የቃጠሎ አደጋ በየአመቱ ወደ 180,000 ሰዎችን ለሞት የሚዳርግ አለም አቀፍዊ ችግር ነው። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ የሚከሰቱት በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች ውስጥ ሲሆን ወደ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ደግሞ በአፍሪካ እና በደቡብ ምስራቅ እስያ ክልሎች ውስጥ ነው፡፡
የቃጠሎ አደጋ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል። ከነዚህም መካከል
- የሞቀ ውሃ ወይም እንፋሎት
- እሳት ወይም ነበልባሎች
- ትኩስ እቃዎች
- ኬሚካሎች
- ኤሌክትሪክ
- ለፀሐይ ከመጠን በላይ መጋለጥ
አብዛኛዎቹ የቆዳ መቃጠል አደጋዎች በቤት ውስጥ መታከም ይችላሉ። ሆኖም ፣ ከባድ የቆዳ መቃጠል ምልክቶችን እና ሊያስከተሉ የሚችሉትን መዘዞች በተገቢው በመረዳት አስፈላጊውን የህክምና እርዳታ ከጤና ባለሙያ በአስቸኳይ ማግኘት አለብዎ።
የቃጠሎ ዓይነቶች
በተቃጠለው የቆዳ ጥልቀት ላይ በመመርኮዝ ቀደም ሲል መጀመሪያ ፣ ሁለተኛ ፣ ሦስተኛ ወይም አራተኛ ደረጃ በመባል ይመደብ ነበር። ይህ ስርዓት አሁን የቀዶ ጥገና ሕክምናን የሚፈልጉ ቃጠሎዎችን በተሻለ ሁኔታ በመለየት በአዲስ የምደባ ስርዓት ተተክቷል ፡፡
- የላይኛው የቆዳ ሽፋን መቃጠል(superficial skin burns) - ቀደም ሲል የመጀመሪያ ደረጃ ቃጠሎ ተብሎ የሚጠራው ይህ የቃጠሎ አይነት የቆዳውን የላይኛው ሽፋን ብቻ የሚያካትት ነው። ህመም ያለው፣ ሲታይ ቀይ የሆነ ሲጫኑት ነጭ የሚሆን ቁስል ያስከትላል። ይህ አይነቱ ቃጠሎ በአጠቃላይ ከ3 እስከ 6 ቀናት ውስጥ ያለ ጠባሳ ይድናል። የፀሐይ የቃጠሎ አደጋ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው ፡፡
- ጥልቀት የሌለው ከፊል የቆዳ መቃጠል (Superficial partial-thickness skin burns)- ቀደም ሲል የሁለተኛ ደረጃ ቃጠሎ ተብሎ የሚጠራው ጥልቀት የሌለው ከፊል የቆዳ መቃጠል፣ ከላይ ያሉትን ሁለት የቆዳ ሽፋኖች መቃጠል ነው። በአየር እንቅስቃሴ ወይም በአየር ሙቀት ለውጦች ምክንያት ህመም ሊኖረው ይችላል፣ ቆዳው ቀይ መሆን እና ብዙውን ጊዜ ውሀ የቋጠረ እብጠት ይኖረዋል ። ይህ አይነቱ የቆዳ ቃጠሎ ከ 7 እስከ 21 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ይድናል። የተቃጠለው ቦታ ከሌላኛው የቆዳ ክፍል ሊጠቁር ወይም ሊነጣ ይችላል ነገርግን ብዙውን ጊዜ ጠባሳ አያስከትልም።
- ጥልቀት ያለው ከፊል የቆዳ መቃጠል( Deep partial-thickness skin burns) - ቀደም ሲል የሶስተኛ ዲግሪ ቃጠሎ ተብሎ የሚጠራው ጥልቀት ያለው ከፊል የቆዳ መቃጠል፣ ወደ ቆዳው የታችኛው ክፍል በጥልቀት ይስፋፋል፣ ግፊት በሚደረግበት ወቅት ህመምም አለው። ሁልጊዜ ማለት ይቻላል ወሃ ያዘሉ እብጠቶችን ይፈጥራል፣ እና በሚጫኑበት ጊዜ ነጭ አይሆንም። ይህ አይነቱ የቆዳ መቃጠል ለመፈወስ ከ 21 ቀናት በላይ ይወስዳል እንዲሁም ጠባሳ ያስከትላል።
- ሙሉ የቆዳ ቃጠሎ( Full-thickness burns) - ቀደም ሲል አራተኛ ደረጃ ቃጠሎ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ የቆዳ ሽፋኖች በማጥቃት ቆዳውን ሙሉ በሙሉ ያጠፋል። የተቃጠለው ቦታ ላይ ያሉ ነርቮች አብረው ስለሚጠፉ ብዙውን ጊዜ ህመም አይኖረውም። የተቃጠለው ቦታ ነጭ፣ ግራጫ ወይም ጥቁር ቀለም ይኖረዋል፤ እናም ቆዳው ደረቅ ይሆናል። ይህ አይነቱ ቃጠሎ የቀዶ ጥገና ሕክምና ያስፈልገዋል፤ የሚያስከትለው ጠባሳም ከባድ ነው።
ምን አይነት የቆዳ መቃጠል ምልክቶችን ሳይ ወደ ጤና ተቋም ልሂድ?
- ቃጠሎው ፊትን ፣ እጆችን ወይም ጣቶችን ፣ ብልትን ወይም እግርን የሚያካትት ከሆነ
- ቃጠሎው መገጣጠሚያ ላይ ወይም አጠገብ ከሆነ (ጉልበት ፣ ትከሻ ፣ ዳሌ)
- ቃጠሎው የሰውነት ክፍልን ከከበበ (ክንድ ፣ እግር ፣ ደረት ፣ ጣት)
- የቃጠሎው ስፋት ከፍተኛ ከሆነ (ከ 7.5 ሴ.ሜ በላይ) ወይም ጥልቀት ያለው ከሆነ፤ ቃጠሎው ሰፊ ወይም ጥልቅ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ከገባዎ የጤና ባለሙያ ማየቱ ተመራጭ ነው ፡፡
- የተጎጂው እድሜ ከአምስት ዓመት በታች ከሆነ ወይም ከ 70 ዓመት በላይ ከሆነ
- የቆዳ ብግነት ምልክቶች ለምሳሌ እንደ መቅላት ፣ ህመም ፣ መግል መያዝ ፣ ወይም ትኩሳት ካለ
- ጢስ ወይም ጋዝ ወደ ውስጥ በመተንፈስ ምክንያት የሚመጣ የመተንፈስ ችግር ካለ
- ለእሳት እና ለጢስ በመጋለጥ ምክንያት የሚመጣ ራስ ምታት ወይም የማቅለሽለሽ ስሜት ካለ
- በኬሚካሎች ወይም በፍንዳታ የሚከሰቱ ከባድ ቃጠሎዎች ከሆኑ
- መብረቅን ጨምሮ በኤሌክትሪክ የሚከሰቱ ቃጠሎዎች ካጋጠሙ
- የመረበሽ/ግራ የመጋባት ስሜት ወይም ራስን መሳት ያለው የፀሐይ ቃጠሎ ከሆነ
- የፈሳሽ እጥረት (dehydration) የታከለበት የፀሐይ ቃጠሎ ከሆነ
ለቆዳ መቃጠል የሚደረግ የሕክምና እርዳታ
ትንሽ የሆኑ የላይኛው ሽፋን የቆዳ መቃጠል እና ጥልቀት የሌለው ከፊል የቆዳ መቃጠል ብዙውን ጊዜ በቤት ውስጥ ሊታከሙ ይችላል። ሆኖም ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ካሉ በጤና ባለሙያ መታየት አለባቸው ፡፡
በቤት ውስጥ የሚከተሉትን እርምጃዎች በመውሰድ ለቃጠሎ የህክምና እርዳታ መስጠት ይችላሉ
ቃጠሎ የተፈጠረበትን የሰውነት ክፍል ማፅዳት
- የተቃጠለ የሰውነት ክፍል አካባቢ ያለ ማንኛውንም ልብስ ያስወግዱ። ነገር ግን ልብሱ በቃጠሎ ምክንያት ከቆዳ ጋር የተጣበቀ ከሆነ ለማላቀቅ አይታገሉ።
- በቀስታ የሚወርድ የቧንቧ ውሃ የተቃጠለው ቆዳ ላይ ከ5 እስከ 10 ደቂቃ ያፍሱ፤ የኬሚካል ቃጠሎ ከሆነ 30 እስከ 40 ደቂቃ ማፍሰስ ያስፈልጋል
- ቆዳውን በአልኮል፣ በአዮዲን ወይም በሌሎች ማጽጃዎች ማጠብ አስፈላጊ አይደለም ፡፡
- ቆዳውን የጥርስ ሳሙና መቀባት በፍጹም አይመከርም።
- በረዶን በቀጥታ በቆዳው ላይ ከማድረግ ይቆጠቡ ምክንያቱም ይህ ቆዳን የበለጠ ሊጎዳ ይችላል።
ቆዳ ኢንፌክሽንን መከላከል
- ከፊል ጥልቀት እና ከዚያ በላይ በሆኑ ቃጠሎዎች ላይ ኢንፌክሽንን ለመከላከል እንደ ፀረ ባክቴሪያ ክሬሞችን መጠቀም ይችላሉ።
- በቆዳ ቃጠሎ ላይ ቅባቶችን ወይም ሌሎች ንጥረ ነገሮችን ፈፅሞ አይጠቀሙ።
- የተቃጠለውን አካባቢ በየቀኑ በሳሙና እና ውሃ በማጠብ የቃጠሎውን ቦታ ንፅህና ይጠብቁ።
- ውሃ ያዘሉ ቁስሎች በንጹህ አጣብቆ በማይይዝ ጨርቅ(ጎዝ) መሸፈን አለባቸው። እንደ አስፈላጊነቱ በየቀኑ አንድ ወይም ሁለቴ ሽፋኑን ይቀይሩ።
- ውሃ ያዘሉ ቁስሎችን በመርፌ ወይም በጥፍር ለማፈንዳት አይሞክሩ ምክንያቱም ይህ በቆዳ ኢንፌክሽን የመያዝ እድልን ይጨምራል።
መንጋጋ ቆልፍ (ቴታነስ) መከላከል
- ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የመንጋጋ ቆልፍ ክትባት ካልወሰዱ እና ቃጠሎው ከላይኛው የቆዳ ሽፋን ጠልቆ የገባ ከሆነ ይህን ክትባት ድጋሚ መውሰድ ያስፈልግዎታል ፡፡
ህመምን ማከም
- በእጅ ወይም በእግር ላይ ያሉ ቃጠሎዎችን ከደረት በላይ ከፍ አደርጎ ማስቀመጥ ወይም መተኛት እብጠትን እና ህመምን ለመከላከል ይረዳል።
- የህመም ማስታገሻ መድሃኒት የሚያስፈልግዎ ከሆነ እንደ ፓራሲታሞል፣ አይቢፕሮፊን ያሉ ከሐኪም ትዛዝ ውጪ የሚገኙ መድሃኒቶችን መውሰድ ይችላሉ። በእነዚህ መድሃኒቶች ህመሞን ካልተቆጣጠሩ በአቅራቢያዎ የሚገኝ የጤና ባለሙያ ያነጋግሩ።
ቆዳውን ከመነካካት እና ከማከክ ይቆጠቡ
- የተቃጠለው ቆዳ መፈወስ ሲጀምር ብዙ ሰዎች ማሳከክ ይረብሻቸዋል። በተቻለ መጠን ቆዳውን ላለማከክ ይሞክሩ ካስፈለገ የቆዳ ድርቀትን የሚከላከሉ ሎሽኖችን (moisturizers) ይጠቀሙ።
ቃጠሎው እየዳነ ካልሆነ፣ የበለጠ ህመም የሚሰማዎ ከሆነ ወይም የቆዳ ኢንፌክሽን ከተፈጠረ በቅርብ ወደ ሚገኝ የጤና ተቋም መሄድ አለብዎት ፡፡
የቃጠሎ አደጋ እንዳይከሰት ምን ማድረግ አለቦት?
በቤትዎ ውስጥ አንዳንድ ለውጦችን በማድረግ የቆዳ ቃጠሎን መከላከል ይቻላል።
- የበራ ሻማ እና ክብሪቶችን ህጻናት የማይደርሱበት ቦታ ያስቀምጡ
- በሚተኙበት ሰዐት፣ ህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች ከወሰዱ፣ የእንቅልፍ ክኒኖች ከወሰዱ ወይም አልኮል ከጠጡ በኋላ አያጭሱ
- በቤትዎ የኦክሲጂን ታንከር ካለ በአቅራቢያው ምንም አይነት እሳት አያቀጣጥሉ
- ትኩስ ምግቦች እና መጠጦች፣ ካውያ የመሳሰሉትን በጠረጴዛዎች ጠርዝ ላይ አያስቀምጡ
- ማብሰያ ምድጃዎች እና ምጣዶችን ከህጻናት ያርቁ ፤ ምግብ በሚያበስሉበት ጊዜ በጭራሽ ልጆን በእጆችዎ አቅፈው መሆን የለበትም
- መኪናዎትን ፀሃይማ ቦታ የሚያቆሙ ከሆነ የመኪና ቀበቶዎችን ብረታማ ክፍል በልብስ ወይም በፎጣ ይሸፍኑ
- ከፀሐይን ጨረር የሚከላከሉ ክሬሞችን (sunscreen) ይጠቀሙ




