የአሜባ ኢንፌክሽን (Amebiasis) በሆድ ዕቃ/አንጀት ውስጥ የሚገቡ ጥገኛ ተህዋሲያን (ፓራሳይት) አማካኝነት የሚመጣ ኢንፌክሽን ነው። ይህ ኢንፌክሽን የሚከሰተው ኢንታሜባ ሂስቶሊቲካ (Entamoeba histolytica) በተባለ ጥገኛ ተህዋስ ምክንያት ነው። ለኢንታሜባ ሂስቶሊቲካ (Entamoeba histolytica) ጥገኛ ተህዋሲያን ብቸኛው መኖሪያ ሰው ነው። ይህ ጥገኛ ተህዋስ በሰገራ አማካኝነት በእንቁላል (ሲስት/Cysts) መልክ ከሰውነት የሚወጣ ሲሆን፤ እርጥበት አዘል እና ሞቃት በሆኑ አካባቢዎች ውስጥ እስከ በርካታ ሳምንታት ድረስ የመቆየት አቅም አለው። እነዚህ ጥገኛ ተዋሕሲያን በትልቁ አንጀት ውስጥ ስለሚኖሩ፣ በበሽታው በተያዙ ሰዎች ሰገራ ውስጥ ይወጣሉ። የንፅህና ሁኔታ ዝቅተኛ በሆነባቸው ቦታዎችም የውሃ አቅርቦቶችን ሊበክሉ ይችላሉ። በተጨማሪም የሰው ሰገራ እንደ ማዳበሪያ በሚጠቀምባቸው አካባቢዎች የሚበቅሉ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን ሊበክሉ ይችላሉ። በበሽታው የተያዙ ሰዎች እጃቸውን በበቂ መጠን ወይም በትክክል ካልታጠቡ ጥገኛ ተዋሕሲያኑ በቆሸሹ እጆቻቸው አማካኝነት ወደ ሌሎች ሰዎች ሊተላለፉ ይችላሉ።
ማንኛውም ሰው በአሜባ ኢንፌክሽን ሊያዝ ይችላል። ነገር ግን የንፅህና ሁኔታቸው ዝቅተኛ በሆነባቸው ሞቃታማ አካባቢዎች ለሚኖሩ ወይም ወደእነዚህ አካባቢዎች ለሚጓዙ ሰዎች በሽታው የመከሰቱ ዕድል የበለጠ ነው። በዓለም ላይ ከሚኖሩ ሰዎች ውስጥ ወደ 10% የሚሆኑት በአሜባ ሊያዙ ይችላሉ። በተለይም በሜክሲኮ፣ ሕንድ፣ ማዕከላዊ አሜሪካ፣ ደቡብ አሜሪካ፣ አፍሪካ እና ሞቃታማ የእስያ አካባቢዎች በሚኖሩ ሰዎች ዘንድ በብዛት ይገኛል።
ይህ ኢንፌክሽን ሊተላለፍ የሚችለው፦
- የተበከለ ምግብ፣ ለምሳሌ በተበከለ ውሃ የታጠቡ ፍራፍሬዎች ወይም አትክልቶችን በመመገብ
- ፓስተራይዝድ ያልሆነ (Unpasteurized) ወተት፣ አይብ ወይም ሌሎች የወተት ተዋጽኦዎች መጠቀም
- የተበከለ ውሃ ወይም በረዶ መጠቀም
- የተበከሉ እቃዎች ነክቶ ከዚያ አፍን መንካት።
- ዝንቦችና በረሮዎች አንዳንድ ጊዜ የአሜባ ተህዋሲያንን ከሰገራ ወደ ምግብ ሊያስተላልፉ ይችላሉ።
- አፈር መብላት በአንዳንድ ባህሎች በስፋት የሚታወቅ ልማድ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ የአሜቢያሲስ ኢንፌክሽን ምንጭ ሊሆን ይችላል።
የአሜባ ኢንፌክሽን ምልክቶች
እንደ የአሜሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከያ ማዕከል (CDC) መረጃ፣ አሜቢያሲስ (Amebiasis) ካለባቸው ሰዎች ውስጥ ወደ 10 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑት ብቻ በኢንፌክሽኑ ምክንያት ይታመማሉ። ምልክቶች በሚታዩበት ጊዜም እንኳ አብዛኛውን ጊዜ ቀላል ናቸው። ምልክቶቹ ብዙውን ጊዜ ከ2 እስከ 4 ሳምንታት ውስጥ የሚጀምሩ ቢሆንም በኋላ ላይም ሊታዩ ይችላሉ።
አንዳንድ ሰዎች ላይ ምልክቶቹ ቀላል ሲሆኑ፣ በታችኛው የሆድ ክፍል ቀላል ሕመም እና የሆድ ውስጥ የሚሰማ ድምፅ እንዲሁም በቀን 2 ወይም 3 ጊዜ ለስላሳ ሰገራ መውጣት ሊኖር ይችላል። በሌሎች ሰዎች ግን እነዚህ አሜባዎች የአንጀትን ግድግዳ ሊወሩ ይችላሉ፤ ይህም በአንጀት ላይ ቁስለት፣ መድማት እና ተቅማጥ የሚያስከትል በሽታ (Amebic dysentery) እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል። በተጨማሪም ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከባድ የሆድ ሕመም፣ ደም የቀላቀለበት ተቅማጥ እና በቀን 10 ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ ተቅማጥ ያስከስታሉ።
አልፎ አልፎ፣ እነዚህ አሜባዎች በደም ዝውውር በኩል ወደ ጉበት በመድረስ አብሰስ (Abscess) ማለትም የመግል ክምችት ሊፈጥር ይችላል። ምልክቶቹ ትኩሳት እና በላይኛው የቀኝ የሆድ ክፍል ላይ ሲነካ የሚሰማ ሕመም ሊያካትቱ ይችላሉ። በጣም ጥቂት በሆኑ ሁኔታዎች ደግሞ ጥገኛ ተዋሕሲው ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች፣ ለምሳሌ ወደ ሳንባ እና አንጎል፣ ሊዛመት ይችላል።
የአሜባ ኢንፌክሽን የሚያስከትላቸው ተጨማሪ የጤና እክሎች (Complications)
የአሜባ ኢንፌክሽኖች በምግብ መፈጨይ ሥርዓት ላይ ከባድ ችግሮችን ሊያስከትሉ ወይም ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊሰራጩ ይችላሉ። እነዚህ የጤና እክሎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
- የትርፍ አንጀት በሽታ (Appendicitis)
- ከባድ የአንጀት እብጠት እና መስፋፋት (ቶክሲክ ሜጋኮሎን /Toxic megacolon)
- የጉበት ወይም የአእምሮ መግል የያዘ እብጠት (Liver or brain abscess)
- የሆድ ክፍልን እና ሆድ ዉስጥ ያሉ አካላት ላይ የሚከሰት የተሰራጨ ኢንፌክሽን (Peritonitis)
- በሳንባ ውስጥ መግል መከማቸት (Empyema)
- የልብ ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች (Pericarditis)
የአሜባ ኢንፌክሽን ምርመራ
የጤና ባለሙያዎች የአሜባ ኢንፌክሽን ምርመራ የሰገራ ምርመራ በማድረግ ያረጋግጣሉ። ለበርካታ ቀናት የሰገራ ናሙናዎችን እንዲሰጡ ሊጠየቁ ይችላሉ። ይህም የአሜባዎች ብዛት ከቀን ወደ ቀን ሊለያይ እና ከአንድ የሰገራ ናሙና ብቻ ለመለየት በጣም ዝቅተኛ ሊሆን ስለሚችል ነው። የሰገራ ናሙናው በማይክሮስኮፕ ይመረመራል። የጥገኛ ተዋሕሲያን ኢንፌክሽንን እና ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመለየት የሚረዱ ሌሎች ምርመራዎችም አሉ፣ እነሱም፦
- የደም ምርመራ።
- የአልትራሳውንድ ምርመራ (Ultrasound)።
- የሲቲ ስካን (CT scan) ምርመራ
- ሲግሞይዶስኮፒ (Sigmoidoscopy) ወይም ኮሎኖስኮፒ (Colonoscopy)።
ለአሜባ ኢንፌክሽን ምን ዓይነት ህክምናዎች አሉ?
ምርመራዎች የኢንታሜባ ሂስቶሊቲካ (E. histolytica) ህዋስ መኖርን ካረጋገጡ፣ የሕመም ምልክቶች ቢኖሩዎትም ባይኖሩዎትም አሜባ ኢንፌክሽን ህክምና ማግኘት አለበት።
አሜባ ኢንፌክሽን በፀረ ተዋሕሲ መድኃኒቶች (Broad-spectrum antiparasitics) እና በአንጀት ውስጥ ያሉ አሜባዎችን የሚያጠፉ መድኃኒቶች (Luminal amebicides)፣ እንደ ሜትሮኒዳዞል (Metronidazole) ወይም ቲኒዳዞል (Tinidazole) ይታከማል። እነዚህ መድኃኒቶች በዋናነት በአንጀት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። የአሜባ እንቁላሎችን (Cysts) ለማስወገድ የሚረዱ መድኃኒቶች፣ እንደ ፓራሞማይሲን (Paromomycin) እና አዮዶኩዊኖል (Iodoquinol)፣ እንዲሁም ሊሰጡ ይችላሉ። ካስፈለገዎት ሐኪምዎ ማቅለሽለሽን ለመቆጣጠር መድኃኒት ሊያዝልዎት ይችላል።
መድኃኒቶቹን ለአንድ ሳምንት ወይም ከዚያ በላይ መውሰድ ሊያስፈልግዎት ይችላል። ሆኖም ብዙ ሰዎች ሕክምናውን ከጀመሩ በጥቂት ቀናት ውስጥ መሻሻል ይጀምራሉ። ምንም እንኳን ጤናዎ ቢሻሻልም፣ ሐኪምዎ እንዳዘዘው ሁሉንም መድኃኒቶች ሙሉ በሙሉ መውሰድዎን ያረጋግጡ።
ሆኖም ግን መድኃኒት እንደገና ከኢንፌክሽኑ እንዳይያዙ ሊከላከልዎት ስለማይችል፣ አሜባዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች መኖርዎን ወይም ወደእነዚህ አካባቢዎች መጓዝዎን ከቀጠሉ፣ አሜቢያሲስ እንደገና ሊከሰትብዎት ይችላል።
አሜባ ኢንፌክሽንን እንዴት መከላከል ይቻላል?
ተገቢ የንፅህና አጠባበቅ የአሜባ ኢንፌክሽንን ለመከላከል ዋናው መንገድ ነው። ኢንፌክሽኑ በብዛት ወደሚከሰትባቸው አካባቢዎች እየተጓዙ ከሆነ፣ የሚከተሉትን የጥንቃቄዎች ያድርጉ፦
- መፀዳጃ ቤት ከተጠቀሙ በኋላ እና ምግብ ከመንካትዎ ወይም ከማዘጋጀትዎ በፊት እጆችዎን በሳሙናና በውሃ በደንብ ይታጠቡ።
- መታጠቢያ ቤቶችንና መፀዳጃ ቤቶችን በተደጋጋሚ ያፅዱ። በተለይም የመፀዳጃ ቤት መቀመጫዎችንና የውሃ ቧንቧ መክፈቻዎችን በጥንቃቄ ያፅዱ።
- ፎጣዎችን ወይም የፊት መጠረጊያ ጨርቆችን ከሌሎች ጋር አይጋሩ።
- ጥሬ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን በደንብ ይጠቡና ወይም ያብስሉ።
- የተረፈ ምግብ ድጋሜ የሚበሉ ከሆነ እንደገና ያሙቁት።
- ከታሸገ ዕቃ ውስጥ የሚገኝ የታሸገ ውሃ ወይም ለስላሳ መጠጥ ይጠቀሙ። ከማሽን የሚወጡ መጠጦችን አይጠጡ።
- የቧንቧ ውሃ መጠጣት ካስፈለገ፣ አፍልተው ወይም የውሃ ማጣሪያን በመጠቀም ያጣሩት።
- ፓስተራይዝድ ያልሆነ ወተት፣ አይብ ወይም ሌሎች የወተት ተዋጽኦዎችን አይጠቀሙ።
- በመንገድ ዳር ከሚሸጡ ምግቦች ይቆጠቡ።




