ሶሪያሲስ (psoriasis)
ሶሪያሲስ (Psoriasis) ማለት ረጅም ጊዜ የሚቆይ በሰዉነታችን የተሳሳተ ምላሽ የሚመጣ የቆዳ በሽታ ሲሆን በጉልበቶች፣ በክርኖች፣ በደረት/ጀርባ (trunk) እና በራስ ቆዳ ላይ የሚያሳክኩና ቅርፊት ያላቸው ሽፍታዎችን የሚያስከትል የቆዳ በሽታ ነው።
በዓለም ዙሪያ በግምት ከ60 እስከ 125 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን የሚያጠቃና ሪፖርት የተደረገ የስርጭት ግምቱ ከ0.6% እስከ 4.8% ገደማ የሚደርስ ሥር የሰደደ የቆዳ ብግነት (ኢንፍላሜሽን) በሽታ ነው።
የሶሪያሲስ ዓይነቶች
አምስቱ ዋና ዋና የሶሪያሲስ ዓይነቶች ፕሌክ፣ ጉቴት፣ ኢንቨርስ፣ ፑስቹላር እና ኤሪትሮደርሚክ ሶሪያሲስ ሲሆኑ፣ እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ልዩ ባህሪያትና የሚወጡባቸው የሰውነት ክፍሎች አሏቸው፦
- ፕላክ ሶሪያሲስ፦ በብዛት የሚከሰተው ዓይነት (ከ80% እስከ 90% የሚሆነውን ክስተት ይሸፍናል) ሲሆን፣ እንደ ክርን፣ ጉልበት እና የራስ ቆዳ ባሉ አካባቢዎች ላይ ከቆዳ ከፍ ባሉና ቅርፊት ባላቸው ሽፍታዎች ተለይቶ ይታወቃል።
- ጉቴት ሶሪያሲስ፦ ብዙውን ጊዜ እንደ የጉሮሮ ኢንፌክሽን (ስትሬፕ ትሮት) ባሉ ኢንፌክሽኖች የሚቀሰቀስ ሲሆን፣ በዋናነት በወጣቶች ደረትና ጀርባ (የሰውነት ግንድ) እንዲሁም እጅና እግር ላይ እንደ ትናንሽ የውሃ ጠብታ ቅርጽ ያላቸው ነጠብጣቦች ሆኖ ይታያል።
- ኢንቨርስ ሶሪያሲስ፦ በቆዳ መታጠፊያዎች ላይ (እንደ ብብት እና ብሽሽት ባሉ ቦታዎች) የሚከሰት ሲሆን፣ በፍትጊያ እና በላብ የሚባባሱ ልስልስ ያሉ ሽፍታዎችን ይፈጥራል።
- ፑስቱላር ሶሪያሲስ፦ ተላላፊ ባልሆኑና መግል በያዙ እብጠቶች የሚታወቅ ሲሆን፣ በተወሰኑ የሰውነት ክፍሎች ላይ ብቻ ተወስኖ ሊቀር (ለምሳሌ በእጅ እና በእግር ላይ) ወይም በመላው ሰውነት ላይ ሊሰራጭ ይችላል።
- ኤሪትሮደርሚክ ሶሪያሲስ፦ እጅግ በጣም አልፎ አልፎ የሚከሰትና በጣም አደገኛው ዓይነት ሲሆን፣ በሰውነት ላይ በስፋት የቆዳ መላላጥና ከፍተኛ መቅላትን ያስከትላል፤ እንዲሁም የሰውነትን ፈሳሽና የሙቀት መጠን የመቆጣጠር አቅም ላይ አደጋ ስለሚጥል አስቸኳይ የሕክምና ክትትል ይፈልጋል።
መንስኤዎቹ እና አጋላጭ ሁኔታዎች
ሶሪያሲስ ትክክለኛውን መንስኤ ሙሉ በሙሉ ግልጽ ባይታወቅም የጄኔቲክስ እና የአካባቢ ሁኔታዎች ጥምረት እንደሆነ ይታመናል።
የተሳሳተ የሰውነት በሽታ የመከላከል ስርዓት ችግር ነው ተብሎ ይታሰባል፤ ይህም አዳዲስ የቆዳ ሴሎችን በፍጥነት እንዲፈጠሩ ፤ እንዲተኩ ያደርጋል።
በአዲሶቹ መተካት የድሮ ሕዋሶች መከማቸት ችግሩ እነዲከሰት ዋነኛ ምክንያት ሲሆን ከአጋላጭ ሁኔታዎች ዉስጥ
- ኢንፌክሽን ፡- እንደ የጉሮሮ መቁሰል ወይም የቆዳ ኢንፌክሽን የመሳሰሉ ኢንፌክሽኖች
- የአየር ሁኔታ፡- በተለይም ቀዝቃዛ፤ ሞቃታማ የአየር ሁኔታዎች
- ጭንቀት
- ማጨስ እና ለሲጋራ ጭስ መጋለጥ
- የአልኮል መጠጥ ሱስ
- አንዳንድ መድሃኒቶች
ምልክቶቹም
- ቆዳችን ላይ ሽፍታ ወይም ቀይ መሆን
- የቆዳ መድረቅ እና መሰነጣጠቅ
- የቆዳ ማሳከክ እና ማቃጠል
- ቆዳ ላይ ቅርፊት የመሰሉ ነገሮች መውጣት
- ብዙ በማከካችን የመጣ የቆዳ መወፈር
ሕክምናዎቹ
ብዙ የሕክምና አይነቶች ሲኖሩ አንዳንዶቹ የአዳዲስ የቆዳ ህዋሳትን እድገታቸውን ሲያዘገዩ ሌሎች ደግሞ ማሳከክን እና ደረቅ ቆዳን ያስወግዳሉ። እንደ ሽፍታዎ መጠን ፣ በሰውነትዎ ፣ በእድሜዎ ፣ በአጠቃላይ ጤናዎ እና በሌሎች ነገሮች ላይ በመመርኮዝ ሐኪምዎ ለእርስዎ ትክክለኛ የሆነ የሕክምና ዕቅድ ይመርጣል። የተለመዱ ህክምናዎች የሚከተሉት ናቸው።
- ስቴሮይድ ክሬሞች
- ቆዳን የሚያለሰልሱ ቅባቶች እና ክሬሞች
- ሬቲኖይድ ክሬሞች
- የጨረር ህክምና
- በአፍ የሚሰጡ እንክብሎች
ማንኛውም ሶሪያሲስ ያጠቃው ሰው የሚከተሉትን ነገሮች በቤት ዉስጥ ማድረግ ይኖርበታል
የሶሪያሲስ በሽታን ሙሉ በሙሉ መከላከል ባይቻልም ከተከሰተ በኋላ ቶሎ ቶሎ ህመሙ እንዳይመጣ ማረግ ይቻላል። ከነሱም ዉስጥ
- ሁልጊዜ ቆዳ እንዳይደርቅ ማድረግ። ቤትዎ ደረቅ አየር እንዳይኖረው ማድረግ ቢችሉና ቆዳዎትን ለስለስና ረጠብ ማድረግ።
- የሚያጨሱ ከሆነ ያቁሙ። ማጨስ የበሽታውን የማጥቃት አቅም ይጨምርለታል።
- አልኮል ተጠቃሚ ባይሆኑ ይመረጣል። አልኮል በሽታውን ያባብሳል።
- በጤና ባለሙያ ለተመጠነና ለታዘዘ የፀሀይ ጨረር ቁስሉን ማጋለጥ።
- ጭንቀትና ውጥረትን ይቀንሱ። ጭንቀት ምልክቱ በህክምና ቢጠፋ እንኳን እንድመለስና በሽታው እንድባባስ ያደርጋል።
- ለብ ባለ ውሀ ሰውነተዎን ይዘፍዝፉት። ፈፅሞ ለስለስ ከማለት ያለፈ ወይም ሞቃት ውሀን እንዳይጠቀሙ። ለብ ካለው ውሀ ላይ ኢፕሰም ጨው፣ ኦሊይቭ ዘይት፣ ሚኒራል ኦይልና ወተት መጨመር ይቻላል።
- ሁል ጊዜ ጤናማ አመጋገብ ከቻሉ ይጠቀሙ። ቀይ ስጋ፣ የሚወጋ ዘይት፣ የተፈበረከ ስኳር፣ ሀይልና ሙቀት ሰጭ ምግብና አልኮልን ባይጠቀሙ ጥሩ ነው። እንዳይባባስና ባለበት እንድገታ ያደርጋል።
- ማንኛውንም ሳሙና፣ ዶዶራንትና ሽቶ ከመጠቀም ይቆጠቡ። የሚስማማዎትን ሳሙና ይምረጡ ወይም ሀኪመዎትን ያማክሩ።
- የተቀነባበሩ የምግብ ግብአቶችን እንደ አሳ ዘይት፣ ቫይታሚን ዲና የተናጠ የወተት ተዋፅኦን መጠቀም
- በመጨረሻም ችግሩ መቸ፣ እንዴት፣ በምንና ለምን እንደሚባባስና እንደሚቀንስ ከራስዎ የ(በሽታ) ህይዎት ተሞክሮም ማወቅ ይጠበቅበዎታል።
የቆዳ ሀኪሞችን በየጊዜው ማማከር እና ክትትል ማድረግ ከበሽታው ጋር የሚኖረንን ህይወት የተሻለ ያድርጉ።




