የአይረን እጥረት

Yosef Tadesse
Nov 11, 2026
images (10)

 

    የአይረን እጥረት ምንድን ነው?

የአይረን እጥረት ማለት በሰውነትዎ ውስጥ በቂ አይረን ሳይኖር ሲቀር ሲሆን በማንኛውም ዕድሜ ላይ ሊከሰት የሚችል በጣም የተለመደ ችግር ነው።

አይረን ለሰውነትዎ አስፈላጊ ማዕድን ሲሆን የቀይ ደም ሴሎችን ለማምረት፤ለጤናማ የሰውነት በሽታ መከላከል ሥርዓት፤ለአእምሮ እንቅስቃሴ (ሥራ)፤ ለጡንቻ ጥንካሬ እና ጉልበት ብረት ያስፈልግዎታል።

በቀይ ደም ሴሎች ውስጥ ብረት ሄሞግሎቢን ከሚባል የፕሮቲን አካል ውስጥ ይገኛል ። ሄሞግሎቢን ኦክሲጅንን በደምዎ አማካኝነት ያጓጉዛል። በሰውነትዎ ውስጥ ያሉ ሴሎች በትክክል መሥራት እንዲችሉ ኦክሲጅንን ከሳንባዎ ወደ ሁሉም የሰውነትዎ ሴሎች ያደርሳል።

 የአይረን እጥረት በዓለም ላይ በጣም የተለመደው የምግብ ንጥረ ነገር (የሥርዓተ-ምግብ) ችግር ነው።

 

 

   የአይረን እጥረት መንስኤው ምንድን ነው?

   የአይረን እጥረት 4 ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ፦

  • በአይረን የበለፀጉ ምግቦችን በበቂ ሁኔታ አለመመገብ
  • በአንዳንድ የሕይወት ደረጃዎች ውስጥ ለአይረን የሚኖረው ፍላጎት መጨመር(በሕፃናት ፡በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ታዳጊዎች (በተለይም ሴቶች)የወር አበባ የሚያዩ ሴቶች ፡ ነፍሰ ጡር የሆኑ ሰዎች፡ የሚያጠቡ ሰዎች)
  • ሰውነታችን ብረትን Absorbtion (የመውሰድ) ችግር ካለበት
  • ደም መፍሰስ(ከፍተኛ የወር አበባ ደም መፍሰስ (ሜኖሬጂያ))፣ የጨጓራና አንጀት ደም መፍሰስ ቁስለት እና እብጠት፣ የትልቅ አንጀት ካንሰር፣ የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን/NSAIDs አዘውትሮ መጠቀም፣ ተደጋጋሚ የደም ልገሳ ወይም ቀዶ ጥገና።

ምልክቶቹ

  • አጠቃላይ ድካም እና ዝለት፦ ሁልጊዜ የሚሰማ ድካም እና የአካላዊ ብርታት መቀነስ።
  • የፊት/የቆዳ መንጣት፦ ያልተለመደ የቆዳ፣ የዐይን የውስጠኛው ሽፋን ወይም የድድ መንጣት (ነጭ መሆን)።
  • የልብ እና የትንፋሽ ምልክቶች፦ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ጊዜ የትንፋሽ ማጠር፣ የልብ ምት መፋጠን (tachycardia) ወይም የደረት መወጠር/መጨናነቅ።
  • የነርቭ ሥርዓት ምልክቶች፦ ማዞር፣ የራስ ቅለት ስሜት፣ ራስ ምታት፣ ወይም የእግር እረፍት ማጣት ስሜት (restless legs syndrome)።
  • አካላዊ ለውጦች፦ የሚሰበሩ እና የጐደጎዱ ጥፍሮች (koilonychia)፣ ለስላሳ ወይም ቁስለኛ ምላስ (glossitis)፣ እና የአፍ ማዕዘናት መሰነጣጠቅ (angular cheilitis)።
  • ፓይካ (Pica)፦ እንደ በረዶ፣ አፈር፣ ጭቃ ወይም ስታርች ያሉ ምግብ ያልሆኑ ነገሮችን የመመኘት/የመፈለግ ስሜት።

የአይረን እጥረት እንዴት ይመረመራል?

የአይረን እጥረት የሚመረመረው በአካላዊ ምርመራ፣ በሕክምና ታሪክ፣ በደም ምርመራዎች (የአይረን መጠን እና የደም ሴሎች ምርመራ) እና ሥር-መንስኤውን ለመለየት በሚደረጉ ተጨማሪ ምርመራዎች አማካኝነት ነው።

  • የሙሉ ደም ምርመራ (CBC)፦ የደም ማነስን ለመለየት የሄሞግሎቢን እና የሄማቶክሪት መጠንን ይለካል። በተጨማሪም የቀይ ደም ሴሎችን ባህሪያት ይገመግማል፦
  •  ልዩ የአይረን ምርመራዎች (Iron Studies)
  • የደም ናሙና በማይክሮስኮፕ መመርመር (Peripheral Blood Smear)
  •  ሥር-መንስኤውን መመርመር(ኢንዶስኮፒ እና ኮሎኖስኮፒ፣የሴሊያክ በሽታ ምርመራ (Celiac Disease Screening)፣የሰገራ ደም ምርመራ (FOBT / FIT)፡የማህፀን አልትራሳውንድ / ምርመራ)

   የሚያስከትለዉ የጤና ችግር

  • ከፍተኛ የሆነ የደም ማነስ
  • የልብ ችግር ፦ ከፍተኛ የሆነ የደም ማነስ በደም ውስጥ ያለውን ዝቅተኛ የኦክሲጅን መጠን ለማካካስ ልብ  ደም በኃይል እንዲረጭ ያስገድደዋል፤ ይህም ለልብ ማበጥ ወይም ለልብ ድካም ሊዳርግ ይችላል።
  • የእርግዝና ጠንቆች ህፃኑ ጊዜው ሳይደርስ የመወለድ፣ ዝቅተኛ የልደት ክብደት የመኖር እና በአዲስ ተወላጅ ህፃን እድገት ላይ ችግሮችን ያስከትላል።
  • የእድገት እና የአእምሮ ዘገምተኝነት፦ በሕፃናት እና በልጆች ላይ የሚከሰት ከፍተኛ የአይረን እጥረት የአካል እድገት መዘግየትን፤የማስታወስ፣ የመማር፣ የእንቅልፍ እና የትኩረት ችግሮች ማጋጠም እንዲሁም የአእምሮ እና የባህሪ እድገት ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል።
  • ለኢንፌክሽን የመጋለጥ አደጋ፦ የተዳከመ የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች የመጋለጥ እድልን ይጨምራል።          

             የአይረን እጥረት እንዴት ይታከማል?

የአይረን እጥረት ህክምና ዋና ዓላማ በሰውነት ውስጥ ያለውን የአይረን መጠን ወደ መደበኛ መጠን ማድረስ እና ለእጥረቱ ምክንያት የሆነውን ሥር-መንስኤ ማከም ነው። 

ህክምናው የሚከተሉትን ዋና ዋና መንገዶች ያካትታል፦

1. የአፍ የአይረን እንክብሎች (Oral Iron Supplements)

  • የመድኃኒት ዓይነቶች፦
  • ፌረስ ሰልፌት (ferrous sulfate)
  • ፌረስ ፉማሬት (ferrous fumarate) 
  • ፌረስ ግሉኮኔት (ferrous gluconate) ያሉ እንክብሎች በሐኪም ትዕዛዝ ይሰጣሉ።

    የአወሳሰድ ዘዴ፦ አይረን በባዶ ሆድ ሲወሰድ የተሻለ መወሰድ አቅም አለው ሆኖም የጨጓራ ህመም የሚያስከትል ከሆነ ከምግብ ጋር ሊወሰድ ይችላል።

    ከቪታሚን ሲ ጋር መውሰድ፦ የአይረን እንክብሎችን ከቪታሚን ሲ (ለምሳሌ ከብርቱካን ጭማቂ) ጋር መውሰድ በሰውነት ውስጥ የአብዞርብሽን አቅማቸውን ይጨምራል፡፡

2. በደም ሥር የሚሰጥ ብረት (Intravenous / IV Iron)

የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ አይረን በቀጥታ በደም ሥር በመርፌ መልክ ይሰጣል፦

  • የአፍ እንክብሎችን መታገስ ወይም መውሰድ በማይቻልበት ጊዜ (በከፍተኛ የጨጓራ ህመም ምክንያት)
  • በአንጀት ህመም ምክንያት አይረን የአብዞርብሽን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ሲቀንስ (ለምሳሌ Celiac disease ወይም IBD)
  • በጣም ከፍተኛ የሆነ የደም ማነስ ሲኖር እና ፈጣን ማገገም ሲያስፈልግ

3. ሥር-መንስኤውን ማከም (Addressing the Underlying Cause)

የአይረን እንክብል መውሰድ ብቻውን በቂ አይደለም፤ ለደም መፍሰሱ ወይም ለብረት እጥረቱ ምክንያት የሆነው ችግር መታከም አለበት ፡፡

  • ከፍተኛ የወር አበባ ደም መፍሰስ፦ በሆርሞን ህክምና ወይም በማህፀን ህክምና ማስተካከል።
  • የጨጓራና አንጀት ደም መፍሰስ፦ የጨጓራ ቁስለትን ማከም፣ ፖሊፕን በቀዶ ጥገና ማስወገድ ወይም ተገቢውን ህክምና ማድረግ።

4. የአመጋገብ ማሻሻያ (Dietary Changes)

በአይረን የበለፀጉ ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ፦

  • የእንስሳት ተዋጽኦ (Heme Iron)፦ ቀይ ሥጋ፣ የዶሮ ሥጋ፣ ዓሳ እና ጉበት 
  • የእፅዋት ተዋጽኦ (Non-Heme Iron)፦ ምስር፣ ባቄላ፣ ስፒናች እና  ማዕድን የበለፀጉ እህሎች
  • ማስታወሻ፦ ሻይ፣ ቡና እና የወተት ተዋጽኦዎችን የአይረ እንክብል ከሚወሰድበት ወይም በአይረን የበለፀገ ምግብ ከሚበላበት ሰዓት ጋር አራርቆ መውሰድ ይመረጣል።

 የብረት እጥረት እንዴት መከላከል ይቻላል?

  • የአመጋገብ ማሻሻያ፦ የሄም (Heme) አይረን ምንጮችን (ቀይ ሥጋ፣ የዶሮ ሥጋ፣ ዓሳ) እና የሄም ያልሆኑ (Non-heme) ብረት ምንጮችን (ባቄላ፣ ምስር፣እንጀራ፤ ስፒናች) መመገብ።
  • የአብዞርብሽን አቅምን ማሳደግ፦  አይረን ያላቸውን ምግቦች ከቪታሚን ሲ (እንደ ብርቱካን ዝርያ ፍራፍሬዎች፣ ቃሪያ) ጋር አጣምሮ መመገብ፣ እንዲሁም ከፍተኛ አይረን ከያዙ ምግቦች ጋር ቡና፣ ሻይ ወይም በካልሲየም የበለፀጉ ምግቦችን አብሮ አለመውሰድ።
  • መደበኛ የምርመራ ክትትል፦ ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጡ የሕብረተሰብ ክፍሎችን (ነፍሰ ጡር ሴቶችን፣ ሕፃናትን እና ተደጋጋሚ የደም ለጋሾችን ጨምሮ) መደበኛ ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል ፡፡

 

Comments (0)