ሙሉ ጊዜውን የጠበቀ እርግዝና ወደ 40 ሳምንታት ገደማ ይቆያል። አንድ ልጅ ያለጊዘው ወይም ከቀኑ በፊት ተወለደ የምንለው ሕፃኑ ከ37 የእርግዝና ሳምንት ቀድሞ ሲወለድ ነው።
ከቀኑ በፊት ወይም ቀድሞ መወለድ በጨቅላ ሕፃን ላይ ከባድ የጤና አደጋዎችን ሊያስከትል ይችላል። ይህ የሆነበት ምክንያት እንደ አንጎል፣ ሳንባ እና ጉበት ያሉ ብዙ የሰውነት ክፍሎች በእርግዝናው የመጨረሻ ሳምንታት ላይም በማደግ ላይ ስለሚሆኑ ነው። ከሚከሰቱት ችግሮች መካከል አንዳንዶቹ ለበርካታ ዓመታት፣ እስከ አዋቂነት ዕድሜ ድረስ እንኳ ላይታዩ ይችላሉ። እነዚህ ከቀናቸው በፊት የተወለዱ ሕፃናት በጨቅላ ሕፃናት ጽኑ ሕክምና ክፍል (NICU ተብሎም በሚጠራው) ውስጥ ልዩ የሕክምና እንክብካቤ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። የጤና ችግሮችን በተቻለ መጠን ቀድሞ ማግኘትና ማከም፣ እንዲሁም ከተቻለ ከቀን በፊት የሚደረግ ወሊድን መከላከል፣ ሕፃናት ረጅም እና ጤናማ ሕይወት እንዲኖራቸው ይረዳል።
በህክምናው አለም ከቀናቸው በፊት የሚወለዱ ሕፃናት በአራት ክፍሎች ይከፈላሉ፦
- በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ከቀናቸው በፊት የተወለዱ (Late preterm)፦ በ34 እና 36 ሳምንታት መካከል የተወለዱ። አብዛኛዎቹ ከቀናቸው በፊት የሚወለዱ ሕፃናት በዚህ ጊዜ ውስጥ የሚወለዱ ናቸው።
- በመካከለኛ ደረጃ ከቀናቸው በፊት የተወለዱ (Moderately preterm)፦ በ32 እና 34 ሳምንታት መካከል የተወለዱ።
- በጣም ቀድመው ከቀናቸው በፊት የተወለዱ (Very preterm)፦ ከ32 ሳምንታት በፊት የተወለዱ።
- በእጅጉ ቀድመው ከቀናቸው በፊት የተወለዱ (Extremely preterm)፦ ከ28 ሳምንታት በፊት የተወለዱ።
አብዛኛዎቹ ከቀናቸው በፊት የሚወለዱ ሕፃናት የሚወለዱት በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ከቀናቸው በፊት በተወለዱበት (Late preterm) ደረጃ ላይ ነው።
ያለጊዘው መወለድ በምን ምክንያት ይከሰታል?
ከቀን በፊት የሚደረግ ወሊድ ያለ ምንም አንድ አበይት ምክንያት በድንገት ሊከሰት ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የሕክምና ባለሙያዎች በሕክምና ምክንያቶች ሳቢያ ምጥ ቀድሞ እንዲጀምር (እንዲቀሰቀስ) ማድረግ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም ሴቶች በሚከተሉት ምክንያቶች ሳቢያ ቀድመው ወደ ምጥ ሊገቡ ይችላሉ፦
- እንደ ስኳር ወይም የልብ ሕመም ያሉ ስር የሰደዱ የጤና ችግሮች መኖር
- እንደ እንግዴ ልጅ ቀድሞ መላቀቅ (placental abruption) ወይም ማህፀን በር የሚጋርድ የእንግዴ ልጅ (placenta previa) ያሉ የፕላሴንታ ችግሮች መኖር
- በእርግዝና ጊዜ የሚኖር ደም ግፊት (Preeclampsia)
- መንታ ወይም ከዚያ በላይ ፅንስ መፀነስ፦ ከ60% ያህሉ መንታ እና ሶስት መንታ ሕፃናት ከቀናቸው በፊት ይወለዳሉ።
- የማህፀን ወይም የማህፀን በር (cervix) ችግሮች መኖር
- በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ደም መፍሰስ ወይም የማህፀን ኢንፌክሽኖች መኖር
- በእርግዝና ወቅት እንደ ዕፅ፣ አልኮል ወይም ሲጋራ ያሉ አደንዛዥ ነገሮችን መጠቀም
- ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ወይም ከ35 ዓመት ሆኖ መጸነስ/መውለድ
- በቤተሰብ ወይም በግል ከቀን በፊት የመውለድ ታሪክ ካላቸው
- ከእርግዝና በፊት ከክብደት በታች የሆኑ ወይም በእርግዝና ወቅት በቂ ክብደት የማይጨምሩ ከሆነ
- በእርግዝናዎች መካከል ከስድስት ወር ያነሰ ጊዜ መኖር። በእርግዝናዎች መካከል ከ18 እስከ 24 ወራት ያህል መቆየት ተመራጭ ነው።
- ከአንድ በላይ የፅንስ መቋረጥ መኖር
- በሰውነት ላይ የደረሱ ጉዳቶች ወይም አደጋዎች ካሉ
ከቀን በፊት የመወለድ የሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች ምንድን ናቸው?
ከቀኑ በፊት የተወለደ ሕፃን ሙሉ በሙሉ ለማደግ በቂ ጊዜ አያገኝም። ይህም ማለት የተወሰኑ የሰውነት ክፍሎች እና ሥርዓቶች ከማህፀን ውጭ ባለው ሕይወት ውስጥ ሕፃኑን ለመደገፍ ዝግጁ ላይሆኑ ይችላሉ።
1.በሕፃን አንጎል ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ
ከቀን በፊት መወለድ በሕፃናት ላይ የረጅም ጊዜ የአእምሮ እና የእድገት እክሎችን ሊያስከትል ይችላል። እነዚህ የአንጎል አሰራር ችግሮች ናቸው። እነዚህም በአንድ ሰው ላይ በሚከተሉት ነገሮች ላይ ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ፦
- አካላዊ እድገት
- የመማር ችሎታ
- ማህበረሰባዊ ግንኙነት
- ራስን መንከባከብ ችሎታ
- ከሌሎች ጋር መግባት/መስማማት
ከቀን በፊት ከመወለድ ጋር የተያያዙ የረጅም ጊዜ የጤና ሁኔታዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
- ሴሬብራል ፓልሲ (Cerebral Palsy / CP)፦ ይህ ጡንቻዎችን የሚቆጣጠሩትን የአንጎል ክፍሎች የሚጎዱ የሁኔታዎች ስብስብ ነው። ይህም በእንቅስቃሴ፣ በአካላዊ አቋም (ቀጥ ብሎ መቆም) እና በሚዛን አጠባበቅ ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል።
- የባህሪ ችግሮች፦ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከቀናቸው በፊት የተወለዱ ሕፃናት በሰዓታቸው ከተወለዱት ይልቅ ለትኩረት ማጣትና ባህሪ መቆጣጠር ችግር (ADHD) የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።
- የአእምሮ ጤና ሁኔታዎች፦ ከቀናቸው በፊት የተወለዱ ሕፃናት በኋለኛው የሕይወት ዘመናቸው ለጭንቀት (Anxiety) ወይም ለድብርት (Depression) የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።
- የነርቭ ሥርዓት እክሎች (Neurological disorders)፦ እነዚህ ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ አንጎልን፣ የሕብረ-ሰረሰርን (spinal cord) እና በሰውነት ውስጥ ያሉ ነርቮችን ይጎዳሉ።
- አንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ (Intraventricular hemorrhage)፦ ኢንትራቬንትሪኩላር ሄሞሬጅ (IVH) ማለት የአንጎል ፈሳሽን (cerebrospinal fluid) በሚይዙት የአንጎል ክፍሎች (ventricles) ውስጥ ወይም ዙሪያ የሚከሰት ደም መፍሰስ ነው። ይህ ሁኔታ ከቀናቸው በፊት በተወለዱ ሕፃናት፣ በተለይም በጣም አነስተኛ የወሊድ ክብደት ባላቸው ሕፃናት (ከ1.5 ኪሎግራም ወይም 3 ፓውንድ ከ5 ኦውንስ በታች የሆኑ) ላይ በጣም የተለመደ ነው። ደም የመፍሰስ አደጋ ሊከሰት የሚችለው ከቀኑ በፊት የተወለደ ሕፃን በአንጎል ውስጥ የሚገኙ የደም ሥሮች በጣም ስስ እና ገና ያላደጉ በመሆናቸው ምክንያት ነው፤ በመሆኑም በቀላሉ ሊፈነዱ ይችላሉ። በዚህ የሚጎዱ አብዛኛዎቹ ሕፃናት ይህ ሁኔታ የሚከሰትባቸው ከተወለዱ በኋላ ባለው የመጀመሪያው ሳምንት ውስጥ ነው።
2. በሕፃን ሳንባ ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ
ከቀን በፊት መወለድ ሕፃኑ የሚከተሉትን ጨምሮ ለሳንባ እና የመተንፈስ ችግሮች እንዲጋለጥ ሊያደርገው ይችላል፦
- አስም፦ ይህ የመተንፈሻ አካላትን የሚጎዳ እና የመተንፈስ ችግርን የሚያስከትል የጤና ሁኔታ ነው።
- ብሮንኮፑልሞናሪ ዲሰፕላዚያ (BPD ተብሎም የሚጠራ)፦ ይህ ከቀናቸው በፊት በተወለዱ ሕፃናት እንዲሁም የመተንፈሻ መሳሪያ (breathing machine) ሕክምና በተደረገላቸው ሕፃናት ላይ ሊከሰት የሚችል የሳንባ በሽታ ነው። ይህ በሽታ በሳንባ ውስጥ እብጠት እና ጠባሳ ሊፈጥር ይችላል። ይህ ሁኔታ ያላቸው ሕፃናት እንደ ሳንባ ምች ላሉ የሳንባ ኢንፌክሽኖች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው። በጊዜ ሂደት ሳንባዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚያገግሙ ቢሆንም፣ ከቀኑ በፊት የተወለደ ሕፃን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ከአስም ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ምልክቶች ወይም የረጅም ጊዜ የሳንባ ጉዳት ሊኖርበት ይችላል።
- አፕኒያ (Apnea)፦ከቀን በፊት መወለድ ምክንያት የሚከሰት አፕኒያ (AOP) ማለት ጊዜያዊ የመተንፈስ መቋረጥ (ከ20 ሴኮንድ በላይ የሚቆይ) ማለት ነው። ይህም ከቀናቸው በፊት በተወለዱ ሕፃናት ላይ የተለመደ ነው። ከአፕኒያ ጋር ተያይዞ አብዛኛውን ጊዜ የልብ ምት መቀነስ እና በደም ውስጥ ያለው የኦክስጅን መጠን መቀነስ ይከሰታል።
- የሪስፓራቶርይ ዲስትረስ ሲንድረም (Respiratory distress syndrome)፦ ይህ የመተንፈስ ችግር ከሕፃኑ የሳንባ አለመብሰል ጋር የተያያዘ የመተንፈስ እክል ነው። ይህ የሚከሰተው ከቀናቸው በፊት የተወለዱ ሕፃናት ሳንባ አብዛኛውን ጊዜ ሳንባዎች ተነፍተው እንዲቆዩ የሚያስችለውን «ሰርፋክታንት» (surfactant) የተባለ ፈሳሽ ስለሚያጥራቸው ነው።
3. ሌሎች የረጅም ጊዜ የጤና ችግሮች
ከቀን በፊት መወለድ ወደ የሚከተሉት የጤና ችግሮች ሊመራ ይችላል፦
- የልብ ችግሮች፦ ከቀናቸው በፊት የተወለዱ ሕፃናት የሚያጋጥሟቸው የተለመዱ የልብ ችግሮች ‘ፓተንት ደክተስ አርቴሪዮሰስ’ (PDA) እና ዝቅተኛ የደም ግፊት ናቸው። ፓተንት ደክተስ አርቴሪዮሰስ በሁለት አስፈላጊ የደም ሥሮች መካከል የሚገኝ ክፍተት/ቀዳዳ ነው። ይህ የልብ ጉድለት አብዛኛውን ጊዜ በራሱ ይዘጋል። ነገር ግን ያለ ሕክምና ከተተወ ወደ ልብ ድካም (heart failure) ያሉ ችግሮች ሊመራ ይችላል።
- የጥርስ ችግሮች፦ ከቀናቸው በፊት የተወለዱ ሕፃናት እያደጉ ሲሄዱ የጥርስ እድገታቸው ሊዘገይ፣ የጥርስ ቀለማቸው ሊቀየር ወይም ጥርሶቻቸው ተጣመው/ተደራርበው ሊበቅሉ ይችላሉ።
- የመስማት ችግር፦ ከቀናቸው በፊት የተወለዱ ሕፃናት በሰዓታቸው ከተወለዱት ይልቅ ለመስማት ችግር የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው።
- ኢንፌክሽኖች፦ የበሽታ መከላከል ሥርዓታቸው ሙሉ በሙሉ ስላላደገ ከቀናቸው በፊት የተወለዱ ሕፃናት አብዛኛውን ጊዜ በሽታ አምጪ ተህዋስያንን መዋጋት ያቅታቸዋል። ይህም ማለት በቀላሉ ለኢንፌክሽኖች ሊጋለጡ ይችላሉ። ሕፃኑ እያደገ ሲሄድም እንኳ ኢንፌክሽኖች አሁንም ችግር ሆነው ሊቀጥሉ ይችላሉ።
- የአንጀት ችግሮች፦ እነዚህ ችግሮች ነክሮታይዚንግ ኢንቴሮኮላይቲስ (NEC ተብሎም በሚጠራው) ምክንያት ሊከሰቱ ይችላሉ። ይህ በጨቅላ ሕፃናት አንጀት ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል የተለመደ ነገር ግን በጣም ከባድ የሆነ በሽታ ነው። አብዛኛዎቹ ነክሮታይዚንግ ኢንቴሮኮላይቲስ ያላቸው ሕፃናት የሚያገግሙ ቢሆንም፣ አንዳንዶቹ ግን እንደ የአንጀት ጠባሳ ወይም መዘጋት ያሉ ተደጋጋሚ የአንጀት ችግሮች ሊኖሩባቸው ይችላል። እነዚህን ችግሮች ለማከም ቀዶ ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላል። የአንጀታቸውን ክፍል ለማስወገድ ቀዶ ሕክምና የተደረገላቸው ሕፃናት ከምግብ ውስጥ ንጥረ ነገሮችን የመጠቀም/የመቀበል ችግር ሊኖራቸው ይችላል።
- የዕይታ ችግሮች (Retinopathy of prematurity) እንደ ሬቲኖፓቲ ኦፍ ፕሪማቱሪቲ / ROP ያሉ)፦ ይህ ብዙ ከቀናቸው በፊት የተወለዱ ሕፃናትን የሚጎዳ የዓይን በሽታ ነው። ያለጊዜ በመወለድ ምክንያት የሚከሰት የአይን ችግር የሚመጣው ሕፃኑ ከተወለደ በኋላ ባሉት ሳምንታት ውስጥ የሕፃኑ ውስጠኛው የአይን ክፍል (ሬቲና/retina) ሙሉ በሙሉ ሳያድግ ሲቀር ነው። ሬቲና ከዓይን በስተጀርባ የሚገኝ የነርቭ ሕዋስ ሽፋን ነው። ይህ ሁኔታ አብዛኛውን ጊዜ ሁለቱንም ዓይኖች ይጎዳል። ከቀናቸው በፊት የተወለዱ ሕፃናት በሰዓታቸው ከተወለዱት ይልቅ ለዕይታ ችግሮች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው።
- የደም ማነስ (Anemia)፦ ይህ የሚከሰተው በቂ የሆነ ጤናማ የቀይ ደም ሕዋሳት ስለማይኖሩ ነው።
- የቆዳ እና ዓይን ቢጫ መሆን (Jaundice)፦ የጃንዲስ በሽታ የሚከሰተው ቢሊሩቢን (bilirubin) የተባለው ኬሚካል በሕፃኑ ደም ውስጥ ሲከማች ነው። በዚህም ምክንያት የሕፃኑ ቆዳ ወደ ቢጫነት የተቀየረ መልክ ሊይዝ ይችላል።
- የሰውነት ሙቀት የመቆጣጠር ችግሮች፦ ከቀናቸው በፊት የተወለዱ ሕፃናት የሰውነት ሙቀትን በፍጥነት ሊያጡ ይችላሉ ምክንያቱም በጊዜያቸው እንደተወለዱ ሕፃናት በሰውነታቸው ውስጥ የተከማቸ ስብ የላቸውም። እንዲሁም በሰውነታቸው ገጽ በኩል የሚባክነውን ሙቀት ለመተካት የሚያስችል በቂ ሙቀት ማመንጨት አይችሉም። የሰውነት ሙቀት በጣም ዝቅ ካለ ‘ሃይፖተርሚያ’ (hypothermia) ወደተባለው አደገኛ ችግር ሊመራ ይችላል። ከቀኑ በፊት በተወለደ ሕፃን ላይ የሚከሰት ሃይፖተርሚያ ወደ መተንፈስ ችግሮች እና ዝቅተኛ የደም ስኳር መጠን ሊመራ ይችላል። በተጨማሪም ከቀኑ በፊት የተወለደ ሕፃን ሰውነቱን ለማሞቅ ብቻ ሲል ከምግብ የሚያገኘውን ሃይል በሙሉ ሊጨርስ ይችላል። ለዚህ ነው አንዳንድ ከቀናቸው በፊት የተወለዱ ሕፃናት በመጀመሪያው ወቅት ማሞቂያ መቆየት የሚያስፈልጋቸው።
- የመማር ችሎታ መቀነስ፦ ከቀናቸው በፊት የተወለዱ ሕፃናት በትክክለኛ ጊዜያቸው ከተወለዱት ሕፃናት ይልቅ በተለያዩ የዕድገት ደረጃዎች ወደኋላ የመቅረት እድላቸው ከፍተኛ ነው። በጣም ቀድሞ የተወለደ ህጻን የትምህርት ዕድሜ ላይ ሲደርስ የመማር እክል የመኖር እድሉ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።




