በውበት ምርቶች ውስጥ የሚገኙ ካንሰር አምጪ ንጥረ ነገሮች
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሸማቾች በቆዳ እንክብካቤ፣ በሜካፕ እና በፀጉር ውበት መጠበቂያ ምርቶች ውስጥ ስላሉት ንጥረ ነገሮች እየተገነዘቡ መጥተዋል። ከእነዚህ ንጥረ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ከካንሰር ጋር የተያያዙ መሆናቸው ስለ ደህንነታቸው ጥያቄዎችን ያስነሳል። የውበት መጠበቂያ ምርቶችን በሚገዙበት እና በሚጠቀሙበት ጊዜ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንዲያደርጉ በዚህ ጽሁፍ ላይ በነዚህ ምርቶች ውስጥ የሚገኙትን የተለመዱ ካንሰር አምጪ ነገሮችን እንመረምራለን።
ካርሲኖጂንስ ምንድን ናቸው?
ካርሲኖጂንስ ኬሚካሎች፣ ውህዶች እና አንዳንድ የተፈጥሮ ንጥረ ነገሮችን ጨምሮ በተለያዩ ቅርጾች ሊገኙ የሚችሉ የሰውነታችን አካላቶችን ወደ ካንሰር ሊያመሩ የሚችሉ ንጥረ ነገሮች ናቸው ። በውበት መጠበቂያ ምርቶች ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ንጥረ ነገሮች ከካንሰር ጋር ሊገናኙ ስለሚችበሉት ሁኔታ ጥናቶች የተደረጉ ሲሆን፣ በተለያዩ ምርቶች ውስጥ የካንሰር አምጪ ንጥረ ነገሮች መኖር የካንሰር መከሰትን እንደማያረጋግጥ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። የካንሰር የመከሰት እድል ብዙውን ጊዜ ለአምጪ ነገሮች ባለ የተጋላጭነት ደረጃ እና በግለሰቡ ተፈጥሯዊ ተጋላጭነት ላይ የተመሰረተ ነው።
በውበት ምርቶች ውስጥ የተለመዱ ካንሰር አምጪ ንጥረ ነገሮች
1. ፎርማልዲሃይድ እና ፎርማልዲሃይድ የሚለቁ ወኪሎች
ፎርማለዳይድ ብዙውን ጊዜ በፀጉር አጠባበቅ ምርቶች፣ በጥፍር ምርቶች እና በአንዳንድ የቆዳ እንክብካቤ ዕቃዎች ውስጥ የሚገኝ የታወቀ ካንሰር አምጪ ንጥረ ነገር ነው። ረዘም ላለ ጊዜ ለፎርማልዲሃይድ መጋለጥ የቆዳ መቆጣት እና የመተንፈስ ችግርን ከማስከተል በተጨማሪ የአንዳንድ ካንሰር በሽታዎች የመከሰት እድልን ሊጨምር ይችላል።
2. ፓራበንስ
ፓራበንስ በመዋቢያ ምርቶች ውስጥ በአይን የማይታዩ የጥቃቅን ህዋሳት እድገትን ለመከላከል ጥቅም ላይ የሚውሉ ንጥረ ነገሮች ናቸው። አንዳንድ ጥናቶች በሰውነት ውስጥ ኤስትሮጅን የተሰኘውን ሆርሞን መምሰል ስለሚችሉ፤ በፓራበን እና በጡት ካንሰር መካከል ግንኙነት ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል። ተጨማሪ ምርምር የሚያስፈልግ ቢሆንም፣ ሸማቾች ከፓራበን-ነጻ የሆኑ ምርቶችን እንደ ቅድመ ጥንቃቄ ቢጠቀሙ ይመረጣል።
3. ፕታሌትስ
እነዚህ ኬሚካሎች በሽቶ እና በመዋቢያዎች ውስጥ ከሚገኙ ንጥረ ነገሮች መካከል ሲሆኑ፣ በሆርሞን መዛባት እና በካንሰር እድገት ውስጥ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከፕታሌትስ-ነጻ ተብለው የተሰየሙ ምርቶችን ይፈልጉ።
4. ቶሉይን
ቶሉይን ብዙውን ጊዜ በጥፍር እና ፀጉር ማቅለሚያዎች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውል ኬሚካል ነው። ረዘም ላለ ጊዜ ለቶሉይን መጋለጥ ካንሰርን ጨምሮ ከብዙ የጤና ጉዳዮች ጋር ተያይዟል። ከቶሉይን ነፃ የሆኑ ምርቶችን መምረጥ እነዚህን አደጋዎች ሊቀንስ ይችላል።
5. የድንጋይ ከሰል ማቅለሚያዎች
በአንዳንድ የፀጉር ማቅለሚያዎች እና ሻምፖዎች ውስጥ የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ማቅለሚያ ታር ከካንሰር አምጪ ንጥረ ነገሮች መካከል ይመደባል። በአሁን ሰአት በከሰል ታር ላይ የተመሰረቱ ማቅለሚያዎችን መጠቀም ቢቀንስም፣ ጸጉርዎን በተደጋጋሚ ቀለም ሚቀቡ ከሆነ ማቅለሚያዎችን በምንገዛበት ወቅት መለያዎችን መፈተሽ አስፈላጊ ነው።
6. ቤንዚን
ቤንዚን በአንዳንድ የፀጉር ውጤቶች እና ሽቶዎች ውስጥ ከሚገኙ ኬሚካሎች አንዱ ሲሆን ከካንሰር አምጪ ንጥረ ነገሮች መካከል ተመድቧል። ለቤንዚን ረጅም ጊዜ መጋለጥ ለደም መታወክ እና ሉኪሚያ ለተሰኘ የደም ካንሰር የመጋለጥ እድልን ይጨምራል። ቤንዚን የሌለባቸውን ምርቶች መምረጥ የበለጠ አስተማማኝ አማራጭ ነው።
7. ከባድ ብረት-አስተኔዎች
እንደ ሊድ፣ ካድሚየም እና ሜርኩሪ ያሉ ከባድ ብረቶች በአንዳንድ መዋቢያዎች ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህ ንጥረ ነገሮች በጊዜ ሂደት በሰውነት ውስጥ ሊከማቹ እና ካንሰርን ጨምሮ ከፍተኛ የጤና አደጋዎችን ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ጠቃሚ ምክሮች
- መለያዎችን ያንብቡ፡- በግዢ ወቅት የምርት መለያዎችን በማንበብ እና በመፈተሽ ከታወቁ ካንሰር አምጪ ንጥረ ነገሮች ነፃ የሆኑትን ይምረጡ።
- ተፈጥሯዊ ምርቶችን ይምረጡ፡- የበለጠ አስተማማኝ አማራጭ ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ተፈጥሯዊ ወይም ኦርጋኒክ ምርቶችን መጠቀም ጎጂ ኬሚካሎችን የሚያስወግዱ አማራጮችን ይሰጣሉ።
- ተጋላጭነትን ይገድቡ፡- የታወቁ ጎጂ ንጥረ ነገሮች ያሏቸው እንደ ፀጉር ማቅለሚያ እና የጥፍር ቀለም ያሉ ምርቶችን የመጠቀም ድግግሞሽን ይቀንሱ።
- ባለሙያዎችን ያማክሩ፡- ስለተወሰኑ ምርቶች የሚያሳስብዎት ነገር ካለ የቆዳ ሐኪም ወይም የጤና እንክብካቤ አቅራቢን ያማክሩ።



