የእግር ጣቶች መጣመም
የእግርዎ ጣቶች ላይ መታጠፍ፣ መደራረብ ወይም ምቾት የሚነሳ እብጠት መጀመሩን ካስተዋሉ ብቻዎን አይደሉም። የእግር ጣቶች ጥመት በሚያስደንቅ ሁኔታ በብዙ ሰዎች ላይ የሚያጋጥም የተለመደ ችግር ሲሆን ብዙውን ጊዜ ቀስ በቀስ እየተባባሰ ስለሚሄድ ብዙ ሰዎች የህክምና እርዳታ ከማግኘታቸው በፊት ከባድ ህመም እስኪያዩ ድረስ ይጠብቃሉ። መልካሙ ዜና፣ አብዛኛዎቹ የእግር ጣቶች ቅርጽ መበላሸት በተለይ በጊዜ ወደ ሃኪሞች ከተሄደ በህክምና መስተካከል የሚችሉ መሆናቸው ነው። በዚህ ጽሁፍ የተለመዱ የእግር ጣቶች ቅርጽ ችግሮችን እና መፍትሄዎችን እናያለን።
የተለመዱ የጣት ቅርጽ እክል ዓይነቶች
ሁሉም የእግር ጣት ጥመቶች ተመሳሳይ አይደሉም። ስለዚህም የተጣመሙበት ልዩ ቅርፅ እና እጥፋት አይነታቸውን ይወስናል። ከነዚህም ወስጥ:-
- ሃመርቶ(መዶሻ ጣት):- የእግር ጣት መካከለኛ መገጣጠሚያ ወደ ታች በመታጠፍ ጣቱን እንደ መዶሻ ሲያደርገው አብዛኛውን ጊዜ በሁለተኛው የእግር ጣት ላይ ያጋጥማል።
- ማሌትቶ:- ከመዶሻ እግር ጋር ተመሳሳይ ሲሆን መታጠፉ የሚከሰትው ግን ከእግር ጥፍር አጠገብ ባለው የጣት መገጣጠሚያ ላይ ነው።
- ክላውቶ፡- የእግር ጣት ወደላይ ቅስትን በመፍጠር በሁለቱም መካከለኛ የጣት መገጣጠሚያዎች ላይ ወደታች ታጥፎ የጫማዎን ሶል ይቆፍራል።
- ቡኒዮንስ(ሃሉክስ ቫልገስ)፡- በትልቁ የእግር ጣት ላይ የሚፈጠር የአጥንት እብጠት ትልቁን ጣት ወደ ውስጠኛ ሌሎች የእግር ጣቶች እንዲጣመም ያደርገዋል።
ለምን ይከሰታል?
የእግር ጣት መጣመም ብዙውን ጊዜ የሚመጣው በጡንቻዎች፣ ጅማቶች ወይም ስሮች ላይ ባለ የሚዛን አለመመጣጠን ሲሆን ብዙ ምክንያቶች ይህንን አለመመጣጠን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ከነዚህም ውስጥ:-
- ትክክል ያልሆነ ጫማ፡- ጠባብ እና ሾጣጣ የሆኑ ከፍተኛ ታኮ ያላቸው ጫማዎች የእግር ጣቶችን ተፈጥሮአዊ ከሆኑ ቦታዎች ውጪ እንዲጨመቁ ያደርጋሉ።
- አደጋ፡- ከአደጋ ወይም ስብራት በሁዋላ በትክክል ያልተፈወሰ የእግር ጣት ሊጣመም ይችላል።
- በዘር የሚመጣ፡- ለእግር ጣት መጣመም የሚያጋልጡ እንደ ጠፍጣፋ ወይም ከፍተኛ ቅስት ያላቸው እግሮች ከወላጆች ወርሰህ ሊሆን ይችላል።
- የጤና ሁኔታዎች፡- እንደ ስኳር በሽታ እና ሩማቶይድ አርትራይተስ ያሉ ነርቮች ወይም የእግር መገጣጠሚያ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ የጤና ሁኔታዎች የእግር ጣቶች አሰላለፍ ላይ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ።
ሕክምና፡- ከቤት እስከ ቀዶ-ጥገና ክፍል
የሕክምና ዓላማው ህመምን መቀነስ እና እንቅስቃሴን መጨመር ሲሆን የእግር ጣትዎ መገጣጠሚያ አሁንም ተንቀሳቃሽ ወይም ግትር ከሆነ ሐኪምዎ የሚከተሉን ሊመክርዎ ይችላል።
የጫማ ለውጦች:- ሰፊና ጥልቅ የሆነ የጣት ማረፊያ ወዳለው ጫማ መቀየር እና ከ2 ኢንች በላይ ተረከዝ ካላቸው ጫማዎች መራቅ።
መደረቢያ እና ፕላስተሮች:- የእግርን ጣት ለማስተካከል እና ግጭትን ለመከላከል መደረቢያዎችን ወይም የአትሌቲክስ ፕላስተሮችን መጠቀም።
ኦርቶቲክስ:- ከተጎዱ መገጣጠሚያዎች ላይ ጫናን በመቀነስ የሚወስዱ እና ክብደትን እንደገና የሚያከፋፍሉ የጫማ ሶሎችን መጠቀም።
የአካል-ብቃት እንቅስቃሴ:- በጣቶችዎ ፎጣ እንደማንሳት ያሉ የጣት ውስጣዊ ጡንቻዎችን ለማጠናከር የሚደረጉ የጣት ስፓርቶችን መስራት።
ቀዶ-ጥገና:- ጉዳቱ ግትር ወይም የሚያሠቃይ ከሆነ፣ የፖዲያትሪስት ሃኪምዎ ጅማትን ለማስለቀቅ ወይም አጥንትዎን ለማስተካከል ቀላል የቀዶ-ጥገና ሂደትን ሊያደርግ ይችላል።
ባለሙያ ማየት መቼ ያስፈልጋል?
የሚከተሉት ችግሮች ካጋጠምዎ ከባለሙያ ጋር ቀጠሮ መያዝ አለብዎ።
- የለመዱዋቸውን ጫማዎች እንዳይለብሱ የሚከለክል የማያቋርጥ ህመም
- ክፍት ወይም በጣት መካከል የተደበቁ ቁስሎች
- በመገጣጠሚያዎች ላይ እብጠት፣ መቅላት ወይም ሙቀት
- በሚዛን ወይም አረማመድ ላይ ለውጥ ሲኖር




