰ የሚሄድ የሆድ ቁርጠት
- ከፍተኛ የእንቅልፍ ስሜት፣ መደበኛ ያልሆነ መፍዘዝ ወይም የንቃተ-ሕሊና መቀነስ
- ለበርካታ ቀናት የቆየ ወይም እየባሰ የሄደ ተቅማጥ



