አለምን ያሳሰበው የሃንታ ቫይረስ (Hantavirus)
አዲሱ አስጊው የመርከብ ወረርሽኝ ፤
በፈረጆቹ 2026 የሜይ ወር መጀመሪያ አከባቢ ላይ ፤ በአዘቦት ጠዋት ላይ ኤም.ቪ ሆንድየስ (MV Hondius) የተባለችው የቅንጦት መዝናኛ መርከብ ከአርጀንቲና ተነስታ ወደ ካናሪ ደሴቶች 147 ተሳፋሪ ይዛ ፤ በመጓዝ ላይ የነበረችው የዚህች መርከብ ጉዞ፤ ባልታሰበ የህክምና ቀውስ ምክንያት ቅዠት ሆነ።
በመርከቧ ላይ አንድ ተሳፋሪ በድንገት ታመመ! ቀጥሎም ሌላኛው ብዙም ሳይቆይ የታመሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጣ።ያልታወቀ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከባድ የመተንፈስ ችግር እና ድንገተኛ የሞት መከሰት ጀመሩ ።
ይህ ድንገተኛ የህክምና አደጋ በኋላ ላይ የሃንታ ቫይረስ (Hantavirus) ወረርሽኝ መሆኑ ተረጋገጠ። በዚህም መርከቧና ተሳፋሪዎቿ የዓለም አቀፍ የጤና ምርመራ እና የመነጋገሪያ ማዕከል ሆኑ።
የዓለም ጤና ድርጅት ቢያንስ 12 አገራት በሃንታ ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን በይፋ አሳውቋል። እንደ ካናዳ፣ ጀርመን፣ ሲንጋፖር፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ሀገራት በቫይረሱ የተጠቁ ተጓዦች በማስተናገዳቸው ወይም ዜጎቻቸው በበሽታው በተያዙ አካባቢዎች በማለፋቸው ሳቢያ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተነግሯቸዋል። ቫይረሱ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት እየሳበ ይገኛል።
ለመሆኑ ሃንታ ቫይረስ ምንድን ነው? ለእኛስ ያሰጋናል ?
ሃንታ ቫይረስ እንደ ኢንፍሉዌንዛ ወይም ኮቪድ-19 አይደለም፤ የሃንታ ቫይረሶች በተለምዶ በሰዎች መካከል በስፋት አይሰራጩም። ይህ የቫይረስ ዝርያ በዋነኝነት እንደ አይጥ ባሉ አጥቢ እንስሳት የሚተላለፍ ሲሆን፤ ከሌሎች ቫይረሶች የሚለየውም ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ "ዙኖቲክ" (zoonotic) በሽታ በመሆኑ ነው።
በሳይንሳዊው ዓለም የሃንታ ቫይረሶች በሁለት ዋና ዋና ቡድኖች ይከፈላሉ፦
የድሮው ዓለም (Old World) ሃንታ ቫይረሶች፦ በአብዛኛው በአውሮፓ እና በእስያ የሚገኙ ሲሆኑ፤ ኩላሊትን የሚያጠቃ ከባድ የጤና እክል (HFRS) ያስከትላሉ።
የአዲሱ ዓለም (New World) ሃንታ ቫይረሶች፦ በአሜሪካ አህጉር የሚገኙ ሲሆን፤ ሳምባን በፈሳሽ እንዲሞላ በማድረግ የመተንፈሻ አካላትን ክፉኛ የሚያጠቁ (HCPS) ናቸው።
ሃንታ ቫይረስ በዋነኝነት የሚሰራጨው በቫይረሱ ከተበከሉ አይጦች ጋር ንክኪ ሲኖር ወይም በአይጦች ሽንት፣ ሰገራና ምራቅ የተበከለ አቧራን ወደ ውስጥ በመተንፈስ ነው። ጥሩው ነገር ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ እድሉ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ነው ሆኖም ግን ንፅህናን መጠበቅና ከአይጦች ንክኪ መራቅ ለደህንነትዎ ወሳኝ ነው። በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ በሚተነፍሱት አየር አማካኝነት ለቫይረሱ ሊጋለጡ ይችላሉ። የቫይረሱ ዋነኛ የመተላለፊያ መንገዶች የሚከተሉት ናቸው፦
- በአየር መበከል (Aerosolization)፦ የአይጥ ሽንት፣ እዳሪ፣ ወይም የአይጥ መኖሪያ ስፍራዎች በሚነኩበት ጊዜ፤ ቫይረሱ በአይን በማይታዩ ብናኞች አማካኝነት ወደ አየር ይገባል። እነዚህ በአየር ላይ የሚንሳፈፉ ጥቃቅን ጠብታዎች ወደ ውስጥ ሲተነፈሱ ቫይረሱን ያስተላልፋሉ።
- አካባቢን በማጽዳት ወቅት፦ አቧራማ የሆኑና አይጥ የሚኖርባቸውን ስፍራዎች ሲጠርጉ ወይም ሲያጸዱ የሚፈጠረው ብናኝ፤ ቫይረሱን በአጋጣሚ ወደ ውስጥ ለመተንፈስ ሰፊ ዕድል ይሰጣል፤ በዚህም ቫይረሱ በትንፋሽ አማካኝነት ወደ ሰውነት ይገባል።
ቀጥተኛ ንክኪ፦ ምንም እንኳን አልፎ አልፎ የሚከሰት ቢሆንም፤ በአይጥ ንክሻ አልያም በአይጥ እዳሪና ሽንት የተበከሉ ነገሮችን ነክቶ አፍን፣ አፍንጫን፣ ወይም አይንን በመንካት ሊተላለፍ ይችላል።
ምልክቶቹስ?
የሃንታ ቫይረስ ፈታኝነቱ መጀመሪያ ላይ እንደ ተራ ጉንፋን መምሰሉ ነው። ምልክቶቹ ከቫይረሱ ጋር ከተገናኙ ከ1 እስከ 8 ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ሊታዩ ይችላሉ። በሽታው ሁለት ደረጃዎች አሉት፦
- የመጀመሪያ ደረጃ (ከ1-5 ቀናት)፦ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከባድ የጡንቻ ሕመም (በተለይ በጭን፣ በወገብ፣ እና በጀርባ ጡንቻዎች)፣ ድካም፣ እና ራስ ምታት ሊሰማ ይችላል።
- በሽታው እየጸና ሲሄድ፦ ቫይረሱ እየገፋ ሲሄድ ታካሚዎች ድንገተኛ የትንፋሽ እጥረት እና የማያቋርጥ ሳል ያጋጥማቸዋል። ይህም የአዲሱ ዓለም የሃንታ ቫይረስ የሳምባ ሕመም (Pulmonary Syndrome) ዋና መለያ ምልክት ነው።
እንደ ሲ.ዲ.ሲ (CDC) መረጃ፤ ለዚህ የሳምባ ችግር ከሚጋለጡ 10 ሰዎች መካከል እስከ 4 የሚሆኑት ፈጣን የሕክምና እርዳታ ካላገኙ ሕይወታቸው ሊያልፍ ይችላል።
ሕክምናውስ ምንድን ነው?
ለሃንታ ቫይረስ እስከ አሁን ድረስ ለዚህ ቫይረስ የተገኘ የተለየ የፀረ-ቫይረስ መድኃኒት የለም። ሕክምናው በዋነኝነት የሚያተኩረው የታካሚውን ምልክቶች በማስታገስ ላይ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ ታካሚው ሆስፒታል ገብቶ በኦክስጅንና በፅኑ ሕክምና (ICU) ድጋፍ እንዲያገኝ ይደረጋል። ቫይረሱ አስከፊ ጉዳት እንዳያደርስ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ብቸኛው መፍትሄ ነው።
ለዚህም ወረርሽኝ ፤ እጅጉን ውጤታማ የሆኑት የመከላከያ መንገዶችም እጅጉን ቀላል ናቸው።
- አይጦች ካሉባቸው አካባቢዎች ራስዎን ያርቁ።
- አይጦች ወደ ቤትዎ ወይም መጋዘንዎ የሚገቡባቸውን ቀዳዳዎች በሽቦ ወይም በሲሚንቶ ይዝጉ።
- አቧራማ መጋዘኖችን ወይም የተተዉ ክፍሎችን ሲያጸዱ፤ መስኮት ይክፈቱ። አየር እንዲገባ ያድርጉ። ብናኝ እንዳይተነፍሱ የመከላከያ ማስኮችን(ቁሶችን) መጠቀም አስፈላጊ ነው።
- ደረቅ የአይጥ እዳሪን በፍጹም አይጥረጉ። ይልቁንም አካባቢውን በበረኪና ለ5 ደቂቃ ያርጥቡትና ከዚያ በእርጥብ ጨርቅ ያጽዱት።
- ለረጅም ጊዜ ተዘግቶ የቆየ ክፍል ውስጥ ከመግባትዎ በፊት ለ30 ደቂቃ ያህል መስኮትና በሮችን ከፍቶ አየር እንዲገባ ያድርጉ!




