ካንሰር ለሕፃናት እና ለታዳጊዎች ቀዳሚ የሞት መንስኤ ነው። የሕፃናት ካንሰር ከ0 እስከ 19 ዓመት የሆኑ ሕፃናትንና ታዳጊዎችን የሚጎዱ የተለያዩ የካንሰር ዓይነቶችን ያብራራል። ይህም የሕፃናት ካንሰር (ከጨቅላ ሕፃናት እስከ 14 ዓመት የሆኑ ሕፃናት) እና የታዳጊዎች ካንሰር (ከ15 እስከ 19 ዓመት የሆኑ ታዳጊዎች) በመባል ሊከፈሉ ይችላሉ።
የሕፃናት ካንሰር ከፍተኛ ሕክምና የሚያስፈልገውና ለሕይወት አደገኛ ሊሆን የሚችል ሁኔታ ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ የሕፃናት ካንሰሮች ግን ሊታከሙ የሚችሉ ናቸው። በሕክምና ዘዴዎች ላይ በተደረጉ አዳዲስ ግኝቶች ምክንያት፣ እንደ ቀዶ ሕክምና፣ የጨረር ሕክምና እና ኪሞቴራፒ ያሉ ሕክምናዎችን በማጣመር ብዙ የሕፃናት ካንሰር ዓይነቶችን ሙሉ በሙሉ ማዳን ይቻላል።
ቁልፍ መረጃዎች
- በአጠቃላይ፣ ከዓዋቂዎች ካንሰር ጋር ሲነጻጸር የሕፃናት ካንሰር አልፎ አልፎ የሚከሰት ነው።
- በዓለም ዙሪያ፣ በየዓመቱ በሕፃናት እና በታዳጊዎች ላይ ወደ 400,000 የሚጠጉ አዳዲስ የካንሰር ታካሚዎች ይረጋገጣሉ።
- ሕፃናት በአብዛኛው ከዓዋቂዎች የተለዩ የካንሰር ዓይነቶች ያጋጥሟቸዋል።
- በጣም የተለመዱት የሕፃናት ካንሰር ዓይነቶች ሊዩኬሚያ (የደም ካንሰር)፣ የአንጎል ዕጢዎች እና ሊምፎማ ናቸው።
- ከዓዋቂዎች ካንሰር በተለየ፣ ለአብዛኞቹ የሕፃናት ካንሰሮች የታወቀ መንስኤ የላቸውም።
- ከዓዋቂዎች ካንሰር ጋር ሲነጻጸር፣ ብዙዎቹ የሕፃናት ካንሰሮች በበለጠ ስኬታማነት ይታከማሉ።
- የሕፃናት ካንሰር የመዳን መጠን አሁን ከ80% በላይ አድጓል።
- ከካንሰር የተፈወሱ ከሦስት ሁለቱ ሕፃናት ለከባድ የረጅም ጊዜ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊጋለጡ ይችላሉ።
- የሕፃናት ካንሰር የመያዝ እና የመሞት መጠን በአጠቃላይ ከሴቶች ይልቅ በወንዶች ልጆች ላይ የላቀ ነው።
የሕፃናት ካንሰር መንስኤዎችን ለመለየት ብዙ ጥናቶች የተደረጉ ቢሆንም፣ በሕፃናት ላይ ከሚከሰቱት ካንሰሮች ውስጥ በጣም ጥቂቶቹ ብቻ በአካባቢያዊ ወይም ከአኗኗር ዘይቤ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች የሚከሰቱ ናቸው።
ለካንሰር የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
የህጻናት ካንሰር መንስኤ በአጠቃላይ ያልታወቀ ቢሆንም፣ አንዳንድ ካንሰሮች ከተወሰኑ ለአደጋ ከሚያጋልጡ ሁኔታዎች ጋር ተያያዥነት አላቸው። ለምሳሌ፦
- እንደ ሲጋራ ማጨስ፣ ከፍተኛ ስብ ያለው ምግብ መመገብ እና ከአደገኛ ኬሚካሎች ጋር መስራት ያሉ የአኗኗር ዘይቤ ምክንያቶች ለአንዳንድ የአዋቂዎች ካንሰሮች አደጋ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም አብዛኞቹ ካንሰር ያለባቸው ሕፃናት ለእነዚህ የአኗኗር ዘይቤ ምክንያቶች ለረጅም ጊዜ ለመጋለጥ በጣም ትናንሽ ናቸው።
- የቤተሰብ የህክምና ታሪክ እና ዘረመል (genetics) ለአንዳንድ የሕፃናት ካንሰሮች ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።
- አንዳንድ የዘረመል መዛባቶች (እንደ Wiskott-Aldrich syndrome እና Beckwith-Wiedemann syndrome ያሉ) አንድ ልጅ በካንሰር የመያዝ እድሉ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ ይታወቃል።
- ለተወሰኑ ቫይረሶች መጋለጥ (ለምሳሌ እንደ ኤፕስታይን-ባር ቫይረስ/EBV እና የኤች.አይ.ቪ/HIV ቫይረስ) እንደ ሆጅኪን እና ኖን-ሆጅኪን ሊምፎማ ላሉ የሕፃናት ካንሰሮች የመጋለጥ እድልን እንደሚጨምሩ ተረጋግጧል።
- እንደ ፀረ-ተባይ መድኃኒቶች፣ ማዳበሪያዎች እና የኃይል መስመሮች (የኤሌክትሪክ ሽቦዎች) ያሉ አካባቢያዊ ሁኔታዎች ከሕፃናት ካንሰር ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ጥናት የተደረገባቸው ቢሆንም፣ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል አንዱም ለሕፃናት ካንሰር መንስኤ ለመሆኑ ምንም ዓይነት አሳማኝ/የተረጋገጠ ማስረጃ አልተገኘም።
- ከፍተኛ መጠን ያላቸው የኪሞቴራፒ እና የጨረር ሕክምናዎች ከካንሰር ጋር ተያያዥነት አላቸው። በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ ካንሰርን ለማከም ለእነዚህ ሕክምናዎች የተጋለጡ ሕፃናት በኋለኛው የሕይወት ዘመናቸው ሁለተኛ ካንሰር ሊይዛቸው ይችላል።
በሕፃናት ላይ ምን አየነት ካንሰሮች ሊከሰቱ ይችላሉ?
ሕፃናትን ሊያጠቁ የሚችሉ ብዙ የተለያዩ የካንሰር ዓይነቶች አሉ። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ በጣም የተለመዱት የሕፃናት ካንሰሮች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል፦
- ሊዩኬሚያ (Leukemia)፦ ሊዩኬሚያ በጣም የተለመደው የሕፃናት ካንሰር ነው። ይህ በደም እና በአጥንት መቅኔ ውስጥ የሚጀምር የነጭ ደም ሕዋሳት ካንሰር ነው። የተለያዩ የሊዩኬሚያ ዓይነቶች አሉ። በሕፃናት ላይ በብዛት የሚታዩት የሊዩኬሚያ ዓይነቶች አኪዩት ሊምፎሳይቲክ ሊዩኬሚያ (ALL) እና አኪዩት ማይሎይድ ሊዩኬሚያ (AML) የሚባሉት ናቸው።
- የአንጎል ካንሰር (Brain cancer)፦ በአንጎል ውስጥ የሚያድግ ካንሰር ሲሆን፣ ሁለተኛው በጣም የተለመደ የሕፃናት ካንሰር ነው። ከማንኛውም የካንሰር ዓይነት በላይ የብዙ ሕፃናትን ሕይወት ይወስዳል። ብዙ ዓይነት የአንጎል እና የሕብረ-ሰረሰር (የጀርባ አጥንት) ዕጢዎች አሉ። ለእያንዳንዱ የሚሰጠው ሕክምና እና የሕመሙ ሂደት የተለያየ ነው። ሁሉም የአንጎል ዕጢዎች ካንሰር አይደሉም። ነገር ግን በሚገኙበት ቦታ ምክንያት አብዛኞቹ ሕክምና ያስፈልጋቸዋል።
- ኒውሮብላስቶማ (Neuroblastoma)፦ ከ5 ዓመት በታች ባሉ ሕፃናት ላይ በብዛት የሚታወቅ ጠንካራ አካል ያለው ዕጢ (solid tumor) ነው።ኒውሮብላስቶማ ያልበሰሉ የነርቭ ሕዋሳት ካንሰር ነው። አልፎ አልፎ ይህ ካንሰር ልጅ ከመወለዱ በፊት የሚፈጠር ሲሆን በእርግዝና ወቅት በሚደረግ አልትራሳውንድ ምርመራ ሊታወቅ ይችላል።
- ዊልምስ ዕጢ (Wilms Tumor)፦ ዊልምስ ዕጢ (ኔፍሮብላስቶማ ተብሎም የሚጠራው) የኩላሊት ካንሰር ነው። ይህ ካንሰር አብዛኛውን ጊዜ ከ3 እስከ 4 ዓመት ዕድሜ ባላቸው ትናንሽ ሕፃናት ላይ ይገኛል። በአንዱ ወይም በሁለቱም ኩላሊቶች ውስጥ ሊያድግ ይችላል።
- ሄፓቶብላስቶማ (Hepatoblastoma)፦ ሄፓቶብላስቶማ በሕፃናት ላይ በብዛት የሚከሰት የጉበት ካንሰር ነው። ይህ ካንሰር ጊዜያቸው ሳይደርስ በሚወለዱ ወይም ሲወለዱ አነስተኛ ክብደት በነበራቸው ሕፃናት ላይ በብዛት ይታያል። እንዲሁም በቤተሰባቸው ውስጥ የካንሰር ታሪክ ባላቸው ሕፃናት ላይ ሊከሰት ይችላል። በብዛት ከ5 ዓመት በታች ባሉ ሕፃናት ላይ የሚታይ ነው።
- ሊምፎማ (Lymphoma)፦ ሊምፎማ ሊምፎሳይትስ በመባል የሚታወቁት የበሽታ መከላከል ሥርዓት ሕዋሳት ካንሰር ነው። አብዛኛውን ጊዜ በሊምፍ እጢዎች፣ አልፎ አልፎ ደግሞ በቶንሲል ወይም በታይመስ (thymus) እጢ ውስጥ ይገኛል። ሊምፎማ በአጥንት መቅኔ እና በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይም ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።
- ራብዶማዮሳርኮማ (Rhabdomyosarcoma)፦ ራብዶማዮሳርኮማ አብዛኛውን ጊዜ እንደ ጡንቻ፣ ስብ፣ አጥንት፣ ወይም መገጣጠሚያዎች እና የደም ስሮች የውስጥ ሽፋን አካባቢ የሚገኙ ኮኔክቲቭ ቲሹ የሚባሉ ህብረህዋሳት (connective tissues) ውስጥ ይጀምራል። ራብዶማዮሳርኮማ በየትኛውም የሰውነት ክፍል ውስጥ ሊፈጠር የሚችል ቢሆንም፣ በጣም የተለመዱት ቦታዎች ግን ራስ፣ አንገት፣ የፊኛ ክፍል፣ የሥነ-ተዋልዶ አካላት፣ እጆች፣ እግሮች፣ ደረት ወይም ሆድ ናቸው።
- ሬቲኖብላስቶማ (Retinoblastoma)፦ ሬቲኖብላስቶማ በዓይን የጀርባ ክፍል (ሬቲና) ውስጥ ይጀምራል። ይህ ብዙም ያልተለመደ የካንሰር ዓይነት ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ በሕፃናት እና ከ5 ዓመት በታች ባሉ ልጆች ላይ ይከሰታል። ሬቲኖብላስቶማ በቤተሰብ ውስጥ ታሪክ ካለ ልጁ ላይም የመከሰት እድሉ ይጨምራል ።
- ኦስቲዮሳርኮማ (Osteosarcoma)፦ ኦስቲዮሳርኮማ በትናንሽ እና በወጣቶች ዘንድ በጣም የተለመደው የአጥንት ካንሰር ነው። አብዛኛዎቹ አጋጣሚዎች በታዳጊዎች እና በወጣቶች ላይ የሚከሰቱ ቢሆንም፣ አልፎ አልፎ በትናንሽ ሕፃናት ላይም ሊከሰት ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ በእጅ ወይም በእግር አጥንቶች ውስጥ ይጀምራል።
- ኢዊንግ ሳርኮማ (Ewing Sarcoma)፦ ኢዊንግ ሳርኮማ በህጻናት እና በወጣቶች ዘንድ ሁለተኛው በጣም የተለመደ የአጥንት ካንሰር ዓይነት ነው። አብዛኛዎቹ አጋጣሚዎች በታዳጊዎች እና በወጣቶች ላይ ይከሰታሉ። አብዛኛውን ጊዜ በዳሌ አጥንቶች፣ በጎድን አጥንቶች ፣ የጀርባ አጥንት (ህብረ-ሰረሰር) እና በረጅም የእግር አጥንቶች ውስጥ ይጀምራል።
ካንሰር እንዴት ይታወቃል (ይመረመራል)?
ልጅዎን ለማከም የመጀመሪያው እርምጃ ትክክለኛ እና ሙሉ የሆነ የሕመም ምርመራ ውጤት (diagnosis) ማግኘት ነው። ልጅዎ ካንሰር እንዳለበት፣ የካንሰሩን ዓይነት እና የሚገኝበትን ቦታ ለመወሰን የልጅዎ ሐኪም የተለያዩ ምርመራዎችን ሊያዝ ይችላል። እነዚህም የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
- የአካላዊ ምርመራ (Physical examination)
- የደም ምርመራዎች
- የሽንት ምርመራዎች
- የምስል ምርመራዎች (Imaging scans)፦ ኤክስ-ሬይ (X-rays)፣ ኤም አር አይ(MRI)፣ ሲቲ ስካን (CT ወይም CAT scan)፣ እና የአጥንት ስካኖችን ጨምሮ ሊታዘዙ ይችላሉ።
- የአጥንት መቅኔ ናሙና (Bone marrow biopsy/aspiration)፦ የደም ሕዋሳትን እና/ወይም መደበኛ ያልሆኑ ሕዋሳትን ቁጥር፣ መጠን እና እድገት በዝርዝር ለመመርመር አብዛኛውን ጊዜ ከዳሌ አጥንት ክፍል ውስጥ አነስተኛ መጠን ያለው የአጥንት መቅኔ ፈሳሽ እና ህብረህዋስ (tissue) የሚወሰድበት ሂደት ነው።
- የሊምፍ እጢ ናሙና(Lymph node biopsy)፦ ከሊምፍ እጢ ውስጥ የህብረህዋስ ናሙና ተወስዶ በማይክሮስኮፕ የሚመረመርበት ሂደት ነው።
- የዕጢ ናሙና(Tumor biopsy)፦ ስለ ዕጢው ዓይነት ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ከዕጢው ላይ የሚወሰድ የህብረህዋስ ናሙና ሲሆን፤ ይህም በቀዶ ሕክምና ወቅት የሚሰበሰብ ነው።
- የአንጎል ፈሳሽ ምርመራ (ሉምባር ፓንክቸር / የስፓይናል ታፕ /Lumbar puncture)፦ አነስተኛ መጠን ያለው የአንጎል እና ሕብረ-ሰረሰር ፈሳሽ (cerebrospinal fluid) በመውሰድ የካንሰር ህዋሳት መሰራጨት መጀመራቸውን ለማረጋገጥ የሚደረግ ምርመራ ነው። በትናንሽ ሕፃናት ላይ ይህ ሂደት ማደንዘዣ በመስጠት ይከናወናል።
- የዘረመል ምርመራዎች (Chromosome analysis and genetic testing)፦ በካንሰር ሴሎች ላይ የሚታዩ የተወሰኑ ለውጦችን ለመፈለግ የዕጢ፣ የደም እና የአጥንት መቅኔ ናሙናዎች ወደ ልዩ ላብራቶሪ ሊላኩ ይችላሉ።
የሕፃናት ካንሰር እንዴት ይታከማል?
የእያንዳንዱ ልጅ ልዩ የሕክምና ሂደት በሚከተሉት በርካታ ነጥቦች ላይ ይመሰረታል፦
- ዕድሜ፣ አጠቃላይ የጤና ሁኔታ እና የህክምና ታሪክ
- የዕጢው ዓይነት፣ የሚገኝበት ቦታ እና መጠን
- ለአንዳንድ ዕጢዎች የዘረመል (ጄኔቲክ) ለውጦች
- የበሽታው የመስፋፋት ደረጃ
- የተወሰኑ መድኃኒቶችን፣ ሂደቶችን ወይም ሕክምናዎችን የመቋቋም ብቃት
- የልጅዎ ሐኪሞች በሽታው ወደፊት እንዴት ሊያድግ/ሊቀጥል እንደሚችል የሚጠብቁት ግምት
በሃኪምዎ ሊመከሩ የሚችሉ በርካታ ሕክምናዎች አሉ። አንዳንዶቹ ዕጢውን ለማከም የሚረዱ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ ከበሽታው ጋር ተያይዘው የሚመጡ ውስብስብ ችግሮችን ወይም የሕክምናውን የጎንዮሽ ጉዳቶች ለማስታገስ የታሰቡ ናቸው። የሕፃናት ካንሰር ሕክምናዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
- ኪሞቴራፒ (Chemotherapy)፦ በጣም የተለመደው የሕፃናት ካንሰር ሕክምና ሲሆን፣ የካንሰር ሕዋሳትን ለመግደል መድኃኒቶችን ይጠቀማል። ኪሞቴራፒ (ወይም ኪሞ) የካንሰር ሕዋሳት የማደግ ወይም የመራባት ብቃታቸውን የሚያስተጓጉሉ የመድኃኒት ቡድኖችን ያመለክታል። የተለያዩ የኪሞቴራፒ መድኃኒት ቡድኖች የካንሰር ሕዋሳትን ለመታገል እና ዕጢዎችን ለማሳነስ በተለያዩ መንገዶች ይሠራሉ። አብዛኛውን ጊዜ የበርካታ ኪሞቴራፒ መድኃኒቶች ቅልቅል (ጥምረት) ጥቅም ላይ ይውላል። ሊታከም ከተፈለገው የካንሰር ዓይነት በመነሳት የተወሰኑ የኪሞቴራፒ መድኃኒቶች በተወሰነ ቅደም ተከተል ሊሰጡ ይችላሉ። ኪሞቴራፒ በሰውነት ውስጥ ሁሉ የሚሰራ (systemic) ሕክምና ነው፤ ይህም ማለት ወደ ደም ዝውውር ውስጥ በመግባት የካንሰር ሕዋሳትን ለመግደል በሰውነት ውስጥ በሙሉ ይንቀሳቀሳል። ሕክምናው በሚከተሉት መንገዶች ሊሰጥ ይችላል፦ በአፍ፣ በጡንቻ ፣ በደም ስር፣ በህብረ-ሰረሰር ።
- የጨረር ሕክምና (Radiation therapy)፦ ይህ ሕክምና ዕጢዎችን የሚያሳንሱ ወይም የሚያጠፉ ጨረሮችን በካንሰሩ ላይ የሚያሳርፍ ማሽን ይጠቀማል። ወይም የልጅዎ ሐኪም ወደ ዕጢው ጨረር የሚልከውን መሣሪያ በሰውነት ውስጥ ሊተክል ይችላል። ከካንሰሩ ዓይነት በመነሳት፣ አንዳንዶች ታካሚዎች በተወሰነ ቦታ ላይ በሚያተኩር (targeted focal) የጨረር ሕክምና ይታከማሉ። ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ተሰራጭተው ሊሆኑ በሚችሉ ዕጢዎች ላይ ደግሞ፣ የጨረር ሕክምናው አልፎ አልፎ ሰፋ ባሉ የሰውነት ክፍሎች ላይ ሊሰጥ ይችላል።
- የአጥንት መቅኔ (የስቴም ሴል ንቅለ ተከላ/ Stem cell transplant)፦ ልጅዎ ሊዩኬሚያ ወይም ሊምፎማ ካለበት ይህ ሕክምና አማራጭ ሊሆን ይችላል። በመጀመሪያ፣ ሕክምና ሰጪው የካንሰር ሕዋሳትን ለመግደል ከፍተኛ መጠን ያለው ኪሞቴራፒ ይጠቀማል። ከዚያም ልጅዎ ከለጋሽ (donor) የተገኘ ጤናማ ደም አምራች ሕዋሳት በደም ስር አማካኝነት እንዲገባለት ይደረጋል። ለስቴም ሴል ንቅለ ተከላ የሚያስፈልጉት ሕዋሳት ከቤተሰብ አባል (አብዛኛውን ጊዜ ከወንድም ወይም እህት)፣ ከማይታወቅ በጎ ፈቃደኛ ለጋሽ ወይም ከራሱ ከታካሚው ሊገኙ ይችላሉ። የስቴም ሴሎቹ ወደ ደም ዝውውር ውስጥ የሚገቡ ሲሆን፣ ወደ አጥንት መቅኔ በመጓዝ አዳዲስ የደም ሕዋሳትን ማመረት ይጀምራሉ። የስቴም ሴል ንቅለ ተከላ ከባድ እና ለሕይወት አስጊ የሆኑ አደጋዎች/ስጋቶች አሉት። ከሂደቱ በፊት ስጋቶቹ እና ጥቅሞቹ በጥንቃቄ ተመዝነው ከልጅዎ የስቴም ሴል ንቅለ ተከላ የሕክምና ቡድን ጋር በሰፊው ሊመከሩበት ይገባል።
- ቀዶ ሕክምና (Surgery)፦ አንዳንድ ጊዜ፣ የሐኪሞች ቡድን ጠንካራ አካል ያላቸውን ዕጢዎች (solid tumors) ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ይችላሉ። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ልጅዎ ከሌሎች ሕክምናዎች ጎን ለጎን ቀዶ ሕክምና ሊያስፈልገው ይችላል።
- ኢሚዩኖቴራፒ እና ታርጌትድ ቴራፒ (Immunotherapy and targeted therapy)፦ ኢሚዩኖቴራፒ የልጅዎ የበሽታ መከላከል ሥርዓት ካንሰርን በተሻለ ሁኔታ እንዲታገል ይረዳል። ታርጌትድ ቴራፒ ደግሞ ከተወሰኑ የዘረመል መዛባቶች (gene mutations) ጋር የተያያዙ የካንሰር ሕዋሳት ድክመቶችን ለይቶ ያጠቃል። ከጨረር እና ከመደበኛ የኪሞቴራፒ ሕክምናዎች ጋር ተያይዘው ከሚመጡት የጎንዮሽ ጉዳቶች (የጸጉር መረገፍ፣ ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ፣ ደም አምራች ሕዋሳት መጎዳት) ይልቅ፣ እነዚህ የተቀናጁ መድኃኒቶች በሰውነት ለመሸከም ቀላል እና የተሻሉ ናቸው። እነዚህ አዳዲስ የካንሰር ሕክምናዎች በመሆናቸው ሊገኙ የሚችሉት በክሊኒካዊ ሙከራ (clinical trial) ውስጥ ብቻ ሊሆን ይችላል።
ከካንሰር የተፈወሰ ሕፃን የወደፊት ህይወቱ እንዴት ነው?
የሕፃናት ካንሰር አብዛኛውን ጊዜ ሙሉ በሙሉ የሚድን ቢሆንም፣ የበሽታው ተፅዕኖ የልጅዎን የረጅም ጊዜ ጤና ሊነካው ይችላል። በቅርብ ጊዜ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ከካንሰር የተፈወሱ ሕፃናት ከአኩዮቻቸው ይልቅ አጠር ያለ የሕይወት ዘመን ሊኖራቸው ይችላል። በአዋቂነት ዕድሜያቸው ለጤና ችግሮች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው። እነዚህ ችግሮች የልብ ሕመሞችን፣ ከሆርሞን ጋር የተያያዙ ሁኔታዎችን እና ሁለተኛ ካንሰሮችን ያካትታሉ።
ነገር ግን የሁሉም ሰው ስጋት እኩል አይደለም። አብዛኛው ነገር በሚሰጠው የሕመም ዓይነት ላይ ይወሰናል። ለምሳሌ፣ የስቴም ሴል ንቅለ ተከላዎች አብዛኛውን ጊዜ ዘግይተው የሚመጡ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ያመጣሉ። በቀዶ ሕክምና እና ዝቅተኛ መጠን ባለው ኪሞቴራፒ የሚደረግ ሕክምና ግን ለወደፊት ችግሮች የማጋለጥ እድሉ አነስተኛ ነው።
ያም ሆነ ይህ፣ ከካንሰር የተፈወሱ ሕፃናት ሁሉ የረጅም ጊዜ ክትትል ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ ክትትሎች ዘግይተው የሚመጡ የሕክምና የጎንዮሽ ጉዳቶችን ለመለየት የሚያስችሉ መደበኛ ምርመራዎችን ያካትታሉ።




