ሄፕታይተስ ኤ በሚባል ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ የጉበት በሽታ ነው፡፡ ቫይረሱ በዋነኛነት በበሽታው በተጠቃ ሰው ሰገራ እና ደም ውስጥ ይገኛል፡፡ ማንኛውም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሰገራ ጋር ንክኪ ያለው ነገር ወደ አፍ ከገባ በሽታው ይተላለፋል። ለዚህም ነው ዋነኛው የመተላለፊያ መንገዱ የተበከለ ምግብ መመገብ እና የተበከለ ውሃ መጠጣት የሆነው።
ምልክቶችስ?
ምንም እንኳን በብዛት በበሽታው የሚጠቁት ሕፃናት ቢሆኑም ብዙውን ጊዜ ምልክቶችን አያሳዩም፡፡ በአንፃሩ በዐዋቂዎች ላይ ከባድ ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል። በአጠቃላይ ግን ቫይረሱ ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ ምልክቶችን እስከሚያሳይ ድረስ ያለው ጊዜ ከ14-28 ባሉት ቀናት ውስጥ ነው፡፡
የ ሄፓታይተስ ኤ በሽታ ምልክቶች ከቀላል እስከ ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ቀላል የሚባሉት ምልክቶች የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ።
- የድካም ስሜት
- ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ
- የምግብ ፍላጎት መቀነስ
- ትኩሳት
- የሆድ ሕመም (የላይኛው ሆድ ክፍል በስተቀኝ በኩል)
ከባድ የሚባሉት ምልክቶች ደግሞ
- የዐይን እና የቆዳ ቀለም ወደ ቢጫነት መቀየር
- የጠቆረ ሽንት መሽናት
- ሰውነትን ማሳከክ
- አልፎ አልፎ ለሞት ሊዳርግ የሚችል የጉበት ጉዳት ያስከትላል፡፡ በአጠቃላይ በበሽታው ከተያዙ 1000 ሕፃናት ውስጥ አንዱ ይሞታል።
አብዛኛውን ጊዜ ምልክቶቹ የሚቆዩት ከ 2 ወራት ለአነሰ ጊዜ ቢሆንም፤ ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆኑ ሕመምተኞች ላይ 6 ወርና ከዚያ በላይ ሊቆዩ ይችላሉ።




