በጨቅላ ህጻናት የሚከሰት ቁርጠት (ኮሊክ)
በጨቅላ ህጻናት የሚከሰት ቁርጠት (ኮሊክ) የምንለው ሌላ ጊዜ ጤነኛ የነበረ ልጅ በቀን ለሶስት ሰአታት ወይም ከዚያ በላይ በሳምንት ለሶስት ወይም ከዚያ በላይ ቀናት ቢያንስ ለሶስት ሳምንታት የሚያለቅስ ከሆነ ኮሊክ እንለዋለን። ብዙ ጊዜ ምልክቶቹም በህጻኑ የመጀመሪያ 3 እስከ 6 ሳምንታት ባሉት የህይወት ጊዜያት ውስጥ ይታያሉ። ከ 10 ህጻናት ውስጥ አንድ ህጻን ላይ ኮሊክ ያጋጥማል።
የልጃችን የማያቋርጥ ለቅሶ ጭንቀት እና ስጋት ሊፈጥርብን ቢችልም ኮሊክ ጊዜያዊ የጤና እክል መሆኑን መረዳት አስፈላጊ ነው። ይህም አብዛኛውን ጊዜ በራሱ ይተዋቸዋል። ብዙ ጊዜም የከባድ የጤና እክል ምልክት አይደለም።
በጨቅላ ህጻናት የሚከሰት ቁርጠት ምልክቶች ምንድን ናቸው?
ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ህጻኑ በቀን ቢያንስ ለሶስት ሰአታት እና ከዚያ በላይ ፤ በሳምንት ቢያንስ ለሶስት ቀናት ያለቅሳል። በአጠቃላይ ማልቀስ የሚጀምረውም በቀን ውስጥ በተመሳሳይ ሰአት ሲሆን ብዙ ጊዜም ቁርጠቱ የሚኖረው ከጠዋት እና ከከሰዓት ይልቅ አመሻሽ ላይ ነው። የቁርጠት ምልክቱ በድንገት የሚነሳ ሲሆን ማለትም ሲስቅ ሲጫወት የነበረ ህጻን በአንዴ ተቀይሮ መነጫነጭ ይጀምራል። ህመሙንም ለማስታገስ እግሮቹን ሊያፈራግጥ ወይም ወደ ላይ ከፍ ሊያረግም ይችላል። በሚያለቅስበት ጊዜም ሆዱ ያበጠ ወይም የጠነከረ ሊመስልም ይችላል።
የጨቅላ ህጻናት ቁርጠት እንዴት ይከሰታል?
የጨቅላ ህጻናት ቁርጠት (ኮሊክ) የሚመጣበት ምክንያት በርግጥ ባይታወቅም በአሁኑ ጊዜ ብዙ የህጻናት ስፔሻሊቲ ሓኪሞች ሁሉም ጨቅላ ህጻናት የሆነ ጊዜ ላይ ቁርጠት (ኮሊክ) ያጋጥማቸዋል ብለው ያምናሉ። አንዳንድ ህጻናት ላይ ይህ ቁርጠት ለሳምንታት ሲቆይ ሌሎች ህፃናት ላይ ደግሞ ለጥቂት ቀናት ብቻ ይቆያል።
ጨቅላ ህጻናት ላይ ቁርጠት የሚቀሰቅሱ ነገሮች
ቀደም ሲል እንዳየነው ጨቅላ ህጻናት ላይ የሚፈጠር ቁርጠት ምክንያቱ ባይታወቅም አንዳንድ ሓኪሞች አንዳንድ ነገሮች ህጻናት ላይ የቁርጠት ምልክትን ይጨምራሉ ብለው ግን ያምናሉ። እነዚህም ቀስቃሽ ነገሮች የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ።
- ረሃብ
- ጀርድ (የጨጓራ አሲድ ወደ የላይኛው የምግብ ትቦ (esophagus) መመለስ)
- ጋዝ (አየር)
- በጡት ወተት ውስጥ የላም ወተት ፕሮቲኖች መኖር
- ፎርሙላ ወተት
- ካጠባን በኃላ ህጻኑን በደንብ አለማስገሳት
- ህጻኑን ከመጠን በላይ መመገብ
- በእርግዝና ወቅት ሲጋራ ማጨስ
- ያልዳበረ የነርቭ ስርዓት ህጻኑ ላይ ቁርጠትን ሊቀሰቅሱ ይችላሉ።
የጨቅላ ህጻናት ቁርጠት ህክምና
የጨቅላ ህጻናት ቁርጠት ምክንያት አለመታወቁ የተረጋገጠ ህክምና እንዳይኖረው ቢያደርግም ህጻን ልጃችን ላይ ቁርጠቱን የሚቀሰቅሱ ነገሮች ለማወቅ መሞከር ግን ህጻኑ በሚያለቅስበት ጊዜ ለማጽናናት እና የሚያለቅስበትን ጊዜ ለመቀነስ ይረዳናል።
የሚከተሉት መንገዶች ህጻኑን ለማረጋጋት ይረዱናል፦
- ልጃችንን በተቻለ መጠን አዘውትሮ መያዝ (ማቀፍ)። ልጃችን በሚያለቅስበት ጊዜ መያዝ በቀን ውስጥ የሚያለቅስበትን ጊዜ ይቀንስልናል። የቤት ውስጥ ስራዎችን በምንሰራበት ጊዜም በዥዋዥዌ መጫወቻ ላይ ማስቀመጥ ሊያረጋጋው ይችላል።
- ልጃችንን አቅፈን ወክ ማድረግ ወይም በመኪና መውሰድ
- የሚያረጋጉ ሙዚቃዎችን መክፈት
- የእንጀራ እናት ጥጦ መስጠት
- የአንጀት እንቅስቃሴውን ለመርዳት ሆዱን ቀስ ብሎ ማሸት እና እግሩን በእጃችን ይዘን በቀስታ እንደሳይክል መንዳት ማንቀሳቀስ
- ልጃችንን በምናጠባበት ጊዜ በተቻለ መጠን ቀና አድርጎ መያዝ
- ልጃችን ጥጦ የሚጠባ ከሆነ እና በሚጠባበት ጊዜ በጣም ብዙ አየር እየዋጠ ከመሰለን የጥጦውን ጫፍ ወይም ጡጦውን መቀየር
- ልጃችን የሚመገበው ፎርሙላ ወተት ከሆነ እና ቁርጠቱ ፎርሙላ ወተት ውስጥ ባለው ፕሮቲን ነው ብለን ካሰብን ከልጃችን ሓኪም ጋር በመወያየት መፍትሔ መፈለግ
- ጡት የምናጠባ ከሆነ የራሳችንን አመጋገብ መቀየር ልጃችን ላይ ያለውን ቁርጠት ሊቀንስልን ይችላል። አንዳንድ ጡት የሚያጠቡ እናቶች አመጋገባቸው ላይ እንደ ቡና እና ቸኮለት ያሉትን ካፊን ያላቸው ምግቦች እና መጠጦች በማስወገድ የልጆቻቸውን የቁርጠት ምልክት መቀነስ ችለዋል።
የጨቅላ ህጻናት ቁርጠት መች ይጠፋል?
የጨቅላ ህጻን ልጃችንን የመረረ ለቅሶ ስናይ ቁርጠቱ ለረጂም ጊዜ የሚቆይ ሊመስለን ቢችልም ብሔራዊ የህጻናት ጤና እና እድገት ማእከል እንዳወጣው መረጃ መሰረት ብዙውን ጊዜ ህጻናት 3 ወይም 4 ወራት ሲሞላቸው የሆድ ቁርጠቱ ይተዋቸዋል። ቁርጠቱ ከ 4 ወራት በላይ የሚቆይ ከሆነ ግን የሌላ የጤና እክል ምልክት ሊሆን ስለሚችል የህጻናት ሓኪሞችን ማማከር ይኖርብናል።
ጨቅላ ህጻናችንን መቼ ወደ ጤና ተቋም እንውሰድ?
በጨቅላ ህጻናት ላይ የሚፈጠር ቁርጠት ብዙውን ጊዜ የሚያስጨንቅ የጤና እክል ባይሆንም የሚከተሉት ምልክቶች አብሮ ከታየባቸው ግን ወደ ጤና ተቋም መውሰድ ይኖርብናል።
- ከ 38°c ( 100.4°F) በላይ የሆነ ትኩሳት
- ተወርዋሪ ትውከት
- የማያቋርጥ ተቅማጥ
- ደም የቀላቀለ ተቅማጥ
- ሰገራ ላይ ንፍጥ የሚመስል ነገር (mucus) መኖር
- የቆዳ መገርጣት እና
- የምግብ ፍላጎት መቀነስ ካለ በፍጥነት የህጻናት ሓኪምን ማማከር ይኖርብናል።



