የፓርኪንሰን በሽታ የአንጎልን የሰውነት እንቅስቃሴ የመቆጣጠር ችሎታ የሚነካ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ ሕክምናውን በአግባቡ የሚከታተሉ አብዛኛው የፓርኪንሰን በሽታ ያለባቸው ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት ሳያጋጥማቸው ለዓመታት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የፓርኪንሰን በሽታ ምልክቶችን ለመቆጣጠር እና የአንድን ሰው የኑሮ ጥራት ለማሻሻል የሚረዱ በርካታ ሕክምናዎች አሉ ፡፡
የፓርኪሰን በሽታ መንሥኤ
የፓርኪንሰን በሽታ መንሥኤ ምን እንደሆነ ሙሉ በሙሉ አይታወቅም፡፡ በአንጎል ውስጥ የተወሰኑ የነርቭ ሴሎች በመደበኛነት እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር የሚረዳ ዶፓሚን (dopamine) የተባለ ኬሚካል ይሠራሉ፡፡ ፓርኪንሰን በአለባቸው ሰዎች ላይ እነዚህ የነርቭ ሴሎች በጊዜ ዶፓሚን የማምረት አቅማቸውን ያጣሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የፓርኪንሰን ምልክቶች ቀስ በቀስ እየታዩ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከበዱ ይመጣሉ። እነዚህ የነርቭ ሴሎች በትክክል መሥራታቸውን የሚያቆሙት እንዴት ወይም ለምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡
ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆኑት የፓርኪንሰን በሽታ የአለባቸው ሰዎች ቢያንስ አንድ በዚህ በሽታ የተጠቃ የቤተሰብ አባል (ወላጅ፣ ወንድም ወይም እኅት) አላቸው፡፡ ይህም በሽታው በዘር የሚተላለፈው በጥቂቶች ላይ ብቻ መሆኑን ያሳያል፡፡
ዕድሜያቸው ከ 50 ዓመት በፊት ፓርኪንሰንስ የሚገኝባቸው ሰዎች ላይ የዘረመል ለውጦች ሚና እንደሚጫወቱ ይገመታል፡፡ የሳይንስ ሊቃውንት የፓርኪንሰን በሽታ ውስብስብ የዘረ መል እና የአከባቢ መንሥኤዎች ውሕደት ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የፓርኪንሰን በሽታ ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ የተለመደ ሲሆን፤ 1 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች የፓርኪንሰን በሽታ እንደአለባቸው ይገመታል። ከሴቶች ይልቅ ወንዶች በዚህ በሽታ የበለጠ ተጠቂ ናቸው።
የፓርኪንሰን በሽታ ምልክቶች
የፓርኪንሰን በሽታ ምልክቶች፤ ከእንቅስቃሴ ጋር የተገናኙ እና ከእንቅስቃሴ ጋር የአልተገናኙ ተብለው በሁለት ይከፈላሉ፡፡
የእንቅስቃሴ ምልክቶች - የፓርኪንሰን ዋና የእንቅስቃሴ ምልክቶች መንቀጥቀጥ (tremor)፣ የእንቅስቃሴ ፍጥነት መቀነስ (bradykinesia)፣ የጡንቻዎች ግትርነት (rigidity) እና ሚዛንን ጠብቆ መቆም ወይም መራመድ አለመቻል (postural instability) ናቸው፡፡
እነዚህ የሕመም ምልክቶች የሚጀምሩት በግራ ወይም በቀኝ ወገን ባለው የሰውነት ክፍል ነው፡፡ ምልክቶቹ እየተባባሱ ሲመጡ አንድ ሰው በእግር መሄድ፣ ማውራት እና ሌሎች መደበኛ የዕለት ተዕለት ተግባሮችን ማከናወን እየቸገረው ይሄዳል፡፡ በተለምዶ በዝግታ የሚባባስ በሽታ ቢሆንም ከአንድ ሰው ወደ ሌላው ይለያያል፡፡ የፓርኪንሰን በሽታ ምልክቶች ለረጅም ጊዜ ውጤታማ በሆነ መንገድ ሊታከሙ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ማንኛውንም አሳሳቢ ምልክቶች ባስተዋሉ ጊዜ የጤና ባለሙያ ማወያየት አስፈላጊ ነው፡፡
- መንቀጥቀጥ - በፓርኪንሰን በሽታ ሳቢያ የሚመጣ የሰውነት መንቀጥቀጥ ሕመምተኛው ከእንቅስቃሴ በኋላ ዕረፍት በሚወስድበት ሰዓት ይስተዋላል። ብዙውን ጊዜ በአንድ እጅ ላይ ይከሠታል፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ ሌላኛው ይዛመታል፡፡
ጭንቀት፣ ደስታ እና ሐዘን መንቀጥቀጡን ሊያባብሱት ይችላሉ፡፡ እግር፣ ከንፈር ፣ መንጋጋ ወይም ምላስን ጨምሮ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች በዚህ በሽታ ምክንያት መንቀጥቀጥ ሊታይባቸው ይችላል፡፡
- የእንቅስቃሴ ፍጥነት መቀነስ - ይህ አጠቃላይ የሆነ የሰውነት መንቀሳቀስ ፍጥነት መቀነስ ነው፡፡
በእጆች ላይ ሲከሠት የልብሶችን ቁልፍ መቆለፍ፣ የጫማ ማሰሪያዎችን ማሰር፣ በኮምፒተር ላይ መጻፍ፣ ሳንቲሞችን ከኪስ ወይም ከቦርሳ ማውጣት የመሳሰሉ ተግባራት ላይ እክል ሊፈጥር ይችላል።
በተጨማሪም ሕመምተኛው ሲራመድ እግሮቹን መጎተት፣ ከጎን ወደ ጎን የሆኑ አጭር እርምጃዎችን እንዲራመድ እና ሚዛንን ያለመጠበቅ ስሜት እንዲሰማው ሊያደርግ ይችላል። ይህ በሽታ ያለበት አንድ ሰው ከተቀመጠበት ወንበር ለመነሣትም ሆነ ከመኪና ለመውረድ ይቸገር ይሆናል፡፡
- የጡንቻዎች ግትርነት - የእጆች፣ የእግሮች ወይም የአካል ጡንቻዎች ግትር ማለትን ያስከትላል፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው እንደ መንቀጥቀጥ እና እንቅስቃሴ መቀነስ ያሉ ምልክቶችን በማሳየት ነው፡፡ እነዚህ የመጀመሪያ ምልክቶች የሚታዩት በተመሳሳይ የሰውነት ከፊል አካላት ላይ ነው፡፡ በሽታው እየገፋ ሲሄድ ሁለቱም የአካል ግማሽ ክፍሎች ይጠቃሉ፡፡
- ደካማ ሚዛን - ስንቆም ወይም ስንራመድ ሚዛናዊ እንድንሆን በመደበኛነት የሚረዱን በአንጎል ውስጥ ቅጽበታዊ ምላሾች አሉ። የፓርኪንሰን በሽታ በአለባቸው ሰዎች ላይ እነዚህ ምላሾች ይዳከማሉ፡፡ ይህም የመውደቅ ዝንባሌን ወይም ሚዛንን ያለመጠበቅ ስሜት ያስከትላል፡፡ ይህ ምልክት አብዛኛውን ጊዜ በሽታው እየተባባሰ ሲመጣ የሚታይ ነው።
- ሌሎች የእንቅስቃሴ እክሎች - የዐይን ክዳን መርገብገብ መቀነስ፣ ከስሜት ጋር የፊት ገጽታ አለመቀያየር፣ የንግግር እክሎች፣ የእይታ መደብዘዝ፣ ምግብ መዋጥ መቸገር፣ የጀርባ አጥንት መጉበጥ ይገኙበታል፡፡
ከእንቅስቃሴ ጋር ያልተገናኙ ምልክቶች - እነዚህ ምልክቶች የሰውን ሥነ ልቦና፣ የስሜት ሕዋሳትን (ለምሳሌ፣ ማሽተት ፣ ጣዕም፣ እይታ) እና የማሰብ ችሎታን ይነካሉ።
- የአስተሳሰብ እክሎች እና የመርሳት በሽታ - የማሰብ እና የማስታወስ ችግሮች በተለምዶ በፓርኪንሰን በሽታ ውስጥ የሚከሠቱ ሲሆን ከቀላል እስከ ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት 40 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑት ፓርኪንሰን በሽታ ያለባቸው ሰዎች በእነዚህ ችግሮች ይጠቃሉ፡፡
- የሥነ ልቦና እክሎች - ለፓርኪንሰን በሽታ መድኃኒት ከሚወስዱ ሰዎች መካከል ከ 20 እስከ 40 በመቶ የሚሆኑት ከገሃዱ ዓለም ጋር በአላቸው ግንኙነት ላይ መታወክ ያጋጥማቸዋል፡፡ ለሌሎች ሰዎች የማይታዩ በትክክል የሌሉ ነገሮች ይታያቸዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ምክንያት የሌለው የጥርጣሬ ስሜት ይኖራቸዋል።
ድብርት፣ ጭንቀት እና ተነሣሽነት ማጣት የፓርኪንሰን በሽታ ያለባቸው ሰዎች የተለመዱ የስሜት መቃወስ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች የሰውን የኑሮ ጥራት በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንሱ እና የእንቅስቃሴ ችግር ምልክቶችን ሊያባብሱ ይችላሉ፡፡
- የእንቅልፍ መዛባት - ለመተኛት መቸገር በፓርኪንሰን በሽታ በተያዙ ሰዎች ላይ በብዛት የሚታይ ችግር ነው። ይህም በአልጋ ላይ የመገላበጥ ችግር፣ የጡንቻ መኮማተር፣ ቅዠት፣ ሕመም እና ቶሎ ቶሎ የመሽናት ፍላጎት ከመኖር ጋር ተያይዞ የሚመጣ ችግር ነው፡፡ 75 በመቶ የሚሆኑ በፓርኪንሰን በሽታ የሚጠቁ ሰዎች በቀን ውስጥ ከመጠን በላይ እንቅልፍ የመተኛት ችግር አለባቸው፡፡ አልፎ አልፎም በሥራ መካከል ድንገተኛ ያልታሰበ እንቅልፍ መጣል ሊያጋጥማቸው ይችላል። ፓርኪንሰንን ለማከም የሚያገለግሉ መድኃኒቶች የቀን እንቅልፍ መተኛትን ሊባባሱ ይችላሉ፡፡
ድንገተኛ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ እንቅልፍ መውሰድ መኪና ለሚነዱ የፓርኪንሰን በሽተኞች አደገኛ ነው፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነት ምልክቶች ከአሉ የጤና ባለሙያ ማማከር እና ማከናወን የማይገባቸውን ተግባራት መለየት አስፈላጊ ነው፡፡
- የነርቭ ሥርዓት መዛባት - ዝቅተኛ የደም ግፊት፣ የሆድ ድርቀት፣ የመዋጥ ችግር፣ ከመጠን ያለፈ ላብ፣ ሽንት መቆጣጠር አለመቻል እና የወሲብ ስሜት ማጣት ችግሮችን ያስከትላል፡፡
- የማሽተት ስሜት ማጣት - አብዛኞቹ የፓርኪንሰን በሽታ የአለባቸው ሰዎች የማሽተት ችሎታቸውን ያጣሉ፡፡ ይህ ብዙውን ጊዜ በበሽታው መጀመሪያ ላይ ሌሎች የታወቁ ምልክቶች ከመከሠታቸው በፊት የሚታይ ምልክት ነው።
- ሕመም - ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት ፓርኪንሰን ያለባቸው ሰዎች ሕመም እንደሚሰማቸው ይናገራሉ፡፡ ሕመሙ ውጋት፣ ማቃጠል ወይም መደንዝዝ ሊሆን ይችላል፡፡ የሕመሙ ስሜት በአንዴ በበርካታ ቦታዎች ላይ ወይም በተወሰኑ የሰውነት ክፍሎች ላይ ብቻ ይሰማል፡፡ በአጠቃላይ የሕመም ስሜቶች ከእንቅስቃሴ ምልክቶቹ ጋር በተመሳሳይ የአካል ክፍሎች ላይ ይከሠታሉ፡፡
ለፓርኪንሰን በሽታ የሚደረግ ምርመራ
የፓርኪንሰን በሽታ ምልክቶች የነርቭ በሽታ ባለባቸው ሌሎች ሰዎች ላይ ሊከሠቱ ይችላሉ፡፡ ሕክምናው ስለሚለያይ ፓርኪንሰንን ከእነዚህ ሌሎች ሁኔታዎች መለየት አስፈላጊ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በበሽታው የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ፓርኪንሰንን በእርግጠኝነት ለማወቅ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ በአጠቃላይ የሚከተሉት ምርመራዎች ይደረጋሉ፡፡
- ከላይ ስለተጠቀሱት ምልክቶች በጥልቅ መወያየት፡፡
- ሙሉ አካላዊ ምርመራ ማድረግ፡፡
- ኤም.አር.አይ (MRI) የፓርኪንሰን በሽታ መኖሩን ለማረጋገጥ ብዙውን ጊዜ ባይረዳም፤ ሌሎች ሊኖሩ የሚችሉ የጤና እክሎችን ለመመርመር ይጠቅማል፡፡
- ለፓርኪንሰንስ በሽታ መድኃኒቶች (carbidopa-levodopa) ያለውን ምላሽ በማየት በሽታው መኖር አለመኖሩን ማወቅ ይቻላል፡፡
በፓርኪንሰን በሽታ የተጠቁ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ይጠብቃቸዋል?
ከአንድ ሰው ወደ ሌላው ስለሚለያይ የፓርኪንሰን በሽታ በአለበት ሰው ላይ ወደፊት የሚያስከትለውን ውጤት ለመተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡ አብዛኞቹ ሰዎች ሕክምናውን በአግባቡ ከተከታተሉ ለብዙ ዓመታት በጥሩ ሁኔታ መኖር ይችላሉ፡፡ ፓርኪንሰን የአለባቸው ሰዎች የአካል ጉዳተኛ እሆን ወይ? ይህ በሽታ ለሞት ይዳርገኝ ወይ? የሚለው ያሳስባቸዋል፡፡ ምንም እንኳን የፓርኪንሰን በሽታ በራሱ ለሞት የሚዳርግ ባይሆንም፤ እንደ መውደቅ፣ በምግብ መታነቅ ወይም ትንታ እና የሳንባ ምች የመሳሰሉ ከፓርኪንሰን ጋር የተያያዙ ችግሮች የመሞት ዕድልን ይጨምራሉ፡፡
ቢሆንም የበሽታው መባባስ ዘገምተኛ መሆኑን እና የሚሰጡት ሕክምናዎችም ምልክቶችን በበቂ ሁኔታ ለመቆጣጠር እንደሚያስችሉ ማስታወሱ አስፈላጊ ነው፡፡




