የህፃናት ጡት አለመጥባት አድማ(Nursing strike)

Elsabet Azezew
Aug 4, 2025
undefined

                        የህፃናት ጡት አለመጥባት አድማ(Nursing strike)

 

             ጡት የሚያጠባ ወላጅ እንደመሆኖ ልጆ በቀን ውስጥ ምን ያህል ጊዜ እንደሚመገብ እና ከወትሮ ያነሰ ወተት ሲወስድ በፍጥነት ሊያስተውሉ ይችላሉ። ልጅዎ በድንገት ጡት የሚጠባበትን ሂደት ሲቀይር ለምን እንደሆነ እና እሱን ለማስተካከል ምን ማድረግ እንዳለብዎ ቶሎ ማወቅ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህ ፅሁፍ የህፃናት ጡት አለመጥባት አድማ ምን እንደሆነ እና አድማውን ለማስቆም ማድረግ ስለሚችሏቸው ነገሮች እንዳስሳለን። 

 

              ጡት አለመጥባት አድማ በጥሩ ሁኔታ ሲጠባ የቆየ ህፃን በድንገት ጡት ለመጥባት ፈቃደኛ የማይሆንበት ሁኔታ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ይህን ባህሪ 3 ወር እስኪሞላቸው ድረስ እና በዙሪያቸው ስላለ ነገር የበለጠ ንቁ እስኪሆኑ ድረስ አይጀምሩም። ወደ ጡት አለመጥባት አድማ የሚገቡ ህፃናት ጡት ለመቀበል እንቢ ቢሉም ባለመጥባታቸው ግን ይነጫነጫሉ፣ ይበሳጫሉ በአጠቃላይም  ደስተኛ አይሆኑም። እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ነገር ህፃናት በሚጠቡበት ጊዜ ትኩረት መሰረቅ ፣ ማሃል ላይ ማቆም እና ጡት ይዘው መጫወት የጡት አለመጥባት አድማ ላይ ናቸው አያስብልም ፤ አድማ ላይ ናቸው ለማለት ሙሉ በሙሉ ለተወሰነ ጊዜ ጡት መጥባት ማቆም ይኖርባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ የጡት መጥባት አድማ ልጁ ጡት ለመጣል (ለመተው) ዝግጁ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። ይህ ግን ትክክል አይደለም ጡት መጣል ህፃኑ 2 አመት እስኪሞላው ድረስ የመፈጠር እድሉ በጣም ዝቅተኛ ሲሆን በድንገት ከማቆም ይልቅ ቀስ በቀስ ጡት የሚጠባበትን ጊዜ እና ቆይታ ይቀንሳል።  

           ጡት አለመጥባት አድማ በምን ምክንያት ይከሰታል?

          ህፃናት በተለያዩ አካላዊ እና ስሜታዊ ሁኔታዎች ወደ ጡት አለመጥባት አድማ ሊገባቡ ይችላሉ። ከእነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ 

            

  • እንደ አፍንጫ መታፈን ፣ የጆሮ ህመም፣ የጉሮሮ እና የአፍ ቁስሎች ያሉ ጡት በሚጠቡበት ጊዜ ምቾት የሚነሱ ሁኔታዎች ካሉ
  • ጥርስ ከማብቀል ጋር የተያያዘ የድድ ህመም ካለ
  • የጡት ወተት ፍሰት አቅርቦት ዝቅተኛ ከሆነ ወይም ፍሰቱ በጣም ብዙ እና ፈጣን ከሆነ በህፃኑ ላይ የመበሳጨት ስሜት ሊፈጥር እና አድማ እንዲያደርግ ሊገፋፋው ይችላል
  • በሆርሞን ወይም በአመጋገብ ለውጥ ምክንያት የጡት ወተት ጣዕም መቀየር ካለ
  • ህፃኑ በሚጠባበት ጊዜ እናቱን የነከሰበት እና ጠንከር ያለ ምላሽ ያሳየችበት ወይም በከፍተኛ ድምፅ ምክንያት የደነገጠበት አጋጣሚ ከነበረ
  •  እናቱ የተበሳጨች ፣ የተጨነቀች ወይም በምታጠባበት ጊዜ በተለያየ ምክንያት ትኩረት ያጣች ከመሰለው
  • እናቱ እንደ ዲኦድራንት፣ ሳሙና፣ ሽቶ፣ ሎሽን ያሉ ቀደም ሲል ስትጠቀምባቸው የነበሩ የግል ንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን ከቀየረች እና የተለየ ጠረን ካመጣች
  • በሚጠቡበት ጊዜ ትኩረታቸውን የሚሰርቅ ሁኔታ ካለ ህፃናት በድንገት ጡት አለመጥባት አድማ ላይ እንዲገቡ ሊያደርጋቸው ይችላሉ።              

       ልጆ ጡት አለመጥባት አድማ ላይ ከሆነ ምን ማድረግ ይችላሉ?

            ጡት አለመጥባት አድማ ለእርሶም ሆነ ለልጆ የሚያስጨንቅ ነገር ቢሆንም የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም  ልጆን በተሳካ ሁኔታ ጡት ወደመጥባት መመለስ ይችላሉ። የጡት አለመጥባት አድማውን ለማቆም ሁለት ዋና ተግዳሮችን ማስተካከል ይኖርቦታል እነዚህም የጡት ወተት አቅርቦቶን መጠበቅ እና ልጅዎ በአግባቡ መመቡን ማረጋገጥ ናቸው።   

            ልጅዎ ከወትሮ ያነሰ ወተት በሚወስድበት ጊዜ የወተት አቅርቦቶን ለመጠበቅ እና ለመቆጣጠር ወተትን በፓምፕ ወይም በእጅ ማለብ የሚያስፈልግ ሲሆን ይህም ሰውነትዎ የወተት መመረት እንደሚያስፈልግ እንዲያውቅ እና ማምረቱን እንዲቀጥል ይረዳል። ይህም ልጅዎ እንደገና ጡት መጥባት በሚጀምርበት ጊዜ በቂ የወተት አቅርቦ እንዲኖረው ያደርጋል። 

             ጡት አለመጥባት አድማ ወቅት ልጅዎ በቂ ምግብ ማግኘቱን ለማረጋገጥ ያለቡትን ወተት በጥጦ ወይም በኩባያ መስጠት ያስፈልጋል። ወተት ለልጆ በጥጦ ወይም በኩባያ መስጠት አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም ወደ ጡት መጥባት እስኪመለሱ ድረስ ግን አስፈላጊውን ያህል ካሎሪ እንዲያገኙ እጂግ በጣም ጠቃሚ ነው። አንዴ ልጆ በቂ ካሎሪ እያገኘ መሆኑን እና በቂ የጡት ወተት አቅርቦ እንዳሎት ካረጋገጡ በኋላ ጡት እንዲወስድ መሞከር ይችላሉ። ልጅዎን ጡት እንዲጠባ የሚያበረታቱባቸው ብዙ መንገዶች ያሉ ሲሆኑ ከእነርሱም ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ

               

  •  ልጅዎ ጋር ቆዳ ለቆዳ ንክኪ እንዲኖሮ አድርገው ካቀፉ በኋላ ቀስ ብለው ጡት ለመስጠት መሞከር
  • የተለያዩ ማቀፊያዎችን እና አስተቃቀፎችን በመሞከር ለልጅዎ ምቾት የሚሰጠውን መለየት 
  • በሚያጠቡበት ጊዜ የልጅዎን ትኩረት ሊሰርቁ የሚችሉ ነገሮችን ለማስወገድ ብርሃን ያልበዛባቸው ወይም ጨለማ ክፍሎችን ይምረጡ
  • በሚያጠቡበት ጊዜ ጭንቀትን ለማስወገድ እና ዘና ለማለት ይሞክሩ
  • በማያጠቡባቸው ጊዜያት ልጅዎ ጋር አውንታዊ ግንኙነት ለመፍጠር መሞከር  
  • ልጅዎ ጡት እንዲጠባ ማበረታታት 
  • ልጅዎ በሚተኛበት ጊዜ ለማጥባት መሞከር 
  • ከሌሎች ጡት ከሚጠቡ ልጅዎች ጋር ልጅዎ ጊዜ እንዲያሳልፍ ማድረግ ይህም እኩያቸውን በማየት እንዲጠቡ ያበረታታቸዋል። 

የልጅዎ ጡት አለመጥባት አድማ መች ሊያስጨንቆ ይገባል?

     ብዙውን ጊዜ የልጅዎች ጡት አለመጥባት አድማ ከጥቂት ቀናት እስከ አንድ ሳምንት ላሉት ጊዜያት ሊቆይ ይችላል። ነገር ግን ልጅዎን ጡት ለማጥባት ሆነ በጥጦ ወይም በኩባያ ለመመገብ ምንም ያህል ጥረት ቢያደርጉም ፈቃደኛ ካልሆነ እና ክብደት እየቀነሰ የሚመጣ ከሆነ ፣ እንደወትሮ ሽንት የማይሸና ወይም ካካ የማይል ከሆነ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ጡት አለመጥባቱ የሚያሳስቦት ከሆነ የህፃናት ስፔሻሊት ሐኪሞችን ማማከር ይኖርቦታል ። 

 

  • እዚህ ላይ ማስተዋል ያለቦት ነገር ልጅዎ ጡት አልወስድም ቢል እንኳን በጥጦ ወይም በኩባያ በአግባቡ የሚመገብ ከሆነ እና ጤናማ እና ደስተኛ ከሆነ የጡት አለመጥባት አድማው ጤናው ላይ ምንም አይነት አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሌለው የሚያሳስብ ሁኔታ አለመሆኑን ነው።                  

           

Comments (0)