የኮሌስትሮል እና ደም ግፊት በሽታ ህክምና
የኮሌስትሮል እና ከፍተኛ የደም ግፊት በሽታዎች አብረው ሲከሰቱ የልብ ድካም እና ስትሮክ የመሳሰሉ ከባድ የጤና ችግሮችን ያስከትላሉ። ከፍተኛ የደም ግፊት የደም ሥሮችዎ ግድግዳዎች እንዲወፈሩ ሊያደርግ ይችላል፣ ይህም ኮሌስትሮል በደም ሥሮች ውስጥ ሲከማች የበለጠ ጎጂ ይሆናል። የልብ ድካም ወይም ስትሮክ የመያዝ እድሉ በከፍተኛ መጠን ይጨምራል።
ከሴቶች ጋር ሲነፃፀር ወንዶች ከፍተኛ የደም ግፊት ካለባቸው ለልብ ድካም የመጋለጥ እድላቸው በሁለት እጥፍ ይበልጣል። ነገር ግን የደም ግፊታቸውን የሚቆጣጠሩ ሰዎች ይህንን የጤና ችግር በእጅጉ ሊቀንሱ ይችላሉ።
ሕክምናው በዋነኝነት የሚከተሉትን ዋና ዋና መንገዶች ያካትታል፦
የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ
- የተመጣጠነ እና ጤነኛ ምግብ መመገብ ፦ ፍራፍሬዎችን፣ አትክልቶችን፣ እና ያልታሹ እህሎችን በብዛት መመገብ፤ እንዲሁም ጨው (ሶዲየም)፣ ቅባት (ስብ) እና ስኳር መቀነስ እና ማሰገድ ይመረጣል።
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፦ በቀን ቢያንስ ለ 30 ደቂቃ ያህል መጠነኛ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ (እንደ ፈጣን እርምጃ መሄድ፣ ውሃ ዋና …) እና በሳምንት ቢያንስ ከ 3 እስከ 5 ቀን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር ይመረጣል።
- ክብደትን መቆጣጠር፦ ከመጠን ያለፈ ውፍረት በደም ግፊት እና በኮሌስትሮል ላይ ከፍተኛ ጫጫታ ስለሚፈጥር ጤናማ ክብደትን መጠበቅ ይኖርብናል።
- አልኮል እና ሲጋራ ማቆም።
2. የህክምና ክትትል እና መድሃኒቶች
- የደም ግፊት መቆጣጠሪያ መድሃኒቶች፦ እንደ ሁኔታዎ ዶክተርዎ የደም ግፊትዎን በመደበኛ ደረጃ የሚያቆዩልዎ መድሃኒቶችን ሊያዝሎት ይችላል።
- ኮሌስትሮል መቆጣጠሪያ መድሃኒቶች፦ በሰውነትዎ ውስጥ የሚመነጨውን መጥፎ ኮሌስትሮል መጠን የሚቀንሱ እና የደም ቧንቧን ጤና የሚጠብቁ እንደ ስታቲን (Statins) ያሉ መድሃኒቶች ሐኪሞ ሊሰጥዎት ይችላል።
የኮሌስትሮል ህክምና ግብ (therapeutic targets of cholesterol treatment)
ለመሆኑ የልብና ተያያዥ የደም ስር ህመም ስጋትን በአስተማማኝነት ለመቀነስ የሚረዳው የኮሌስትሮል ህክምና ግብ ምን መሆን አለበት?
ኮሌስትሮልን በተገቢው ሁኔታ ማከም የልብን እና ተያያዥ የደም ስር ህመሞችን ተጋላጭነት ለመቀነስ ይረዳል። ከፍ ያለ የኮሌስትሮል መጠን በተለይም የጎጂ ኮሌስትሮል የሚፈለገውን ያክል ቁጥጥር ውስጥ አለመሆን ለልብ ድካም፣ ለስትሮክ እና ሌሎችም የደም ስር ህመሞች ተጋላጭነት በእጅጉ እንደሚጨምር ያለጥርጥር የተረጋገጠ ሳይንስ ነው።
ኮሌስትሮልን ለማከም በርካታ ውጤታማ እና ወጭ ቆጣቢ ህክምናዎች ያሉት ቢሆንም በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ተገቢውን ትኩረት ስላልተሰጠው ተላላፊ ያልሆኑ የልብና የደም ስር ህመሞች እንደወረርሽኝ እየተሳፋፉ መጥተዋል።
በዚህ ጽሁፍ በ2019 በታተመው የአውሮፓ የልብ ማህበር የኮሌስትሮል ህክምና መመሪያ ላይ በመመርኮዝ የእያንዳንዱን ሰው የልብ ህመም ተጋላጭነት መሰረት ያደረገ የኮሌስትሮል ሕክምና ግቦችን እናያለን። እነዚህን ግቦች በመረዳት የልብዎን ጤንነት ለመጠበቅ ተግባራዊ እርምጃወችን ይውሰዱ።
በዚህ የኮሌስትሮል ህክምና መመሪያ መሰረት ዋናው የኮሌስትሮል ሕክምና ግብ ጎጂ ኮሌስትሮልን (LDL-C) መቀነስ ነው። ምክንያቱም የደም ስር ቧንቧዎችን በመዝጋት ሂደት ዋናው ጠላት ይህ ጎጂ ኮሌስትሮል ስለሆነ ነው። የዚህ ጎጂ ኮሌስትሮል መጠን ምን ያህል መውረድ አለበት የሚለው የሚወሰነው አጠቃላይ የልብ ህመም ተጋላጭነትን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ስለሆነም ለሁሉም ሰው የሚሆን ተመሳሳይ ግብ ሳይሆን እንደየ ግል ተጋላጭነት የኮሌስትሮል የቁጥጥር መጠን ይለያያል።
- የልብ ህመም ተጋላጭነትህ/ሽ በጣም ከፍተኛ (very high risk) ከሆነ (ለምሳሌ፡ ቀደም ሲል የልብ ድካም ወይም ስትሮክ አጋጥሞ ከነበር፣ ከስኳር ህመም ጋር የተያያዙ የደም ስር ህመሞች ካሉ) አላማው ጎጂ ኮሌስትሮልን ከ55 mg/dL በታች ማውረድ ነው።
- የልብ ህመም ተጋላጭነትህ/ሽ ከፍተኛ (high risk) ከሆነ (ለምሳሌ የደም ግፊት ካለብህ፣ የስኳር ህመም፣ ወይም ሌሎች የልብ ህመም አጋላጭ መንስኤዎች ካሉ) የጎጂ ኮሌስትሮል አላማው ከ70 mg/dL በታች ማድረግ ነው።
- የልብ ህመም ተጋላጭነትህ/ሽ መጠነኛ (moderate risk) ከሆነ የጎጂ ኮሌስትሮል ግቡ ከ100 mg/dL በታች ማድረግ ነው።
- ለተቀሩት የልብ ህመም ተጋላጭነታቸው ዝቅተኛ (low risk) ለሆኑ ግለሰቦች በአጠቃላይ ግቡ ጎጂ ኮሌስትሮልን ከ 116 mg / dL ያነሰ እንዲሆን ማድረግ ነው።
በህክምና ውስንነት ከላይ የጠቀስናቸውን ግቦች ማሳካት ባይቻል እንኳ የኮሌስትሮል መጠንን የተቻለውን ያክል መቀነስ በተለይም ኮሌስትሮልን ከመጀመርያው መጠን ቢያንስ በ50% መቀነስ የልብ ሕመምን አደጋ ለመቀነስ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።
መደበኛ የጤና ምርመራዎች፣ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች (እንደ ጤናማ አመጋገብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ) እና እንዳስፈላጊነቱ የኮሌስትሮል መድሃኒት መውሰድ እነዚህን ግቦች ለማሳካት የየራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ።
በተለይም የስኳር ህመም ያላቸው፣ የልብና ተያያዥ የደም ስር ህመም ያላቸው፣ የኮሌስትሮል መጠን በከፍትኛ ሁኒታ የጨመረባቸው እንዲሁም ተደራራቢ አጋላጭ ህመም (multiple risk factors) ያላቸው የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒት ያለማቋረጥ መውሰድ ተገቢ ነው።
ዋናዎቹ የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒቶች ስታቲን (statin) በመባል ይታወቃሉ። በርካታ የስታቲን መድሃኒት አይነቶች ቢኖሩም ኮሌስትሮልን በከፍተኛ ሁኔታ በማስተካከል ውጤታማነታቸው የተረጋገጠው ሮሱቫስታቲን (Rosuvastatin) እና አቶርቫስታቲን (Atorvastatin) የተባሉት የስታቲን መድሃኒቶች ናቸው።
የኮሌስትሮል መጠንዎን እና የህምክና ግብዎን በመረዳት እና ተጨባጭ ስራ በመስራት ለልብ ህመም ተጋላጭነትዎን በእጅጉ ይቀንሱ።
የደም ግፊት ህክምና ግብ (High Blood Pressure treatment goal)
ከፍተኛ የደም ግፊት የልብና የደም ዝውውር ችግርን የሚያመጣ የደም ግፊት መጨመር ሁኔታ ነው፡፡ የደም ግፊት መጨመር የልብ ደም ቧንቧ በሽታ, የደም መፍሰስ እና በጭንቅላት ውስጥ የደምመፍሰስ (መርጋት), የልብ ድካምና እና የኩላሊት በሽታ ከሚያመጡ ዋና ዋና አጋላጭ ሁኔታዎች አንዱ ሲሆን ነገር ግን መከላከል የምንችለው ሁኔታ ነው፡፡
ከፍተኛ የደም ግፊት መጨመር ከተከሰተ በኋላ መድሃኒት ሳይጀምሩ በአኗኗር ሁኔታ እና አመጋገብ ለማስተካከል ከተወሰነ በኋላ ምንም ለውጥ ለ 3 እስከ 6 ወር ከሌለ ወድያውኑ መድሃኒት መጀመር ይኖርቦታል።
ዋና ዋና የህክምና ግቦች፡
- መደበኛ የደም ግፊት መጠን (Target): የብዙሃኑ አዋቂዎች ግብ የደም ግፊትን ከ (130/80 mmHg) በታች ማድረግ ነው።
- ለከፍተኛ የልብና ደም ቧንቧ ህመም ተጋላጭ የሆኑ (High Risk): የስኳር ህመም፣ የኩላሊት ህመም ወይም የልብ ህመም ታሪክ ላላቸው ታማሚዎች የደም ግፊታቸው ከ (120/80 mmHg) በታች መሆን አለበት።
ይህ ግብ የሚሳካው የህይወት ዘይቤን በማስተካከል እና አስፈላጊ ከሆነም ሀኪም በሚያዘው መድሃኒት በመታገዝ ነው።
ግቡን ለማሳካት የሚወሰዱ እርምጃዎች፡
- የአኗኗር ዘይቤ ማስተካከል (Lifestyle Adjustments):
- የጨው መጠን መቀነስ፡ በቀን ከ (1500 mg) ያልበለጠ ጨው መጠቀም።
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፡ በሳምንት ቢያንስ ለ 150 ደቂቃ መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ።
- አመጋገብ፡ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ እና አጠቃላይ ጤናማ የሆኑ ምግቦችን መመገብ።
- ክብደትን መቀነስ እና አልኮልን መገደብ።
- የህክምና ክትትል (Medication and Monitoring):
- ሀኪምዎ የሚያዝልዎትን የደም ግፊት መቆጣጠሪያ መድሃኒቶች (ለምሳሌ እንደ ACE inhibitors, ARBs, Diuretics ወይም CCBs) ሳይቆራረጡ በየቀኑ ሁሌም በተመሳሳይ ሰዓት መውሰድ።
- በቤት ውስጥ የደም ግፊትን በየጊዜው መለካት እና ከሀኪምዎ ጋር በመመካከር የህክምና ግቡ የተመታ መሆኑን ማረጋገጥ።
እነዚህን የሕክምና ግቦች መረዳት በጤናዎ ላይ የተሻሉ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ እና ለጤናማ ህይወት አስፈላጊ እርምጃዎችን እንዲወስዱ እንደአንድ ግብኣት ይረዳል ።




