ሄሞራጂክ ፊቨር (Hemorrhagic Fever)

Elsabet Azezew
Nov 18, 2025
undefined

                                 ሄሞራጂክ ፊቨር (Hemorrhagic Fever) 

     በአሁኑ ወቅት በደቡበ ኢትዮጵያ ክልል በጅንካ ከተማ ምንነቱ በመረጋገጥ ላይ ያለ የሄሞራጂክ ፊቨር (Hemorrhagic Fever) በሽታ መከሰቱን እና እስከ አሁን 8 ሰዎች በበሽታው የተጠረጠሩ መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል። 

     የወጣው መግለጫው የተከሰተውን በሽታ " ምንነቱ በመረጋገጥ ላይ ያለ የሄሞራጂክ ፊቨር " ሲል የጠራው ሲሆን የሚከተለቱን ምልክቶች እንደሚያስከትልም ተገልጿል

  • በአፍንጫ ፣ በአፍ እና በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ደም መድማት
  • ትኩሳት
  • ማስቀመጥ እና 
  • ማስመለስ ከምልክቶቹ መካከል የተወሰኑት ናቸው። 

     የቫይረስ ሄሞራጂክ ፊቨር (Viral Hemorrhagic Fevers) ከቁጥጥር ውጪ የሆነ  የደም መፍሰስን ሊያስከትሉ የሚችሉ የቫይረስ ኢንፌክሽኖች ስብስብ ነው።

     በዚህ ቡድን ውስጥ የሚገኙት ቫይረሶች የሚያስከትሉት የበሽታ ክብደት ይለያያል። ብዙዎቹ ቀላል በሽታን ቢያስከትሉም ሁሉም ግን የደም ሥሮችን ሊጎዱ እና የደም መርጋት (clot) ችሎታን ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ። ይህም ለሕይወት አስጊ የሆኑ ችግሮችን ያስከትላል። 

            ሄሞራጂክ ፊቨር ሊያስከትሉ የሚችሉ በሽታዎች የሚከተሉት ናቸው

1)ክራይሚያ ኮንጎ ሄሞራጂክ ፊቨር (Crimean–Congo Hemorrhagic Fever )

 

     በዋናነት በሃያሎማ መዥገሮች (Hyalomma ticks) የሚተላለፍ የቫይረስ በሽታ ሲሆን እነዚህም መዥገሮች በከብት እርባታና በጎች በሚሰማሩበት አካባቢ በብዛት ይገኛሉ ። የቫይረሱ ዋና ተሸካሚዎች (reservoirs) ላሞች፣ ፍየሎች እና በጎች ሲሆኑ በሽታውንም ምንም አይነት ምልክት ሳያሳዩ በውስጣቸው ይይዛሉ። ሰዎች ይህን ቫይረስ በመዥገር ንክሻ ወይም በበሽታው ከተያዙ እንስሳት ደም ወይም ስጋ ጋር በመነካካት ነው። በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እና በአማራ ክልሎች በርካታ የቫይረሱ ወረርሽኞች ሪፖርት ተደርጓል። በሽታው በድንገት የሚከሰት ትኩሳት ፣የጡንቻ ሕመም፣ ከጨጓራና አንጀት ደም መፍሰስ፣ ቆዳ ስር የሚኖሩ ቀይ ወይም ወይንጠጅ ቀለም ያላቸው ሽፍታዎች(petechiae) እና የጉበት ጉዳት ምልክቶችን ያስከትላል።  

 

2) የሪፍት ቫሊ ትኩሳት (Rift Valley Fever)

 

     በከባድ ዝናብ እና በጎርፍ ጊዜ በብዛት የሚከሰት የቫይረስ በሽታ ነው። የቫይረሱ ዋና ተሸካሚዎች በጎች፣ ፍየሎች እና ከብቶች ሲሆኑ ወደ ሰው የሚተላለፈው ደግሞ በተበከሉ አዴስ (Aedes) ወይም ኩሌክስ (Culex) የተባሉ የወባ ትንኞች ንክሻ ወይም በበሽታው ከተያዙ እንስሳት ደም፣ ስጋ ወይም ከእንስሶቹ ከምናገኛቸው ምርቶች ጋር ንክኪ ሲኖር ነው።

    ይህ በሽታ እንደ ኬንያ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ ባሉ የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ውስጥ በርካታ ወረርሽኞችን አስከትሏል ። እንደ አፋር፣ ሶማሌ እና ደቡብ ክልል ባሉ የኢትዮጵያ ዝቅተኛ ክፍሎች (lowland areas) የመሰራጨት አደጋም ሊኖር እንደሚችል ይነገራል ። የሪፍት ቫሊ ትኩሳት የሰውነት ቢጫ መሆን ፣ትኩሳት፣ የእይታ ችግር፣ ከአፍንጫ፣ ከድድ ፣ከቆዳ ፣ በአጠቃላይ በሰውነት ውስጥ ደም መፍሰስ እና የጉበት ብግነትን ያስከትላል። 

 

3) ቢጫ ወባ (Yellow Fever)

 

     ቢጫ ወባ (Yellow Fever) በዋነኝነት አዴስ ኤጂፕቲ (Aedes aegypti) በተባለችው የወባ ትንኝ የሚተላለፍ የቫይረስ በሽታ ነው። ይህ በሽታ በኢትዮጵያ ውስጥ በተወሰኑ አካባቢዎች በብዛት የሚታይ ሲሆን በደቡብ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን ፣ በወላይታ እና በጋምቤላ ክልሎች የተረጋገጡ ወረርሽኞች ሪፖርት ተደርጓል። በሽታው አብዛኛውን ጊዜ የሚጀምረው በትኩሳት ሲሆን ከዚያም የሰውነት ቢጫ መሆንን ያስከትላል። በሽታው ከበድ ያለ ከሆነ ደግሞ የደም መፍሰስን በተለይ  'ጥቁር ትውከት(black vomit)' የሚባለውን ደም ማስታወክ ያስከትላል።  

 

4) ዴንጊ ትኩሳት (Dengue Fever) እና የዴንጊ ደም መፍሰስ ትኩሳት (Dengue Hemorrhagic Fever) 

 

    ይህ በሽታ በኢትዮጵያ በተለይም በድሬዳዋ፣ በጎዴ፣ በሶማሊ ክልል እና በአፋር ውስጥ ከ 2013 ወዲህ መታየት የጀመረ በከተማ አካባቢ በምትራባው አዴስ ኤጂፕቲ (Aedes aegypti) የወባ ትንኝ የሚተላለፍ የቫይረስ በሽታ ነው። ለሕይወት አስጊ የሆነ የደም መፍሰስን የሚያስከትለው የበሽታው አይነት የሚከሰተው ለሁለተኛ ጊዜ በበሽታው በተያዙ ሰዎች ላይ ነው። 

 

5) ላሳ ትኩሳት (Lassa Fever) 

 

    በኢትዮጵያ ውስጥ እምብዛም ያልተለመደ ነገር ግን ሊከሰት የሚችል የቫይረስ በሽታ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች በሚገኙ ማስቶሚስ (Mastomys) በተባሉ አይጦች አማካኝነት ይተላለፋል። የሚተላለፈውም የተበከሉ አይጦች ሽንት፣ ሰገራ ወይም በበሽታው ከታመመ ሰው ሰውነት ከሚወጣ ፈሳሽ ጋር ንክኪ ሲኖር ነው። የተረጋገጠ ወረርሽኝ ባይከሰትም በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ አልፎ አልፎ በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች እንደነበሩ ግን ሪፖርት ተደርገዋል።

 

6) የኢቦላ እና ማርበርግ ቫይረስ 

 

    የኢቦላ እና ማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝ እስካሁን ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ውስጥ ተከስቶ የማያውቅ ሲሆን የበሽታው የመከሰት ስጋት በዋነኛነት ከጎረቤት ሃገራት እንዳይገባ ነው። በተለይ ማርበርግ ቫይረስ በዩጋንዳ እና ኬንያ ውስጥ ተከስቷል። ሁለቱም በሽታዎች ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉት በሰውነት ፈሳሾች ንክኪ አማካኝነት ነው።

 

                     ሄሞራጂክ ፊቨር እንዴት ይመረመራሉ?

    ሐኪምዎ በሚያሳዩት ምልክቶች እና ከዚህ በፊት በሽታው ወደዳለበት ቦታ ጉዞ አድርገው ከነበረ የሄሞራጂክ ፊቨር በሽታ እንዳለብዎ ሊጠራጠሩ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም በሽታው እንዳለብዎ ለማረጋገጥ ከሰውነትዎ ፈሳሽ ናሙናዎችን በመውሰድ ይመረምራል። የሚከተሉትን ናሙናዎች በመውሰድ ምርመራ ሊያደርግሎት ይችላል 

  • የደም ምርመራ 
  • ከጉሮሮ የሚወሰድ ናሙና (Throat swab)
  • የሽንት ምርመራ እና
  • የአንጎል እና የአከርካሪ አጥንት ፈስሽ ምርመራ (Lumbar puncture / Spinal tap)

                    ሄሞራጂክ ፊቨር እንዴት ይታከማሉ?

    ለ ሄሞራጂክ ፊቨር የተለየ መድኃኒት የለውም። ነገር ግን ለጥቂት የበሽታው ዓይነቶች የፀረ-ቫይረስ ህክምናዎች አሏቸው ። አብዛኛውን ጊዜ ሐኪምዎ ምልክቶችዎን በማከም በተረጋጋ የጤና ሁኔታ ላይ እንዲሆኑ ያደርጋል ። የሚሰጥዎት ህክምና የሚከተሉትን ሊያካት ይችላሉ :- 

  • ሪባቪሪን(Ribavirin) የተባለ የፀረ-ቫይረስ መድኃኒት  
  • እንደ ኢንማዜብ (Inmazeb) እና ኢባንጋ (Ebanga) ያሉ ለኢቦላ በሽታ ህክምና የተፈቀዱ መድኃኒቶች
  • የኦክስጅን ድጋፍ ወይም በማሽን እንዲተነፍሱ (mechanical ventilation) ሊደረግ ይችላል
  • በደም ሥር የሚሰጡ ፈሳሾች (Intravenous fluids)
  • እንደ ማቅለሽለሽ እና የህመም ስሜት ያሉ ምልክቶችን ለማስታገስ የሚረዱ መድኃኒቶች ይሰጦታል። 

                  ከሄሞራጂክ ፊቨር ማገገም ይቻላል?

    ቀለል ከሆኑ የሄሞራጅክ ፊቨር ዓይነቶች ማገገም ይቻላል። ላሳ ትኩሳት፣ ዴንጊ ትኩሳት እና ቢጫ ወባ ብዙውን ጊዜ ቀላል ምልክቶችን ስለሚያስከትሉ ከእነዚህ በሽታዎች ሙሉ በሙሉ በቀላሉ ማገገም ይቻላል። ሌሎች እንደ ማርበርግ እና ኢቦላ ያሉ በሽታዎች ግን ብዙውን ጊዜ ገዳይ ናቸው።

 

             በሄሞራጂክ ፊቨር ምክንያት የሚከሰተው የሞት መጠን ምን ያህል ነው?

    የሚከሰተው የሞት መጠን እንደ ቫይረሱ አይነት ይለያያል። ለምሳሌ ማርበርግ እና ኢቦላ እጅግ ገዳይ የሆኑ የሄሞራጂክ ፊቨር በሽታ ዓይነቶች ሲሆኑ በአማካይ ከ 40 በመቶ በላይ የሚሆኑት በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ለእልፈተ ህይወት ይዳረጋሉ። ነገር ግን በላሳ ወይም በዴንጊ ትኩሳት ከተጠቁ ሰዎች መካከል የሚሞቱት 1 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። 

 

               ሄሞራጂክ ፊቨርን መከላከል ይቻላል ?

የሚከተሉትን ቅድመ ጥንቃቄዎች በማድረግ ለሄሞራጂክ ፊቨር ያሎትን የመጋለጥ እድል መቀነስ ይችላሉ 

 

  • ክትባት ይውሰዱ

            ቢጫ ወባ፣ ዴንጊ ትኩሳት እና ኢቦላ ክትባት አሏቸው።

  • ከትንኝ ንክሻዎች እራስዎን ይጠብቁ 

            የመከላከያ ልብሶችን በመልበስ፣ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር በመጠቀም እንዲሁም በትንኞችና በመዥገሮች ላይ ውጤታማ የሆኑ የፀረ ነፍሳት መከላከያ ፊኒቶችን በመጠቀም ከትንኝ ንክሻዎች እራስዎን መጠበቅ ይችላል።

  •  ሄሞራጂክ ፊቨርን ሊያስተላልፉ ከሚችሉ አይጦች፣ የሌሊት ወፎችና ሌሎች እንስሳት ጋር ንክኪ እንዳይኖርዎት ያድርጉ።
  • ከሰው ደምና የሰውነት ፈሳሾች ጋር ቀጥተኛ ንክኪን ያስወግዱ። 

 

Comments (0)