የማርበርግ ቫይረስ በሽታ
የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የተከሰተው ሄሞራጂክ ፊቨር የማርበርግ ቫይረስ በሽታ እንደሆነ አረጋግጧል። ይህም በሀገሪቱ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተከሰተ የገለፀ ሲሆን የማርበርግ ቫይረስ እንደሆነ የተረጋገጠውም በበሽታው ተጠርጥረው ከሚገኙ ሰዎች የናሙና ምርመራ ከተደረገ በኋላ ነው።
ቀደም ሲል የማርበርግ ሄሞራጂክ ፊቨር በመባል የሚታወቀው የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ማርበርግ (MARV) እና ራቭን (RAVV) በተባሉ ቫይረስዎች ይከሰታል። ይህ በሽታ ከባድ እና ብዙ ጊዜ ለሞት የሚዳርግ ሲሆን በአማካይ 50 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው ምክንያት ህይወታቸው ያልፋል። በቀደሙት ወረርሽኞችም የሟቾች መጠን ከ24 እስከ 88 በመቶ እንደሚደርስ ይነገራል።
የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ከኢቦላ ቫይረስ በሽታ ጋር በሕክምናው ረገድ ተመሳሳይነት ያላቸው ሲሆን ሁለቱም በሽታዎች አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ቢሆኑም ከፍተኛ የሞት መጠን ያላቸውን ወረርሽኞች ያስከትላሉ።
የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው በ1967 በጀርመን ማርበርግ እና ፍራንክፈርት እንዲሁም በሰርቢያ ቤልግሬድ በተከሰቱ ወረርሽኞች አማካኝነት ነው። እነዚህም ወረርሽኞች ከኡጋንዳ ለላብራቶሪ ሙከራ ታስበው በመጡ የአፍሪካ አረንጓዴ ዝንጀሮዎች (African green monkeys) ምክንያት ተከስተዋል። ከእነዚህ ወረርሽኞች በኋላም በአንጎላ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ በኢኳቶሪያል ጊኒ፣ በጋና፣ በጊኒ፣ በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በታንዛኒያ እና በኡጋንዳ የተለያዩ ወረርሽኞች ሪፖርት ተደርገዋል።
የማርበርግ ቫይረስ በሽታ እንዴት ይተላለፋል?
አብዛኞቹ በሰው ልጅ የተከሰቱት የቫይረሱ ኢንፌክሽኖች ሮሴተስ ፍሩት ባትስ የተባሉ የሌሊት ወፎች በሚኖሩባቸው የማዕድን ማውጫ ስፍራዎች እና ዋሻዎች አካባቢ ለረጅም ጊዜ በቆዩ ሰዎች ላይ ነው።
ቫይረሱም አንዴ ወደ ሰው ከገባ በኋላ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው በበሽታው በተጠቃ ግለሰብ ደም፣ የሰውነት ፈሳሽ እንዲሁም የተበከሉ አልባሳት ወይም የአልጋ ልብስዎች እና ቁሳቁሶች ጋር ንክኪ ሲኖር ነው ። ከዚህ በተጨማሪ በበሽታው ምክንያት የሞቱ ሰዎችን ለመቅበር ሲባል የሚኖር ንክኪ ለበሽታው ስርጭት አስተዋፅኦ ያደርጋል።
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ሰዎች የበሽታውን ምልክት ከማሳየታቸው በፊት በሽታውን ሊያስተላልፉ አይችሉም። አንዴ ምልክት ማሳየት ከጀመሩ በኋላም ግን ደማቸው ውስጥ ቫይረሱ እስካለ ድረስ በሽታውን ያስተላልፋሉ።
የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የማርበርግ ቫይረስ በሽታ በድንገት ሊከሰት እና በፍጥነት ሊባባስ ይችላል። ቫይረሱ በደም ውስጥ ከገባ ከ2 እስከ 21 ባሉት ቀናት ውስጥ በድንገት የሚከሰት ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከባድ ራስ ምታት ፣ የጡንቻ ህመም እና ከፍተኛ ድካም ይጀምራል።
በሦስተኛው ቀን ብዙዎቹ ታማሚዎች ከባድ ተቅማጥ፣ የሆድ ቁርጠት፣ ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ ያጋጥማቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ ከ2ተኛ እስከ 7ተኛ ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ የማያሳክክ ሽፍታ ሊወጣባቸው ይችላል።
በአምስተኛው ቀን ከአፍንጫ፣ ከድድ፣ ከሴት ብልት፣ በትውከት፣ በሰገራ ወይም መርፌ የተወጉባቸው ቦታዎች ላይ የሚኖር ከፍተኛ ደም መፍሰስ ይከሰታል። በነርቭ ሥርዓት ጉዳት ምክንያትም እንደ ግራ መጋባት፣ የመነጫነጭ እና የመበሳጨት ስሜት ሊከሰት ይችላል። አልፎ አልፎ የወንዶች የዘር ፍሬ ብግነትም ያጋጥማል።
በሽታው በጣም ከተባባሰ ደግሞ ምልክቶች ከታዩ ከ8 እስከ 9 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ደም መፍሰስ ምክንያት ሞት ይከሰታል።
የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ምርመራ ምን ይመስላል ?
የማርበርግ ቫይረስ በሽታን እንደ ወባ ፣ ታይፎይድ ፣ ሼጌሎስስ (shigellosis)፣ የማጅራት ገትር እና ከሌሎች ሄሞራጂክ ፊቨር በሽታዎች ለመለየት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ። ሐኪምዎ የሚያሳዩአቸው ምልክቶች በማርበርግ ቫይረስ መከሰታቸውን ለማረጋገጥ የሚከተሉትን ምርመራዎች ሊያደርግሎት ይችላል።
- አንቲቦዲ ካፕቸር ኢንዛይም ሊንክድ ኢሚኖሶርበንት አሰይ ምርመራ (antibody-capture enzyme-linked immunosorbent assay - ELISA)
- አንቲጅን ካፕቸር ዲተክሽን ምርመራ (antigen-capture detection tests)
- ሪቨርስ ትራንስክሪፕቴዝ ፖሊሜሬዝ ቼን ሪያክሽን ምርመራ (reverse transcriptase polymerase chain reaction - RT-PCR assay) እና
- ቫይረሱን ለመለየት የሴል ካልቸር ምርመራ ሊደረግሎት ይችላል ።
የማርበርግ ቫይረስ በሽታ እንዴት ይታከማል?
የማርበርግ ቫይረስ በሽታ እስካሁን መድኃኒት ወይም ክትባት አልተገኘለትም። ይሁን እንጂ ቀደም ብሎ የሚሰጥ የድጋፍ እና የእንክብካቤ ህክምና ለምሳሌ በቂ ፈሳሽ መስጠት (rehydration) እና የተወሰኑ ምልክቶችን ማከም ሕይወትን ሊታደግ ይቻላል።
የማርበርግ ቫይረስ በሽታን እንዴት መከላከል ይቻላል?
የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመከላከል፡
- ከታመሙ ሰዎች ደምና የሰውነት ፈሳሽ ጋር ንክኪ እንዳይኖሮት ይጠንቀቁ።
ከማርበርግ ቫይረስ በሽታ ካገገመ ሰው የዘር ፈሳሽ (semen) ውስጥ ቫይረሱ መጥፋቱን በምርመራ እስካልተረጋገጠ ድረስ ንክኪ እንዳይኖሮት።
ወንድ ታማሚዎች ከበሽታው ካገገሙ በኋላ እስከ 7 ሳምንታት ቫይረሱን በዘር ፈሳሻቸው አማካኝነት ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ስለዚህ ከበሽታው ያገገሙ ወንድዎች እና የግብረስጋ ግንኙነት አጋሮቻቸው በሽታው የመተላለፍ እድል እንዳለው በማወቅ በግብረስጋ ግንኙነት ወቅት ኮንዶምን መጠቀም እና የእጅ እና የግል ንፅህናቻውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
- ከታመመ ሰው የሰውነት ፈሳሽ ጋር ንክኪ ሊኖራቸው የሚችሉ ዕቃዎችን አይንኩ።
- የማርበርግ ቫይረስ በሽታ በስፋት የተሰራጨባቸው ባታዎች አካባቢ የሚኖሩ ከሆነ ከሌሊት ወፎች እና ከዝንጀሮዎች ጋር ንክኪን ያስወግዱ።




