የሕፃናት ለሰዓታት ያለማቋረጥ ማልቀስ
ማልቀስ ለሕፃናት መሠረታዊ የመግባቢያ መንገድ ነው። ሕፃናት ሲራቡ፣ ሲደክማቸው፣ ዳይፐራቸው ሲሞላ፣ በጣም ሲሞቃቸው ወይም ሲበርዳቸው ሊያለቅሱ ይችላሉ። ነገር ግን ከተለመደው ውጪ የአንድ ሕፃን ለረጅም ሰዓት ያለማቋረጥ እና በምንም መንገድ ሊረጋጋ በማይችል ሁኔታ ማልቀስ በቸልታ ሊታይ አይገባም። ምክንያቱ ቀላል ሊሆን ቢችልም፣ አንዳንድ ጊዜ ፈጣን የሕክምና ግምገማ የሚያስፈልገው ሕመም ምልክት ሊሆን ይችላል።
ለረጅም ጊዜ ለምን ሊያለቅሱ ይችላሉ?
1. ረሃብ
አዲስ የተወለዱ ሕፃናት በተደጋጋሚ መመገብ ስለሚያስፈልጋቸው በቂ ወተትን ካላገኙ ለረጅም ጊዜ ሊያለቅሱ ይችላሉ።
2. የሆድ አየር ወይም የሆድ ምቾት ማጣት
በሆድ ውስጥ የአየር መከማቸት የሕፃናትን ምቾት ሊያሳጣ ስለሚችል፤ ከተመገቡ በኋላ አየር ካልወጣላቸው ሊያለቅሱ ይችላሉ።
3. ኮሊክ
አንዳንድ ጤናማ ሕፃናት ያለግልጽ ምክንያት በተደጋጋሚ እና ለረጅም ጊዜ ሊያለቅሱ ይችላሉ። ባለሙያዎች ይህንን ሁኔታ ኮሊክ ይሉታል። ብዙውን ጊዜ ኮሊክ በሕፃኑ የመጀመሪያ ሳምንታት የሚከሰት ሲሆን ከ4–6 ሳምንት ባለው እድሜ ላይ ሊባባስ እና ከ3–4 ወር ባለ እድሜ አካባቢ ሊቀንስ ይችላል።
4. የሙቀት ለውጥ
ህጻናት ልብሳቸው በጣም ከበዛ፣ ከበረዳቸው ወይም ከመጠን በላይ ከሞቃቸው ሊያለቅሱ ይችላሉ።
ማልቀስ የሕመም ምልክት ሊሆን ይችላል
በተለይም ማልቀሱ በድንገት ከጀመረ፣ ከተለመደው የተለየ ከሆነ ወይም ከሌሎች ምልክቶች ጋር ከተያያዘ ሕፃኑ በሕመም ላይ ሊሆን ይችላል።
ሊኖሩ ከሚችሉ ምክንያቶች መካከል፦
- ትኩሳት ወይም ኢንፌክሽን
- የጆሮ ሕመም
- የሆድ ቁርጠት
- የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን
- የሆድ ድርቀት
- እንደ አንጀት መጠላለፍ ያሉ አስቸኳይ የሆድ ችግሮች እና
- ሌሎች ከባድ ሕመሞች ጥቂቶቹ ናቸው።
🚨 አስቸኳይ ሕክምና መቼ ያስፈልጋል?
ላለማቋረጥ በሚያለቅሱ ሕፃናት ላይ የሚከተሉትን ምልክቶች ካዩ ወዲያውኑ ወደ ጤና ተቋም ይውሰዱአቸው።
- በጣም የተለየ የማይቋረጥ ማልቀስ
- ከፈተኛ ትኩሳት
- ለመተንፈስ መቸገር
- ከመጠን በላይ መድከም፣ ለመንቃት መቸገር ወይም ምላሽ መቀነስ
- መመገብ አለመቻል ወይም ከመደበኛው በጣም ያነሰ መመገብ
- ተደጋጋሚ አረንጓዴ ትውከት
- በሰገራ ውስጥ ደም
- የሆድ መነፋት ወይም መጠንከር
- የሽንት መጠን መቀነስ
- የቆዳ ወይም የከንፈር ወደ ሰማያዊ መለወጥ
- ማንቀጥቀጥ
- በመውደቅ ወይም በሌላ አደጋ ጉዳት ከደረሰ በኋላ የሚመጣ የማይቋረጥ ማልቀስ እና
- የሕፃኑ ባህሪይ ከተለመደው የተለየ መስሎ መታየት
በቤት ውስጥ ምን ማድረግ ይችላሉ?
ሕፃናት በአጠቃላይ ጤናማ ከሆኑ እና አስቸኳይ ምልክት ከሌላቸው፦
1. ረሃብ ካለ ይመግቧቸው
የሕፃናትን የረሃብ ምልክቶች በመመልከት በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ይመግቧቸው።
2. ዳይፐርን ይመልከቱ
እርጥብ ወይም የሞላ ዳይፐር ምቾት ሊነሳ ይችላል።
3. ከመመገብ በኋላ አየር እንዲያወጣ ያግዙ
ሕፃናትን ከመገቡ በኋላ በተገቢው ሁኔታ በመያዝ አየር እንዲወጣላቸው ያግዙ።
4. በቀስታ ያባብሉ
ሕፃናትን በእቅፍ መያዝ፣ በቀስታ በማወዛወዝ እና በዝግታ በማጫወት ለማረጋጋት ይሞክሩ።
5. አካባቢውን ጸጥ ያድርጉ
ብርሃን፣ ጫጫታ ወይም የሰዎች መብዛት ሕፃናትን ሊያስጨንቅ ይችላል።
ሕፃናትን በጭራሽ በሃይል አይነቅነቁ!
የሕፃናት ለረጅም ጊዜ ማልቀስ ለተንከባካቢ እጅግ አስጨናቂ ሊሆን ይችላል። ቁጣ ወይም ተስፋ መቁረጥ ቢሰማዎትም ሕፃናትን በሃይል መነቅነቅ አይገባም።
የሕፃናት አንጎል እና አንገት በጣም ስስ ስለሆነ በኃይል መነቅነቅ ከባድ የአንጎል ጉዳትን፣ የዓይን ውስጥ ደም መፍሰስን እና ሞትን ሊያስከትል ይችላል።
በጣም ከተበሳጩ፦
- ሕፃናቱን በአስተማማኝ የመኝታ ቦታ በጀርባ አስተኝተው ይተውአቸው።
- ለጥቂት ደቂቃዎች ከነርሱ ርቀው ራስዎን ያረጋጉ።
- ከቤተሰብ ወይም ከሚያምኑት ሰው እርዳታ ይጠይቁ።
- ማልቀሱ ከቀጠለ ወይም ሕፃናቱ ላይ የሕመም ምልክትን ካዩ የሕክምና ምክር ያግኙ።
የሕፃናት ማልቀስ ለብቻው የከባድ ሕመም ምልክት አይደለም። ነገር ግን ማልቀሱ ከተለመደው የተለየ፣ ከባድ ወይም ለሰዓታት የሚቆይ እና በምንም መንገድ ማረጋጋት የማይቻል ከሆነ ወይም ከሌሎች ምልክቶች ጋር አብሮ የመጣ ከሆነ በጤና ባለሙያ ማስገምገም ያስፈልጋል።




