ክትባቶች የሚሠሩት የተዳከመ ወይም ሕይወት የሌለውን የቫይረስ ወይም የባክቴሪያ ዓይነት ወደ ሰውነት በማስገባት ነው። ይህም የሰውነት የበሽታ መከላከያ ሥርዓት (Immune system) ፀረ እንግዳ አካላት (Antibodies) እንዲያመነጭ በማነሳሳት፣ ሰውነት በኋላ ላይ እውነተኛው ኢንፌክሽን ቢገጥመው እንኳ የመከላከል አቅም እንዲኖረው ያዘጋጀዋል። ሰውነት ለክትባቱ የሚሰጠው ምላሽ አንዳንድ ጊዜ ጊዜያዊ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያስከትል ይችላል፤ ይህም ሰውነት የበሽታ መከላከል አቅሙን እየገነባ መሆኑን የሚያሳይ መንገድ ነው።
ሕፃናት ከእናታቸው የሚያገኙት የተወሰነ የበሽታ መከላከያ ቢኖርም፣ ይህ ጥበቃ ብዙውን ጊዜ ሕፃኑ እስከ 6 ወር ዕድሜ ድረስ ብቻ ይቆያል። የሕፃናት ክትባቶች በለጋ ዕድሜ የሚሰጡት ሕፃናት በዚህ ዕድሜ ለከባድ በሽታዎች የበለጠ ተጋላጭ ስለሆኑ ነው። እንደ ኩፍኝ (Measles) እና የጉድፍ (Chickenpox) ያሉ በሽታዎች በጨቅላ ሕፃናትና በትንንሽ ልጆች ላይ ለሕይወት አስጊ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ቀደም ብሎ ክትባት የሚሰጡት፣ ሕፃናትን ከእነዚህ በሽታዎች ለመጠበቅ አስፈላጊ ስለሆነ። ክትባቶችን ልጁ እስኪያድግ ድረስ ማዘግየት ከበሽታዎች በቂ ጥበቃ ለመስጠት እድሉ በጣም እንዲዘገይ ሊያደርግ ይችላል።
በሕፃናትና በልጆች ላይ የሚከሰቱ የክትባት የጎንዮሽ ጉዳቶች
ልጅዎ ማንኛውንም ዓይነት ክትባት ቢወስድ፣ በብዛት ሊከሰቱ የሚችሉ ጥቂት የጎንዮሽ ጉዳቶች አሉ። እነዚህ ብዙውን ጊዜ ቀላል፣ ለአጭር ጊዜ የሚቆዩ እና አሳሳቢ ያልሆኑ ናቸው፦
ክትባት በተሰጠበት አካባቢ ላይ ያለ ምላሽ
ከክትባት በኋላ በብዛት የሚከሰተው ምላሽ ነው። ይህ ማለት ሰውነት እንደ ስጋት የተገነዘበውን ነገር ለመቋቋም ተጨማሪ ነጭ የደም ሴሎችን መርፌ ወደ ተወጋው ቦታ እየላከ ነው ማለት ነው። ብዙውን ጊዜ ከ2 እስከ 3 ቀናት ብቻ የሚቆይ ሲሆን ምንም ዓይነት ሕክምና አያስፈልገውም። ይህ ምላሽ የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያስከትል ይችላል፦
- ሕመም፦ ልጅዎ ክትባቱ በተሰጠበት ቦታ ላይ ሲነካ ህመም ሊሰማው ይችላል።
- እብጠት፦ በመርፌው ቦታ ዙሪያ ትንሽ ጉብታ ወይም መቅላት ሊታይ ይችላል።
ትኩሳት
ትኩሳት ማለት የሰውነት ሙቀት ከ38°C በላይ መሆን ነው። ትኩሳት በትንንሽ ሕፃናት ላይ በብዛት የሚከሰት ሲሆን፣ ብዙውን ጊዜ ግን ቀላል ነው። የልጅዎ ፊት ሲነኩት ሞቃት ከሆነ እና ፊቱ ከቀይ ወይም የሞቀ የሚመስል ከሆነ፣ ትኩሳት ሊኖረው ይችላል። የልጅዎን የሰውነት ሙቀት ቴርሞሜትር በመጠቀም መለካት ይችላሉ። ትኩሳቱ ብዙውን ጊዜ በ24 ሰዓታት ውስጥ ይጀምርና ከ1 እስከ 2 ቀናት ይቆያል።
የምግብ ፍላጎት መቀነስ
ከክትባት በኋላ ልጅዎ ከወትሮው ያነሰ ምግብ ሊመገብ ይችላል። ይህ ብዙውን ጊዜ ጊዜያዊ ሲሆን፣ የምግብ ፍላጎቱም በ1 ወይም 2 ቀናት ውስጥ ወደ መደበኛው ሊመለስ ይገባል።
የእንቅስቃሴ መቀነስ
ልጅዎ ከወትሮው የበለጠ የደከመ ወይም የተረበሸ ሊመስል ይችላል። ይህም ሰውነቱ የበሽታ መከላከያ አቅሙን ለመገንባት በትጋት እየሰራ ስለሆነ ነው። ብዙ ሕፃናት ከክትባት በኋላ ከወትሮው በላይ ሊተኙ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ በሌሊት ሊረበሹ ወይም በደንብ ላይተኙ ይችላሉ። ሁለቱም የተለመዱ ምላሾች ናቸው።
ብስጭትና መረበሽ
ከክትባት በኋላ አንዳንድ ሕፃናት የበለጠ ሊበሳጩ ወይም ሊያለቅሱ ይችላሉ። ከወትሮው የበለጠም ከእርሶ መለየት ላይፈልጉ ለማረጋጋት አስቸጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ብዙውን ጊዜ በመርፌው ቦታ ላይ በሚሰማ ምቾት ማጣት ወይም በአጠቃላይ ጤናቸው ጥሩ ባለመሆኑ ሊከሰት ይችላል።
ዘግይተው የሚከሰቱ ምላሾች
እንደ የጉድፍ እና የኩፍኝ ክትባት ያሉ ክትባቶችን ከወሰዱ በኋላ ትኩሳትና የቆዳ ሽፍታ ሊከሰት ይችላል። እነዚህ ምልክቶች ዘግይተው ይጀምራሉ፤ ብዙውን ጊዜም ከ1 እስከ 4 ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ይከሰታሉ።
ከባድ የአለርጂ ምላሽ (Anaphylaxis)
ከባድ የአለርጂ ምላሽ በጣም አልፎ አልፎ ይከሰታል። ብዙውን ጊዜ ክትባቱ ከተሰጠ በኋላ በ20 ደቂቃ ውስጥ ይጀምራል፤ አንዳንድ ጊዜ ግን ከክትባቱ በኋላ እስከ 2 ሰዓት ድረስ ሊከሰት ይችላል።
ልጅዎ ምቾት ካጣ ምን ማድረግ ይችላሉ?
ከክትባት በኋላ የመጀመሪያዎቹ 2 ቀናት ሊከሰቱ የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ለመቆጣጠር በተለይ አስፈላጊ ጊዜያት ናቸው። በዚህ ጊዜ ልጅዎ ምቾት እንዲሰማው የሚከተሉትን ማድረግ ይችላሉ፡
- ጡት ማጥባት ወይም ተደጋጋሚ ፎርሙላ መስጠት፦ ብዙ ጊዜ መመገብ ልጅዎ በቂ ፈሳሽ እንዲያገኝና እንዲረጋጋ ይረዳል። የጡት ወተት የልጅዎን የበሽታ መከላከያ አቅም ሊያጠናክሩ የሚችሉ ፀረ እንግዳ አካላት (Antibodies) ይዟል።
- ፈሳሽ መስጠት፦ በተለይ ልጅዎ ትኩሳት ካለው የሰውነት ውሃ እጥረት (Dehydration) እንዳይከሰት እንደ ውሃ (ከ 6 ወር በላይ ከሆነ) ወይም ወተት ያሉ በቂ ፈሳሾችን ይስጡት።
- መዳበስ እና ማጽናናት፦ ልጅዎን በቅርብ ይያዙት፣ መዝሙሮች ይዘምሩለት ወይም ታሪኮችን ያንብቡለት። ከልጅዎ ጋር በቅርብ መሆንና ረጋ ያለ አካባቢ መፍጠር ምቾት እንዲሰማው ይረዳል።
- በቅባት ማሸትን እና ማንጠራራትን ያስወግዱ፦ እነዚህ ክትባት የተሰጠበትን ቦታን ሊያስቆጡ እና ምቾት ማጣቱን ሊያባብሱ ይችላሉ።
- በቀዝቃዛ ፎጣ መያዝ፦ ቀዝቃዛና እርጥብ ጨርቅ ወይም የጥጥ ፎጣ በክትባቱ መርፌ ቦታ ላይ ለ15–20 ደቂቃ ያህል ያድርጉ። ይህንን ለ10 ደቂቃዎች፣ በቀን 3 ጊዜ ያድርጉ። ይህ እብጠትንና ምቾት ማጣትን ሊቀንስ ይችላል።
- ሕመምና ትኩሳትን መቆጣጠር፦ ምንም እንኳን ከክትባት በኋላ ፓራሲታሞል (Paracetamol) በመደበኛነት መስጠት ባይመከርም፣ ሕመም ወይም ትኩሳት ካለ ግን ለማስታገስ ፓራሲታሞል (Paracetamol) መጠቀም ይቻላል። ነገር ግን የልጅዎን የሕፃናት ሐኪም ቀድመው ያማክሩ። ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት አስፕሪን (Aspirin) አይስጡ!
- ቀለል አርጎ ማልበስ፦ ልጅዎን ቀለል ባለ ልብስ ያልብሱት። በጥብቅ ልብስ አይሸፍኑት ወይም አይጠቅልሉት።
የሕክምና እርዳታ መቼ መፈለግ አለብዎት?
አብዛኛዎቹ የክትባት የጎንዮሽ ጉዳቶች ቀላልና ለአጭር ጊዜ የሚቆዩ ቢሆኑም፣ አንዳንድ ጊዜ የሕክምና እርዳታ መፈለግ ያስፈልጋል። ልጅዎ ከሚከተሉት ምልክቶች ካሳየ የሕፃናት ሐኪሙን ያነጋግሩ፦
- ከ39.5°C በላይ የሆነ ትኩሳት ወይም ከ3 ቀናት በላይ የሚቆይ ትኩሳት ቀላል ትኩሳት ከክትባት በኋላ ሊጠበቅ ይችላል፤ ነገር ግን ከፍተኛ ወይም ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ትኩሳት ሌላ ምክንያት ሊኖረው ስለሚችል ምርመራ ያስፈልገዋል።
- ከ3 ሰዓታት በላይ የማያቋርጥ ማልቀስ ሕፃናት ከክትባት በኋላ መረበሽ የተለመደ ቢሆንም፣ ልጅዎ ምንም ነገር ሊያረጋጋው ካልቻለ ወይም በከፍተኛ ድምፅ የሚያለቅስ ከሆነ የሕክምና ምክር መፈለግ ይገባል።
- ከባድ የአለርጂ ምላሽ ምልክቶች፦እነዚህም የፊት፣ የከንፈር ወይም የምላስ እብጠት፣ የመተንፈስ ችግር፣ በሰውነት ላይ በስፋት የሚከሰት የቆዳ ሽፍታ (Hives) ወይም በድንገት የሰውነት መደከምና መልፈስ ሊያካትቱ ይችላሉ። አብዛኛዎቹ የአለርጂ ምላሾች ክትባቱ ከተሰጠ በኋላ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ስለሚከሰቱ ክትባት ከተሰጠ በኋላ በጤና ተቋሙ እንዲቆዩና እንዲታዩ ይጠየቃሉ።
- ማስታወክ ወይም ተቅማጥ፦ ከ24 ሰዓት በላይ ከቀጠለ።
- የሚጥል በሽታ (Seizures) ከተከሰተ።
- የተለመደ ያልሆነ ባህሪ ወይም አሳሳቢ የሆነ ከመጠን በላይ እንቅልፍ ከታየ።




