ውርጃ (Abortion)
ውርጃ ምንድን ነው?
ውርጃ ማለት ፅንስ 28 ሳምንት ከመሆኑ በፊት በተለያየ ምክንያት መቋረጥ ማለት ነው። ከ50-70% የሚፈጠር እርግዝና እናቶች እርጉዝ መሆናቸው ሳይታወቅ ይቋረጣሉ።ከእነዚህ ውስጥ 80% ውርጃ የሚፈጠረው እርግዝናው 12 ሳምንት ከመሆኑ ወይም ከ3 ወር በፊት ነው።
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በዓለማችን ላይ ከሚፈጠሩ እርግዝናዎች ውስጥ ከ 8 – 20% የሚሆኑት ከ 20 ሳምንታት በፊት ይቋረጣሉ።
ውርጃ በሁለት አይነት መንገድ ይከሰታል። የመጀመሪያው ምንም አይነት የህክምና ጣልቃ ገብነት ሳይኖር በራሱ የሚከሰት(spontaneous Abortion) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በእናትየው ፍላጎት በመድሀኒት/በመሳሪያ የሚደረግ(Induced abortion) ነው።
ውርጃ ይፈቀዳል ወይ ?
በኢትዮጵያ ሕግ ውርጃ በተወሰኑ ልዩ ሁኔታዎች ብቻ ይፈቀዳል። ከእነዚህም መካከል ፣
- እርግዝናው የእናትዬዋን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ ።
- ፅንሱ ከተወለደ በኋላ በሕይወት መቆየት እንዳይችል የሚያደርግ የጤና እክል ካለው።
- በመደፈር ወይም በዝምድና ግንኙነት (incest) የተከሰተ እርግዝና ከሆነ።
- እናትየዋ ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰች ሕፃን ወይም የአእምሮ እክል ያለባት ከሆነች።
- ሕይወት አድን አስቸኳይ የሕክምና ድጋፍ በሚያስፈልግበት ጊዜ።
ለውርጃ የሚያጋልጡ ሁኔታዎችስ ምንድን ናቸው?
ውርጃ እጅግ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩትም ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።
1.የዘረ መል ችግር (chromosomal abnormality)
የትኛውም ፅንስ ሲፈጠር ከሴት 23 ከወንድ 23 በመውረስ 46 chromosome ይዞ ይፈጠራል። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ይህ ሂደት ሊበላሽ ወይም ሊዛባ ይችላል። አንዳንዱ 45, አንዳንዱ 47 አልፎ አልፎ ደግሞ 69 ክሮሞዞም ይዞ ይፈጠራል። ይህም ፅንሱ እድገት እንዳይኖረው እና በውርጃ መልክ እንዲወጣ አስተዋፅኦ ያደርጋል። Down syndrome, Edward syndrome, Patau syndrome የተባሉ የክሮሞዞም ችግሮች ለዚህ ተጠቃሽ ምሳሌ ናቸው።
2.የስኳርና የታይሮይድ ችግር
የስኳር ህመም በፅንስ እድገት ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ያደርጋል። በተለይም የስኳር መጠናቸውን ባልተቆጣጠሩ ሴቶች ላይ ተደጋጋሚ ውርጃ እንዲሁም የአፈጣጠር ችግር ሊኖር ይችላል።
3. የማህፀን ግድግዳ እርስ በርስ መጣበቅ (Asherman syndrome)
የማህፀን ግድግዳ በኢንፌክሽን ፣ በተደጋጋሚ ውርጃ (induced abortion)፣ በሰርጀሪ እንዲሁም በተፈጥሮአዊ መንገድ ሲጣበቅ የተፈጠረው ፅንስ ማህፀን ውስጥ እንዳይጣበቅና እንዳያድግ ይሆናል።
4.የማህፀን ግድግዳ አፈጣጠር ችግር (Uterine Anomalies)
ብዙ አይነት የማህፀን አፈጣጠር ችግር ያሉ ሲሆን አንዳንዶቹ ሁለት ክፍል ያለው (Septated) ፤ አንዳንዱ ሁለት ራስ (bicornuate) ፤ አንዳንዱ ሁለት የተለያየ ማህፀን (didelphys) ሆነው ሊፈጠሩ ይችላሉ።
አብዛኛውን ጊዜ ከተደጋጋሚ ውርጃ ጋር የሚገናኘው ሁለት የተለያየ ክፍል ያለው የማህፀን ግድግዳ (septate uterus) ነው።
5. የማህፀን ግድግዳ እጢ (leiomyoma)
ይህ እጢ ምንም ምልክት ሳያሳይ ብዙ ሴቶች ላይ የሚገኝ ሲሆን ጥቂት ሴቶች ላይ የመካንነት ወይም ተደጋጋሚ ውርጃ ሊያስከትል ይችላል።
6. ኢንፌክሽን
በተለያዩ የባክቴሪያና የቫይረስ ኢንፌክሽኖች እንደ CMV, TOXOPLASMA, CHLAMYDIA, MYCOPLASMA የመሳሰሉ ኢንፌክሽኖች ለውርጃ ሊዳርጉ ይችላሉ። በተለያዩ እንፌክሽኖች ምክንያት የሚኖር የሰውነት ትኩሳት 37.8ºC ወይም ከዚያ በላይ ያላቸው ነፍሰ ጡር ሴቶች ፅንስ የማስወረድ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
7. የደም መርጋት በሽታ (Thrombophilia)
በሰውነት ደም ስር ውስጥ ደም በተለያዪ ምክንያቶች ሊረጋና ደም ስር ሊዘጋ ይችላል። SLE ,APAS እንዲሁም የተለያዩ የዘረ መል አፈጣጠር ችግሮች ደም እንዲረጋና ወደ ፅንሱ የሚወስደውን የደም ስር በመዝጋት እድገት እንዳይኖረውና በውርጃ መልክ እንዲወጣ ሊያደርጉ ይችላሉ።
8. አልኮል፣ ሲጋራ እና ከፍተኛ ካፊን ያላቸው ነገሮች
አልኮልና ሲጋራ በየትኛውም የእርግዝና ጊዜ በጭራሽ መወሰድ የሌለባቸው ሲሆን ከተወሰዱ ግን ውርጃ የመከሰት እድሉን ከፍ ያደርጉታል። በቀን ከ 10 በላይ ሲጋራን ማጨስ ፅንስ የማስወረድ ዕድልን ይጨምራል፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የካፌይን መጠን ያላቸው መጠጦችን አብዝቶ መጠቀም ውርጃን ሊያስከትሉ ይችላሉ።ጥናቶች እንደሚያሳዩት ካፌይን (ቡና) መውሰድ የፅንስ መጨንገፍ አደጋን አይጨምርም፡፡ ነገር ግን በጣም ከፍተኛ የሆነ የካፌይን መጠን ማለትም 1000 ሚግ ወይም 10 ኩባያ ቡና ከ 8 – 10 ሰዓት ውስጥ ከተወሰደ ለውርጃ የመጋለጥ እድልን ይጨምራል።
9. ጨረርና የኬሞቴራፒ መድሀኒቶች
ጨረርና ኬሞቴራፒ በከፍተኛ ሁኔታ ውርጃ ሊያስከትሉ ይችላሉ። የትኛዋም ነፍሰ ጡር እናት ቀጨረር የመጋለጥ እድሏን መቀነስ አለባት።
10. የማህፀን ጫፍ መድከም (cervical insufficiency)
በተለይም ደግሞ በሁለተኛው የእርግዝና ወቅት (2nd Trimester) የሚኖር የእርግዝና መቋረጥ ምክንያቱ የማህፀን ጫፍ መስነፍ/መድከም ሊሆን ይችላል።
ይህም በሰርጀሪ ፣በወሊድ ጊዜ በሚያጋጥም መተርተር እንዲሁም በተፈጥሮ የማህፀን ጫፍ መድከም ሊያጋጥም ይችላል።
11. አደጋ
በማሕፀን ላይ የሚደርስ አደጋ የፅንስ መጨንገፍ ዕድልን ከፍ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህ አንዳንድ እንደ ቅድመ ወሊድ ያሉ ምርመራ (Amniocentesis, Chorionic villi sampling) ዓይነቶችን ያጠቃልላል።
12. ሌሎች ምክንያቶች
በዕድሜ የገፉ ሴቶች ከወጣት ሴቶች ይልቅ ለውርጃ የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው ።
ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ክስተት(ውርጃ) ከነበረ ፣ የጨረር ሕክምናዎች፣ ለአካላዊ እና ለአካባቢያዊ ውጥረት መዳረግ ለፅንስ መውረድ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ።
ምልክቶቹስ ምንድን ናቸው?
በጣም የተለመዱት ምልክቶቹ በመጀመሪያ የእርግዝና ወቅቶች አካባቢ በማሕፀን በኩል የደም መፍሰስ እና ከእንብርት በታች የሆድ ሕመም መከሠት ናቸው።
ይሁን እንጂ በጤነኛ እርግዝና ሒደት ላይም የደም መፍሰስ እና ምቾት ማጣት ሊከሠት ይችላል፡፡ ይህም ብዙውን ጊዜ በራሱ የሚስተካከል ሲሆን የጤና ባለሙያን ማማከር ግን አስፈላጊ እና ጠቃሚ ነው።
የውርጃ ዓይነቶች
ምንም አይነት የህክምና ጣልቃ ገብነት ሳይኖር በራሱ የሚከሰት(spontaneous Abortion) የተለያዩ የውርጃ ዓይነቶች አሉ እነሱም ፦
አስጊ የፅንስ መጨንገፍ (Threatened abortion) ፦በእርግዝና መጀመሪያ አካባቢ የደም መፍሰስ ቢኖርም ነገር ግን እናትዬዋ ሌሎች አስጊ ምልክቶች አይኖሯትም ማለት ነው። የማሕፀን በር እንደተዘጋ ይቆያል፡፡ የማሕፀን መጠንም ከፅንሱ ዕድገት ጋር ተመጣጣኝ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ፅንሱ በሕይወት አለ ማለት ነው፡፡ ( በልብ ምት ወይም በአልትራሳውንድ ምርመራ ሊታወቅ ይችላል) ፡፡ የብዙ እናቶች ዕጣ ፈንታ የሚሆነውም የደም መፍሰሱ እየቀነሰ ይሔድ እና እርግዝናው እስከ መጨረሻው ሊቀጥል ይችላል፡፡ በአንዳንድ እናቶች ደግሞ የደም መፍሰሱ እየከበደ እና የፅንስ መውረድ ሊከሠት ይችላል፡፡
የማይቀር የፅንስ መጨንገፍ (Inevitable abortion) ፡- በዚህ ጊዜ የፅንሱ መውረድ አይቀሬ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የማሕፀን ጫፍ በር ክፍት ይሆናል፡፡ የደም መፍሰስ ከባድ እየሆነ ወይም እየጨመረ ይሔዳል፡፡ የሆድ ቁርጠትና የእንሽርት ውኃ መፍሰስ ይኖራል ማለት ነው።
ያልተሟላ የፅንስ መጨንገፍ (Incomplete abortion) ፡-ቁርጥራጭ የፅንስ አካል መውጣት እና የደም መፍሰስ ይኖራል፡፡ ነገር ግን የተወሰነ የፅንስ አካል እና የእንግዴ ልጅ በማሕፀኗ ውስጥ ቀርቷል ማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜም የማሕፀን ጫፍ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡ የደም መፍሰስ ከባድ ሊሆን እና ሊቀጥል ይችላል፡፡
ሙሉ የፅንስ መጨንገፍ (Complete abortion) ፡- ይህም ያለ ሕክምና እርዳታ ሙሉ ለሙሉ ፅንሱ ወርዷል ማለት ነው። ይህ ከ 12 የእርግዝና ሳምንታት በፊት የተለመደ የውርጃ ዓይነት ነው፡፡ ምርመራ በማድረግም የማሕፀን በር እንደተዘጋ ማወቅ ይቻላል። በተጨማሪም በማሕፀን ውስጥ የእርግዝና ከረጢት ምልክት አይታይም፡፡ ይህንንም በአልትራሳውንድ ምርመራ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
ኢንፌክሽን የፈጠረ የፅንስ መጨንገፍ (Septic abortion) ፡-አንዳንድ ሴቶች ፅንስ ከአስወረዳቸው በኋላ ማሕፀናቸው ኢንፌክሽን ሊፈጥር ይችላል። ምልክቶቹም ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት ፣ የሆድ ሕመም፣ በማሕፀን በኩል ደም መፍሰስ እና ወፍራም መጥፎ ሽታ ያለው የማሕፀን ፈሳሽ ናቸው።
ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ውርጃ የሚባለው ምንድን ነው?
ውርጃ ደኅንነቱ ያልተጠበቀ የሚባለው ከሚከትሉት ውስጥ አንዱን ወይም ሁለቱንም ሲያሟላ ነው።
- አስፈላጊው የሕክምና ባለሙያ በአልሆነ ሰው ከተከናወነ ወይም
- የሕክምና ደረጃን በማይመጥን አካባቢ ከተፈፀመ ነው።
የሚደረጉ ምርመራዎች?
ውርጃ ምልክቶችን በማየት እና አካላዊ ምርመራዎችን በማድረግ እንዲሁም በሕክምና መሣሪያዎች ምርመራ ሊታወቅ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የደም መፍሰስ፣ የማሕፀን በር ክፍት መሆን ወይም የፅንሱን አካል በማሕፀን በር ጫፍ ላይ በማየት ሊሆን ይችላል፡፡
አልትራሳውንድ – ይህ ምርመራ መጀመሪያ ላይ ፅንሱ በሕይወት መኖር አለመኖሩን ለማየት ይጠቅማል። ውርጃው ከተፈጸመ በኋላ ደግሞ ፅንሱ ሙሉ በሙሉ መጠረግ አለመጠረጉን ለማየትም ያገለግላል።
የሕክምና አማራጮች ምንድን ናቸው?
አብዛኛው ጊዜ ፅንስ መውረድ ከጀመረ ማስቆሚያ የሕክምና መንገድ የለውም፡፡ የፅንሱ መውረድ የማይቀር በሚሆንበት ወይም ሙሉ በሙሉ በአልተጠናቀቀበት ጊዜ የእናትዬዋ ጤና እና ሌሎች ሁኔታዎች ላይ በመመርኮዝ የተለያዩ የሕክምና አማራጮች አሉ፡፡
ሦስቱ ዋና ዋና አማራጮች ፡- ቅርብ ክትትል፣ መድኃኒት ወይም የማሕጸን መጥረግ ሕክምና ናቸው፡፡
- የቅርብ ክትትል – ሙሉ በሙሉ ፅንሱ የወረደባቸው ሴቶች ላይ እና በሙሉ ጤንነት ላይ ያሉ ከ13ኛው የእርግዝና ሳምንት በፊት ውርጃ የአጋጠማቸው ሴቶች በጤና ባለሙያ የቅርብ ክትትል ማድረግ ብቻውን በቂ ነው። ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንታት ባለው ጊዜ ወስጥ የማሕፀኑ ይዘቶች በራሳችው ይወጣሉ፡፡ ይህም ከሆነ በኋላ ቀሪ የሽል አካል አለመኖሩን ለማረጋገጥ የአልትራሳውንድ ምርመራ ይደረጋል፡፡
- የመድኃኒት ሕክምና – በአንዳንድ ሁኔታዎች ሽሉ በሙሉ እንዲወጣ ማሕፀንን ለማነቃቃት መድኃኒቶች ይሰጣሉ፡፡ መድኃኒቱ በአፍ ወይም በብልት ሊሰጥ ይችላል፡፡
- የማሕፀን መጥረግ ሕክምና – ለፅንስ መውረድ ከተለመደው ሕክምና አንዱ (manual vacuum aspiration) ቀጭን ቱቦ በመጠቀም የማሕፀኑን ይዘት ስቦ የሚያወጣ መሣሪያ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ (dilation and curettage) የማሕፀንን በር በማስፋት የሚስብ እና ረጋ ያለ የመቧጠጥ እንቅስቃሴ ያለው መሣሪያ በመጠቀም የማሕፀኑን ይዘቶች ለማስወገድ የሚጠቀም ሕክምና ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሕክምና ከባድ የደም መፍሰስ ወይም ኢንፌክሽን ላለባቸው ሴቶች ይመከራል፡፡
ከውርጃ በኋላ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎችስ ምን ምን ናቸው ?
- ውርጃን ተከትሎ ለሚመጡት ሁለት ሳምንታት ሴቶች ከወሲባዊ ግንኙነት እንዲታቀቡ ወይም በብልት ውስጥ ማንኛውንም የንጽሕና መጠበቂያ ቁስ እንዳይከቱ ይመከራሉ። ያልታቀደ እርግዝናን ለመከላከል የወሊድ መቆጣጠሪያ ወዲያውኑ መጀመር ያስፈልጋል፡፡ በማሕፀን ወስጥ የሚቀመጥን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት የወሊድ መቆጣጠሪያ ሊጀመር ይችላል።
- የማሕፀን መጥረግ ሕክምና ከተካኼደ በኋላ ኢንፌክሽንን ለመከላከል የሚሰጠውን መድኃኒት በአግባቡ መውሰድ ያስፈልጋል። ከውርጃ በኋላ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከባድ የደም መፍሰስ፣ ከባድ የሆድ ሕመም ካለ ወደ ጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል ።
- የደም ዓይነት Rh ኔጌቲቭ (Rh negative) ከሆነ አንታይ ዲ (anti-D) የተባለ ለቀጣይ እርግዝና ሾተላይ እንዳይከሠት የሚከላከል መድኃኒት መሰጠቱን ማረጋገጥ አለብን።
- ሥነ ልቦና ጤንነት – የእርግዝና መጨናገፍ ከፍተኛ ሐዘን ያስከትላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህ ስሜት ጠንካራ እና ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል። አንዲት ሴት በእርግዝና ማጣት ምክንያት የሚሰማት ጥልቅ ሐዘን እና ድብርት ለበርካታ ሳምንታት የሚቀጥል ከሆነ የሥነ ልቦና አማካሪ ማነጋገር ይመከራል።
- እንደገና ለማርገዝ ከመሞከር በፊት በተለምዶ ከ 2 እስከ 3 ወር መጠበቅ እንደሚገባ ቢነገረም፤ ከዚያ በአነሰ ጊዜ ማርገዝ የተለየ አደጋ እንደሌለው ጥናቶች ያሳያሉ። ይሁንና እርግዝናው የተፈለገ እና የታቀደ መሆን አለበት፡፡
የፅንስ መጨናገፍ (ውርጃን) እንዴት መከላከል ይቻላል?
ብዙውን ጊዜ የፅንስ መጨናገፍን መከላከል ባይቻልም የጤናማ እርግዝና የመሆን ዕድልን ለመጨመር ጥንቃቄ ማድረግ ይቻላል። ይህም የሚከተሉትን ያካትታል።
- ፎሊክ አሲድ እና ካልሲየም ያለው ምግብ መመገብ (ፍራፍሬዎች፣ ዓሣ፣ የተጣራ ወተት የመሳሰሉት)
- የቅድመ ወሊድ ቫይታሚኖችን መውሰድ
- ሐኪም በሚፈቅደው ልክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ
- ጤናማ የሰውነት ክብደት እንዲኖር ማድረግ
- አደንዛዥ ዕፅ፣ አልኮል እና ሲጋራ ማስወገድ
- ያልተጣራ የወተት ተዎጽዖ፣ ጥሬ ሥጋ አለመመገብ
- የሚወስዱትን የካፌን መጠን መገደብ
- ከዚህ በፊት የሚወስዷቸው መድኃኒቶች ካሉ ከሐኪም ጋር መነጋገር
- የቅድመ ወሊድ ቀጠሮዎች እንዳያመልጡ በሚገባ መከታተል፤ ከሐኪም ጋር በማንኛውም የሚያሰጋ ወይም የሚያሳስብ ጉዳይ ላይ መወያየት
- ትኩሳት፣ የሆድ ሕመም፣ የፅንሱ እንቅስቃሴ መቀንስ ወይም የደም መፍሰስ ካጋጠመ ወዲያውኑ ወደ ጤና ተቋም መሄድ ይገባል፡፡
በቀጣይ እርግዝና ወቅት መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች ምን ይመስላሉ ፦
- የቅድመ ወሊድ ክትትልን በአግባቡ ማድረግ
- ስለ እርግዝና አደገኛ ምልክቶች የበለጠ ለማወቅ ሐኪምን ማማከር
- የፅንሱን እንቅስቃሴ መከታተል – ከ18 እስከ 22 የእርግዝና ሳምንታት ጀምሮ ፅንሱ መንፈራገጥ ይጀምራል፡፡ በየቀኑ ጠዋት እና ማታ የሕፃኑን እንቅስቃሴዎች መዝግቦ መያዝ፡፡ በ 2 ሰዓት ጊዜ ውስጥ ቢያንስ 10 እንቅስቃሴዎች ሊሰማ ይገባል። የፅንሱ እንቅስቃሴ እየተሰማ ከአልሆነ ጣፋጭ ነገር ወስዶ በጎን ጋደም በማለት ለመከታተል መሞከር። የፅንሱ እንቅስቃሴ ከቀነሰ ወይም ከጠፋ ወደ ጤና ተቋም መሄድ፡፡




