የተሰበረ አጥንት እንዴት ይጠገናል?

Eyasu Yebeltal
Nov 27, 2026
1775877771765

         የተሰበረ አጥንት እንዴት ይጠገናል?

የአጥንት መሰበር አስጨናቂ እና ህመም ያለው ተሞክሮ ሲሆን ከአደጋ ወይም ከስፖርት ጉዳት በኋላ በብዛት ያጋጥማል። መልካሙ ዜና ሰውነትዎ ራሱን የመፈወስ አስደናቂ ችሎታ ያለው መሆኑ ሲሆን ከስብራት እንዴት እንደሚፈወሱ መረዳቱ ለማገገም ትክክለኛውን እርምጃ እንዲወስዱ ይረዳዎታል።

የአጥንት ስብራት ምንድን ነው?

የአጥንት ስብራት ማለት በቀላሉ ከትንሽ ስንጥቅ እስከ ሙሉ አጥንቱ ወደ ሁለት የተለያዩ ክፍሎች የሚለያይበትን ሁኔታ ያካትታል። የተለመዱ የአጥንት ስብራት መንስኤዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ:-

  • መውደቅ ወይም ቀጥተኛ መመታት
  • የስፖርት እንቅስቃሴ ጉዳቶች
  • የመኪና ወይም የሞተር ሳይክል አደጋዎች
  • የአጥንት መሳሳት (ኦስቲዮፖሮሲስ)

መንስኤው ምንም ይሁን ምን የፈውስ ሂደቱ ተመሳሳይ መንገድን ይከተላል።

የአጥንት ስብራት እንዴት ይድናል?

አጥንቶች ያለማቋረጥ ራሳቸውን የሚያድሱ ሕያው ህብረህዋሳት ሲሆኑ ስብራት በሚከሰትበት ጊዜ ሰውነትዎ በሦስት ዋና ዋና ደረጃዎች የሚከናወን የተፈጥሮ ጥገና ሂደት ወዲያውኑ ይጀምራል።

1. የሰውነት ቁጣ ደረጃ (የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት)

  • ልክ ከስብራት በኋላ በተሰበረው አጥንት አካባቢ የደም መፍሰስ ይከሰታል። 
  • ይህም የደም መርጋትን በመፍጠር ልዩ የፈውስ ሴሎችን ይሰበስባል።
  • በዙሪያው ያለው ሕብረ-ሕዋስ እብጠት እና ለንክኪ ህመም ያለው ይሆናል። ይህም የተለመደ የፈውስ አካል ነው።

2. የጥገና ደረጃ (በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት)

  • ኦስቲዮብላስት የሚባሉ ህዋሳት በስብራቱ አካባቢ ለስላሳ አጥንት መፍጠር ይጀምራሉ።
  • ቀስ በቀስ ይህ ለስላሳ አጥንት ይበልጥ እየጠነከረ በመሄድ በተሰበሩ የአጥነት ጫፎች መካከል ያለውን ክፍተት ያስተካክላል።
  • ይህ ደረጃ የስብራቱ አይነት እና ቦታ ላይ በመመስረት ከ 4 እስከ 8 ሳምንታት ሊቆይ ይችላል።

3. የማሻሻያ ደረጃ (ከብዙ ወራት እስከ አንድ ዓመት)

  • የተከማቸው ጠንካራ የአጥንት ህብረ-ህዋስ ቀስ በቀስ ወደተስተካከለ እና ጠንካራ አጥንት ይለወጣል።
  • አጥንቱም ነባር መደበኛ መዋቅሩን እና ጥንካሬን ሲያገኝ አንዳንድ ጊዜ ከበፊቱ የበለጠ ጠንካራ ሊሆን ይችላል።

ለፈውስ የሚፈጀው አጠቃላይ ጊዜ እንደ እድሜ፣ አጠቃላይ ጤና እና የአጥንቱ አይነት ይለያያል።

ፈውስ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ምክንያቶች

አንዳንድ ነገሮች የአጥንትን ፈውስ ሊያፋጥኑ ወይም ሊያዘገዩ ይችላሉ፡-

ፈውስን የሚረዱ ነገሮች

  • አጥንትን በትክክል ወደቀድሞ ቦታ መመለስ (በጀሶ ማሰር ወይም ቀዶ-ጥገና)
  • ጥሩ አመጋገብ (በተለይ በካልሲየም፣ በቫይታሚን ዲ እና በፕሮቲን የበለጸገ አመጋገብ)
  • ሲጋራ ማጨስ እና አልኮል መጠጣትን ማስወገድ
  • ስለ እንቅስቃሴ እና እረፍት የሃኪምዎን መመሪያዎች በመከተል

ፈውስን የሚያዘገዩ ምክንያቶች

  • ደካማ የአጥንት ደም አቅርቦት
  • ኢንፌክሽን
  • ማጨስ
  • ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የስኳር በሽታ
  • ያለጊዜ ክብደትን እንዲሸከም ማድረግ ወይም 
  • እንደገና መጎዳት

ህክምና

የሃኪምዎ ዋና ግብ ሰውነትዎ የፈውስ ስራውን በሚያከናውንበት ጊዜ የተሰበሩት የአጥንት ቁርጥራጮችን በትክክለኛው ቦታ ላይ ማስቀመጥ ነው። ሕክምናው የሚከተሉትን ሊያካትት ይችላል:-

  • በጀሶ ማሰር፡- ስብራቱ በትክክል መፈወስ እንዲችል አጥንቶቹ ወደ ድሮ ቦታቸው ተመልሰው በጀሶ እንዳይንቀሳቀሱ ይታሰራል። 
  • መጎተት፡- የአጥንቶችን  ቀጥነት ለመጠበቅ በቁዋሚ ክብደት የሚኖር ለስላሳ መጎተት።
  • ቀዶ-ጥገና፡- አጥንትን የድሮ ቦታው ለማቆየት የብረት ማሰሪያ ወይም ዘንጎችን በቀዶ-ጥገና መጠቀም።

የኤክስሬይ ክትትል አጥንትዎ ምን ያህል እየተፈወሰ እንደሆነ ለመከታተል ይረዳል።

በማገገም ወቅት እራስዎን መንከባከብ

ፈውስዎን ለመደገፍ እና ችግሮችን ለመከላከል ጥቂት ምክሮች፡-

  • መመሪያዎችን በጥንቃቄ ይከተሉ 
  • የተመጣጠነ ምግብን ይመገቡ:- በካልሲየም የበለጸጉ እንደ ወተት፣ እርጎ፣ ቅጠላ ቅጠሎች እና ቫይታሚን ዲ ን ያካትቱ ምግቦችን ይመገቡ።
  • በጥንቃቄ ይንቀሳቀሱ:- ዶክተርዎ ወይም ፊዚዮቴራፒስትዎ የሚመክሩዎትን እንቅስቃሴዎች ብቻ ያድርጉ።
  • ማጨስን እና አልኮልን ያስወግዱ:- የአጥንት ጥገናን ሊቀንሱ ይችላሉ።
  • አደጋዎችን ይከታተሉ:- እንደ የከፋ ህመም፣ መቅላት፣ እብጠት ወይም ትኩሳት ያሉ የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ሲመለከቱ ለሐኪምዎ ያሳውቁ።

አጥንቱ ከተፈወሰ በኋላ ጥንካሬን፣ የመገጣጠሚያ መተጣጠፍን እና እንቅስቃሴን ወደ ነበረበት ለመመለስ የፊዚዮቴራፒ ሕክምና ሊያስፈልግዎ ይችላል። ማገገም ቀስ በቀስ የሚመጣ ሂደት ስለሆነ ሰውነትዎን በትዕግስት ይጠብቁ። አብዛኛዎቹ ስብራቶች በተገቢው እንክብካቤ ሙሉ በሙሉ መዳን እና ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዎች መመለስ ይችላሉ።

Comments (0)