የፅንስ ቀዶ ጥገና
የፅንስ ቀዶ ጥገና ጽንስ ከመወለዱ በፊት አንዳንድ የአፈጣጠር ጉድለቶችን ለማከም የሚያገለግል እጅግ አስደናቂ የሕክምና ሂደት ነው። በእርግዝና ወቅት የቀዶ ጥገና ሀሳቡ አስጨናቂ ቢመስልም የቴክኖሎጂ እድገቶች እና የቀዶ ጥገና ዘዴዎች ለአንዳንድ ቤተሰቦች ህይወትን የሚቀይር አማራጭ አድርገውታል። ይህ ጽሁፍ የፅንስ ቀዶ ጥገና እንዴት እንደሚደረግ፣ ከቀዶ ጥገናው በፊት፣ በቀዶ ጥገናው ወቅት እና ከቀዶ ጥገናው በኋላ ምን እንደሚጠብቁ ለመረዳት ይረዳዎታል።
የፅንስ ቀዶ ጥገና ምንድን ነው?
የፅንስ ቀዶ ጥገና ገና በማኅፀን ውስጥ ያለ እና በማደግ ላይ ያለ ፅንስ ላይ የሚደረግ በጣም ልዩ የቀዶ ጥገና ሂደቶች ስብስብ ነው። የዚህ ቀዶ ጥገና ግብ ጽንሱ ከተወለደ በኋላ ከመጠባበቅ ይልቅ አንዳንድ ከባድ ሁኔታዎችን ቀደም ብሎ ማረም ወይም ማሻሻል ሲሆን ይህም ለህፃኑ እና ለእናቱ የተሻለ ውጤትን ያስገኛል። የፅንስ ቀዶ ጥገና ማድረግ በሚከተሉት ሁኔታዎች ጊዜ ሊታሰብ ይችላል:-
- የጽንሱን ህይወት ወይም የህይወት ጥራት አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲኖር
- የቀዶ ጥገና ቅድመ ጣልቃገብነት የጽንሱን ዘላቂ ጉዳት ወይም ተግባር ማጣትን ሲከላከላል እና
- ጽንሱ ላይ ያለው ችግር ቀዶ ጥገናው ከሚያስከትለው አደጋ ሲበልጥ
በፅንስ ቀዶ ጥገና ሊታከሙ የሚችሉ ሁኔታዎች
ሁሉም በጽንስ ላይ የሚከሰቱ ችግሮች የፅንስ ቀዶ ጥገና የሚያስፈልጋቸው አይደሉም። በፅንስ ቀዶ ጥገና ሊታከሙ ከሚችሉ የተለመዱ ሁኔታዎች መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉትን ያካትታሉ:-
- ስፓይና ባይፊዳ የተሰኘ የህብለ ሰረሰር መዘጋት ችግር
- ተፈጥሮአዊ ዲያፍራማቲክ ሄርኒያ
- ከመትያ-ወደ-መንትያ ደም መላሽ ሲንድሮም
- የሳምባ አየር ቧንቧዎች አፈጣጠር ችግር እና
- የፊኛ መውጫ መዘጋት
የፅንስ ቀዶ ጥገና ደህንነቱ የተጠበቀ እና ጠቃሚ አማራጭ መሆኑን ለመወሰን እያንዳንዱ ሁኔታ በማህጸን እና ፅንስ ሐኪሞች፣ በሕፃናት ቀዶ ጥገና ሐኪሞች እና በሌሎች ባለሙያዎች ቡድን በጥንቃቄ መገምገም ይገባዋል።
የፅንስ ቀዶ ጥገና ዓይነቶች
ሶስት ዋና ዋና የፅንስ ቀዶ ጥገና መንገዶች አሉ:-
- ክፍት የፅንስ ቀዶ ጥገና:- በፅንሱ ላይ በቀጥታ ቀዶ ጥገናን ለመስራት የእናቲቱን ሆድ እና ማህፀን መክፈትን ያካትታል።ይህ ቀዶ ጥገና የጽንሱን የአከርካሪ አጥንት ለመጠገን ብዙውን ጊዜ ያገለግላል። ይህ ቀዶ ጥገና ከተደረገ በሁዋላ የአሁኑም ሆነ የወደፊት እርግዝናዎችን በምጥ መውለድን ይከለክላል።
- ፌቶስኮፒክ የጽንስ ቀዶ ጥገና:- ይህ የጽንስ ቀዶ ጥገና ጥቃቅን ቀዳዳዎችን በእናቲቱ ሆድ እና ማህጸን በኩል በመክፈትና ወደ ውስጥ በመግባት ሲከናወን በትንንሽ መሳሪያዎች እና ካሜራ በመታገዝ ይደረጋል። ይህ ቀዶ ጥገና ከመትያ-ወደ-መንትያ ደም መላሽ ሲንድሮም፣ የሳንባ እብጠት ችግር እና የመሳሰሉት ላለባቸው እችግዝናዎች በብዛት ይደረጋል።
- በምስል የሚመራ የጽንስ ቀዶ ጥገና:- ይህ የጽንስ ቀዶ ጥገና በመርፌ ወይም በቀጫጭን ቱቦዎች በመጠቀም ሂደቶችን ለማከናወን የአልትራሳውንድ ወይም የኤምአርአይ ምስል እገዛ መጠቀምን ያካትታል።
ምን ይጠበቃል
- ከቀዶ ጥገና በፊት:- አልትራሳውንድ፣ ኤም.አር.አይ፣ የጄኔቲክ ምርመራ እና ከተለያዩ ስፔሻሊስቶች ጋር የሚደረግ ምክክር ከቀዶ ጥገናው በፊት የሚከናወኑ ሂደቶች ናቸው ። ይህ ምክክር ጥቅሞቹን፣ ጉዳቶቹን እና የረጅም ጊዜ ተጽኖዎቹን ለመረዳት ይረዳዎታል።
- በቀዶ ጥገና ወቅት:- የቀዶ ጥገናው ሂደት አጠቃላይ ወይም አካባቢያዊ ማደንዘዣን ሊጠቀም ሲችል የቀዶ ጥገና ቡድኑ እርስዎን እና ልጅዎን በሂደቱ ጊዜ ከአደጋ ለመጠበቅ የተለያዩ እርምጃዎችን ይወስዳል።
- ከቀዶ ጥገና በኋላ:- ለቅርብ ክትትል ከቀዶ ጥገናው በኋላ ሆስፒታል ውስጥ መቆየት ሊኖርብዎ ሲችል ያለጊዜው የሚጀምር ምጥን ለመከላከል የእንቅስቃሴ ገደቦች እና መድሃኒቶች ሊታዘዙልዎት ይችላሉ። ከሆስፒታል ከወጡ በኋላም የሕፃኑን እድገት ለመከታተል መደበኛ የጽንስ ክትትል አስፈላጊ ነው።
አደጋዎች
በቀዶ ጥገናው ምክንያት የሚከተሉት አደጋዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ።
- ያለጊዜው መወለድ
- ኢንፌክሽን
- የማህፀን መተርተር (ከክፍት ቀዶ ጥገና በሁዋላ)
- ከማደንዘዣ የሚመጡ ችግሮች
በአንዳንድ ሁኔታዎች የድህረ ወሊድ ህክምና የበለጠ ውጤታማ አማራጭ ሊሆን ስለሚችል እነዚህን አደጋዎች ከህክምና ቡድንዎ ጋር በጥንቃቄ ማመዛዘን በጣም አስፈላጊ ነው።
የፅንስ ቀዶ ጥገና ውስብስብ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ተስፋ የሚሰጥ ዘመናዊ የሕክምና አስደናቂ እድገት ነው። ለሁሉም የጽንስ ችግሮች ይህ ቀዶ ጥገና ተገቢ ባይሆንም ለአንዳንድ ቤተሰቦች የልጃቸውን ጤና እና የወደፊት ሁኔታን በእጅጉ ሊያሻሽል ይችላል።




