የወንድ ልጅ ግርዛት ምንድን ነው?
የወንድ ልጅ ግርዛት ማለት የወንድ ልጅ ብልት ሸለፈት ( የቆዳ ጫፍ) በቀዶ ህክምና ማስወገድ ማልት ነው።
የወንድ ልጅ ግርዛት ጥቅሞች
የወንድ ልጅ ግርዛት ከበርካታ የጤና ጥቅሞች ጋር ይያያዛል። ከነዚህም መካከል፡
- በሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን (UTI) የመጠቃት እድልን ይቀንሳል
- በአባላዘር እና በኤች. አይ. ቪ ቫይረስ የመጠቃት እድልን ይቀንሳል
- በወንድ ብልት ካንሰር የመያዝ እድልን ይቀንሳል
- ከብልት ላይ የሚነሱ የቆዳ በሽታዎች ይከላከላል
- በሴት ባልደረባቸው ላይ ሊከሰት የሚችለውን የማህጸን በር ጫፍ ካንሰርን ይቀንሳል
- ንጽህናን ይጨምራል
የወንድ ልጅ ግርዛት ጉዳት አለው?
የወንድ ልጅ ግርዛት ቀዶ ጥገና ህክምና እንደ መሆኑ መጠን እንደ ማንኛውም የቀዶ ጥገና ሂደት የተወሰነ አደጋ አለው። ከግርዛት የሚመጡ ችግሮች እምብዛም አይከሰቱም፣ ከከሰቱም ብዙውን ጊዜ ቀላል ናቸው። ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች የሚከተሉት ናቸው፡
- ደም መፍሰስ
- ኢንፌክሽን ወይም ጠባሳ መፈጠርን
- ከመጠን በላይ የሆነ ሸለፈት መወገድ ወይም ደግሞ በቂ ያልሆነ ሸለፈት ሳይወገድ መቅረት
- የብልት ቆዳ መቆጣት እና ህመም (በተለይ ከዳይፐር ጋር ሲነካካ)
ነገር ግን እነዚህ ችግሮች ጥሩ ስልጠና ባለው ሃኪም እና በህክምና ተቋም ውስጥ ከተደረጉ የመከሰት እድላቸው አነስተኛ ነው።
አንድ ህጻን ልጅ መቼ መገረዝ አልበት?
አብዛኛዎቹ ግርዛቶች የሚደረጉት ህጻኑ ከተወለደ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ 10 ቀናት ነው። ነገር ግን ያለጊዜያቸው የተወለዱ ሕፃናት ወይም ልዩ የሕክምና ችግሮች ያለባቸው ሕፃናት እስኪገረዙ ድረስ ተጨማሪ ጊዜ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።
ከግርዛት በኋላ ምን ማድረግ አለብን?
ከግርዛት በኋላ ቁስሉ ቫዝሊን በነካ ፋሻ ከላይ እንዳለው ምስል ይጠቀለላል። ከ24- 48 ሰዓት በኋላ ይህ ፋሻ ይፈታል። ቁስሉ እስኪድን 7 እስከ 10 ቅን ይፈጅበታል፤ በዚህም ጊዜ በደንብ መንከባከብ ያስፈልጋል። ከነዚህም እንክብካቤዎች መካከል፡
- በቀን አንዴ አካባቢውን በንፁህ ውሃ ማጽዳት
- ቁስሉ ከዳይፐር ጋር እንዳይጣበቅ ዳይፐር በቀየሩ ቁጥር ቫዝሊን (petroleum jelly) መቀባት
- ዳይፐር እንደቆሸሸ ቶሎ መቀየር
ቁስሉ አካባቢ ሊቀላ፣ ሊያብጥ፣ እና ትንሽ ቢጫ ፈሳሽ ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን የሚከተሉት ምልክቶች ካዩ ወደ ጤና ተቋም ይሂዱ
- ደም ያለማቆም የሚፈስ ከሆነ
- ግርዛቱ አካባቢ ያለው መቅላትና እብጠት በ48 ሰዓታት ውስጥ መቀነስ ካልጀመረ።
- ልጅዎ ትኩሳት ካለው
- ልጅዎ በጣም የታመመ ከመሰለ
- ልጅዎ ከቀዶ ህክምናው በኋላ በ12 ሰዓታት ውስጥ ሽንት ካልሸና
- ከቁስሉ ላይ አረንጓዴ ወይም መጥፎ ሽታ ያለው ፈሳሽ ከወጣ



