የጥርስ ሕመም

Biruh Tesfaye
Sep 16, 2026
severe tooth ache northmead

የጥርስ ሕመም ማለት በጥርስ ውስጥ ወይም በጥርስ አካባቢ የሚሰማ ህመም ነው። የጥርስ ሕመም የሚከሰተው በጥርስ ሥር ያለው ወይም ጥርሱን የሚከብበው ነርቭ ሲቆጣ ነው።

የጥርስ ሕመም ሊከሰት የሚችልባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ። የጥርስ ወይም የድድ ኢንፌክሽን፣ የጥርስ መበስበስ፣ የጥርስ ላይ የሚድርስ ጉዳት፣ ጥርስ መውለቅ ወይም ለከፍተኛ ሙቀት ወይም ቅዝቃዜ መጋለጥ የጥርስ ሕመም በጣም የተለመዱ ምክንያቶች ናቸው። ጥርስ ከተነቀለ በኋላም ሕመም ሊከሰት ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ሕመም ከሌላ የሰውነት ክፍል ተነስቶ ወደ መንጋጋ ሊሰራጭ ስለሚችል የጥርስ ሕመም ሊመስል ይችላል። በተለምዶ ሕመም ሊመነጭባቸው የሚችሉት ቦታዎች የመንጋጋ መገጣጠሚያ፣ ጆሮ፣ የሳይነስ ክፍሎች እና አልፎ አልፎም የልብ ችግሮች ናቸው።

የጥርስ ሕመም ሊያስከትሉ የሚችሉ ሌሎች ምክንያቶች፦

  • በጥርሶች መካከል ምግብ መቀርቀር
  • በጥርስ ሥር ወይም በድድ ላይ እብጠት ወይም ኢንፌክሽን መከሰት
  • ጥርስን ማፋጨት
  • ጥርስ በድንገት መሰንጠቅ ወይም መሰበር
  • በጊዜ ሂደት የጥርስ ሙሌት (Filling) መሰባበር
  • ጥርሶች በድድ ውስጥ መውጣት መጀመር፣ ለምሳሌ በልጆች ጥርስ በሚወጣበት ጊዜ።
  • የመንጋጋ ጥርሶች (Wisdom teeth) በበቂ ቦታ እጥረት ምክንያት በድድ ውስጥ በመደበኛ ሁኔታ መውጣት ወይም ማደግ አለመቻል (Impacted wisdom tooth)
  • ከጥርስ ማስተካከያ መሣሪያዎ (Braces) ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖር

የጥርስ ሕመምዎ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ በትክክል ማወቅ አይቻልም። ይህ የሚወሰነው ሕመሙን በሚያስከትለው ዋና ምክንያት ላይ ነው። ለምሳሌ፣ ጊዜያዊ የድድ መቆጣት ካለ፣ ብዙውን ጊዜ በአንድ ወይም በሁለት ቀናት ውስጥ በራሱ ሊሻሻል ይችላል። ነገር ግን የጥርስ መቦርቦር (Cavity) ወይም በጥርስ ሥር የሚፈጠር መግል የይዘ ኢንፌክሽን (Abscess) ካለ፣ ሕመሙ አንዳንድ ጊዜ ሊቀንስና እንደገና ሊመለስ ቢችልም፣ ሙሉ በሙሉ በራሱ አይጠፋም።

የጥርስ ሕመም ምልክቶች

በመጀመሪያ የጥርስ ሕመም ቀላል ወይም ዝቅተኛ ሊሆን ቢችልም፣ እብጠት እየጨመረ ሲሄድ ሕመሙም ሊባባስ ይችላል። የጥርስ ሕመም ከጥርስ ወይም ከመንጋጋ አልፎ ወደ ጉንጭ ሊሰራጭ ይችላል።

ሌሎች ከጥርስ ሕመም ጋር የተያያዙ ምልክቶች፦

  • ምግብ ሲያኝኩ በጥርስ ወይም በመንጋጋ ላይ ሕመም መሰማት
  • ራስ ምታት
  • ሞቃት ወይም ቀዝቃዛ ነገር ጥርሱን ሲነካው ለጥቂት ሰከንዶች ሕመም ሊሰማ ይችላል። ጣፋጭ ወይም አሲዳማ ምግቦችም ምቾት ሊነሱ ይችላሉ።
  • በጥርስ ዙሪያ ወይም በድድ ላይ ደም መፍሰስ ወይም ፈሳሽ/መግል መውጣት
  • በጥርስ ዙሪያ ወይም በመንጋጋ ላይ እብጠት መኖር
  • በጥርስ ወይም በአፍ አካባቢ ጉዳት መድረስ
  • መጥፎ የአፍ ጠረን መኖር
  • ትኩሳት
  • በአፍ ውስጥ መጥፎ ጣዕም መሰማት
  • የአንገት ወይም የመንጋጋ ፍርንትት እጢዎች (Lymph glands) ማበጥ
  • ወደ ጉንጭ፣ ጆሮ ወይም መንጋጋ ሊሰራጭ የሚችል ህመም

እነዚህ ምልክቶች አንዳንድ ጊዜ ከጥርስ መበስበስ፣ ከጥርስ መሰንጠቅ ወይም ከድድ በሽታ ጋር ሊያያዙ ይችላሉ። የጥርስ መበስበስ ወይም በድድ አካባቢ የሚታይ መቅላት የሕመሙን ምንጭ ሊያመለክት ይችላል። የተበከለውን ጥርስ በቀስታ ሲነኩት ሕመሙ የበለጠ ሊጨምር ይችላል። ይህም ጥርሱ ከውጭ ሲታይ መደበኛ ቢመስልም ችግር ያለበትን ጥርስ ለመለየት ሊረዳ ይችላል።

ለጥርስ ሕመም መቼ የሕክምና እርዳታ መፈለግ አለብዎት?

ጥርስዎ ሲያምዎ ወደ የጥርስ ሐኪም መሄድን አያዘግዩ። የጥርስ ቀዳዳዎችና ስንጥቆች በጊዜ ሂደት እየባሱ ሊሄዱ ይችላሉ። ከሚከተሉት ሁኔታዎች አንዱ ካለ ጥርስ ሐኪምዎን ያማክሩ፦

  • ያለ ሐኪም ትእዛዝ የሚገኝ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒት ሕመሙን ካላስታገሰው።
  • የጥርስ ሕመም ከ1–2 ቀናት በላይ ከቆየ እንዲሁም አፍዎን በሰፊው ሲከፍቱ ሕመም ከተሰማዎት 
  • ጥርስ ከተነቀለ በኋላ ከባድ ሕመም ካለ። ይህ በጥርስ ከተነቀለ ከ2ኛ ወይም 3ኛ ቀን በኋላ ሊከሰት ይችላል። ይህም የደም መርጋት (Blood clot) በመውጣቱ የጥርሱ አጥንት ለአየር እንዲጋለጥ ስለሚያደርግ ነው። ይህ ከተከሰተ በ24 ሰዓት ውስጥ የጥርስ ሐኪም ማየት አለብዎት።
  • ሕመሙ ከድድ ወይም ከፊት እብጠት ጋር ከተያያዘ፣ ወይም በጥርስ ዙሪያ ፈሳሽ/መግል ካለ። እነዚህ ምልክቶች በጥርስ፣ በድድ ወይም በመንጋጋ አጥንት ዙሪያ ኢንፌክሽን መኖሩን ሊያመለክቱ ይችላሉ። በጥርስ ውስጥ መግል መያዝ(Dental abscess) ካለ ጸረ ባክቴሪያ መድኃኒት እና መግልን በመክፈት ማስወጣት (Drainage) ሊያስፈልግ ይችላል። 
  • በጉዳት ምክንያት ጥርስ ከተሰበረ ወይም ከቦታው ከተነቀለ። ይህ ከተፈጠረ በተቻለ ፍጥነት የጥርስ ሐኪምን ያነጋግሩ። በልጆች የወተት ጥርሶች ሲጎዱ የሚደረገው ሕክምና ከትልልቅ ልጆችና አዋቂዎች ቋሚ ጥርስ ጉዳት የተለየ ነው። የልጅ ቋሚ ጥርስ ሙሉ በሙሉ ከወለቀ፣ በቀስታ በንጹህ ውሃ ይጠቡትና በተቻለ ፍጥነት ወደ ቦታው ለመመለስ ይሞክሩ፤ ከዚያም ወዲያውኑ የጥርስ ሐኪም ያማክሩ። ወደ ቦታው መመለስ ካልቻሉ፣ በትንሽ መጠን ወተት ውስጥ ወይም በንጹህ ውሃ ውስጥ አስቀምጠው ወዲያውኑ የጥርስ ሐኪም ያግኙ።
  • የመጨረሻው መንጋጋ ጥርስ (Wisdom tooth) ሕመም ካስከተለ። የመጨረሻው መንጋጋ ጥርስ በአፍ ውስጥ መውጣት ሲጀምር በሚታየው የጥርሱ ክፍል ዙሪያ ያለው ድድ ሊቆጣና ሊያብጥ ይችላል። በብዛት የሚጎዳው የታችኛው የመጨረሻው መንጋጋ ጥርስ ሲሆን ሕመሙ ወደ መንጋጋና ጆሮ ሊሰራጭ ይችላል። አካባቢው ሊያብጥ ስለሚችል አፍን በትክክል መዝጋትም ሊከብድ ይችላል። በከባድ ሁኔታ በጉሮሮና በአፍ ወለል ላይ የሚሰማ ሕመም መዋጥን ሊያስቸግር ይችላል።
  • ከፍተኛ ትኩሳት ወይም ብርድ ብርድ ማለት ካለ። ይህ ከጥርስ የተነሳ ኢንፌክሽን ስርጭትን ሊያመለክት ይችላል።
  • በቅርቡ የጭንቅላት ወይም የፊት ጉዳት አጋጥምዎት ከነበርዎት። ከጉዳቱ በኋላ ራስ ምታት፣ የማዞር ስሜት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ ወይም ሌሎች የሚያሳስቡ ምልክቶች ካሉዎት፣ ከጥርስ ጉዳቱ በተጨማሪ የበለጠ ከባድ ጉዳት ሊኖር ይችላል።
  • ማንኛውም የመንጋጋ ሕመም ከደረት ሕመም ጋር ከተከሰተ። የመንጋጋ ሕመም ብዙ ጊዜ ከጥርስ ችግር የሚመጣ ቢሆንም፣ አንዳንድ ጊዜ ከሌላ የሰውነት ክፍል የሚመነጭ የተላለፈ ሕመም ሊሆን ይችላል። በተለይ የልብ ሕመም ያለባቸው፣ የስኳር በሽታ ያለባቸው ወይም የልብ ቀዶ ሕክምና ያደረጉ ሰዎች የመንጋጋ ሕመምን ሊያጋጥማቸው ይችላል። የመንጋጋ ወይም የጥርስ ሕመም ከማዞር፣ ከላብ መብዛት ወይም ከመተንፈስ ችግር ጋር ከተከሰተ ወዲያውኑ ሐኪም ያማክሩ።
  • መዋጥ ከተቸገሩ፣ ወይም ከድድ ከፍተኛ ሕመም ወይም ደም መፍሰስ ካለ። የበሽታ መከላከያ አቅም የተዳከመ ከሆነ፣ የስኳር በሽታ ካለዎት ወይም ስቴሮይድ (Steroid) መድኃኒት የሚጠቀሙ ከሆነ ለኢንፌክሽን የበለጠ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ። በእነዚህ ሁኔታዎች ኢንፌክሽኖች የበለጠ ከባድና ሰፊ ሊሆኑ ወይም በተለያዩ የበሽታ አምጪ ተህዋስያን ሊከሰቱ ይችላሉ። ስለዚህ የጥርስና የድድ ኢንፌክሽኖች የበለጠ ጠንካራ ሕክምና ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

ለጥርስ ሕመም የሚደረጉ ምርመራዎች እና ህክምና

የታካሚውን የሕክምና ታሪክ በዝርዝር መሰብሰብ እና የአፍና የጥርስ ምርመራ ማድረግ ብዙውን ጊዜ ትክክለኛውን ምርመራ (Diagnosis) ለማድረግ በቂ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ የጥርስና የመንጋጋ የራጅ ምስሎች ይወሰዳሉ።

የጥርስ ሕመምን ለማከም የሚረዱ በርካታ የሕክምና አማራጮች አሉ። ለእርስዎ ተገቢው የሕክምና ዘዴ የሕመሙ ሁኔታና ክብደት ላይ ይመረኮዛል። 

የጥርስ ሕመም ህክምና

  • ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒቶች (Antibiotics) እና የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች (Pain relievers) የጥርስ ሕመም ምልክቶችን ሊያስታግሱ ይችላሉ፤ ነገር ግን ውጤታቸው ጊዜያዊ ነው። አንቲባዮቲክ ከወሰዱ በኋላ ኢንፌክሽኑ ቢጠፋም፣ ዋናው የሕመሙ ምክንያት ካልታከመ ኢንፌክሽኑ እንደገና ሊመለስ ይችላል። ይሁን እንጂ የጥርስ ሐኪምዎን ለማግኘት እየጠበቁ ሳሉ፣ ሕመሙን ለመቀነስ ያለ ሐኪም ትእዛዝ የሚገዙ የሕመም ማስታገሻዎችን፣ ለምሳሌ ፓራሲታሞል እና ኢቡፕሮፌን መውሰድ ይችላሉ።
  • ጥርስ መሙላት (Dental fillings): በጥርስዎ ላይ ትንሽ የጥርስ መቦርቦር ካለ ወይም ትንሽ የጥርስ ክፍል ከተሰበረ፣ የጥርስ ሐኪምዎ ጥርስዎን ሊሞላው ይችላል። በዚህ ሂደት የተጎዳው የጥርስ ክፍል ይወገዳል፤ ከዚያም የተፈጠረው ባዶ ቦታ በጠንካራ የጥርስ መሙያ ቁሳቁስ ይሞላል።
  • የጥርስ ክዳን (Dental crowns): ትልቅ የጥርስ መቦርቦር ወይም የጥርስ ስንጥቅ ካለ፣ የጥርስ ክዳን (Dental crown) ሊያስፈልግ ይችላል። ይህ እንደ ጥርስ ቅርጽ የተሠራ “ክዳን” ሲሆን ሙሉውን ጥርስ ይሸፍናል። ጥርሱን ያጠናክራል እና ተጨማሪ ጉዳት የመድረስ እድሉን ይቀንሳል። አንዳንድ ጊዜ የጥርስ ቀዳዳው ወይም ስንጥቁ በመሙያ ለመጠገን በጣም ትልቅ፣ ነገር ግን የጥርስ ክዳን ለመጠቀም በቂ ያልሆነ ሊሆን ይችላል።በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የጥርስ ሐኪምዎ ኢንሌይ (Inlay) ወይም ኦንሌይ (Onlay) ሊመክር ይችላል። እነዚህ በጥርሱ መጠንና ቅርጽ ተመርከዘው የሚሠሩ የሴራሚክ ጥገናዎች ሲሆኑ፣ እንደ ትንሽ የእንቆቅልሽ ቁራጭ በጥርሱ ላይ ወይም ውስጥ ይገጠማሉ።
  • የጥርስ ሥር ሕክምና (Root canal therapy): ከጥርስ መቦርቦር ወይም መሰንጠቅ የሚመጡ ባክቴሪያዎች የጥርስ ውስጣዊ ለስላሳ ክፍል (Tooth pulp) ውስጥ ከገቡ፣ የጥርስ ሥር ሕክምና (Root canal) ሊያስፈልግ ይችላል። በዚህ ሂደት በጥርሱ ውስጥ ያሉ የተቆጡ ነርቮች እና የደም ሥሮች ይወገዳሉ። ከዚያም የጥርሱ ውስጣዊ ክፍሎች በጥንቃቄ ይጸዳሉ፤ በመቀጠልም የጥርስ ውስጣዊ ክፍል (pulp chamber) እና የጥርስ ሥር መስመሮች (root canals) በመሙያ ቁሳቁስ ይሞላሉ። በአብዛኛዎቹ ሁኔታዎች ጥርሱን ለመጠበቅና ለማጠናከር በተጨማሪ የጥርስ ክዳን (Crown) ሊያስፈልግ ይችላል።
  • ጥርስን ማውለቅ (Tooth extraction): አብዛኛዎቹ የጥርስ ሐኪሞች ተፈጥሯዊ ጥርስን ማዳን በሚችሉበት ጊዜ ማዳንን ይመርጣሉ። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ጥርሱን ማዳን የማይቻል ሊሆን ይችላል።ጥርስዎ በከፍተኛ ሁኔታ ከተጎዳ፣ ጥርሱን ማውለቅ ሊያስፈልግ ይችላል። በዚህ ሂደት የጥርስ ሐኪምዎ ጥርሱን ከሚገኝበት የጥርስ መቀመጫ በጥንቃቄ ያስወግዳል፤ ከዚያም የተከማቸውን ኢንፌክሽን ያጸዳል። ጥርስዎ መነቀል ካስፈለገ፣ ስለ ጥርሱ መተካት አማራጮች ከጥርስ ሐኪምዎ ጋር ይወያዩ። 
  • የድድ በሽታ ሕክምና: የጥርስ ሕመምዎ የሚከሰተው በድድ በሽታ ምክንያት ከሆነ፣ የጥርስ ሐኪምዎ ሕመሙን ለማስታገስ ዋናውን የድድ በሽታ ሊያክሙት ይችላሉ። ይህም የተከማቸ የጥርስ ቆሻሻ(plaque) እና ታርታር (tartar) ለማስወገድ ጥልቅ የጥርስ ጽዳት፣ የድድ ኢንፌክሽን ካለ አንቲባዮቲክስ፣ አንዳንድ ጊዜም ቀዶ ሕክምናን ሊያካትት ይችላል።
  • የኦርቶዶንቲክ ሕክምና: ጥርሶችዎ ጠማማ፣ ተጨናንቀው ወይም በትክክል ባለመሰለፋቸው ምክንያት ሕመም እያስከተሉ ከሆነ፣ የጥርስ ሐኪምዎ የኦርቶዶንቲክ ሕክምና (Orthodontic treatment)፣ ለምሳሌ የጥርስ ማስተካከያ ብሬስ (braces) ሊመክር ይችላል። እነዚህ ጥርሶችን ቀጥ ለማድረግ እና አነካከስን ለማስተካከል በመርዳት በአፍ ላይ የሚፈጠረውን ጫና ይቀንሳሉ።
  • የአፍ መከላከያ (Mouth guard): የጥርስ ሕመምዎ በእንቅልፍ ጊዜ ጥርስዎን በመፋጨት የሚከሰት ከሆነ፣ በሌሊት የአፍ መከላከያ መጠቀም ሕመሙን ለማስታገስ ሊረዳ ይችላል። የአፍ መከላከያ በእንቅልፍ ጊዜ በጥርሶች ላይ የሚለበስ ከፕላስቲክ ወይም ከጎማ የተሠራ መሣሪያ ሲሆን፣ ጥርሶች እርስ በርስ እንዳይፋተጉ ይከላከላል። 
  • ሌሎች የሕመሙን መንስኤዎች ማከም: ሳይነሳይተስን (Sinusitis) ካለብዎ ሐኪምዎ በአንቲባዮቲክስ ወይም የአፍንጫ መታፈንን በሚቀንሱ መድኃኒቶች (Decongestants) ሊያክም ይችላል። አልፎ አልፎ፣ የአፍንጫ መተንፈሻ መንገዶችን ለመክፈት ቀዶ ሕክምና ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል። የልብ ወይም የሳንባ በሽታዎች ካሉም ለነሱ አግባብ የሆኑ ህክምናዎች ይደረጋሉ። 

ለጥርስ ሕመም የቤት ውስጥ መፍትሄዎች አሉ?

የቤት ውስጥ መፍትሄዎች በቀላሉ ሊዘጋጁ እና የጥርስ ሕመምን ለጊዜው ሊያስታግሱ ይችላሉ። ነገር ግን የጥርስ ሕመምዎ የማይቋረጥ ከሆነ፣ ለሕክምና የጥርስ ሐኪም ማማከር ያስፈልጋል።

ቀላል ሕመም ካለብዎት፣ በቤት ውስጥ ሊሞክሯቸው የሚችሉ ጥቂት የጥርስ ሕመም መፍትሄዎች የሚከተሉት ናቸው፦

  • በጨው ውሃ መጉመጥ: ጨው ተፈጥሯዊ ፀረ-ተህዋስያን ነው። በሞቀ የጨው ውሃ መጉመጥ እብጠትን ሊቀንስ፣ በአፍ ውስጥ ያሉ ቁስሎች እንዲድኑ ሊረዳ እና የጥርስ ሕመምን ሊያስታግስ ይችላል። ½ የሻይ ማንኪያ ጨው በ8 ኦውንስ (ወደ 240 ሚሊ ሊትር) ሞቅ ባለ ውሃ ውስጥ ይቀላቅሉ። ለ30 ሰከንድ ያህል አፍዎ ውስጥ ይያዙት፣ ከዚያም ይትፉት።
  • በሃይድሮጅን ፐርኦክሳይድ መጉመጥመጥ:  በሃይድሮጅን ፐርኦክሳይድ መጉመጥመጥ የጥርስ ሕመምን እና እብጠትን ሊያስታግስ ይችላል። በተጨማሪም የሚደማ ድድ እንዲድን ሊረዳ ይችላል። ንጹህ ሃይድሮጅን ፐርኦክሳይድን በፍጹም አፍዎን ለመጉመጥ አይጠቀሙ። 3% ሃይድሮጅን ፐርኦክሳይድ እና ውሃን እኩል መጠን በመቀላቀል የአፍ መጉመጫ ይዘጋጁ። ከጉመጣችሁ በኋላ ይትፉት፣ አይዋጡት። ከተፉት በኋላ አፍዎን በንጹህ ውሃ ብዙ ጊዜ ይታጠቡ። 
  • ነጭ ሽንኩርት: ነጭ ሽንኩርት ባክቴሪያን ለመግደል እና ሕመምን ለማስታገስ ሊረዳ ይችላል። አንድ ነጭ ሽንኩርት ቀስ ብለው ማኘክ ወይም ማኘክ ሕመም ካስከተለ፣ ነጭ ሽንኩርትን በመፍጨት በጥርስዎ ላይ መቀባት ይችላሉ። 
  • በረዶ: በተጎዳው አካባቢ ላይ በረዶ መጫን የደም ሥሮች እንዲጠቡ በማድረግ ሕመምን እና ብግነትን ሊቀንስ ይችላል። የበረዶ እቃ ወይም የቀዘቀዙ አትክልቶችን በንጹህ ፎጣ ጠቅልለው፣ ከውጭ በኩል በመንጋጋዎ ላይ ለ20 ደቂቃ ያህል ይያዙት። ይህንንም በቀን ብዙ ጊዜ ይድገሙ።
  • ናና (Peppermint): ናና የማደንዘዝ ባህሪ ስላለው የጥርስ ሕመምን ሊያስታግስ ይችላል። ለናና የሚንት ጣዕምና ሽታ የሚሰጠው ሜንቶል (Menthol) ደግሞ ፀረ-ባክቴሪያ ባህሪ እንዳለው ይታወቃል። አንድ ማንኪያ የደረቁ የናና ቅጠሎችን በአንድ ኩባያ የፈላ ውሃ ውስጥ በመጨመር ለ20 ደቂቃ ያቆዩት። ከቀዘቀዘ በኋላ በአፍዎ ውስጥ ለትንሽ ደቂቃ ይያዙት፣ ከዚያም መትፋት ወይም መዋጥ ይችላል። በተጨማሪም ሕመሙ እስኪቀንስ ድረስ ትንሽ ሞቅ ያለ እና እርጥብ የናና ሻይ ከረጢት (teabag) በጥርሱ ላይ ለብዙ ደቂቃዎች መያዝ ይችላል። እንደ ጊዜያዊ መፍትሄ፣ ጥቂት የናና ዘይት (Peppermint oil) ጠብታዎች በጥጥ ላይ በማድረግ በተጎዳው ጥርስ ላይ መያዝም ሊረዳ ይችላል።
  • ጦስኝ (Thyme): በጦስኝ ዘይት ውስጥ ዋናው ንጥረ ነገር የሆነው ታይሞል (Thymol) ፀረ-ተህዋስያን እና ፀረ-ፈንገስ ባህሪያት አሉት። አንድ ጠብታ የጦስኝ ዘይትን በአንድ ብርጭቆ ውሃ ውስጥ በመጨመር በአፍ ውስጥ ይያዙ። ሌላው መንገድ ጥቂት ጠብታዎች የጦስኝ ዘይትን ከውሃ ጋር በመቀላቀል በጥጥ ላይ ማድረግ ነው፣ ከዛም ጥጡን በሚያምመው ጥርስ ላይ በቀስታ መጫን ይችላሉ።
  • የሬት ጄል (Aloe vera): በአሎቬራ ተክል ቅጠሎች ውስጥ የሚገኘው የአሎቬራ ጄል (Aloe vera gel) በተለምዶ ለቃጠሎ እና ለቀላል ቁስሎች ሕክምና ይጠቀማል። አንዳንድ ሰዎች ይህንን ጄል ድድን ለማጽዳት እና ህመምን ለማስታገስ ይጠቀማሉ። ጥናቶች እንዳሳዩት አሎቬራ ተፈጥሯዊ ፀረ-ባክቴሪያ ባህሪ ስላለው፣ የጥርስ መበስበስን የሚያስከትሉ ጀርሞችን ሊያጠፋ ይችላል። ጄሉን በአፍ ውስጥ በሚያምመው አካባቢ ላይ መቀባት የሕመም ስሜቱን ሊያስታግስ ይችላል።
  • ቅርንፉድ (Cloves): ቅርንፉድ በውስጡ ዩጂኖል (Eugenol) የተባለ እንደ ተፈጥሯዊ ማደንዘዣ የሚሠራ ኬሚካል ይዟል። ቅርንፉድ በተጨማሪም ፀረ-ብግነት እና ፀረ-ባክቴሪያ ባህሪያት ስላሉት፣ የጥርስና የድድ ኢንፌክሽኖችን ለመዋጋት ሊረዳ ይችላል። ትንሽ የጥጥ ቁራጭ በቅርንፉድ ዘይት (Clove oil) በማራስ የሚያመው ጥርስ አካባቢ ያድርጉ። የደረቀ ሙሉ ቅርንፉድም ሊረዳ ይችላል። የቅርንፉድ ዘይት እንዲወጣ አንድ ሙሉ ቅርንፉድን በቀስታ ማኘክ እና እስከ 30 ደቂቃ ድረስ በተጎዳው ጥርስ ላይ መያዝ ይችላሉ።
  • የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች: ያለ ሐኪም ትእዛዝ የሚገዙ መድኃኒቶች፣ እንደ ፓራሲታምል (Acetaminophen) እና ኢቡፕሮፌን (Ibuprofen)፣ የጥርስ ሕመምን ለጊዜው ሊያስታግሱ ይችላሉ። ነገር ግን አስፕሪን (Aspirin) ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት መስጠት የለበትም።

የጥርስ ሕመምን መከላከል እችላለሁ?

የጥርስ ሕመምን ሁልጊዜ መከላከል አይቻልም። አንዳንድ ጊዜ ከእርስዎ ቁጥጥር ውጭ በሆኑ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል። ነገር ግን የጥርስ ሕመም የመከሰት እድልዎን ለመቀነስ ልታደርጓቸው የምትችሏቸው ነገሮች አሉ፦

  • በፍሎራይድ (Fluoride) የበለፀገ የጥርስ ሳሙና እና ለስላሳ የጥርስ ብሩሽ በመጠቀም ጥርስዎን በቀን 2 እስከ 3 ጊዜ ይቦርሹ።
  • በጥርሶችዎ መካከል ያለውን ቦታ በጥርስ ማጽጃ ክር (Floss) በመጠቀም በቀን አንድ ጊዜ ያጽዱ።
  • ፀረ-ባክቴሪያ የአፍ መጉመጫ (Antibacterial mouthwash) በቀን ሁለት ጊዜ ይጠቀሙ።
  • ጣፋጭ ምግቦችን እና መጠጦችን የሚወስዱትን መጠን ይቀንሱ።
  • ለመደበኛ የጥርስ ምርመራ እና ጽዳት በየጊዜው የጥርስ ሐኪምዎን ይጎብኙ።
  • እንደ ማጨስ ያሉ የጥርስ ችግር ሊያስከትሉ ከሚችሉ ልምዶች ይቆጠቡ። 
  • በስፖርት ሲሳተፉ ጉዳትን ለመከላከል የጥርስ መከላከያ (Dental guard) ወይም የጭንቅላት መከላከያ (Headgear) ይጠቀሙ። 

     

    የጥርስ ሕመም ካለ ጥርስዎን መቦረሽ አለብዎት? የጥርስ ሕመም ቢኖርብዎትም ጥርስዎን መቦረሽዎን መቀጠል አለብዎት። በሚቦርሹበት ጊዜ ምቾት ላይሰማዎት ቢችልም፣ ጥርስዎን መቦረሽ በጥርስዎ እና በአፍዎ ውስጥ የሚከማቹ ባክቴሪያዎችን ለመቀነስ ይረዳል። ይህም የጥርስ ሕመሙ እንዳይባባስ ወይም ኢንፌክሽን እንዳይከሰት ሊረዳ ይችላል።

Comments (0)