መሃንነት (Infertility) መንስኤዎቹ፣ ምርመራው እና የሕክምና አማራጮች
ልጅ መውለድ የብዙ ባለትዳሮች ፍላጎት ቢሆንም፣ አንዳንዶች ለረጅም ጊዜ ቢሞክሩም እርግዝና ማግኘት ይቸገራሉ። ይህ ሁኔታ መሃንነት ተብሎ ይጠራል። መሃንነት በወንዶችም ሆነ በሴቶች ላይ ሊከሰት የሚችል የጤና ችግር ሲሆን፣ በትክክለኛ ምርመራና ሕክምና ሊታገዝ ይችላል።
መሃንነት ምንድን ነው?
መሃንነት የወንድ ወይም የሴት የመራቢያ ሥርዓት ችግር ሲሆን፣ መከላከያ ሳይጠቀሙ በመደበኛነት የግብረ ሥጋ ግንኙነት እያደረጉ ለ12 ወራት ወይም ከዚያ በላይ እርግዝና ማግኘት አለመቻል ነው።
መሃንነት በሁለት ይከፈላል፦
- የመጀመሪያ ደረጃ መሃንነት : ከዚህ በፊት ፈጽሞ እርግዝና ካልተከሰተ።
- ሁለተኛ ደረጃ መሃንነት : ቀደም ሲል እርግዝና ከተከሰተ በኋላ እንደገና ለማርገዝ መቸገር።
ምን ያህል ሰዎች በመሃንነት ይጠቃሉ?
የዓለም ጤና ድርጅት በ2023 ባወጣው ሪፖርት መሠረት፣ በዓለም ዙሪያ በመውለድ ዕድሜ ላይ ካሉ ሰዎች መካከል አንድ ከስድስትኛ ያህሉ በሕይወታቸው ወቅት በመሃንነት ይጠቃሉ። ይህም መሃንነት የተለመደ የጤና ችግር መሆኑን ያሳያል።
የመሃንነት መንስኤዎች
መሃንነት ከወንድ፣ ከሴት፣ ከሁለቱም በአንድ ላይ ወይም ምክንያቱ በምርመራ ሊታወቅ በማይችል ሁኔታ ሊከሰት ይችላል።
ሀ. የወንድ መሃንነት መንስኤዎች
የወንድ መሃንነት በአብዛኛው ከዘር ፍሬ ምርት፣ ብዛት፣ እንቅስቃሴ ወይም ቅርጽ ጋር በተያያዙ ችግሮች ይከሰታል።
- የዘር ፍሬ ምርትና ጥራት ችግር፦ የዘር ፍሬ ብዛት መቀነስ፣ እንቅስቃሴው መዳከም ወይም የቅርጽ መዛባት።
- የአካል ችግሮች፦ የዘር ፍሬዎች ወደ ከረጢታቸው አለመውረድ እና Varicocele (በዘር ፍሬ ከረጢት ውስጥ ያሉ ደም መላሽ ቧንቧዎች መስፋት)።
- የሆርሞንና የዘረመል ችግሮች፦ የዘር ፍሬ ምርትን የሚቆጣጠሩ ሆርሞኖች መዛባትና አንዳንድ የዘረመል ችግሮች።
- ኢንፌክሽኖች፦ እንደ ቂጥኝ እና ጨብጥ ያሉ በግብረ ስጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች።
- የዘር ፍሬ መውጣት ችግር፦ በዘር ፍሬ ማስተላለፊያ ቱቦዎች መዘጋት ወይም የወሲብ ችግሮች።
- የአኗኗር ሁኔታዎች፦ ሲጋራ ማጨስ፣ ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት፣ ለጎጂ ኬሚካሎች እና ጨረሮች መጋለጥ።
- የካንሰር ሕክምና፦ ኬሞቴራፒና የጨረር ሕክምና የዘር ፍሬ ምርትን ሊጎዱ ይችላሉ።
ለ. የሴት መሃንነት መንስኤዎች
- የእንቁላል መለቀቅ መዛባት : እንቁላል በመደበኛነት አለመመረት ወይም አለመለቀቅ።
- የእንቁላል ማስተላለፊያ ቱቦ መዘጋት: በኢንፌክሽን፣ የማህጸን እና እንቁልጢ አካባቢ ቀዶ ጥገና ፣ ከማህጸን ውጭ እርግዝና በኋላ ውስብስብ ወይም በሌሎች ምክንያቶች።
- የማህፀን ችግሮች፦ እንደ ማህጸን እጢ (Fibroids)፣ ፖሊፕ እና የማህፀን አወቃቀር መዛባት።
- Endometriosis፦ በማህፀን ውስጥ መኖር ያለበትን ሕብረ ሕዋስ የሚመስል ሕብረ ሕዋስ ከማህፀን ውጭ ሲያድግ።
- ዕድሜ፦ የሴት ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ የእንቁላል ብዛትና ጥራት ይቀንሳሉ።
- የሆርሞን ችግሮች፦ የታይሮይድ እጢ መዛባትና ሌሎች የሆርሞን ሚዛን ችግሮች።
መሃንነት እንዴት ይመረመራል?
ሁለቱም ባለትዳሮች በአንድ ጊዜ መመርመር አስፈላጊ ነው።
በወንዶች፦
- Semen Analysis፦ የዘር ፍሬ ብዛት፣ እንቅስቃሴና ቅርጽ መመርመር።
- የሆርሞን ምርመራ።
- የዘር ፍሬ አካላዊ ምርመራና አስፈላጊ ሲሆን አልትራሳውንድ።
በሴቶች፦
- የወር አበባ ታሪክና የእንቁላል መለቀቅ ምርመራ።
- የሆርሞን ምርመራ።
- የማህፀንና የእንቁላል አልትራሳውንድ።
- Hysterosalpingography (HSG)፦ የእንቁላል ማስተላለፊያ ቱቦዎች ክፍት መሆናቸውን ለማወቅ የሚደረግ ምርመራ።
መሃንነት ይታከማል?
የሕክምናው ዓይነት በችግሩ መንስኤ፣ በዕድሜና በሁለቱም ባለትዳሮች የጤና ሁኔታ ይወሰናል።
- የመድኃኒት ሕክምና፦ የእንቁላል መለቀቅን ለማነቃቃት የሚረዱ መድኃኒቶችና የሆርሞን ሕክምና።
- ቀዶ ጥገና፦ እንደ ቱቦ መዘጋት፣ አንዳንድ የማህፀን ችግሮችና Varicocele ያሉ ሁኔታዎችን ለማከም።
- IUI : በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀ የወንድ ዘር ፍሬ በቀጥታ ወደ ማህፀን ውስጥ የሚገባበት ዘዴ።
- IVF : እንቁላልና የወንድ ዘር ፍሬ ከሰውነት ውጭ በላቦራቶሪ ውስጥ እንዲገናኙ ተደርጎ የተፈጠረው ፅንስ ወደ ማህፀን የሚመለስበት ዘዴ።
- ICSI (Intracytoplasmic Sperm Injection): አንድ የወንድ ዘር ፍሬ በቀጥታ ወደ እንቁላል ውስጥ የሚገባበት ልዩ የሕክምና ዘዴ።
መሃንነትን ለመከላከል ምን ማድረግ ይቻላል?
ሁሉንም የመሃንነት ምክንያቶች መከላከል ባይቻልም፣ አንዳንድ የጤና ልምዶች የመራባት ጤናን ለመጠበቅ ይረዳሉ።
- ሲጋራ አለማጨስ እና ከመጠን በላይ አልኮልን ማስወገድ።
- ጤናማ የሰውነት ክብደትን መጠበቅና አዘውትሮ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ።
- የአባላዘር በሽታዎችን መከላከልና በቶሎ ማከም።
- ለጎጂ ኬሚካሎችና ለጨረር አላስፈላጊ መጋለጥን መቀነስ።
መቼ ወደ ሐኪም መሄድ ያስፈልጋል?
የመሃንነት ምርመራ መቼ መጀመር እንዳለበት በሴቷ ዕድሜ ላይ ይመረኮዛል።
- ከ35 ዓመት በታች ለሆኑ ሴቶች፦ ለ12 ወራት (1 ዓመት) ያለመከላከያ መደበኛ ግንኙነት ካደረጉ በኋላ እርግዝና ካልተፈጠረ ምርመራ መጀመር ይመከራል።
- 35 ዓመትና ከዚያ በላይ ለሆኑ ሴቶች፦ ለ6 ወራት ያለመከላከያ መደበኛ ግንኙነት ካደረጉ በኋላ እርግዝና ካልተፈጠረ ምርመራ መጀመር ይመከራል።
- ከ40 ዓመት በላይ ለሆኑ ሴቶች፦ ረጅም ጊዜ ሳይጠብቁ ወዲያውኑ የሕክምና ምክርና ምርመራ ማግኘት ይመከራል።
በተጨማሪም እንደ የወር አበባ መዛባት፣ የዳሌ ሕመም(PID) ፣ Endometriosis፣ ቀደም ሲል የመራቢያ አካላት ችግር ወይም በወንድ የዘር ፍሬ ላይ የታወቀ ችግር ካለ የተጠቀሱትን ጊዜያት ሳይጠብቁ ምርመራ መጀመር ያስፈልጋል።
መሃንነት የሴት ብቻ ችግር ሳይሆን የወንድንም የሚመለከት የጤና ጉዳይ ነው። ስለዚህ ባለትዳሮች ችግሩን በጋራ መጋፈጥና ሁለቱም በአንድ ጊዜ መመርመር አስፈላጊ ነው። መሃንነት የሚያሳፍር ነገር ሳይሆን የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልገው የጤና ችግር ነው። በትክክለኛ ምርመራና በተገቢው ሕክምና ብዙ ባለትዳሮች የወላጅነት ሕልማቸውን ማሳካት ይችላሉ።




