መጥፎ የትንፋሽ ጠረን (Halitosis)
መጥፎ የትንፋሽ ጠረን (halitosis) ከአፍ ወይም ከአፍንጫ የሚወጣ ማንኛውም አስፀያፊ ሽታ ሲሆን እድሜ ሲጨምር የመከሰት እድሉ አብሮ እየጨመረ ቢመጣም ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ህጻናት ላይ ጀምሮ ሊታይ የሚችል የጤና እክል ነው።
በበርካታ አገራት በተደረጉ ጥናቶች መሰረት መጥፎ የትንፋሽ ጠረን ከ15 እስከ 30 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ላይ የሚታይ በሽታ ነው።ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከመቶ አዋቂ ሰዎች ሶስቱን ያጠቃል። በበሽታው ተጠቂ ከሆኑት ከመቶ ሰዎች ዘጠናዎቹ ላይ አፋቸው ውስጥ በሚፈጠሩ ችግሮች የሚከሰት ሲሆን ከመቶ አስር ሰዎች ላይ ደግሞ ከአፍ ውጪ ባሉ ችግሮች የሚፈጠር ነው።
መጥፎ የትንፋሽ ጠረን በምን ምክንያት ይመጣል?
- ከአፍ የሚነሳ መጥፎ ጠረን- መጥፎ የትንፋሽ ጠረን ከ80 እስከ 90 በመቶ በሚሆኑ ሰዎች ላይ አፍ ውስጥ በሚፈጠር እክል ምክንያት ይጀምራል፡፡ ይህ በአብዛኛው በምራቅ ፣ በምግብ ፍርስራሽ ፣ በደም እና ከአፍንጫ ወደ አፍ የሚወርድ ፈሳሽ ውስጥ የሚገኙ ፕሮቲኖች የአፍ ንፅህና ካልተጠበቀ አፍ ውስጥ በሚገኙ በ መቶዎች የሚቆጠር ዝርያ ባላቸው ባክቴሪያዎች በሚሰባበሩበት ወቅት የሚለቀቁ ውህድ ጋዞች እንደ ተረፈ ምርት ከሚለቁት ቮላታይል ሰልፈር ኮምፓውንድ (Volatile sulfur compounds) በሚፈጥሩት ጠረን ምክንያት ይመጣል።
- ከአፍ የሚወጣው መጥፎ ጠረን በዋነኝነት የሚመጣው በጥርሶች መካከል እና በኋለኛው የምላስ ክፍል ከሚገኘው የባክቴሪያ ክምችት ነው
- ሰው ሰራሽ ወጪ ገቢ ጥርስ ለረጅም ሰዓታት ያለማፅዳትና ሌት ተቀን አድርጎ በመታየት፣ የምራቅ ምርት መቀነስ። ሰው በእንቅልፍ በሚያሳልፍበት ወቅት የምራቅ ምርት ከመቀነስም በሻገር ሙሉ ለሙሉ ሊቆምም በመቻሉ ለባክቴሪያዎች መራባት የጎላ አስተዋፆ ያደርጋል፣
- የተበላሹ የጥርስ ሙሌቶች ፣የድድ መምገል፣ጥልቅ የጥርስ መቦርቦር፣ የተለያዩ የጥርስ እና የድድ ኢንፌክሽኖች እና ሰው ሰራሽ ጥርሶች እንዲሁ መጥፎ ሽታ ሊያስከትሉ ይችላሉ ፡፡
- ፆም ላይ በሚኮንበት ወቅት (የተለያዩ ምግብ ዓይነቶች አፍ የማፅዳት አቅም ስላላቸው መጥፎ የአፍ ጠረን ይቀንሳሉ)፣ በቀን ውስጥ በቂ ውኃ አለመውሰድ፣ አፍ ውስጥ የቆሻሻ ክምችት ሲኖር መጥፎ ሽታ ሊያስከትሉ ይችላሉ ፡፡
- አፍ በሚደርቅበት ጊዜ መጥፎ የአፍ ሽታ ብዙውን ጊዜ የከፋ ይሆናል ፣ ለዚህም ምክንያቱ የውህድ ጋዞች የበለጠ ስለሚለቀቁ እና የምራቅ የማጣራት ስራ ስለሚቀንስ ነው።
- የተለያዩ የአፍ ውስጥ ካንሰሮችና ቁስለቶች ሲኖሩ የአፍ መጥፎ ጠረንን የመጨመር አቅም ኣላቸው።
- ከአፍንጫ የሚነሳ መጥፎ ጠረን- ሁለተኛው የተለመደው መጥፎ የትንፋሽ ጠረን መንሰኤ ከአፍንጫ የሚነሱ እክሎች ሲሆኑ ከ 5 እስከ 8 በመቶ ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ላይ ይታያል፡፡ ከአፍንጫ የሚነሱ መጥፎ ጠረኖች ብዙውን ጊዜ “የአይብ አይነት” ሽታ ሲኖራቸው ይህም ከሌሎች መጥፎ የትንፋሽ ጠረን ዓይነቶች ይለያቸዎል
- የአፍንጫ ኢንፌክሽን (sinusitis) ፣ በአየር ፍሰት ወይም በአፍንጫ በሚወጣው ፈሳሽ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር እክል እንደ አፍንጫ ወስጥ የሚፈጠር እባጭ (nasal polyps ) ፣ የክንፈር እና ላንቃ መሰንጠቅ ያለባቸው ህጻናት፣ የአፍንጫ ቀዶ ጥገና ያደረጉ ሰዎች እና በአፍንጫ የሚነፉ መድሃኒቶች አዘውትረው የሚጠቀሙ ሰዎች በዚህ አይነቱ መጥፎ ጠረን የመጠቃት እድላቸው ሰፊ ቢሆንም ምንም አይነት አካላዊ እክል የሌለባቸው ሰዎች ላይም ሊፈጠር ይችላል።
- በልጆች ላይ ባዕድ አካላትን በአፍንጫቸው ቀዳዳ ውስጥ ማስገባት ከአፍንጫ ለሚወጣ መጥፎ ጠረን የተለመደ ምክንያት ነው
- ከቶንሲል የሚነሳ መጥፎ ጠረን- - ወደ 3 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ላይ የቶንሲል በሽታ ለመጥፎ የትንፋሽ ጠረን ምክንያት ነው
- አንዳንድ ሕመምተኞች በሚያስሉበት ጊዜ መጥፎ ሽታ ያላቸው ጥቃቅን ጠጠሮች በአፋቸው ሲወጣ ሊያስተውሉ ይችላሉ። እነዚህ በቶንሲል ውስጥ የሚፈጠሩ “tonsilloliths” ጠጠሮች ሲሆኑ በአለምአቀፍ ደረጃ ወደ 7 በመቶ የሚሆኑ ሰዎችን የሚያጠቃ በሽታ ነው። እነዚህ ጠጠሮች በውስጣቸው የተለያዩ መጥፎ ጠረን የሚያመጡ ውህድ ጋዞችን የሚያመርቱ ባክቴሪያዎች የያዙ ናቸው።
- ከመስቄ(esophagus) ፣ ከሆድ ወይም ከአንጀት የሚነሱ ችግሮች መጥፎ የትንፋሽ ጠረን የማምጣት እድላቸው እጅግ አናሳ ነው።
- ከዚህም በተጨማሪ የሳንባ ኢንፌክሽኖችን ፣ የኩላሊት በሽት ፣ የጉበት በሽታ ፣ የስኳር በሽታ፣ ሲጋራ ማጨስ እና የተለያዩ ካንሰሮች መጥፎ የትንፋሽ ጠረን ሊያስከትሉ ይችላሉ።
መጥፎ የትንፋሽ ጠረንን የሚያባብሱ ሁኔታዎች
- ከአፍንጫ ወደ አፍ የሚንጠባጠብ ፈሳሽ በምላስ ስር መከማቸት
- የጥርስ ንፅህናን አለመጠበቅ (በተለይም በጥርሶች መካከል በተገቢው አለማጸዳት)
- ተገቢ ያልሆነ የጥርስ ህክምና ( የተሳሳተ ብሬስ አስተሳሰር ፣ የጥርስ ሙሌቶች መፍሰስ …)
- በአፍ መተንፈስ እና ሌሎች ደረቅ አፍን የሚያስከትሉ ምክንያቶች (ለምሳሌ ፣ ጾም ፣ መድኃኒቶች ፣ ረዘም ላለ ጊዜ ንግግር ማድረግ እና ጭንቀት)
- ንጸህናቸውን ያልጠበቁ ሰው ሰራሽ ጥርሶች
- አልኮል መጠጣት
- ከመጠን በላይ ክብደት መጨመር
- የወር አበባ
- በጥርሶች መካከል የሚጣበቁ የፕሮቲን ምግቦች
- ቀይ እና ነጭ ሽንኩርት በሚመገቡበት ጊዜ
መጥፎ የትንፋሽ ጠረን እና ማህበራዊና ስነልቦናዊ ጫና
መጥፎ የአፍ ጠረን ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ጫና ያሳድራሉ ከሚባሉ የበሽታ ዓይነቶች ኣንዱ ነው። ይህ የበሽታ ዓይነት ከስነ-ልቦና ጫና ባለፈ በትዳር አጋሮች መካከልም የሻከረ ግንኙነት የመፍጠር አቅምም ኣለው።
ሕክምናው ምንድን ነው?
ተለይተው የሚታወቁ የጥርስም ሆነ ስራዐታዊ በሽታዎች ካሉ ህክምና ማድረግ ያስፈልጋል ፡፡ህክምናው ከመጀመሩ በፊት የመጥፎ የአፍ ጠረኑን ምክንያትች መለየት ኣለበት። መጥፎ የአፍ ጠረን ካለባቸው መቶ ሰዎች ዘጠናዎቹ አፍ ውስጥ በሚፈጠሩ ችግሮች ስለሆነ በቂ የአፍ ንፅህና መጠበቅ። ሌሎች የሰውነት በሽታዎችን ከለየን በኋላ ከሆነ ተገቢውን ህክምና በማግኘት የመጥፎ የትንፋሽ ጠረንን መቀነስ እና ማጥፋት እንችላለን።
አብዛኞቹን መጥፎ የትንፋሽ ጠረኖች የሚከተሉትን በመተግበር ማስወገድ ይቻላል
- በየቀኑ በተገቢው መልኩ የጥርስ ሳሙናና ብሩሽ ተጠቅሞ በቀን ሁለቴ ጥርስን ማፅዳት እና በጥርስ መካከል ያለውን ክፍተት ማጸዳት (flossing)
- የምላስን የኋለኛ ክፍል ለዚህ ተብለው በተዘጋጁ ማጸጃዎች ማጠብ
- አልኮል ያልያዙ የአፍ ሳሙናዎችን (non-alcoholic mouthwash) በመጠቀም በጥልቀት መጉመጥመጥ ፤ ይህም ማታ በእንቅልፍ በፊት ሲከናወን የበለጠ ውጤታማ ይሆናል
- አፍ ውስጥ የተከማቸ ቆሻሻ ካለ በሐኪም ማፀዳት
- ፋይበር ያላቸው ምግቦችን መመገብ
- የምራቅ የመመንጨት መጠን የሚጨምሩ ነገሮችን ለምሳሌ ከስኳር ነፃ የሆኑ ማስቲካዎች ለአጭር ጊዜ (አምስት ደቂቃ በቂ ነው) ማዘውተር የምራቅ መመንጨትን ስለሚጨምር ምራቅ ውስጥ የሚገኘውን ላይሶዛይም(Lysozyme) የተባለውን ኢንዛይም መጠን ስለሚጨምር የባክቴሪያዎች ቁጥር እጅጉን ይቀንሳል። ማስቲካ አፍ በሚደርቅበት ወቅት ወይም ከምግብ በኋላ መጠቀም ይመከራል።
- ከፍተኛ ፕሮቲን የያዙ ምግቦችን አለማዘውተር ለመጥፎ የአፍ ጠረን ምክንያት ከሆኑት ከቮላታይል ሰልፈር ኮምፓውንድስ ተጋላጭነትን ይቀንሳል
- በቂ ውሃ መጠጣት (በቀን እስከ 2 ሊትር መጠጣት ይመከራል)
- የሚወስዱትን የአልኮል እና የቡና መጠን መቀነስ
- ፀረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች ጊዜያዊ እፎይታ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አያስገኙም
- ሰው ሰራሽ ጥርስ ማታ ሲተኙ አፅድቶ በንፁህ ውኃ ነክሮ ማሳደር መጥፎ የአፍ ጠረንን ለማስወገድ ከሚረዱ መንገዶች መካከል ኣንዱ ነው።




