ጆሮ ደግፍ (Mumps)

Elsabet Azezew
Aug 4, 2025
undefined

                                       ጆሮ ደግፍ (Mumps)    

                 የጆሮ ደግፍ በሽታ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው በምራቅ ፣ በአፍንጫ ፈሳሽ እና በቅርብ ግንኙነት በሚተላለፍ  ቫይረስ የሚመጣ እጅግ በጣም ተላላፊ በሽታ ነው። ይህም በዋነኝነት ፓሮቲድ የተባለውን ከጆሮዎቻችን ፊት ለፊት የሚገኝ የምራቅ እጢ የሚያጠቃ ሲሆን የዚህ እጢ እብጠትን ያስከትላል። 

 

            የጆሮ ደግፍ በሽታ በአለም ዙሪያ የሚከሰት በሽታ ሲሆን ምንም እንኳን አልፎ አልፎ እንደ ወረርሽኝ በዓመት ውስጥ በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት የሚችል ቢሆንም በዋነኝነት ግን ከክረምት መጨረሻ እስከ ፀደይ መጀመሪያ ድረስ ባሉት ጊዜያት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ይታያል። አብዛኛውን ጊዜ በትምህርት ቤት ዕድሜ ላይ ባሉ ልጆች እና በኮሌጅ ዕድሜ ላይ ባሉ ወጣቶች ላይ ይከሰታል። ዕድሜአቸው ከአንድ አመት በታች በሆኑ ህፃናት ላይ ግን እምብዛም የማይታይ ሲሆን ይህም የሚሆንበት ምክንያት ከእናታቸው በሚያገኙት ፀረ እንግዳ አካላት ጥበቃ አማካኝነት ነው።  

 

             የጆሮ ደግፍ በሽታ ምልክቶች ምን ምንድን ናቸው? 

            የጆሮ ደግፍ በሽታ ምልክቶች አብዛኛውን ጊዜ ለቫይረሱ ከተጋለጥን ከ 16 እስከ 18 ቀናት ባሉት ጊዜያት ውስጥ መታየት የሚጀምሩ ሲሆኑ ብዙውን ጊዜ እንደ ትኩሳት ፣ ራስ ምታት ፣ የጡንቻ ህመም ፣ ድካም እና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ባሉ ለጥቂት ቀንናት በሚቆዩ ምልክቶች ይጀምራል። እነዚህን ምልክቶች ተከትሎም በ 48 ሰአታት ውስጥ የፓሮቲድ ምራቅ እጢ ማበጥን ያስከትላል ።

           የፓሮቲድ ምራቅ እጢ እብጠት እድሜአቸው ከ 2 እስከ 9 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ህፃናት ላይ ብዙውን ጊዜ የሚታይ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የምራቅ እጢ እብጠት ከመፈጠሩ  በፊት የፓሮቲድ የምራቅ እጢ ህመም ይኖራል። ከእዚህም ጋር ተያይዞ አልፎ አልፎ የጆሮ ህመምም ሊኖር ይችላል። የፓሮቲድ ምራቅ እጢ እብጠት በአንድ ወይም በሁለት ጆሮአችን በኩል ሊሆን የሚችል ሲሆን እብጠቱ እስከ 10 ቀናትም ሊቆይ ይችላል ።

 

                        የጆሮ ደግፍ በሽታ ህክምና

           የጆሮ ደግፍ በሽታ በቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ በሽታ በመሆኑ ለፀረ ባክተሪያ(አንቲባዮቲችስ) ሆነ ለሌሎች መድሃኒቶች ምላሽ አይሰጥም። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ያለምንም ህክምና በራሱ ጊዜ ሙሉ በሙሉ የሚድን በሽታ ነው። በበሽታውም ወቅት የሚከተሉትን በቤት ውስጥ በማድረግ ምልክቶችን ማስታገስ እንችላለን 

 

  • በቂ እረፍት ማድረግ 
  • ትኩሳትን ለመቀነስ እንደ ፓራስታሞል እና አይቦፕሮፌን ያሉ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን መውሰድ 
  • የምራቅ እጢዎችን እብጠት ለመቀነስ እብጠቱ ላይ በረዶ መያዝ
  • በትኩሳት ምክንያት የሚመጣን የሰውነት ድርቀት ለመከላከል በቂ ውሃ መጠጣት 
  • ጠንከር ያሉ ምግቦችን በምንመገብበት ጊዜ የእብጠቱን ህመም ሊቀሰቅስብን ስለሚችል እንደ ሾርባ ፣ እርጎ እና ሌሎች ለስለስ ያሉ ለማኘክ የማይከብዱ ምግቦች በመመገብ 
  • በምራቅ እጢያችን ላይ የበለጠ ህመም ሊያስከትሉ የሚችሉ አሲዳማ ምግቦች እና መጠጦችን ከአመጋገብ ማስወገድ
  • በቫይረሱ ከተያዝን ጊዜ ጀምሮ የፓሮቲድ እጢዎቻችን እስከሚያብጡ ድረስ ቫይረሱን ወደ ሌሎች ሰዎች የማስተላለፍ እድላችን ከፍተኛ በመሆኑ በእነዚህ ቀናት ውስጥ  እራሳችንን ማግለል ተገቢም ነው።  

ከጆሮ ደግፍ ጋር ተዛምደው የሚመጡ የጎንዮሽ ጉዳቶች ምን ምንድን ናቸው?

           ከጆሮ ደግፍ በሽታ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንብዛም የሚታዩ ባይሆኑም ካልታከሙ ግን ለከባድ ችግር ሊያደርሱ ይችላሉ። ጆሮ ደግፍ በሽታ በዋነኝነት የፓሮቲድ ምራቅ እጢን የሚጎዳ ቢሆንም አእምሮ እና መራቢያ አካላትን ጨምሮ ሌሎች የሰውነት ክፍሎችን ሊያጠቃም ይችላል።ጆሮ ደግፍ በሽታ ከሚያስከትለው የጎንዮሽ ጉዳቶች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው

 

  • የወንድ ልጅ የዘር ፍሬ ብግነት 
  • የእንቁልጢ ብግነት ፤ ይህ የሴቷን እንቁላል አይጎዳውም ይሁን እንጂ አንዲት ሴት በእርግዝና ወቅት በጆሮ ደግፍ በሽታ ከተያዘች የፅንስ መጨናገፍ የሚያጋጥምበት እድል ከፍተኛ ነው   
  • ማጅራት ገትር በሽታ እና የአንጎል ብግነት
  • የቆሽት ብግነት 
  • ቋሚ የመስማት ችግር ፤ ይህም ከ10,000 ሰዎች 5 ሰዎች ላይ የሚፈጠር ሁኔታ ሲሆን ቫይረሱ ጆሮ ውስጥ ካሉት መዋቅሮች ውስጥ አንዱ የሆነውን ኮክልያ በማጥቃት የመስማት ችሎታን ይጎዳል። 

ጆሮ ደግፍ በሽታን በክትባት መከላከል የሚቻል ሲሆን በአንዳንድ ሃገራት በመደበኛነት ከ ኩፍኝ ክትባት ጋር አብሮ ከ12 እስከ 15 ወራት ባሉት የህይወት ጊዜያት ውስጥ ለህፃናት ይሰጣል። ይሁን እንጂ በሃገራችን በኢትዮጵያ ክትባቱ እስካሁን አይሰጥም።                                           

Comments (0)