ወቅታዊ ጉንፋን (ኢንፍሉዌንዛ) ምንነት፣ መንስኤዎች እና የስርጭት መንገድ

Tsion Girma
Oct 8, 2026
Screenshot 2026 10 08 113515

ኢንፍሉዌንዛ (ወቅታዊ ጉንፋን) ምንድን ነው?

የአየር ንብረት በሚቀያየርበት እና የብርድ ወራት በሚገባበት ወቅት በርካታ ሰዎች ለተለያዩ የመተንፈሻ አካል በሽታዎች ይጋለጣሉ። ከእነዚህም መካከል በሳይንሳዊ ስሙ ኢንፍሉዌንዛ (Influenza) በመባል የሚታወቀው እና በማህበረሰቡ ዘንድ "ወቅታዊ ጉንፋን" የሚባለው ዋነኛው ነው።

ብዙ ሰዎች ወቅታዊ ጉንፋንን ከተራ የመተንፈሻ አካል መታወክ (Common Cold) ጋር ያመሳስሉታል። ነገር ግን ኢንፍሉዌንዛ በተወሰነ የቫይረስ አይነት የሚመጣ፣ ድንገተኛ እና አንዳንዴም ለከፍተኛ የጤና እክል እና ለህይወት ህልፈት ሊዳርግ የሚችል የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን ነው።

ወቅታዊ ጉንፋን በየዓመቱ በተወሰኑ የወቅቶች መፈራረቅ ላይ በስፋት የሚከሰት ሲሆን፣ በአለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያጠቃል። በሽታውን በቅርበት መረዳት፣ የመከላከያ መንገዶችን ማወቅ እና  የቤት ውስጥና የህክምና እንክብካቤ ማድረግ የራስንም ሆነ የቤተሰብን ጤና ለመጠበቅ ወሳኝ ነው።

የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ዓይነቶች

የጉንፋን በሽታን የሚያመጡት ቫይረሶች በዋናነት በካቴጎሪ ይከፈላሉ፦

  • ኢንፍሉዌንዛ ኤ (Influenza A)፦ ይህ በጣም አደገኛ እና በፍጥነት የመለወጥ (Mutation) ባህሪ ያለው የቫይረስ አይነት ነው። በሰዎችና በእንስሳት (እንደ ወፎች እና አሳማዎች) ላይ ሊከሰት ይችላል። በታሪክ ውስጥ የተከሰቱ የወረርሽኝ ማዕበሎችን (Pandemics) በማስከተል ይታወቃል።
  • ኢንፍሉዌንዛ ቢ (Influenza B)፦ ይህ አይነት በሰዎች መካከል ብቻ የሚሰራጭ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ በየዓመቱ በሚከሰቱ ወቅታዊ የጉንፋን ማዕበሎች ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ አለው። ምንም እንኳን እንደ አይነት ኤ ፈጣን ወረርሽኝ ባያስከትልም፣ ጠንካራ የህመም ስሜት ያመጣል።
  • ኢንፍሉዌንዛ ሲ (Influenza C)፦ ይህ አይነቱ ቫይረስ ቀላል የመተንፈሻ አካል ችግር የሚያስከትል ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ ከባድ ህመም ወይም ወረርሽኝ አያስከትልም።
  • ኢንፍሉዌንዛ ዲ (Influenza D)፦ በዋናነት እንስሳትን (በተለይም ከብቶችን) የሚያጠቃ ሲሆን በሰዎች ላይ ህመም እንደሚያስከትል አልተረጋገጠም።

በሽታው እንዴት ይሰራጫል?

የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ በጣም በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ የቫይረስ አይነት ነው። ዋነኞቹ የመተላለፊያ መንገዶች የሚከተሉት ናቸው፦

  1. በአየር ጠብታዎች (Respiratory Droplets)፦ ህመምተኛው ሰው ሲስል፣ ሲያስነጥስ ወይም ሲናገር ከአፉና ከአፍንጫው የሚወጡ ጥቃቅን የፈሳሽ ጠብታዎች በአየር ውስጥ በመሰራጨት በአቅራቢያ የሚገኙ ሰዎችን ያጠቃሉ።
  2. በንክኪ (Direct & Indirect Contact)፦ ቫይረሱ ያረፈበትን ዕቃ (እንደ የበር እጀታ፣ ስልክ፣ ጠረጴዛ፣ ወይም የጋራ መጠቀሚያ ዕቃዎች) በመንካት ከዚያም እጅን ወደ አፍንጫ፣ አፍ ወይም አይን በማስጠጋት ይተላለፋል።
  3. የተጨናነቁ እና የአየር ዝውውር የሌላቸው ቦታዎች፦ በቂ የአየር ዝውውር በሌላቸው ክፍሎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በህዝብ ማጓጓዣዎች እና በመስሪያ ቤቶች ውስጥ ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ይሰራጫል።

የጉንፋን ወቅት (Flu Season) መቼ ይከሰታል?

በአለም አቀፍ ደረጃ ወቅታዊ ጉንፋን አየር በሚቀዘቅዝበት ወቅት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል።

በሞቃታማ እና ወይናደጋ ሀገራት (እንደ ኢትዮጵያ ያሉ) የጉንፋን ስርጭት ከአየር ንብረት ለውጥ፣ ከዝናብ ወቅት (ክረምት) እና ከቅዝቃዜ ወራት ጋር ተያይዞ ይከሰታል። በቅዝቃዜ ወቅት ሰዎች በቤት ውስጥ በስፋት የሚሰበሰቡ በመሆኑ እና ቅዝቃዜው የቫይረሱን በአየር ላይ የመቆየት እድል ስለሚያራዝመው በሽታው በፍጥነት ይስፋፋል።

ዋና ዋና የወቅታዊ ጉንፋን (ኢንፍሉዌንዛ) ምልክቶች

የኢንፍሉዌንዛ ምልክቶች ቫይረሱ ወደ ሰውነት ከገባ ከ1 እስከ 4 ባሉት ቀናት ውስጥ በድንገት ይከሰታሉ። ከተራ ጉንፋን በተለየ ሁኔታ ኢንፍሉዌንዛ ሰውን በአንድ ጊዜ ከእግር እስከ ራስ የሚያደክም ህመም አለው።

  • ከፍተኛ ትኩሳት፦ ድንገት የሚጀምር እና ከ38°C (100.4°F) በላይ የሚሆን ትኩሳት፣ ከብርድ ብርድ ማለት እና ማንቀጥቅጥ ሊኖረው ይችላል።
  •  የሰውነት እና የጡንቻ ህመም፦ በተለይም በጀርባ፣ በእግሮች እና በትከሻ ላይ የሚሰማ የሃይል ማጣት እና የጡንቻ ቁስለት።
  • ኃይለኛ ደረቅ ሳል፦ ሳንባን እና ጉሮሮን የሚያቆስል ሳል በመጀመርያው ሳምንት በስፋት ይስተዋላል።
  • የጉሮሮ መቁሰል እና ህመም፦ ምግብ ወይም ፈሳሽ ለመዋጥ የሚያስቸግር የጉሮሮ እብጠት።
  • ከባድ ራስ ምታት እና የአይን ህመም፦ ከግንባር ጀርባ የሚሰማ ጫና እና ራስ ምታት።
  • ከፍተኛ ድካም፦ ከህመሙ ማገገም ከተጀመረ በኋላም ቢሆን ለሳምንታት ሊቆይ የሚችል የሰውነት  ድካም።
  • የአፍንጫ መታፈን ወይም ፈሳሽ መብዛት፦ ምንም እንኳን ከአፍንጫ ፈሳሽ መውጣት ከተራ ጉንፋን ጋር ቢያያዝም በኢንፍሉዌንዛም ላይ ሊከሰት ይችላል።
  • የምግብ ፍላጎት ማጣት እና የሆድ ህመም፦ በተለይም ህጻናት ላይ ማስታወክ፣ ተቅማጥ እና የሆድ ህመም ሊታይ ይችላል።

ከተራ ጉንፋን (Common Cold) ጋር ያለው ልዩነት

ብዙ ሰዎች የሁለቱን ህመሞች ልዩነት ባለመገንዘባቸው ምክንያት ተገቢውን ጥንቃቄ አያደርጉም።

  • የምልክቶች አጀማመር፦ ተራ ጉንፋን በሂደት እና በዝግታ የሚጀምር ሲሆን፣ ኢንፍሉዌንዛ ግን በድንገትና በአጭር ሰዓታት ውስጥ ይባባሳል።
  • ትኩሳት፦ በተራ ጉንፋን ወቅት ትኩሳት ወይም በጣም ዝቅተኛ ነው፤ በኢንፍሉዌንዛ ጊዜ ግን ከፍተኛ ትኩሳት የተለመደ ነው።
  • የህመሙ ክብደት፦ የኢንፍሉዌንዛ የሰውነት ህመም እና ድካም በጣም ኃይለኛ ሲሆን ተራ ጉንፋን ግን ቀለል ያለ ነው።

ከፍተኛ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች

ማንኛውም ሰው በወቅታዊ ጉንፋን ሊያዝ ቢችልም፣ ከተወሰኑ ሰዎች ጋር ሲነጻጸር በሽታው አደገኛ እና ለሞት ሊዳርግ የሚችልባቸው ክፍሎች አሉ፦

  • ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት፦ በተለይም ዕድሜያቸው ከ2 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት የበሽታ መከላከል አቅማቸው ገና ባለመልመዱ ምክንያት።
  • አረጋውያን (ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ)፦ የእድሜ መጨመር ጋር ተያይዞ የበሽታ መከላከል አቅማቸው በመቀነሱ።
  • ነፍሰ ጡር እናቶች፦ በእርግዝና ወቅት በሚከሰቱ የሆርሞን እና የሰውነት ለውጦች ምክንያት።
  • ሥር የሰደደ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች፦ እንደ የስኳር በሽታ፣ የልብ ህመም፣ የሳንባ ህመም (አስም/ከፍተኛ ሳል)፣ የኩላሊት ወይም የጉበት በሽታ ያለባቸው።
  • የበሽታ መከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ፦ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ፣ በካንሰር ህክምና ወይም በሌሎች የመከላከል አቅምን በሚቀንሱ መድኃኒቶች ላይ ያሉ ሰዎች።

ኢንፍሉዌንዛ ሊያመጠው የሚችለው የጤና እክል  (Complications)

ኢንፍሉዌንዛ በትክክል ካልተካከመ እና ካልተጠበቀ ወደሚከተሉት ከባድ የጤና ችግሮች ሊያደግ ይችላል፦

1. የሳንባ ምች (Pneumonia)፦ በቫይረሱ ወይም በተጨማሪ ባክቴሪያ ምክንያት የሚከሰት የሳንባ ኢንፌክሽን ሲሆን፣ ለህይወት አደገኛ ሊሆን ይችላል።

2. የሳይነስ እና የጆሮ ኢንፌክሽን፦ በተለይም ህጻናት ላይ የጆሮ ህመም እና እብጠት ያስከትላል።

3. የልብ እና የጡንቻ እብጠት (Myocarditis/Myositis)፦ ቫይረሱ ወደ ልብ ጡንቻዎች በመሰራጨት የልብ ምትን እና ስራን ያዛባል።

4. የነባር ህመሞች መባባስ፦ አስም ያለባቸው ሰዎች ላይ የሳንባ ቱቦ ጥበት ማስከተል፣ ወይም የስኳር ታካሚዎች ላይ የስኳር መጠንን ከፍ በማድረግ የጉንፋኑ የጎንዮሽ ጉዳቶች ናቸው።

ሕክምና፣ መከላከል እና የቤት ውስጥ እንክብካቤ

የወቅታዊ ጉንፋን (ኢንፍሉዌንዛ)  መከላከያ መንገዶች

1. የጉንፋን ክትባት (Flu Vaccine)

የወቅታዊ ጉንፋን ክትባት በሽታውን ለመከላከል እና ከባድ ጉዳቶችን ለማስቀረት በጣም ውጤታማው መንገድ ነው። የጉንፋን ቫይረስ በየዓመቱ ቅርጹን እና ባህሪውን ስለሚቀይር፣ የአለም ጤና ድርጅት በሚያወጣው መረጃ መሰረት ክትባቱ በየዓመቱ ተሻሽሎ ይዘጋጃል።

  • ክትባቱ በየዓመቱ መወሰድ አለበት።
  • ከፍተኛ ተጋላጭ የሆኑ ወገኖች (ህጻናት፣ አረጋውያን፣ ነፍሰ ጡሮች እና ባለሙያዎች) ቅድሚያ ማግኘት አለባቸው።

2. የግል ንፅህና እና ስነ-ምግባር

  • እጅን አብዝቶ መታጠብ፦ እጅን በሳሙና እና በውሃ ቢያንስ ለ20 ሰከንድ መታጠብ፣ ወይም አልኮል ያለውን የእጅ ማጽጃ (Sanitizer) መጠቀም።
  • አፍን እና አፍንጫን መሸፈን፦ በሚስሉበት ወይም በሚያስነጥሱበት ወቅት በክንድ ውስጠኛ ክፍል ወይም በአንሶላ/ቲሹ መሸፈን፣ የተጠቀሙበትን ቲሹ ወዲያውኑ ወደ ቆሻሻ መጣል።
  • ከንክኪ መቆጠብ፦ ያልተታጠበ እጅን ወደ አይን፣ አፍንጫ እና አፍ አለ ማስጠጋት።
  • ርቀት መጠበቅ፦ የጉንፋን ምልክት ከታየባቸው ሰዎች ጋር የራቀ ግንኙነት ማድረግ እና የበሽታው ምልክት ሲኖር ከስራ ወይም ከተምህርት ቤት በማረፍ በቤት ውስጥ መቆየት።

የቤት ውስጥ እንክብካቤ እና ህክምና

አብዛኛዎቹ የጉንፋን ታካሚዎች በቤት ውስጥ በሚደረግ ጥንቃቄ እና እንክብካቤ ከ1 እስከ 2 ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ያገግማሉ።

ሀ. በቂ እረፍት ማድረግ

ሰውነት ቫይረሱን ለመታገል ከፍተኛ ጉልበት ስለሚፈልግ፣ አልጋ ላይ በመተኛት በቂ እረፍት ማድረግ የማገገም ሂደቱን በፍጥነት ያፋጥነዋል።

ለ. ፈሳሽ ነገሮችን አብዝቶ መጠጣት

ትኩሳት እና ላብ የሰውነት ፈሳሽ እንዲቀንስ ስለሚያደርጉ፣ በቂ ፈሳሽ መውሰድ አስፈላጊ ነው፦

  • ሞቅ ያለ ውሃ፣ የፍራፍሬ ጭማቂዎች እና  መረቅ (Soup)።
  • ሞቅ ያለ ሻይ ከማር እና ሎሚ ጋር፦ የጉሮሮ ህመምን ያረግባል፣ ሳልን ያረጋጋል።

ሐ. የቤት ውስጥ ተፈጥሯዊ መፍትሄዎች

  • የጨው ውሃ  (Gargle)፦ በግማሽ የሻይ ማንኪያ ጨው በሞቀ ውሃ በመበጥበጥ ጉሮሮን መጉመጥመጥ የጉሮሮ እብጠትን ያቀልላል።
  • የእንፋሎት ትንፋሽ (Steam Inhalation)፦ የፈላ ውሃ ላይ የባህር ዛፍ ቅጠል ወይም ጥቂት ጠብታ ዘይት በመጨመር እንፋሎቱን በመታጠን የተዘጋ አፍንጫን ይከፍታል።

መ. የመድኃኒት ህክምና

  • የህመም እና ትኩሳት ማስታገሻዎች፦ እንደ ፓራሲታሞል (Paracetamol) ወይም ኢቡፕሮፌን (Ibuprofen) ያሉ መድኃኒቶች ትኩሳትን ለማውረድ እና የሰውነት ህመምን ለመቀነስ ይረዳሉ።
  • ጥንቃቄ፦ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት (Aspirin) መስጠት በፍጹም የተከለከለ ነው (የሬይ ሲንድሮም - Reye's Syndrome የተባለ አደገኛ የጉበት እና የጭንቅላት በሽታ ስለሚያስከትል)።
  • ፀረ-ባክቴሪያ መድኃኒቶች (Antibiotics)፦ አንቲባዮቲክስ ባክቴሪያን እንጂ ቫይረስን ስለማይገድሉ ለጉንፋን ህክምና አይጠቅሙም። ያለ ሐኪም ትዕዛዝ አንቲባዮቲክ መውሰድ ተገቢ አይደለም።

ወዲያውኑ ወደ ህክምና ጣቢያ መሄድ የሚያስፈልጋቸው የአደጋ ምልክቶች

የጉንፋን ህመም ከተራ ወደ ከባድ ደረጃ ሲሸጋገር የሚከተሉት የሬድ ፍላግ (Red Flag) ምልክቶች ይታያሉ። እነዚህ ምልክቶች ከተከሰቱ በአስቸኳይ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል፦

በአዋቂዎች ላይ፦

  • ከፍተኛ የመተንፈስ ችግር ወይም የትንፋሽ እጥረት።
  • በደረት ወይም በሆድ አካባቢ የሚሰማ ጽኑ ህመም ወይም ጫና።
  • ድንገተኛ የማዞር ወይም የንቃተ ህሊና መዛባት።
  • ኃይለኛ እና የማይቆም ማስታወክ።
  • የጉንፋን ምልክቶች ተሻሽለው ከቆዩ በኋላ በድጋሚ በከፋ ትኩሳት እና ሳል የመመለስ ሁኔታ።

በህጻናት ላይ፦

  •  በፍጥነት መተንፈስ ወይም የመተንፈስ መቸገር (የደረት አጥንት መግባት)።
  • የፊት፣ የከንፈር ወይም የጥፍር ሰማያዊ መሆን (የኦክስጅን እጥረት)።
  • በቂ ፈሳሽ አለመውሰድ እና የሽንት መጠን በጣም መቀነስ።
  • ለመንቃት መቸገር ወይም ምላሽ አለመስጠት።
  • ህጻኑ በጣም ከመበሳጨታቸው የተነሳ ለመታቀፍ እንኳ እምቢ ማለት።

Comments (0)