ማራቶን መሮጥ ለጤና ጎጂ ነው?

Eyasu Yebeltal
Oct 15, 2026
photo 2026 10 15 14 45 18

            ማራቶን መሮጥ ለጤና ጎጂ ነው?

ማራቶን ወይም 42.2 ኪሎ ሜትር መሮጥ ከፍተኛ ቁርጠኝነትን እና ዝግጅትን የሚጠይቅ ትልቅ የአካል ብቃት ስኬት ነው። ታዲያ ይህ ከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለጤና ጎጂ ነው? መልሱ የሚወሰነው በእርስዎ የአካል ብቃት ደረጃ፣ በስልጠናዎ፣ በህክምና ታሪክዎ እና ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ በኋላ በሚያደርጉት ሰውነትን መልሶ የማደስ ሂደት ላይ ነው።

ለአብዛኛዎቹ ጤናማ አዋቂዎች፣ ማራቶንን በቂ ልምምድ በማድረግ መሮጥ በርካታ የጤና ጥቅሞችን ሊያስገኝ ይችላል። ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችንም ያካትታል።

     ማራቶን መሮጥ የሚሰጣቸው የጤና ጥቅሞች

  • የልብ ጤናን ያሻሽላል፡- አዘውትሮ መሮጥ የልብ ጡንቻን በማጠናከር የልብና የደም ሥር ስርአት ብቃትን ያሻሽላል።
  • ክብደትን ለመቆጣጠር ይረዳል፡- ሩጫ ካሎሪዎችን በማቃጠል ክብደት የመቀነስ ጥረትን ይደግፋል።
  • የአእምሮ ጤናን ያሻሽላል፡- የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጭንቀትን ሊቀንስ፣ ስሜትን ሊያሻሽል እና በራስ መተማመንን ሊገነባ ይችላል።
  • ጽናትን ያሻሽላል፡- የማራቶን ስልጠና ጥንካሬን በማዳበር ለረጅም ጊዜ ያለድካም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ ጽናትን ያሻሽላል።

     ሊያጋጥሙ የሚችሉ የጤና አደጋዎች

ማራቶን መሮጥ ጥቅሞች ቢኖሩትም፤ በሰውነት ላይ ከፍተኛ ጫናን ሊፈጥር ይችላል።

  • የጡንቻ እና የመገጣጠሚያ ጉዳቶች፡- ከመጠን በላይ የሚደረግ ልምምድ የመገጣጠሚያ ህመም፣ የጅማቶች ጉዳት እና  በከፍተኛ ጫና ምክንያት የሚፈጠር የአጥንት ስብራትን ሊያስከትል ይችላል።
  • የሰውነት ድርቀት እና ከፍተኛ ሙቀት፡- የሰውነትን ፈሳሽ ከመጠን ማጣት እና ከፍተኛ ሙቀት በዚህ እንቅስቃሴ ወቅት አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ።
  • የኩላሊት ጫና፡- ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የኩላሊት ተግባር ላይ ጊዜያዊ ጫናን ሊያደርግ ይችላል።
  • የልብ ችግሮች፡- ከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በተለይም በልብ በሽታ ባለባቸው ሰዎች ላይ አደገኛ የልብ ክስተቶችን ሊያስከትል ይችላል።
  • ዝቅተኛ የደም ሶዲየም፡- በሩጫ ወቅት ከመጠን በላይ ውሃን መጠጣት ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ሃይፖናትሪሚያ የሚባል አደገኛ የደም ሶዲየም ዝቅ ማለት ሁኔታን ሊያስከትል ይችላል።

     ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ማራቶንን እንዴት መሮጥ ይችላሉ?

አደጋዎችን ለመቀነስ፡-

  • የተዋቀረና ክብደቱ ቀስ በቀስ እየጨመረ የሚሄድ የስልጠና እቅድን ይከተሉ
  • ስልጠናን ለመደገፍ የሚያስችል በቂ ኃይል የሚሰጥ የተመጣጠነ ምግብን ይመገቡ
  • በሩጫ ወቅት በቂና ከመጠን ያላለፈ ፈሳሽን ይውስዱ
  • በቂ እንቅልፍ በማግኘት የማገገም ጊዜን ይውሰዱ
  • ሥር የሰደደ ወይም ከባድ ህመም ካለብዎ ስልጠናን ከመጀመርዎ በፊት የህክምና ምክርን ይፈልጉ
  • አሳሳቢ ምልክቶች ካጋጠሙዎት የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማቆም አስቸኳይ የህክምና እርዳታን ይፈልጉ

     ማራቶን ለጥሩ ጤና ግዴታ አስፈላጊ ነው?

አይደለም! ማራቶን የግል ግብ እንጂ የህክምና መስፈርት አይደለም። የእግር ጉዞን በማድረግ፣ ብስክሌት በመንዳት፣ በመዋኘት ወይም አጭር ሩጫዎችን በማድረግ ጤናዎን ማሻሻል ይችላሉ። አብዛኛዎቹ አዋቂዎች በሳምንት በአጠቃላይ ከ150-300 ለሚሆኑ ደቂቃዎች መካከለኛ አካላዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የሚመከር ሲሆን፤ ቢያንስ በየሁለት ቀናት ደግሞ የጡንቻ ማጠናከሪያ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ አለባቸው።

በአግባቡ በመዘጋጀት ማራቶንን መሮጥ ለጤና መጥፎ ባይሆንም አልፎ አልፎ አደጋዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ቀስ በቀስ በመሠልጠን፣ ሰውነትን በማዳመጥ እና ከማጠናቀቂያ ጊዜ ይልቅ ጤናን ቅድሚያ በመስጠት የተሳካ የማራቶን እንቅስቃሴን ማድረግ ይችላሉ።

Comments (0)