የጨጓራና የአንጀት ቁስለት በሽታ የሚባለው ከስሙ መረዳት እንደምንችለው በጨጓራ እና ዶድነም ተብሎ በሚጠራው በትንሹ አንጀት የላይኛው ክፍል ውስጥ የሚፈጠር ቁስለት ነው ፡፡
የጨጓራና የትንሹ አንጀት ቁስለት በሽታ የሚፈጠረው እንዴት ነው?
የጨጓራ የዶድነም የውጨኛው ክፍልን ጨጓራ ከሚያመነጨው አሲድ (HCL) ለመከላከል የሚረዱ የተለያዩ መንገዶች አሉ። ከነዚህም ውስጥ ዋነኛው የላይኛውን ክፍል የሚያለብሰው የሙከስ ሽፋን (mucous layer) የሚባለው ሽፍን ነው። ይህ የሙከስ ሽፋን ከተጎዳ ጨጓራ የሚያመነጨው አሲድ ቀጥታ በመሄድ ጨጓራን እና ዶድነምን ይጎዳዋል። በመቀጠልም ቁስለቱ ይፈጠራል።
የጨጓራና የትንሹ አንጀት ቁስለት ምልክቶች ምንድን ናቸው?
በዚህ በሽታ የሚሰቃቱ ሰዎች ቁስለቱ እንዳለበት ቦታ የተለያዩ ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ። ለምሳሌ የዚህ በሽታ ዋናው ምልክት የላይኛው የሆድ ክፍል እና የታችኛው የሆድ ክፍል አካባቢ ያለ የህመም ስሜት ሲሆን የጨጓራ ቁስለት ያለባቸው ሰዎች ላይ ህመሙ ከምግብ በኃላ ይባባሳል። በተቃራኒው ቁስለቱ የላይኛው የትንሹ አንጀት ላይ ከሆነ ህመሙ ከምግብ በኃላ ይቀንሳል። በዚህ ምክንያት የዶድናል ቁስለት ያላቸው ሰዎች ህመሙ በጣም የሚያስቸግራቸው ሌሊት ከ 5 ሰዐት ጀምሮ እስከ 8 ሰዐት ባለው ጊዜ ነው።
በዚህ በሽታ የሚሰቃዩ ሰዎች የሚያሳዩት ሌሎች ምልክቶችም አሉ። ከነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹ
- የሆድ መንፋት
- ቶሎ መጥገብ
- የምግብ ፍላጎት ማጣት
- ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ
- ቁስለቱ ከደማ ደግሞ ደም የቀላቀለ ወይም የጠቆረ ሰገራ ልናይ እንችላለን። አንድ አንድ ሰዎች ደግሞ ደም ሊያስመልሱ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በትንሽ በትንሹ መድማቱ ለረጅም ጊዜ ከቀጠለ በሽተኛው ሳይታወቀው የደም ማነስ ምልክቶች ሊኖሩት ይችላል።
የጨጓራና የዶድነም ቁስለት እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?
የጨጓራና የዶድነም ቁስለት የሚያመጡ ሁለት ዋና ዋና ነገሮች አሉ።
እነሱም
- ኤች ፓይሎሪ የሚባል የጨጓራ ባክቴሪያ እና
- ኤንኤስኤአይዲ (NSAID) የሚባሉ የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶች ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም እንደ ማጨስ እና አብዝቶ መጨነቅ ያሉ ምክንያቶች የጨጓራና የዶድነም ቁስለት ሊያመጡ ይችላሉ። አልፎ አልፎ ደግሞ በቤተሰቡ ውስጥ ይህ በሽታ ይለባቸው ሰዎች የበለጠ የመጠቃት አዝማሚያ አሳይተዋል።



