ፎርኒየር ጋንግሪን (Fournier’s Gangrene) ምንድን ነው?
ፎርኒየር ጋንግሪን የብልትዎን ወይም በብልት አካባቢ ያሉ የሰውነት ክፍሎችን የሚያጠቃ፣ እምብዛም የማይከሰት ነገር ግን ለሕይወት አስጊ የሆነ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ነው። ይህ በሽታ ኔክሮታይዚንግ ፋሻይቲስ (ሥጋን የሚበላ በሽታ) የተሰኘው የሕመም ዓይነት ሲሆን፣ በፍጥነት የሚባባስ እና አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልገው ነው።
የፎርኒየር ጋንግሪን በሽታን የሚያስከትሉ ባክቴሪያዎች የትኞቹ ናቸው?
የፎርኒየር ጋንግሪን በሽታን የሚያስከትሉት አናሮቢክ (anaerobic) ወይም ኤሮቢክ (aerobic) የሚባሉ የባክቴሪያ ዓይነቶች ናቸው።
- አናሮቢክ ባክቴሪያዎች ኦክሲጅን ባለበት አካባቢ መኖርም ሆነ ማደግ አይችሉም።
- ኤሮቢክ ባክቴሪያዎች ደግሞ ኦክሲጅን ባለበት አካባቢ መኖርና ማደግ ይችላሉ።
የፎርኒየር ጋንግሪን በሽታን በብዛት የሚያስከትሉት ኤሮቢክ ባክቴሪያዎች የሚከተሉት ናቸው፡
- ኢ. ኮላይ (Escherichia coli / E. coli)
- ክሌብሲላ (Klebsiella)
- ፕሮቲየስ (Proteus)
- ስታፊሎኮከስ (Staphylococcus)
- ስትሬፕቶኮከስ (Streptococcus)
የፎርኒየር ጋንግሪን በሽታን በብዛት የሚያስከትሉት አናሮቢክ ባክቴሪያዎች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡
- ባክቴሮይድስ (Bacteroides)
- ክሎስትሪዲየም (Clostridium)
- ፔፕቶስትሬፕቶኮከስ (Peptostreptococcus)
የፎርኒየር ጋንግሪን ምልክቶች
የፎርኒየር ጋንግሪን ምልክቶች በድንገት የሚጀምሩ እና በጣም በፍጥነት እየተባባሱ የሚሄዱ ናቸው።
- ከፍተኛ ሕመም እና እብጠት፦ በብልት፣ በፊንጢጣ ወይም በብሽሽት አካባቢ ድንገተኛ እና ከባድ ሕመም፣ እንዲሁም ሲነካ የሚያም እብጠት መከሰት።
- የቆዳ መቅላትና ትኩሳት፦ የተጠቃው አካባቢ ቆዳ መቅላት፣ ማበጥ እና ሲነካ ሙቀት መኖር።
- መጥፎ ጠረን ያለው ፈሳሽ፦ ከቆዳው ወይም ከቁስሉ አካባቢ እጅግ በጣም መጥፎ ጠረን ያለው ፈሳሽ ወይም መግል መውጣት።
- ትኩሳት እና አጠቃላይ የሕመም ስሜት፦ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ድካም እና የሰውነት መቆራረጥ (ሕመም) ስሜት።
- የቆዳ ቀለም መቀየር (የሕዋስ ሞት ምልክት)፦ በሽታው እየባሰ ሲሄድ የቆዳው ቀለም ወደ ወይን ጠጅ፣ ሰማያዊ፣ ግራጫ ወይም ወደ ጥቁር መቀየር (ይህ የቆዳ ሕዋሳት መሞታቸውን ወይም ጋንግሪን መፈጠሩን ያሳያል)።
- በቆዳ ስር የአየር መከማቸት (Crepitus)፦ ያበጠው ቆዳ ሲነካ ወይም ሲጫን ከቆዳው ስር የአየር አረፋዎች እንዳሉ ዓይነት የሚንኳኳ ወይም የሚፈነዳ ድምፅ/ስሜት መኖር (ይህ የሚከሰተው ባክቴሪያዎቹ በቆዳ ስር ጋዝ ስለሚያመነጩ ነው)።
- የልብ ምት መፍጠን እና የደም ግፊት መቀነስ፦ ኢንፌክሽኑ ወደ ደም ውስጥ ሲሰራጭ (Sepsis) የልብ ምት መጨመር፣ የደም ግፊት መውረድ እና ራስን መሳት ሊያስከትል ይችላል።
- የሕመም ስሜት መጥፋት፦ በመጀመሪያ አካባቢ ከፍተኛ ሕመም ቢኖርም፣ በሽታው የቆዳ ነርቮችን ሲገድል ግን በአካባቢው የመደንዘዝ ወይም ሕመም ያለመሰማት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል።
አጋላጭ ሁኔታዎች
- የስኳር በሽታ (በተለይ በደንብ ያልተቆጣጠሩት ወይም የተወሰኑ የስኳር መድኃኒቶችን የሚወስዱ)
- የበሽታ መከላከል አቅም መዳከም (ለምሳሌ HIV፣ ስቴሮይድ መድኃኒቶች፣ ካንሰር)
- ከፍተኛ የአልኮል መጠጥ አጠቃቀም፣ ማጨስ እና ከባድ ውፍረት
- ሥር የሰደደ የስቴሮይድ አጠቃቀም
- በወንዶች ላይ በብዛት ይታያል (ምንም እንኳን በሴቶች እና በልጆች ላይም ሊከሰት ቢችልም)
በሽታውን ለመለየት ምን አይነት ምርመራዎች ይደረጋሉ?
ብዙውን ጊዜ ለምርመራ የሚሆን በቂ ጊዜ አይኖርም፤ ህመሙ አደገኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በአስቸኳይ ቀዶ ጥገና ሊያስፈልግ ይችላል። ነገር ግን ጊዜ ካለ ሀኪምዎ የሚከተሉትን ምርመራዎች ሊያዝ ይችላል፦
- ሲቲ ስካን (CT scan): የኢንፌክሽኑን መነሻ ለማወቅ በሰውነት ውስጥ የተከማቸ ጋዝ እና ፈሳሽ መኖሩን ያሳያል።
- አልትራሳውንድ (Ultrasound): ይህንን በሽታ ወይም ተመሳሳይ ምልክት ያላቸውን ሌሎች የብልት አካባቢ ኢንፌክሽኖችን ለመለየት ይረዳል። እንዲሁም በቆዳ ስር አየር መኖሩን ይፈትሻል።
- ኤክስ-ሬይ (X-ray / ራጅ): በሰውነት ህብረ ህዋሳት ውስጥ አየር መኖሩን እና የት ድረስ እንደተሰራጨ ለማየት ይረዳል።
- የደም ምርመራዎች: በሰውነት ውስጥ ከፍተኛ ኢንፌክሽን መኖሩን፣ የሰውነት ንጥረ ነገሮች መዛባትን እና የደም መመረዝን (septic shock) ለመለየት ይጠቅማል።
ሕክምና
- አስቸኳላይ የቀዶ ሕክምና (surgical debridement): የሞቱ እና የተበከሉ ሕብረ ሕዋሳትን በፍጥነት ማስወገድ ዋናው እና ወሳኙ ሕክምና ነው።
- አንቲባዮቲክስ፡ ሰፊ ሽፋን ያላቸው የደም ሥር አንቲባዮቲኮች (broad-spectrum IV antibiotics) ወዲያውኑ ይሰጣሉ።
- ድጋፍ ሰጪ እንክብካቤ፡ ፈሳሽ መስጠት፣ የደም ግፊትን ማረጋጋት እና እንደ አስፈላጊነቱ ተደጋጋሚ የቁስል ጽዳት ወይም የመልሶ ግንባታ ቀዶ ሕክምና ማድረግ።
የፎርኒየር ጋንግሪን የሚያስከትላቸው ጉዳቶች
ይህ ሕመም በጊዜ ካልታከመ የሚከተሉትን ከባድ ችግሮች ሊያስከትል ይችላል፦
- የኩላሊት ሥራ ማቆም
- ከባድ የመተንፈስ ችግር (ሳንባ በአግባቡ አየር መቀበል አለመቻል)
- የደም ሥሮች መዘጋት
- ሰገራን በሆድ በኩል በተገጠመ ከረጢት ለማስወጣት መገደድ
- የልብ ድካም (ልብ ደምን በአግባቡ መግፋት አለመቻል)
- የልብ ምት መዛባት (በጣም መፍጠን ወይም መዘግየት)
- የአንጀት እንቅስቃሴ መቆም (ምግብ እና ሰገራ በአንጀት ውስጥ መጓዝ አለመቻል)
- የወሲብ ፍላጎት ወይም የመፈጸም አቅም ማጣት
- ወደ አንጎል የሚሄድ ደም መቋረጥ (የአንድ ጎን ሰውነት መሽመድመድ)
- የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን
ይህ ሕመም እስከ ሞት ድረስ ሊያደርስ ይችላል።
መከላከያ መንገዶች
የፎርኒየር ጋንግሪን በሽታን መከላከል ይቻላል? ጤናማ ሆኖ መቆየት እና እንደ ስኳር በሽታ ወይም የሱስ ችግሮች ያሉ ሌሎች የጤና እክሎችን መቆጣጠር በሽታውን ለመከላከል ምርጡ መንገድ ነው። እንዲሁም የብልት አካባቢዎን የቆዳ ቀለም መቀየር፣ እብጠት እና የህመም ስሜት የመሳሰሉ የኢንፌክሽን ምልክቶች መኖራቸውን አዘውትረው በመፈተሽ የከፋ ጉዳትን መቀነስ ይችላሉ።
ተጋላጭነትዎን ለመቀነስ የሚከተሉትን ያድርጉ፦
- የብልት አካባቢዎን ንጽህና መጠበቅ።
- አካባቢውን የሚላጩ ከሆነ መቆረጥን ለመከላከል ንጹህ እና ስለታም ምላጭ መጠቀም።
- በአካባቢው ለሚፈጠር ማንኛውም ቁስል ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ።
- ተመጣጣኝ የሰውነት ክብደትን መጠበቅ።
- ሲጋራ ማጨስ ወይም ሌሎች የትምባሆ ምርቶችን መጠቀም ማቆም።
የደም ዝውውርዎን ማሻሻልም ተጋላጭነትን ይቀንሳል፤ ለዚህም፦
- ቅባት እና ኮሌስትሮል የበዛባቸውን ምግቦች በመቀነስ ለልብ ጤናማ የሆኑ ምግቦችን መመገብ።
- አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ።




