በልጆች ላይ የውሃ እጥረት (Dehydration) ምንድነው?
ድርቀት (Dehydration) የሚከሰተው የሕፃናት አካል ከተቀበለው የውኃና ፈሳሽ መጠን በላይ በከፍተኛ ሁኔታ ሲያጣ ነው። የሕፃናት የሰውነት መጠን አነስተኛ በመሆኑና ፈሳሽ በፍጥነት ስለሚያጡ፣ ለድርቀት የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ምልክቶቹን ቀድሞ ማወቅና ተገቢውን ሕክምና ማድረግ የሕፃኑን ሕይወት ለማዳን ወሳኝ ነው።
በህፃናት ላይ ለውሃ እጥረት (Dehydration) መንስኤ የሚሆኑ ነገሮች
የውሃ እጥረት የሚከሰተው ህፃናት ከሚወስዱት መጠን በላይ ፈሳሽ በሰውነታቸው ውስጥ ሲያጡ ነው። ዋና ዋናዎቹ መንስኤዎች የሚከተሉት ናቸው፦
- ተቅማጥ – በተለይም ተቅማጡ ተደጋጋሚ ወይም ከፍተኛ በሚሆንበት ጊዜ ዋነኛው መንስኤ ነው።
- ትውከት – የውሃ እና ጠቃሚ የሆኑ ጨዎች እጥረት ያመጣል።
- ትኩሳት – የሰውነት ፈሳሽ እጥረትን ይጨምራል፤ በተለይም ህፃኑ በቂ ፈሳሽ የማይወስድ ከሆነ።
- ከፍተኛ ላብ – በሞቃታማ አየር፣ በሰውነት እንቅስቃሴ ወቅት ወይም በትኩሳት ምክንያት ሊከሰት ይችላል።
- በቂ ፈሳሽ ባለመውሰድ – በህመም፣ በምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ለመዋጥ በመቸገር ወይም ፈሳሽ ለመጠጣት በመከልከል ምክንያት ሊሆን ይችላል።
- በተደጋጋሚ መሽናት – እንደ ስኳር ህመም ያሉ ህመሞች በሽንት በኩል ከፍተኛ የፈሳሽ ማጣት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
- ቃጠሎ – ከፍተኛ የሆነ የቃጠሎ አደጋ ከፍተኛ የፈሳሽ ማጣትን ያመጣል።
በጨቅላ ህፃናት ላይ የውሃ እጥረት በፍጥነት ሊከሰት ይችላል፤ ምክንያቱም የሰውነታቸው የፈሳሽ መጠን አነስተኛ በመሆኑ እና ፈሳሽ ለማግኘት ሙሉ በሙሉ በአዋቂዎች ላይ ስለሚደገፉ ነው።
የድርቀት ደረጃዎች እና ምልክቶች
1. ቀላል እና መካከለኛ ድርቀት (Mild to Moderate Dehydration)
- የአፍ እና የከንፈር መድረቅ
- በለቅሶ ጊዜ እንባ አለመኖር ወይም ማነስ
- የሽንት መጠን መቀነስ (የዳይፐር እርጥበት ከወትሮው መቀነስ ወይም ከ 6 ሰዓት በላይ ሽንት አለመሸናት)
- ሽንት ጥቁር አረንጓዴ ወይም ጥቁር ቢጫ መሆን
- የሕፃኑ አናት (ላንቃ) ትንሽ ገባ ማለት
- መበሳጨት እና እልህኛ መሆን
2. ከፍተኛ ድርቀት (Severe Dehydration) - አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ የሚፈልግ!
- በጣም ድካም፣ ከፍተኛ እንቅልፍማነት ወይም ፈጣን ምላሽ አለመስጠት
- የዓይኖች ገባ ገባ ማለት
- በጣም ደረቅ አፍ እና ምላስ
- የእጅ እና የእግር መቀዝቀዝ ወይም የቆዳ ቀለም መለወጥ
- የልብ ምት በፍጥነት መምታት እና ፈጣን ትንፋሽ
- ቆዳን በጣት ይዞ ሲለቁት በፍጥነት ወደ ነበረበት አለመመለስ (Skin Turgor)
የመጀመሪያ ሕክምና እና እንክብካቤ
1.ኦ.አር.ኤስ (ORS - Oral Rehydration Salts) መስጠት፡
- ለድርቀት ሕክምና በጣም አስተማማኝ አማራጭ የሕክምና ORS ነው። ORS በውኃ ውስጥ ተበጥብጦ የሚሰጥ ሲሆን፣ በውስጡ ሰውነት ያጣቸውን ጨዎችና ስኳር በአስተማማኝ ሁኔታ ይዟል።
- ማሳሰቢያ፡ ORS በሚዘጋጅበት ጊዜ በጥቅሉ ላይ በተጻፈው መመሪያ መሠረት በትክክለኛው የውኃ መጠን ብቻ መበጥበጥ አለበት።
2.የጡት ወተት ማጥባትን መቀጠል፡
- የሚጠቡ ሕፃናት ከሆኑ የጡት ወተት ማጥባቱን ሳያቋርጡ በተደጋጋሚና በብዛት ማጥባት ያስፈልጋል።
3.ፈሳሾችን በትንሽ በትንሹ መስጠት፡
- ሕፃኑ የሚያስመልሰው ከሆነ ፈሳሹን በማንኪያ በየ 5-10 ደቂቃው በትንሽ በትንሹ መስጠት ይመረጣል።
4.መወገድ ያለባቸው ነገሮች፡
- ለሕፃናት የታሸጉ የፍራፍሬ ጭማቂዎችን፣ ለስላሳ መጠጦችን ወይም በጣም ስኳር የበዛባቸውን ነገሮች አለመስጠት (ተቅማጡን ሊያባብሱ ይችላሉ)።
- ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የተቅማጥ ወይም የትውከት መድኃኒቶችን ለሕፃናት አለመስጠት።
5.ዚንክ (Zinc Supplementation):
- በተቅማጥ ምክንያት ለሚመጣ ድርቀት የዚንክ ተጨማሪ መድኃኒት (Zinc supplement) ለ 10-14 ቀናት መስጠት የተቅማጡን ቆይታና ጽናት ይ ቀንሳል።
ወደ ሕክምና centre/ሐኪም ዘንድ መቼ መሄድ ያስፈልጋል?
ሕፃኑ ከታች ከተጠቀሱት ምልክቶች አንዱ እንኳን ካሳየ በአስቸኳይ ወደ ሕክምና ተቋም መወሰድ አለበት፡
- ሕፃኑ ዕድሜው ከ 3 ወር በታች ከሆነ
- ፈሳሽ ወይም ORS ጨርሶ መቀበል ካልቻለ ወይም በተደጋጋሚ የሚያስመልስ ከሆነ
- ከፍተኛ ድርቀት ምልክቶች (እንቅልፍማነት፣ የዓይን ገባ ገባ ማለት፣ የላንቃ መግባት) ካየሁበት
- ተቅማጡ ከ 24 ሰዓት በላይ ከቆየ ወይም ደም የተቀላቀለበት ከሆነ
- ከፍተኛ ትኩሳት ካለው




