የጉዞ ማቅለሽለሽ ምንድን ነው? እንዴትስ ማከም ይቻላል?

Eyasu Yebeltal
Nov 20, 2026
Gemini Generated Image l65ua6l65ua6l65u

           የጉዞ ማቅለሽለሽ ምንድን ነው? እንዴትስ ማከም ይቻላል?

በመኪና፣ በአውቶቢስ፣ በአውሮፕላን ወይም በጀልባ ሲጓዙ ማዞር፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ ወይም ምቾት ማጣት ያጋጥምዎታል? ይህ ችግር የጉዞ ማቅለሽለሽ (Motion Sickness) ሊሆን ሲችል፤ በሁሉም ዕድሜ ያሉ ሰዎች ላይ ሊከሰት የሚችል የተለመደ የጤና እክል ነው።

የጉዞ ማቅለሽለሽ ምንድን ነው?

የጉዞ ማቅለሽለሽ በምንጓዝበት ጊዜ አንጎላችን ከዓይኖች፣ ከውስጥ ጆሮ እና ከሌሎች የስሜት ሕዋሳት ከእንቅስቃሴው የሚቃረኑ መረጃዎችን ሲቀበል የሚከሰት ችግር ነው። ለምሳሌ:- በሚንቀሳቀስ መኪና ውስጥ ሲጓዙ ውስጣዊ ጆሮዎ የመንቀሳቀስ ስሜትን ይገነዘባል። ነገር ግን ዓይኖችዎ በሞባይል ስልክ ላይ ካተኮሩ፣ የሚታየው ነገር የማይንቀሳቀስ ሊሆን ይችላል። ይህ የመረጃ አለመጣጣም ማቅለሽለሽንና ማዞርን ሊያስከትል ይችላል።

የጉዞ ማቅለሽለሽ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

የተለመዱ የጉዞ ማቅለሽለሽ ምልክቶች የምንላቸው፦

  • ማዞር
  • ማቅለሽለሽ
  • የምራቅ መብዛት 
  • ማስታወክ
  • ማላብ
  • ራስ ምታት
  • የፊት መገርጣት እና 
  • ድካም ናቸው።

አብዛኛውን ጊዜ ጉዞው ሲቆም እነዚህ ምልክቶች ይቀንሳሉ።

የጉዞ ማቅለሽለሽን እንዴት መከላከል ይቻላል?

ከጉዞ በፊትና በጉዞ ወቅት የሚከተሉትን ቀላል ምክሮች ይተግብሩ፦

  1. ተገቢውን መቀመጫ ይምረጡ፦ በመኪና ወይም በአውቶቡስ የፊት መቀመጫ ላይ፣ በአውሮፕላን ከክንፎቹ አካባቢ እና በጀልባ መሃል አካባቢ ይቀመጡ።
  2. ሩቅ ያለውን አድማስ ይመልከቱ፦ መጽሐፍ ከማንበብ ወይም ስልክ ከመጠቀም ይልቅ ወደ ሩቅ ያለ ነገር ይመልከቱ።
  3. ቀላል ምግብ ይመገቡ፦ ከጉዞ በፊት ከባድና ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች ያስወግዱ።
  4. በቂ እንቅልፍን ያግኙ፦ ድካም የማቅለሽለሽ ስሜትን ሊያባብስ ይችላል።
  5. ንጹህ አየር ያግኙ፦ መስኮት መክፈት ከቻሉ በተሽከርካሪው ውስጥ አየር ያስገቡ።
  6. አልኮልን ያስወግዱ፦ አልኮል መጠጣት ማቅለሽለሽንና ማዞርን ሊያባብስ ይችላል።

የጉዞ ማቅለሽለሽን እንዴት ማከም ይቻላል?

አብዛኛውን ጊዜ ቀላል የጉዞ ማቅለሽለሽ በእረፍት፣ ንጹህ አየር በማግኘትና የጉዞ እንቅስቃሴን በማቆም የሚሻል ሲሆን፤ ምልክቶቹ ካልቀነሱ ወይም በተደጋጋሚ ከተከሰቱ የሚከተሉት መድኃኒቶች ሊረዱ ይችላሉ፦

  • ዳይሜንሃይድራይኔት (Dimenhydrinate)፦ የጉዞ ማቅለሽለሽንና ማስታወክን ለመከላከልና ለማስታገስ የሚያገለግል መድኃኒት ነው።
  • ሜክሊዚን (Meclizine)፦ ከጉዞ ጋር የተያያዘ ማዞርና ማቅለሽለሽን ለመከላከል ይረዳል።
  • ስኮፖላሚን/ሃዮሲን (Scopolamine/Hyoscine)፦ የጉዞ ማቅለሽለሽን ለመከላከል በቆዳ ላይ እንደ ፕላስተር የሚለጠፍ የመድኃኒት አይነት ነው።

እነዚህ መድኃኒቶች እንቅልፍ ማምጣት፣ አፍን ማድረቅና የዓይን እይታን ማደብዘዝ የመሳሰሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊኖሯቸው ይችላል። በተለይም ለህጻናት፣ ለነፍሰ ጡር ሴቶችና ሌሎች የጤና ችግር ላለባቸው ሰዎች ከመጠቀማችን በፊት የጤና ባለሙያዎችን ማማከር አስፈላጊ ነው።

ወደ ህክምና መቼ መሄድ ያስፈልጋል?

ከጉዞ በኋላም ማዞር፣ ማቅለሽለሽ ወይም ማስታወክ ከቀጠለ፣ በተደጋጋሚ ከተከሰተ ወይም ከባድ ራስ ምታትና የሚዛን መጠበቅ ችግር ከተከሰተ የጤና ባለሙያዎችን ያማክሩ። ድንገተኛ የሰውነት ድክመት፣ የመናገር ችግር፣ የደረት ሕመም ወይም ራስን መሳት ከተከሰተ ወዲያውኑ ሕክምናን ያግኙ።

የጉዞ ማቅለሽለሽ የተለመደና መቆጣጠር የሚቻል የጤና ችግር ሲሆን ተገቢውን መቀመጫ መምረጥ፣ ወደ አድማስ መመልከት፣ በጉዞ ወቅት ስልክ ከመጠቀም መቆጠብና በቂ እረፍትን ማድረግ ምልክቶቹን ለመቀነስ ይረዳሉ። እነዚህ የመከላከያ ዘዴዎች በቂ ካልሆኑ ተገቢውን መድኃኒት በመጠቀም ጉዞዎን የበለጠ ምቹ ማድረግ ይችላሉ።

Comments (0)