በጠፍጣፋ ወይም ወደ ውስጥ በገቡ የጡት ጫፎች ምክንያት ጡት ለማጥባት ተቸግረሻል?

Elsabet Azezew
Nov 11, 2026
image 2026 09 01 140353717

            በጠፍጣፋ ወይም ወደ ውስጥ በገቡ የጡት ጫፎች ምክንያት ጡት ለማጥባት ተቸግረሻል? 

ጠፍጣፋ ወይም ወደ ውስጥ የገቡ የጡት ጫፎች ማጥባትን ፈታኝ ሊያደርጉት ይችላሉ። 

የጡት ጫፍ ቅርጽና መጠን በተፈጥሮ ከሰው ሰው ይለያያል ፤ አንዳንዶቹ ወደ ውጭ የወጡ፣ አንዳንዶቹ ጠፍጣፋ፣ ሌሎቹ ደግሞ ወደ ውስጥ የገቡ ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ የጡትሽ ጫፍ ቅርጽ በእርግዝና ወቅት ወይም ከወሊድ በኋላ ሊለወጥ ይችላል።

መልካሙ ዜና ጡት ማጥባት በጡት ጫፍ ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም! ልጅሽ በትክክል ጡት መያዝ (Latch) እንዲችል፣ የጡቱን ጫፍ ብቻ ሳይሆን በዙሪያው ያለውን ጥቁር ክፍል (Areola) ጭምር አብሮ መያዝ አለበት። 

ስለዚህ ጠፍጣፋ ወይም ወደ ውስጥ የገቡ የጡት ጫፎች ቢኖሩሽም ተስፋ አትቁረጪ፤ በትክክለኛ የአቀማመጥ ዘዴ፣ በትዕግሥትና በበቂ ድጋፍ ልጅሽን በተሳካ ሁኔታ ማጥባት ትችያለሽ። 

ጠፍጣፋ ወይም ወደ ውስጥ የገቡ የጡት ጫፎች ካሉሽ ልጅሽን በቀላሉ ለማጥባት የሚከተሉትን ምክሮች ተከተይ ፦

           1. የጡትሽ ጫፎች ምን ዓይነት ምላሽ እንደሚሰጡ ፈትሺ

ጠፍጣፋ የሚመስሉ የጡት ጫፎች በሙሉ በእርግጥ ጠፍጣፋ ላይሆኑ ይችላሉ።አንዳንዶቹ ትንሽ ሲነኩ ወይም ሲነቃቁ በተፈጥሮ ወደ ውጭ ይወጣሉ። 

ይህን ለመፈተሽ በአውራ ጣትሽና በአመልካች ጣትሽ የጡትሽን ጥቁር ክፍል (Areola) ቀስ አድርገሽ ወደ ውስጥ በመጫን ለጥቂት ሰከንዶች ያዢ። 

  • የጡትሽ ጫፍ በሚነቃቃበት ጊዜ ወደ ውጭ የሚወጣ ከሆነ ልጅሽ በቀላሉ ጡት እንዲይዝ ይረዳዋል። 
  • ጠፍጣፋ ሆኖ የሚቀር ወይም ወደ ውስጥ የሚገባ ከሆነ ግን ተጨማሪ ዘዴዎችን መጠቀም ሊያስፈልግሽ ይችላል። 

           2. የጡትሽን ጫፍ ለማነቃቃት ሞክሪ 

ማጥባት ከመጀመርሽ በፊት የጡትሽን ጫፍ ቀስ አድርገሽ በማሸት ወይም ቀዝቃዛና እርጥብ ጨርቅ በላዩ ላይ በመያዝ ለጊዜውም ቢሆን ወደ ውጭ እንዲወጣ ማድረግ ትችያለሽ። 

           3. የጡት ወተት ማለቢያ (Breast Pump) ተጠቀሚ

የጡትሽን ጫፍ በማነቃቃት ብቻ ወደ ውጭ ማውጣት ካልተቻለ የጡት ወተት ማለቢያ (Breast Pump) መጠቀም ትችያለሽ። የማለቢያው የመሳብ ኃይል ጠፍጣፋ ወይም ወደ ውስጥ የገባን የጡት ጫፍ ቀስ አድርጎ ወደ ውጭ ለመሳብ ይረዳል። ይህም በተለይ በጣም ወደ ውስጥ ለገቡ የጡት ጫፎች የተሻለ መፍትሔ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ለዚሁ ዓላማ የተሠሩ "የጡት ጫፍ ማውጫዎች" (Nipple extractors) በመባል የሚታወቁ መሣሪያዎችን መጠቀም ትችያለሽ። አብዛኞቹ መሣሪያዎች ከልብስ ሥር የሚደረጉና ትንሽ ኩባያ የሚመስሉ ሲሆኑ፣ የጡቱን ጫፍ ቀስ አድርገው በመሳብ ይይዙታል። እነዚህን መሣሪያዎች አዘውትሮ መጠቀም በጊዜ ሂደት በዙሪያው ያሉትን ሕዋሳት በማላላት የጡት ጫፍ ወደ ውጭ እንዲወጣ ያግዛሉ። 

           4. በእጅሽ ጡትሽን እለቢው 

አንዳንዴ ጡትሽ በወተት ሞልቶ ሲወጠር ጠንካራ ሊሆን ይችላል፤ ይህም የጡትሽ ጫፍ እንዲደፈጠጥ በማድረግ ልጅሽ በትክክል እንዳይዘው ሊያደርገው ይችላል። 

ስለዚህ ጡትሽ ከተወጠረ ማጥባት ከመጀመርሽ በፊት በእጅሽ ጥቂት ወተት አልበሽ አውጪ። ይህም ጡትሽ እንዲለሰልስና ልጅሽ በቀላሉ ጡት እንዲይዝ ይረዳዋል። 

           5. የጡት ጫፍ መከላከያ (Nipple Shield) ወይም የጡት ኮፍያ (Breast Shells) ተጠቀሚ 

ጠፍጣፋ ወይም ወደ ውስጥ የገቡ የጡት ጫፎችሽን ለማውጣት ከተቸገርሽ የጡት ጫፍ መከላከያዎችን ወይም የጡት ኮፍያዎችን መጠቀም ትችያለሽ። 

የጡት ጫፍ መከላከያ (Nipple Shield) በጡት ጫፍና በዙሪያው ባለው ጥቁር ክፍል ላይ የሚደረግ፣ ለስላሳና የጡት ጫፍ ቅርጽ ያለው ሽፋን ሲሆን ልጅሽ በቀላሉ ጡት እንዲይዝ ይረዳል። ሆኖም ይህን መሣሪያ ያለአግባብ መጠቀም ልጅሽ በቂ ወተት እንዳያገኝ ወይም  የጡት ወተት ከጡትሽ ሙሉ በሙሉ እንዳይወጣ ሊከለክለው ስለሚችል እንደ ጊዜያዊ እርዳታ ብቻ ጥቅም ላይ መዋል አለበት። 

የጡት ኮፍያ (Breast Shells) ጡት በማታጠቢበት ወቅት የሚደረጉ ቀላል የፕላስቲክ ሽፋኖች ናቸው። እነዚህ ጠፍጣፋ ወይም ወደ ውስጥ የገቡ የጡት ጫፎችን በስሱ ሳብ አድርገው ለማውጣት የሚያግዙ ከመሆናቸውም በላይ የቆሰሉ የጡት ጫፎች ከልብስ ጋር እንዳይፋተጉ ይከላከላሉ። 

እነዚህ መሣሪያዎች በትክክል ጥቅም ላይ ሲውሉ በምታጠቢበት ወቅት ጠቃሚ ድጋፍ ይሰጣሉ። 

           6. ልጅሽ ጡትሽን በትክክል እንዲይዝ (Latch) ደግፈሽ ያዢው  ደግፈሽ ያዥው

በምታጠቢበት ወቅት ጡትሽን ደግፈሽ መያዝ ልጅሽ በምቾትና በትክክል ጡት እንዲይዝ ይረዳዋል። ለዚህም ልትሞክሪያቸው የምትችያቸው ሁለት ዋና ዋና የአያያዝ ዘዴዎች አሉ፦ 

የ"C" አያያዝ (C-Hold)

የ"C" አያያዝ በጡትሽ ላይ የተሻለ ቁጥጥር እንዲኖርሽና የጡትሽን ጫፍ ወደ ልጅሽ አፍ በቀላሉ ለማስገባት ይረዳሻል። 

  • አውራ ጣትሽን ከላይ፣ የተቀሩትን ጣቶችሽን ደግሞ ከታች አድርገሽ ያዢ (ጣቶችሽ ከጡትሽ ጥቁር ክፍል/Areola ጀርባ መሆናቸውን አረጋግጪ 
  • ልክ ሳንድዊች እንደምትዢው አውራ ጣትሽንና ሌሎችን ጣቶችሽን በመጠቀም ቀስ አድርገሽ ጡትሽን ጫን አድርገሽ ያዢው። 

የ"V" አያያዝ (V-Hold)

የ"V" አያያዝ ጡትሽን ለመደገፍ እና ቅርጽ ለመስጠት ሁለት ጣቶችሽን የምትጠቀሚበት ዘዴ ነው። 

  • የአመልካች እና የመካከለኛ ጣቶችሽን ከላይ በጡትሽ ጫፍ ዙሪያ የ"V" ወይም የመቀስ ቅርፅ እንዲይዙ አድርገሽ አስቀምጪ
  • የጡትሽ ጫፍና ጥቁሩ ክፍል (Areola) ወደ ውጭ እንዲወጡ ለማገዝ ጣቶችሽን ቀስ አድርገሽ ወደ ደረትሽ አቅጣጫ ጫን አድርገሽ ያዢ። 

ለአንቺና ለልጅሽ ይበልጥ የሚመቸውን ዘዴ ለመለየት ሁለቱንም አማራጮች ሞክሪያቸው። 

          7. በጊዜው እርዳታና ድጋፍ ጠይቂ

ጡት ማጥባት ብቻሽን የምትታገዪበት ነገር መሆን የለበትም።

ልጅሽ ደጋግሞ ጡት ለመያዝ የሚቸገር ከሆነ፣ በምታጠቢበት ወቅት ሕመም የሚሰማሽ ከሆነ ወይም ስለወተትሽ መጠን ሥጋት ካለሽ የጤና ባለሙያ አማክሪ። በጊዜው የምታገኚው ድጋፍና እርዳታ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።

          8. የቀዶ ሕክምና አማራጮችን ግምት ውስጥ ማስገባት ትችያለሽ 

ሌሎች የመፍትሔ መንገዶች ካልሰሩ ወደ ውስጥ የገቡ የጡት ጫፎችን ለማስተካከል የቀዶ ሕክምና አማራጭን መጠቀም ይቻላል። 

ለጠፍጣፋ ወይም ወደ ውስጥ ለገቡ የጡት ጫፎች የሚደረጉ የተለያዩ የቀዶ ሕክምና ዓይነቶች አሉ ። አንዳንድ የቀዶ ሕክምና ዓይነቶች የወተት አስተላላፊ ቱቦዎችን ሳይጎዱ የሚከናወኑ በመሆናቸው ከሕክምናው በኋላ ማጥባት ትችያለሽ፤ ሌሎች ግን የማጥባት አቅምሽን ሊቀንሱት ወይም ሊጎዱት ይችላሉ። 

በመሆኑም የቀዶ ሕክምናውን ጥቅምና ጉዳት በመገምገም ለአንቺ የተሻለውን አማራጭ ለመምረጥ ከሐኪምሽ ጋር መማከር አስፈላጊ ነው። 

ስለሆነም ጠፍጣፋ ወይም ወደ ውስጥ የገቡ የጡት ጫፎች መኖራቸው ልጅሽን ማጥባት አትችይም ማለት እንዳልሆነ ተረድተሽ  እነዚህን ቀላል ዘዴዎች በመጠቀም ልጅሽን በተሳካ ሁኔታ ማጥባት ትችያለሽ።

Comments (0)