ከካርዲዮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና ክብደት ከማንሳት የቱ ይሻላል?
በስፖርቱ አለም ዉስጥ በካርዲዮ እና በክብደት ማንሳት መካከል ያለው ክርክር ለብዙ አሥርተ ዓመታት ቀናተኛ ተሟጋቾችን ይዞ ቀጥሏል። የእነዚህን ሁለት አይነት ልምምዶች ልዩነቶች፣ ጥቅሞች እና ምርጥ ውህደት መረዳት የአካል ብቃት ጉዞዎን በእጅጉ ይጠቅማል። ስለ ስፖርት እንቅስቃሴዎ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲያደርጉ ለማገዝ የካርዲዮ እና ክብደት ማንሳት ባህሪያትን፣ ጥቅሞችን እና ልዩነትን እንመርምር።
የካርዲዮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ
የካርዲዮቫስኩላር እንቅስቃሴ በተለምዶ ካርዲዮ በመባል ሲታወቅ፣ የልብ ምትዎን የሚጨምሩ እና የልብና የደም ዝውውር ሥርዓትን ውጤታማነት የሚያሻሽሉ እንቅስቃሴዎችን ያካትታሉ። እነዚህ ልምምዶች በዋናነት የልብ ምትዎን ረዘም ላለ ጊዜ ከፍ በማድረግ እና ጽናትን በማጎልበት አጠቃላይ የልብ ጤናን ይጠብቃሉ።
የካርዲዮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ምሳሌዎች
ታዋቂ የካርዲዮ ልምምዶች ሩጫ፣ ብስክሌት መንዳት፣ ዋና፣ ፈጣን የእግር ጉዞ፣ ዳንስ እና የኤሮቢክ ትምህርቶችን ያካትታሉ። እነዚህ እንቅስቃሴዎች የልብ ምትዎን ወደ መካከለኛ እና ወደ ከፍተኛ ጥንካሬ ከፍ ለማድረግ በማሰብ ትላልቅ የጡንቻ ቡድኖችን እና ሙሉ ሰውነትን ያሳትፋሉ።
የካርዲዮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጥቅሞች
- ልብንና ሳንባን በማጠናከር የልብና የደም ዝውውር ጤናን ያሻሽላል
- ጽናትን እና ብርታትን ያሳድጋል
- ካሎሪ በማቃጠል ክብደትን ለመቀነስ ይረዳል
- ጭንቀትን ይቀንሳል
- የእንቅልፍ ጥራትን ያሻሽላል
የወሲብ ግንኙነት አቅምን ያሻሽላል
ክብደት ማንሳት
ክብደት ማንሳት ወይም የመቋቋም ስልጠና ጥንካሬን እና ጡንቻን ለመገንባት ክብደት ማንቀሳቀስን ወይም የክብደት እንቅስቃሴ ተቃውሞ መጠቀምን ያካትታል። ይህ ዓይነቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጡንቻ መኮማተር ላይ ተቃውሞ ለመፍጠር በተለምዶ ነፃ ክብደቶችን፣ የክብደት ማሽኖችን፣ የመከላከያ ባንዶችን ወይም የሰውነት ክብደትን ይጠቀማል።
የክብደት ማንሳት እንቅስቃሴ ምሳሌዎች
የክብደት ማንሳት ልምምድ ምሳሌዎች ክብደት ተሸክሞ ወይም በሰውነት ብቻ ቁጢጥ ማለት፣ ፑሽ አፕ፣ሲት አፕ፣ በጀርባ ተኝቶ ክብደት ወደላይ መግፋት(Bench press)፣ ክብደት ተሸክሞ እጅን ማጠፍ እና የመሳሰሉትን ያካትታሉ ። እነዚህ ልምምዶች የተወሰኑ የጡንቻ ቡድኖችን ያነጣጠሩ እና የጡንቻን እድገት እና የጥንካሬ እድገትን ለማነቃቃት
የክብደት ማንሳት ጥቅሞች
- የጡንቻን መጠንን ለመጨመር
- የተግባር ጥንካሬ ( Functional Strength ) ለመጨመር
- የአጥንት ጥንካሬን ለማሻሻል
- መገጣጠሚያዎችን ለማጠናከር እና መተጣጠፍን ለማጎልበት
- ሜታቦሊዝምን ከፍ ለማድረግ
- ደካማ የሰውነት ክፍልን ለማጎልበት
- ለተስተካከለ አቁዋም እና
- ለአጠቃላይ የአካል ብቃት አስተዋፅኦ በማድረግ የዕለት ተዕለት ስራዎችን ቀላል ያደርጋል
የትኛው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የተሻለ ነው?
ካርዲዮ ወይም ክብደት ማንሳት የላቀ ነው የሚለው ጥያቄ በግለሰቡ የአካል ብቃት ግብ ላይ የተመሰረተ ነው። የካርዲዮ ልምምዶች የልብና የደም ቧንቧ ጤናን ፣ ጽናትን እና ካሎሪ ማቃጠልን በማሻሻል ክብደታቸውን ለመቀነስ ወይም የኤሮቢክ አቅምን ለማዳበር ለሚፈልጉ ተስማሚ ያደርጋቸዋል። በሌላ በኩል፣ ክብደት ማንሳት የጡንቻዎች መጠንን ለማሳደግ፣ ጥንካሬን ለመጨመር፣ የሰውነት አቁዋምን ለማስተካከል እና ሜታቦሊዝምን ለማስተካከል ለሚፈልጉ ተወዳዳሪ የለውም።
ካርዲዮ እና የክብደት ማንሳትን እንዴት በአንድ ላይ ማካተት ይቻላል
አጠቃላይ የጤና ጥቅሞችን ለማግኘት ብዙውን ጊዜ ካርዲዮ እና ክብደት ማንሳትን አጣምሮ መስራት ተመራጭ ነው። ሁለቱንም አይነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማካተት በብዙ መንገዶች ሊሳካ ይችላል፣ ለምሳሌ እያንዳንዱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በበቂ ሁኔታ መሰራቱን ለማረጋገጥ የካርዲዮ እና የክብደት ቀናትን በፕሮግራም በመቀያየር መስራት፣ በአንድ ቀን ለእያንዳንዳቸው የተወሰኑ ክፍለ ጊዜዎችን መወሰን፣ እንደ ክሮስ ፊት ያሉ ጥምር ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የካርዲዮ እና የጥንካሬ ስልጠናን ወደ አንድ ክፍለ ጊዜ በማዋሃድ መስራት ይቻላል። ለምሳሌ አሁን ከተጠቀሱት ወስጥ በሳምንታዊ መርሃ ግብር የተለያዩ የጡንቻ ቡድኖች ላይ የሚያተኩር የሶስት ቀናት ክብደት ማንሳት፣ ከሁለት እስከ ሶስት ቀናት እንደ ሩጫ፣ ዋና ወይም ብስክሌት መንዳት ያሉ እንቅስቃሴዎች መስራት እና ለማገገም ከአንድ እስከ ሁለት ቀን እረፍት ማረግ ሊጠቀስ ይችላል። ይህ አካሄድ የልብና የደም ሥር (cardiovascular) ጤናን, የጡንቻን እድገትን እና አጠቃላይ ደህንነትን የሚያበረታታ የተሟላ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ያረጋግጣል ።
በመጨረሻም ለማጠቃለል ምርጡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከግለዊ ግቦችዎ፣ ምርጫዎችዎ እና አጠቃላይ የጤና ሁኔታዎ ጋር የሚስማማ ነው። ለአጠቃላይ የአካል ብቃት እና ክብደት አስተዳደር ሁለቱንም የካርዲዮ እና የክብደት ማንሳትን የሚያካትት ሚዛናዊ አሰራር ተስማሚ ነው። ለፍላጎትዎ ተስማሚ የሆነ ፕሮግራም ለማዘጋጀት እና ጉዳትን ለመከላከል ተገቢውን እቅጽ እና ቴክኒኮችን ለማረጋገጥ ከአካል ብቃት ባለሙያ ጋር በመመካከር ጤናማ ህይወቶን ይጀምሩ።




